ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 25 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 25

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ሃያ አምስት በዚህች ዕለት #የአቡነ_ዮሐንስ_ከማ_ዘግብጽ፣ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ #አቡነ_ዮሐንስ_ከማ_እጨጌ#አምስቱ_መቃባውያን ዕረፍታቸው ነው፡፡


ታኅሣሥ ሃያ አምስት በዚህች ዕለት የግብጹ አቡነ ዮሐንስ ከማ ዐረፈ፡፡ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ምእመናን ከእርሱም በቀር ልጅ የላቸውም በዚህም ዓለም በሠርጉ ደስ ይላቸው ዘንድ ወደው ላሕይዋ ደም ግባቷ ያማረ ድንግል ብላቴና ያለ ፈቃዱ አጋቡት። ወደ ጫጒላ ቤትም በሌሊት ገብቶ ዘወትር እንደሚጸልይ ቆመ ወዚያች ብላቴናም ቀረብ ብሎ "ይህ ዓለም ፍላጎቱ ኃላፊ እንደ ሆነ አንቺ ታውቂያለሽ ሥጋችንን በንጽሕና ለመጠበቅ እርስ በርሳችን እንስማማ ዘንድ ትፈቅጂአለሽን?" አላት። እርሷም "ወላጆቼ አስገድደው ላንተ አጋቡኝ እንጂ ሥጋዊ ፍትወትን እንዳላሰብኳት ሕያው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው አሁንም እንሆ እግዚአብሔር ልመናዬን ፈጸመልኝ" ብላ መለሰችለት።
ከዚህም በኋላ ድንግልናቸውን በንጽሕና ይጠብቁ ዘንድ ሁለቱም ተስማምተው በአንድነት በአንድ ዐልጋ ላይ እየተኙ ብዙ ዘመናት ኖሩ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ በመውረድ ክንፎቹን አልብሷቸው ያድራል። ከጽድቃቸውም ብዛት የተነሣ ማንም ያልዘራትንና ያልተከላትን የወይን ተክልን እግዚአብሔር በቤታቸው አበቀለ አድጋ ወጥታ ከቤታቸው ጣሪያ በላይ ተንሳፈፈች እርሷም የድንግልናቸውን መጠበቅ ታመለክታለች። ይህ ሥራ በሰው ተፈጥሮ ላይ ይከብዳልና ሁለት ወጣቶች በአንድነት የሚተኙ ከቶ የፍላጎት ሓሳብ አይነሣምን? እሳትን የሚታቀፍ ሥጋው የማይቃጠል ማን ነው? የእግዚአብሔር ረድኤት የምትጠብቀው ከልሆነች። ወላጆቻቸውም ብዙ ዘመን ሲኖሩ ልጅን እንዳልወለዱ ባዩ ጊዜ ጐልማሶች ስለ ሆኑ መሰላቸው።
ከዚህም በኋላ የከበረ ዮሐንስ ከማ ይህም ካም ማለት ነው እንዲህ አላት "እህቴ ሆይ እኔ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሒጄ እመነኵስ ዘንድ እሻለሁ ግን ያላንቺ ፈቃድ ምንም ምን ማድረግ አይቻለኝም" እርሷም "የምትሻውን አድርግ እግዚአብሔርም ከእኔ የተፈታሕ ያድርግህ" አለችው። ይህንንም በአለችው ጊዜ ወደ ደናግል ገዳም ወሰዳት በዚያም መንኵሳ እመምኔት ሆነች ድንቆች ተአምራቶችንም የምታደርግ ሆነች እግዚአብሔርንም አገለገለችው።
የከበረ ዮሐንስ ከማም ወደ አስቄጥስ ገዳም ይሔድ ዘንድ በወጣ ጊዜ ፊቱ የሚያበራ ሰው ተገለጠለትና ስለ አወጣጡ ጠየቀው ዮሐንስም ከማም "እግዚአብሔር ከፈቀደ እኔ መነኰስ መሆንን እሻለሁ" አለው። ያም ፊቱ የሚያበራ እንዲህ ብለቀ መከረው "ከአባ መቃርስ ገዳም ወደ ሚኖር ወደ ከበረ አባ ዳሩዲ በዓት ሒደህ በርሱ ዘንድ ኑር እርሱም ያመነኵስህ የምንኵስናንም ሥርዓት ያስተምርህ" ያም ፊቱ ብሩህ የሆነ ወደ አባ ዳሩዲ በዓት እስከ አደረሰው ድረስ እያጽናናው አብሮት ተጓዘ። ይህ አባ ዳሩዲም ተቀብሎ አመነኰሰው እስከ ዕረፍቱም ጊዜ የምንኵስናን ሕግና ሥርዓት አስተማረው።
ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ከአባ ዮሐንስ ሐጺር ገዳም በስተ ምዕራብ ሒዶ ለራሱ ከዚያ ማደሪያ ይሠራ ዘንድ አዘዘው ወደዚያም በሔደ ጊዜ ሦስት መቶ ሰዎች ወደርሱ ተሰበሰቡ የምንኵስናንም ልብስ አለበሳቸው ቤተ ክርስቲያንን ለራሳቸውም ማደሪያዎችን ሠሩ። ሥርዓትን ምስጋናን የእመቤታችንን የማርያምን ውዳሴ አስተማራቸው። በአንዲትም ዕለት የእመቤታችንን የማርያምን ውዳሴዋን በመንፈቀ ሌሊት ቁመው ሲጸልዩ የከበረ ሐዋርያዊ አትናቴዎስ ተገለጠለትና የረቀቁ ምሥጢሮችን ገለጠለት ከዚያችም ዕለት ወዲህ በሠለስቱ ደቂቅ ጸሎት ፍጻሜ የቅዱስ አትናቴዎስ ስም የሚጠሩ ሆኑ።
ከዚህም በኋላ በአንዲት ዕለት እመቤታችን የከበረች ድንግል ማርያም ተገለጣለት "ይህች ቦታ ለዘላለሙ የኔ ማደሪያ ናት እኔም ካንተ ጋር እንደኖርኩ ከልጆችህ ጋር እኖራለሁ ስሜም በዚህ ገዳም ሲጠራ ይኖራል" አለችው ይህች ቤተ ክርስቲያን አምላክን በወለደች በእመቤታችን ስም የተመሠረተች ናትና። በላይኛውም ግብጽ ገዳማት አሉ በውስጣቸውም የሚኖሩ መነኰሳት በእርሱ ጥላ ሥር መሆን ወደው ወደርሳቸው መጥቶ የርሱን ሥርዓተ ማኅበርና ሕግ ያስተማራቸው ዘንድ እየለመኑት ወደርሱ መልክትን ላኩ እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱን ስሙ ሲኖዳ የሚባለውን ጠርቶ "እኔ እስክመለስ ለመነኰሳቱ ቁሙላቸው" አለው። እርሱም አባ ዮሐንስ ከማ ከላይኛው ግብጽ እስሚመለስ በእግሮቹ ቆመ አላንቀላፋም በምድር ላይም አልተኛም።
በተመለሰም ጊዜ ቁሞ እግሮቹም አብጠው ተልተው ከእርሳቸው ትል ሲወጣ አገኘው አባ ዮሐንስም "ልጄ ሲኖዳ ሆይ ለምን ይህን አደረግህ እኔ ቁምላቸው ብሎ ያዘዝኩህ ስለ እኔ ሁነህ እንድታስተዳድራቸው ሥራቸውን እንድትቆጣጠር እንድታዝዛቸውም ነበር" አለው። እርሱም ከእግሮቹ በታች ሰግዶ "አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ ከበጎ ሥራ ምንም ምን አልሠራሁምና" አለው።
ከዚህም በኋላ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ድካም ተለይቶ በዘላለማዊ የተድላ ማደሪያ የሚያርፍበት ጊዜ ሲቀርብ ጥቂት ታሞ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ በዚህች ቀን አስረከበ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ኢትዮጵያዊው አቡነ ዮሐንስ ከማ ዘእጨጌ ዐረፉ፡፡ ይኸውም ጻድቅ አባት አገራቸው ሰሜን ጎንደር ነው፡፡ በብዙዎቹ ቅዱሳን ገድል ላይ ታሪካቸው ተደጋግሞ የተጠቀሰ ሲሆን ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ደጋግሞ ያመሰገናቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ከቀደምት አንጋፋ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ሲሆኑ መጽሐፍ "ኮከብ ዘገዳም" ይላቸዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ይህኛውንም አባት ግብፃዊ ናቸው ይሏቸዋል፡፡ ነገር ግን ስማቸውን ከላይ ከጠቀስናቸው ከግብፃዊው አባት ከአባ ዮሐንስ ከማ ጋር አንድ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያዊው አቡነ ዮሐንስ ከማ ትግራይ የሚገኘውን ቀብፅያ ገዳምን የቆረቆሩ ሲሆን ብዙ ቅዱሳን አባቶችንም በማመንኰስ የቤተ ክርስቲያን ከዋክብት የተባሉትን ቅዱሳን መነኰሳትን አፍርተዋል፡፡ በገዳማቸው ቀብፅያ የምትገኘው እጅግ አስገራሚዋና ተአምራትን የምትሠራው መቋሚያቸው ዛሬም ድረስ አለች፡፡
1250 ዓመት ያስቆጠረችውን ይህችን የጻድቁን ተአምረኛ መቋሚያ ሀገሬው በጠመንጃ ይጠብቃታል፡፡ እንደ ሰው ድምፅ የምታሰማበት ጊዜ አለ፡፡ ጻድቁ ሰሜን ጎንደር ምድረ ጸለምት ትልቅ ገዳም አላቸው። ዕረፍታቸው በዚህች ቀን ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ዕለት አምስቱ መቃብያን በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡ እነዚህም ቅዱሳን በሜዶናውያንና በሞዓባውያን ዘመነ መንግሥት የነበሩ ናቸው፡፡ ክፋትን የሚወዳት ስሙ ጺሩጻይዳን የሚባል አንድ ንጉሥ ነበር ከሥልጣኑም በታች የጸኑ ጭፍሮች አሉ የሚያመልካቸው ኃምሳ በወንዶች ሃያ በሴቶች አምሳል የተሠሩ ጣዖቶች አሉት በጥዋትና በማታ መሥዋዕትን ያቀርብላቸዋል ሰዎችንም እንዲሠዉ ያስገድዳቸው ነበር።
ከብንያም ወገንም የሆነ ስሙ መቃቢስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ ለርሱም መልከ መካሞች የጸኑ ሦስት ልጆች አሉት ከእርሳቸውም ግሥላውን እንደ ዶሮ አንቆ የሚገድል አለ። በአንዲት ዓመታትም አንበሳ የሚገድል አለ እነርሱም ውበትንና ግርማን የተሸለሙ ናቸው ከሁሉ የሚሻል የልብ ውበትንም እነርሱ የሥጋ ሞትን ያልፈሩ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ናቸውና። ንጉሡም "እናንት ዓመፀኞች ለአማልክቶቼ እንዴት አትሰግዱም" አላቸው እነርሱም በአንድ ቃል "እኛ ለረከሱ አማልክቶችህ አንሰግድም እኛንም አንተንም ለፈጠረ ሕዝቡንም በዕውነትና በቅንነት ትጠብቅ ዘንድ ላነገሠህ አንተ ቸለል ብለህ ለዘጋኸው ለእግዚአብሔር እንሰግዳለን እንጂ" ብለው መለሱለት።
ከዚህም በኋላ የተራቡ አራዊትን በላያቸው እንዲሰዱ አዘዘ እነዚያም ለቅዱሳን ሰግደው ተመልሰው ከከሀድያን ሰባ አምስት ሰዎችን ገደሉአቸው። እሊህንም ቅዱሳን ወደ ወህኒ ቤት ጨመሩአቸው ሌሎች ሁለት ወንድሞቻቸውም መጥተው ከእርሱ ጋር ተቀላቀሉ። ንጉሡም አምስቱን ወንድማማቾች አይቶ እጅግ ተቆጥቶ ከሚነድ እሳት ውስጥ ይጨምሩአቸው ዘንድ አዘዘ ነፍሳቸውንም በእግዚአብሔር እጅ አስረከቡ።
ከዚህም በኋላ የቅዱሳኑን ሥጋ አመድ እስከሚሆን ያቃጥሉ ዘንድ ዳግመኛ አዘዘ እሳቱም ከቶ አልነካቸውም ዳግመኛም ከባዶች ደንጊያዎችን ከሥጋቸው ጋር አሥረው ከባሕር ውስጥ ያሰጥሟቸው ዘንድ አዘዘ ባሕሩም አልዋጣቸውም ለዱር አራዊትና ለሰማይ ወፎች እንዲጥሏቸው አዘዘ አዕዋፍም ክንፎቻቸውን ጋርደውላቸው ዐሥራ አራት ቀኖች ኖሩ ሥጋቸውም እንደ ፀሐይ አበራ ከዚህ በኋላ ይቀብሩአቸው ዘንድ አዘዘ።
ከዚህም በኋላ ያንን የእግዚአብሔርን ሕግ የዘነጋ ንጉሥ ሌሊት በዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ እሊህ ቅዱሳን ተቆጥተው ሰይፋቸውን መዝዘው በፊቱ ቁመው ታዩት በነቃም ጊዜ የሚበቀሉት መስሎታልና ፈርቶ ተንቀጠቀጠ። እነዚያም የከበሩ ሰማዕታት "ክፉ ነገርን ስላደረግህብን እኛስ ክፉ ነገርን አንከፍልህም በነፍስ ፍዳ የሚያመጣ እግዚአብሔር ነውና ፍዳንስ የሚከፍልህ ፈጣሪያች እግዚአብሔር አለ። ነገር ግን ስለዕውቀትህ ማነስና ስለ ልቡናህ ድንቁርና እኛ ደኅነኞች እንደሆን ተገልጠን ታየንህ እኛንስ የገደልከን መስሎህ ድኅነትን አዘጋጀህልን። የጣዖቶችህ ካህናትና አንተ ግን ለዘላለሙ መውጫ ወደሌለባት ወደ ገሀነም ትወርዳላችሁ" አሉት ከዚህም በኋላ ከርሱ ተሠወሩ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages