ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 25 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 25

 #ቅዱስ_መርቆሬዎስ_ሰማዕት (ፒሉፓዴር)

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ሃያ አምስት በዚች ቀን የስሙ ትርጓሜ መርቆሬዎስ የሆነ ፒሉፓዴር በሰማዕትነት አረፈ። መርቆሬዎስም ማለት የአብ ወዳጅ ማለት ነው በሁለተኛ ትርጓሜ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው።


ይህም ቅዱስ አስሊጥ ከምትባል አገር ነው እርሷም የአባቱና የአያቱ አገር ናት እርሱ ግን ተወልዶ ያደገው በሮሜ ከተማ ነው። የአባቱና የአያቱ ሥራቸው አውሬ ማደን ነበር በአንዲት ዕለትም እንደልማዳቸው ለማደን ወጡ ከገጸ ከለባት ወገንም ሁለት ወንዶች ተገናኙአቸውና የቅዱስ መርቆሬዎስን አያት በሉት። ሁለተኛም አባቱን ሊበሉት ፈለጉ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክም ከለከላቸው፤ ከእርሱ የሚወጣ መልካም ፍሬ ስለአለ አትንኩት አላቸው።
ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ዙሪያቸውን በእሳት ከበባቸው። በተቸገሩ ጊዜም ወደ ቅዱስ መርቆሬዎስ አባት መጥተው ሰገዱለት። በዚያንም ጊዜ እግዚአብሔር ፍጥረታቸውን ወደገራምነት ለወጠውና እንደ በጎች የዋሆች ሆኑ። አብረውትም ወደ መንደር ገቡ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ በተወለደ ጊዜ ስሙን ፒሉፓዴር ብለው ጠሩት። የውሻ መልክ ያላቸውም በእነርሱ ዘንድ ብዙ ዘመናት የሚኖሩ ሆኑ ከዚህም በኋላ ክርስቲያኖች ሆኑ። የቅዱስ መርቆሬዎስ ወላጆች አስቀድሞ አረማውያን ነበሩና የክርስትና ጥምቀትንም ጸጋ በተቀበሉ ጊዜ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ኖኅ ብለው ሰየሙት። እናቱንም ታቦት አሏት። ፒሉፓዴርንም መርቆሬዎስ ብለው ሰየሙት።
የውሻ መልክ ያላቸው ግን የእግዚአብሔር መልአክ በተገለጸላቸው ጊዜ እንደ ነገራቸው ለቅዱስ መርቆሬዎስ አባት የሚታዘዙና የሚያገለግሉ ሆኑ። ንጉሡም የኖኅንና የውሻ መልክ ያላቸውን ዜና በሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀረባቸው በዚያንም ጊዜ እግዚአብሔር በንጉሡ ፊት የቀድሞ ፍጥረታቸውን መልሶላቸው ንጉሡ ያቀረባቸውን ሁሉንም አራዊት አጠፏቸው።
ንጉሡም ይህን በአየ ጊዜ እጅግ ፈራ፤ የአራዊትንም ተፈጥሮአቸውን ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲማልድ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ለመነው። እርሱም በለመነ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ተፈጥሮአቸውን መልሶላቸው ገራሞች ሆኑ።
ከዚህም በኋላ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ንጉሡ ወስዶ ገዥና የሠራዊት አለቃ አድርጎ ሾመው። የውሻ አርአያ ያላቸውም ይታዘዙለት ነበር። ከእርሳቸውም የተነሣ ሁሉም ይፈሩ ነበር።
ከዚህም በኋላ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት የሾመውን ንጉሥ ይወጋ ዘንድ ከሀዲ ንጉሥ ተነሣ። ንጉሡም ከጦር ሠራዊት ጋር የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ወደ ጦርነት ላከው። ከሀዲው ንጉሥ ግን እነዚያን የውሻ አርአያ ያላቸውን አባብለውና ሸንግለው ወደርሱ ያመጧቸው ዘንድ ወታደሮችን ላከ። በአመጧቸውም ጊዜ ሃይማኖታቸውን ይለውጡ ዘንድ አብዝቶ ሸነገላቸው፤ ባልሰሙትም ጊዜ ሊአሠቃያቸው ጀመረ አንዱ አምልጦ ሸሽቶ ወደ ጌታው ሔደ። ሁለተኛውም በሰማዕትነት ሞተ።
ከጦር ሜዳ የቅዱስ መርቆሬዎስ አባት በተመለሰ ጊዜ ሚስቱንና ልጁን ፈለጋቸው ግን አላገኛቸውም። ንጉሡ የሱ ወገኖች ድል እንደሆኑ በሰማ ጊዜ የቅዱስ መርቆሬዎስ አባት መኰንኑ የሞተ መስሎት ነበርና የቅዱስ መርቆሬዎስን እናት ወስዶ ሊአገባት ፈለገ። ከንጉሥ ወታደሮችም አንዱ ንጉሡ ያሰበውን በጽሙና ነገራት። እርሷም ይህንኑ ወታደር ከሀገር ውስጥ በሥውር ያወጣት ዘንድ ለመነችውና ከልጇ ከብፁዕ መርቆሬዎስ ጋር ወጥታ ወደ ሌላ አገር ሔደች።
ንጉሡም ከእርሱ የሆነውን የመኰንኑም የመርቆሬዎስን አባት ሚስቱን ለማግባት ማሰቡን እንዳይነግሩት አዘዘ። የውሻ መልኮች ያላቸው ከእርሱ ጋር እንዳሉ የተቆጣም እንደሆነ እንደሚአመጣቸውና አገሮችን ያጠፋሉ ብሎ ይጠራጠራልና ስለዚህ እጅግ ይፈራዋል።
ከዚህም በኋላ ደግሞ በንጉሡ ላይ ጦርነት ተነሣ። የቅዱስ መርቆሬዎስም አባት ወደ ጦርነቱ ወጣ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ይዘው ማረኩት። ወደ ሮሜውም ንጉሥ አቀረቡት ንጉሡም ክርስቲያን ነበርና የተማረከው መኰንን ክርስቲያን መሆኑን በአወቀ ጊዜ አልገደለውም። በክብር አኖረው እንጂ እጅግም ወደደውና ከጥቂት ቀኖች በኋላ በመርዶሳውያን አገሮች ሁሉ ላይ ገዥ አድርጎ ሾመው።
ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ፈቃድ ሚስቱና ልጁ መርቆሬዎስ ወዳሉበት አገር ደረሰ። ሚስቱም በቤተ ክርስቲያን ደጃፍ በአየችው ጊዜ ባሏ አንደሆነ አወቀችው። እርሱ ግን አላወቃትም።
በአንዲትም ዕለት እርሱና ጭፍሮቹ ከእንግዳ ማረፊያ ቤት በወጡ ጊዜ ልጅዋን መርቆሬዎስን ወስዳ ያማሩ ልብሶችን አልብሳ ሒዶ ከመኰንኑ ፈረስ ላይ እንዲቀመጥ አዘዘችው። እርሱም አባቱ ነው። በተቀመጠ ጊዜም ጭፍሮች ይዘው ወደ መኰንኑ ፊት አቀረቡት መኰንኑም ልጁ እንደሆነ አላወቀምና በእርሱ ላይ ተቆጣ።
የመርቆሬዎስም እናት መጥታ ጌታዬ ሆይ እኛ መጻተኞች ነን አንተም መጻተኛ እንደሆንክ በአወቅሁ ጊዜ ልጅህ ሁኖ ልጄ ከአንተ ጋር እንዲሆን አሰብኩ አለችው። እርሱም ጠየቃት እንዴት እንደተሰደደችም መረመራት እርሷም ሚስቱ እንደሆነች ነገረችው በዚያንም ጊዜ አወቃት ልጁን መርቆሬዎስንም አወቀው እጅግም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑት ያንንም የእንግዳ ማረፊያ ቤት ቤተ ክርስቲያን አደረጉት እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በአንድነት ኖሩ።
ከዚህም በኋላ አባቱና እናቱ በሞቱ ጊዜ ንጉሡ ቅዱስ መርቆሬዎስን ወስዶ በአባቱ ፈንታ በመርዶሳውያን አገር ላይ ሾመው። ቅዱስ መርቆሬዎስም መኰንንነትን በተሾመ ጊዜ ያ ገጸ ከልብ ከርሱ ጋር ነበር ወደ ጦርነትም አብሮት የሚወጣ ሆነ።
ለመዋጋትም በሚሻ ጊዜ የቀድሞ የአራዊት የሆነ ተፈጥሮውን እግዚአብሔር ይመልስለት ነበር ማንም ሊቋቋመው የሚችል የለም። ለቅዱስ መርቆሬዎስም ታላቅ የድል አድራጊነት ኃይል ተሰጠው ዜናውም በሁሉ ቦታ ተሰማ ከቤተ መንግሥት ሰዎችም ከፍ ከፍ አለ።
እንዲህም ሆነ ያን ጊዜ በዚያን ወራት በሮሜ አገር ጣዖትን የሚያመልክ ዳኬዎስ የሚባል ንጉሥ አለ። ጠላቶቹም የበርበር ሰዎች ተነሡበት። እርሱም ከእርሳቸው ጋር ሊዋጋ ሠራዊቱን ሰብስቦ ወጣ። እነርሱ ግን እንደ ባሕር አሸዋ ብዙ ነበሩ ብዛታቸውንም በአየ ጊዜ ደንግጦ እጅግ ፈራ። ቅዱስ መርቆሬዎስም እግዚአብሔር ያጠፋቸው ዘንድ በእጃችንም አሳልፎ ሊሰጣቸው አለውና አትፍራ አለው።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ የእግዚአብሔርን መልአክ በውጊያው ውስጥ አየው የተሳለ ሰይፍም በእጁ ውስጥ አለ ያቺንም ሰይፍ ሰጠውና እንዲህ አለው ጠላቶችህን ድል በአደረግህ ጊዜ ፈጣሪህ እግዚአብሔርን አስበው።
ጠላቶቹንም ድል አድርጎ በሰላም ተመለሰ መልአኩም ዳግመኛ ተገልጦለት ለምን የፈጣሪህን የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ረሳህ አለው።
ጦርነቱም ከተፈጸመ በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረግ በዓልን ሊያደርግ ወደደ። ቅዱስ መርቆሬዎስም ለበዓል ማክበር አብሮት አልወጣም ወደ ቤቱ ሔደ እንጂ። ሰዎችም ቅዱስ መርቆሬዎስ እንዳልመጣና ዕጣንን በማሳረግም እንዳልተባበረ አስረዱት።
በዚያንም ጊዜ ንጉሥ መልእክተኞችን ልኮ ቅዱስ መርቆሬዎስን ወደርሱ አስመጣው። በመዘግየቱም አድንቆ ለአማልክት ዕጣን ለማሳረግ ከእኔ ጋር ያልመጣህ የእኔን ፍቅር እንዴት ተውህ አለው። በዚያንም ጊዜ ትጥቁንና ልብሱን ወረወረለትና ንጉሡን እንዲህ አለው። እኔ ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም ለረከሱ ጣዖታትም አልሰግድም።
ንጉሥ ዳኬዎስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ። እርጥብ በሆኑ የሽመል በትሮች እንዲደበድቡት አዘዘ። ሁለተኛም ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ ይገርፉት ዘንድ አዘዘ ንጉሡ እንዳዘዘ ይህን ሁሉ አደረጉበት።
በዚያንም ጊዜ የአገር ሰዎች ስለ ቅዱስ መርቆሬዎስ እንዳይነሡበት ፈርቶ የቀጰዶቅያና የእስያ ክፍል ወደ ሆነች ወደ ቂሣርያ በብረት ማሠሪያ አሥሮ ላከው። በዚያም እንዲአሠቃዩት አዘዘ ከአሠቃዩትም በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ እንዳዘዘ ራሱን በሰይፍ ቆረጡትና ተጋድሎውን ፈጽሞ በመንግሥተ ሰማያት የሕይወት አክሊልን ተቀበለ።
የማይጠፋ ሰማያዊ አክሊልንም ተቀዳጅቶ ወደ ዘላለም ሕይወት ከገባ በኋላ በዓለሙ ሁሉ አብያተ ክርስተያናት ታነፁለት። እግዚአብሔርም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራትን በውስጣቸው ገለጠ።
ከተአምራቱም አንዲቱ ዑልያኖስ በነገሠ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ካደ። በዚያንም ወራት ቅዱስ ባስልዮስ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ነበረ ተአምራቱ በተጻፉበት መጽሐፍ እንደተጻፈ ምእመናን በጽኑዕ ሥቃይ ዑልያኖስ ባሠቃየ ጊዜ መክሮ አስተምሮ ከስሕተቱ ይመልሰው ዘንድ ቅዱስ ባስልዮስ ወደርሱ መጣ።
ዑልያኖስም ቅዱስ ባስልዮስን በአየው ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችንን ሰደበ። ቅዱስ ባስልዮስንም አሠረው። በዚያ በእሥር ቤትም የቅዱስ መርቆሬዎስን ሥዕል አይቶ በፊቱ ቅዱስ ባስልዮስ ጸለየ ሥዕሉም ከቦታው ታጣ። ያን ጊዜ ወደ ዑልያኖስ ሒዷልና በጦርም ወግቶ ገደለውና ወዲያውኑ ወደቦታው ተመለሰ ከጦሩም አንደበት ደም ይንጠፈጠፍ ነበር። ቅዱስ ባስልዮስም ከሀዲ ዑልያኖስን እንደገደለው አውቆ እንዲህ ብሎ ተናገረ የክርስቶስ ምስክር ሆይ የእውነት ፀር የሆነ ዑልያኖስን ገደልከውን ያን ጊዜ አዎን እንደሚል ሥዕሉ ራሱን ዘንበል አደረገ ቅዱስ ባስልዮስም ደስ ብሎት እግዚአብሔርን አመሰገነ።
የዚህም የቅዱስ መርቆሬዎስ ሌላው ተአምር ከምስር አገር ከመሳፍንት ወገን የሆነ አንድ የእስላም ወጣት ነበረ የእስላሞችንም ሕጋቸውንና መጻሕፍቶቻቸውን ተምሮአል። በአንዲትም ዕለት ወደ ባሕር ዳርቻ በመንገድ አልፎ ሲሔድ አንድ የተፈረደበትን ሰው አገኘ። አስቀድሞ እስላም የነበረ አሁን የክርስትና ጥምቀትን የተጠመቀ የንጉሥ ጭፍሮችም ይዘውታል። ሊአቃጥሉትም ጉድጓድን ምሰው በውስጡ ታላቅ እሳት አንድደው አዘጋጅተውለታል። ብዙዎች ሰዎችም ሲቃጠል ለማየት ተሰብስበው ነበር።
ያም የመስፍን ልጅ ወጣት እስላም ወደ ተፈረደበት ሰው ቀረብ ብሎ "አንተ ከሀዲ ሰው ወደ ሲኦል ለመግባት ለምን ትሮጣለህ በኋላም በገሀነም እሳት ውስጥ ለመኖር አንተ እግዚአብሔርን ባለ ልጅ ታደርገዋለህና ሦስት አማልክትንም የምታምን ነህና ክፉ ነገር ነውና ይህን ስድብ ትተህ እኔን ስማኝ" አለው ።
ያ የተፈረደበትም እንዲህ ብሎ መለሰለት "እኛ የክርስቲያን ወገኖች ሦስት አማልክትን የምናመልክ ከሀድያን አይደለንም። አንድ አምላክን እናመልካለን እንጂ ይኸውም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው። ወልድ ከአባቱ ከእግዚአብሔር ልዩ አይደለም። የራሱ ቃሉ ነው እንጂ። መንፈስ ቅዱስም ሕይወቱ ነው። የሃይማኖታችን ምሥጢር ከአናንተ የተሠወረ ድንቅ ነው። ዛሬ ለአንተ ልብህ ጨለማ ነው በውስጡ የሃይማኖት ብርሃን አልበራም በኋላ ግን ልብህ በርቶልህ እንደ እኔ ስለ ክርስቶስ ስም በመጋደል መከራውን ትቀበላለህ።"
ያም ወጣት እስላም በሰማው ጊዜ እጅግ ተቆጣ ጫማውንም ከእግሮቹ አውልቆ አፉን ፊቱንና ራሱን ጸፋው። ይህ የምትለው ከእኔ ዘንድ አይደረግም እያለ አብዝቶ አሠቃየ። የተከበረው ሰማዕትም ይህን ያልኩህን አስበህ የምትጸጸትበት ጊዜ አለህ አለው።
በዚያንም ጊዜ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው ሥጋውን ከእሳት ማንደጃ ውስጥ ጨመሩ ከዚህም በኋላ እሳቱ ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ታላቅ አጥር ሆነ። የንጉሥም ወታደሮች እየጠበቁት ሦስት ቀን ኖረ። ከዚህም በኋላ ከቶ እሳት ምንም ሳይነካው እንደ ተፈተነ ወርቅ ሆኖ ሥጋውን አገኙት። ይህንንም ለንጉሥ ነገሩት። እርሱም እንዲቀብሩት አዘዘ።
ያ ወጣት እስላም ግን እያዘነ ወደ ቤቱ ገባ እርሱ ክርስቲያን እንደሚሆን ስለተናገረው ከኀዘኑ ብዛት የተነሣ የማይበላና የማይጠጣ ሆነ። እናቱና ወንድሞቹም ወደርሱ ተሰብስበው የማትበላ የማትጠጣ በአንተ ላይ የደረሰ ምንድን ነው አሉት። ክብር ይግባውና ለጌታችን ኢየሱስ ምስክር የሆነው የተናገረውን ነገራቸው። እነርሱም ይህ አሳች የተናገረውን ተወው በልብህ አታስበው እያሉ አጽናኑት። እርሱ ግን ከቶ ምንም አልተጽናናም።
በዚያም ወራት ወደሐሰተኛ ነቢያቸው መቃብር ለመሔድ የሚሹ ሰዎችን አይቶ ከእሳቸው ጋር መሔድ እፈልጋለሁ ብሎ ለአባቱ ነገረው። አባቱም እጅግ ደስ ብሎት የሚበቃውን ያህል የወርቅ ዲናር ሰጠው ለወዳጁም አደራ ብሎ ሰጠውና አብሮት ሔደ።
በሌሊትም ሲጓዙ እነሆ ብርሃን የለበሰ አረጋዊ መነኰስ ተገለጸለት በፊቱም ቁሞ ትድን ዘንድ ና ተከተለኝ አለው እንዲሁም ሁለተኛና ሦስተኛ ተገልጦ ተናገረው።
በደረሱም ጊዜ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ አገራቸው ተመለሱ ሰባት ቀንም ያህል ተጓዙ። እነርሱም በሌሊት ሲጓዙ ስለ ሥጋዊ ግዳጅ ያ ወጣት ከገመል ላይ ወርዶ ለመጸዳዳት ዘወር አለ። ባልንጀሮቹም በበረሀ ውስጥ ትተውት ሔዱ ከእሳቸው ጋር የሚጓዝ መስሏቸዋልና በተነሣም ጊዜ ተቅበዘበዘ ወዴት እንደሚሔድ አላወቀምና አራዊትም እንዳይበሉት ፈርቶ ደነገጠ።
በዘያንም ጊዜ በምስር አገር በአባቱ ቤት አቅራቢያ ያለች የሰማዕት የቅዱሰ መርቆሬዎስን ቤተ ክርስቲያን አስታውሶ በልቡ እንዲህ አለ። ሰዎች ሁሉ በእርሷ ዘንድ እየተሳሉ ይፈጸምላቸዋል። በዚያንም ጊዜ የክርስቶስ ምስክር መርቆሬዎስ ሆይ በዚህ በረሀ ካሉ አራዊት አፍ በዛሬዋ ሌሊት ካዳንከኝና ያለ ጥፋት ካወጣኸኝ እኔ ክርስቲያን እሆናለሁ ብሎ ተሳለ።
ወዲያውኑ መልኩ የሚያምር ጎልማሳ የከበረ ልብስ የለበሰና የወርቅ መታጠቂያ በወገቡ የታጠቀ በፈረስ ተቀምጦ ወደርሱ መጣና አንተ ከወዴት ነህ እንዴት በዚህ በረሀ ውስጥ ጠፋህ አለው። ወጣቱም ስለ ሥጋ ግዳጅ ከገመል ላይ ወረድኩ ባልነጀሮቼ ትተውኝ ሔዱ አለው ባለ ፈረሱም ና በኋላዬ በፈረሱ ላይ ተፈናጠጥ አለው በዚያንም ጊዜ ወደ አየር በረረ በምስር አገር ወዳለች የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን እንደ ዐይን ጥቅሻ አደረሰውና እንደተዘጋች ከውስጧ አስገባው። ከፈረሱም ላይ አውርዶ በዚያ አቆመው ወደ መጋረጃ ውስጥም ገብቶ ከእርሱ ተሠወረ።
የቤተ ክርስቲያኑም መጋቤ በሌሊት በመጣ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍቶ ሲገባ ይህን ወጣት ከመካከል ቁሞ አገኘው። ደንግጦ ሊጮህ ፈለገ ጠቀሰውና ወደኔ ዝም ብለህ ና አለው ወደርሱም ሲቀርብ ይቺ ቦታ የማናት አለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መጋቢም ይቺ በምስር አገር ያለች የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ናት። አንተን ግን ልቡ እንደ ጠፋ ሰው ስትናገር አይሃለሁ ከዚህ ምን አመጣህ አሁንም ንገረኝ አለው። ወጣቱም እንዲህ ብሎ መለሰለት ልቤ እንዴት አይጠፋ እኔ በዛሬው ሌሊት በእገሌ በረሀ ሳለሁ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ሰው ተገለጠልኝና ከኋላው በፈረሱ አፈናጠጠኝ ከዚህም አድርሶ ተወኝ አለው።
መጋቢውም የዚያችን በረሀ ስም በሰማ ጊዜ አደነቀ እንዲህም አለው ልብህ ጠፍቷል በማለቴ መልካም የተናገርኩህ አይደለምን የምትናገረውን አታውቅምና የዚያ በረሀ መጠኑ የሃያ ሁለት ቀን ጉዞ የሚያስጉዝ ስለ ሆነ በእርግጥ አንተ ወንበዴ ነህ የቅዱስ ሰማዕት መርቆሬዎስ ኃይል ያለ ገመድ አሥሮሃል፣ እርሱ የዚህን ዓለም ክብር ንቆ የተወ፣ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ስም ከሀዲዎች ጽኑ ሥቃይ አሠቃይተው የገደሉት፣ ክርስቶስም በመንግሥቱ ውስጥ የተቀበለው፣ በቦታዎችም ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ታነፁለት በውስጣቸውም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። እርሱ መርቆሬዎስ ለተማፀነበት ሁሉ ይማልዳልና ድንቆች የሆኑ ታላላቅ ተአምራትንም ያደርጋልና።
ያም ወጣት መጋቢውን መልኩ እንዴት ነው ምን ይመስላል አለው መጋቢውም አካሉ አንተን ይመስላል አለው ይህንንም ብሎ ወደ ሥዕሉ ወስዶ ገልጦ አሳየው ወጣቱም በእገሌ በረሀ የታየኝ በእውነት ይህ ነው። በፈረሱም ላይ አፈናጥጦ ወደዚህ ያደረሰኝ ይህ ነው። እነሆ ታጥቋት በወገቡ ላይ ያየኋት የወርቅ መታጠቂያው ይቺ ናት። ስማኝ ልንገርህ እኔ በዚች አገር የምኖር አባቴም ስሙ ረጋ የሚባል መስፍን የሆነ እስላም የሆንኩ ሰው ነኝ። ክርስቲያንም ለመሆን ይች ምልክት ትበቃኛለች አሁንም በቦታ ውስጥ ሠውረኝ ለማንም ሥራዬን አትግለጥ። የክርስትና ትምህርትን አስተምሮ የእግዚአብሔርን መንገድ የሚመራኝን አምጣልኝ አለው። እርሱም ያለውን ሁሉ አደረገለት የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው።
ከዚህም በኋላ ወደ ነቢያቸው መቃብር የሔዱ እሊያ እስላሞች በአንድ ወራቸው ደረሱ። ዘመዶቻቸውም ሊቀበሏቸው ወጡ። ይህን ወጣት የመስፍን ልጅ ግን አላገኙትም። አባቱም አደራ ያስጠበቀውን ወዳጁን በጠየቀው ጊዜ እርሱም በበረሀ ውስጥ ቀርቶ እንደ ጠፋ እያለቀሰ ነገረው አባቱም በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀዶ አለቀሰ እንዲሁም ቤተሰቦቹ ሁሉም አርባ ቀኖች ያህል አለቀሱለት።
ከዚህም በኋላ በጥዋት ከቤተ ክርስቲያን ሲወጣ ይህን ክርስቲያን የሆነውን ወጣት አንድ እስላም አየው። ወደ ወላጆቹም ሒዶ እንዲህ ብሎ ነገራቸው ልጃችሁ በበረሀ ውስጥ የሞተ ከሆነ በመርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ያየሁት እርሱን ባልመሰለኝ ነበር፤ እስቲ ሒዳችሁ አረጋግጡ። በሰሙም ጊዜ በስውር ሒደው ፈለጉት አግኝተውትም ይዘው ወሰዱት። እንዲህም አሉት በወገኖቻችን መካከል ልታሳፍረን ይህ የሠራኸው ምንድን ነው አሉት። እርሱም እኔ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታዬና በፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ ብሎ መለሰላቸው።
ይህንንም ሲል ታላቅ ሥቃይን አሠቃይተው ከጨለመ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት። ሽንታቸውን በላዩ እየደፉ የቤት ጥራጊም እያፈሰሱበት ያለ መብልና ያለ መጠጥ በዚያ ሰባት ቀንና ሌሊት ኖረ። እናቱ ግን ቀንም ሌሊትም በላዩ የምታለቅስ ሆነች ከልቅሶዋም ብዛት የተነሣ ከጉድጓድ አውጥተው እኛ ወደማናይህ ቦታ ሒድ አሉት። ወዲያውኑ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሒዶ በዚያ እያገለገለና እየተጋደለ ሁለት ዓመት ኖረ።
ከዚህም በኋላ በላዩ የትንቢት ጸጋ ያደረበት አንድ መነኰስ ወደ ምስር ከተማ ሒደህ ሃይማኖትህን ከምትገልጽ በቀር በዚህ መኖር ለአንተ አይጠቅምህም አለው። ወዲያውኑ ተነሥቶ ወደ ምስር ከተማ ሔደ።
አባቱም በአየው ጊዜ ሐኪም ወደ ሚባል ንጉሥ ወስዶ ይህ ልጃችን ነበር የእስልምና ሃይማኖትን ትቶ ወደ ክርስቲያን ሃይማኖት ገብቷል አለው። ንጉሡም ስለአንተ የሚናገሩት ዕውነት ነውን አለው። እርሱም በበረሀ ውስጥ ሳለ በሌሊት ቅዱስ መርቆሬዎስ እንደ ተገለጸለትና ከእርሱ ጋር በፈረስ እንዳስቀመጠው፣ በምስር አገር ወዳለች ቤተ ክርስቲያኑ የሃያ ሁለት ቀን መንገድ እንደ ዐይን ጥቅሻ አድርሶ ከውስጥዋ እንዳስገባው፣ ሥዕሉንም አይቶ ያመጣው እርሱ መሆኑን እንደ ተረዳ ለንጉሡ ነገረው።
ንጉሡም በሰማ ጊዜ እጅግ አደነቀ። ታላቅ ፍርሀትም አደረበት አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምነኝ አለው። እርሱም በቅዱስ መርቆሬዎስ ስም ዳግመኛም በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን እንድሠራ ታዝልኝ ዘንድ እሻለሁ አለው።
ንጉሡም በአስቸኳይ እንዲታነፁለት አዘዘለት። በውስጣቸውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ። እርሱም አበ ምኔት ሁኖ ወደርሱ ብዙዎች መነኰሳት ተሰበሰቡ። ሁለት ድርሳናትንም ደረሰ። ከሀዲያንንም አስተምሮ ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሳቸው እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ ። ለዚህም መነኰስ የክርስትና ጥምቀትን በተቀበለ ጊዜ ያወጡለት ስም ዮሐንስ ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ መርቆሬዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages