አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥር ሃያ ሦስት በዚች ዕለት አሕዛብን ለሚያስተምር ለከበረ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ የሆነ የከበረ ሐዋርያ ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት ሞተ። የዚህም ቅዱስ ልደቱና እድገቱ ልስጥራን ከሚባል አገር ነው አባቱም ከዋክብትን የሚያመልክ ዮናናዊ ነው እናቱ ግን በኦሪት ሕግ ጥላ ሥር ያለች ናት።
የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም በልስጥራን ሀገር በሰበከ ጊዜ ይህ ጢሞቴዎስ ስብከቱንና ትምህርቱን ሰማ እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያደርጋቸውን ድንቆች ተአምራቶችን አይቶ እሊህም ተአምራቶች አስተዋዮችና ጥበበኞች የሚደነግጡባቸው ናቸው ስለዚህም ወደ ሐዋርያ ጳውሎስ ሒዶ በእርሱ ትምህርት በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቆ የሐዋርያ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ ሆነ ወደ ብዙ አገሮችም ተከትሎት በመሔድ ከእርሱ ጋር ደከመ ታላቅ መከራና ብዙ ኀዘንም ደርሶበታል ሐዋርያው ጳውሎስም በኤፌሶን ውስጥ በአንዲት አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾመው።
በዚያንም ጊዜ ወደርሷ ገብቶ ለሰዎቿ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከ ብዙዎችንም ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ከዚህም በኋላ በዙሪያዋ ወዳሉ ብዙዎች አገሮች በርቀትም ለሚገኙ አገሮችም የከበረ ወንጌልን ሰበከላቸው።
የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም ሁለት መጻሕፍቶችን ጽፎ ወደርሱ ልኳል እርሳቸውም ሕዝቡን የሚያስተምርባቸው ራሱም ከቢጽ ሐሳውያን የሚጠበቅባቸው ቅስና ወይም ዲቁና ሊሾም የሚገባውንና የማይገባውን የሚለይበት ክህነት በማይገባው እጁን እንዳይጭን የሚያስጠነቅቁ ናቸው ጢሞቴዎስን ደግሞ ለርሱ ተወዳጅ ልጁ አድርጎ ይጠራዋል መልእክቶቹንም በእርሱ እጅ ወደ አገሮች ልኳል።
በላያቸው የተሾመባቸውን የክርስቶስን መንጋዎች ፈጽሞ በጠበቀ ጊዜ በትምህርቶቹ በተግሣጾቹና በድርሰቶቹ ልቡናቸውን ብሩህ አደረገ አይሁድንና ዮናናውያንን ይገሥጻቸውና ይዘልፋቸው ነበር እነርሱም ቀንተውበት ሁሉም በጠላትነት ተነሡበት ተሰብስበውም ገደሉት ምእመናንም ሥጋውን አንሥተው ቀበሩት ጻድቅ ቈስጠንጢኖስም እስከ ነገሠ በዚያው ኖረ እርሱም ስለ ሥጋው አስቦ ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ በጥር ወር በሃያ ሰባት ቀን አፈለሰው በዚያችም ቀን በዓል አደረገለት።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment