አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት ሃያ አምስት በዚች ቀን የከበሩ #ቅዱስ_አውሳንዮስ፣ #ቅዱስ_ፊልሞና፣ #ቅድስት_ሉቅያ ድንግልም በሰማዕትነት ሞቱ፣ የከበረ ሐዲስ #ቅዱስ_እንጦኒ (ረውሕ) በሰማዕትነት ሞተ፣ ከግብጽ አገር ከእስሙናይን አውራጃ የሆነ የከበረ አባት #ቅዱስ_አቡፋና አረፈ።
የካቲት ሃያ አምስት በዚች ቀን የከበሩ አውሳንዮስና ፊልሞና ስሟ ሉቅያ የሚባል አንዲት ድንግልም በሰማዕትነት ሞቱ።
እሊህ ቅዱሳንም በአፍራቅያ ሀገር ሳለ በከበረ ሐዋርያ ጳውሎስ ትምህርት ያመኑ ናቸው ከሀድያንም ዝሑራ በሚባል ኮከብ ስም ለሚጠሩት ለአርታዳሚ ጣዖት በዓልን በአደረጉ ጊዜ አይተው በስሕተታቸው ሊዘብቱ እሊህ ቅዱሳን ተሰብስበው ወደ ጣዖቱ ቤት ገቡ ሰዎችም ለጣዖቱ ሲሠዉና ከፍ ከፍ ሲያደርጉት በአዩአቸው ጊዜ በክብር ባለቤተ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እሳትነት ልባቸው ነደደ ከጣዖቱም ቤት ወጥተው ወደ ክርስቶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሔደው የክብር ባለቤት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብሩንና ልዕልናውን አብዝተው አመሰገኑ።
ከዚያ ካሉት አንድ ሰው በሰማቸው ጊዜ በጣዖታቸው ላይ እንደ ዘበቱ የተናገሩትን ልብ ብሎ በመኰንኑ ዘንድ ወነጀላቸው መኰንኑም በፈረስ ተቀምጦ ሔደ ከወታደሮቹም ጋር ቤተ ክርስቲያኒቱን ከበባት ከምእመናንም ሰዎች የሸሹ አሉ። እሊህንም ሦስቱን ቅዱሳን ያዛቸው የብረት ዘንጎችን በእሳት አግለው በቅዱሳኑ ጐኖች ውስጥ አደረጉት ከዚህም በኋላ የከበረ አውሳንዮስን ወደ ጒድጓድ ወረወሩትና ነፍሱን እስከ ሰጠ ድረስ በደንጊይ ወገሩት።
የከበረ ፊልሞናንና የከበረች ሉቅያን ግን ብዙ ጊዜ በጸና ሥቃይ ያሠቃዩአቸው ጀመር ነፍሳቸውንም ይወስድ ዘንድ እግዚአብሔርን ለመኑት እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ነፍሳቸውን ወሰደ።
በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ እነሆ የምስክርነታቸውና የሃይማኖታቸው መታሰቢያ ተጽፎአል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት የከበረ ሐዲስ እንጦኒ በሰማዕትነት ሞተ ይህም ረውሕ የሚባል ነው። ይህም ከከበሩ ዐረቦች ወገን የቆሮስ ሰው የሆነ ብዙ ገንዘብ ያለው ነው በሰማዕታት አለቃ በቴዎድሮስ ገዳም አጠገብ በወንዝ ዳርቻ የሚኖር ነው ይህም ጐልማሳ አብያተ ክርስቲያናትን የሚቃወም ሁኖ ቅዱስ ቍርባንን በመስረቅ ኀብስቱን ይበላዋል የከበረ ደሙንም ከጽዋው ውስጥ ይጠጣል የመሠዊያውንም ልብስ ገፎ በእሳት ያቃጥለዋል በክርስቲያን ሃይማኖትም ላይ ይዘብታል።
መኖሪያ ቤቱ ከከፍታ ቦታ ላይ ስለ ሆነ ካህናት ሲያገለግሉ ይታዩት ነበር። በአንዲትም ዕለት በቅዳሴ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ተከፍቶ አየ በፈረስም ተቀምጦ መጣ የቅዱስ ቴዎድሮስንም ሥዕል ተመልክቶ በፍላፃዎች ወጋው ። አንዲቱም ፍላፃ ተመልሳ መሐል እጁን ነደፈችው በጭንቅም ከእጁ ላይ መዘዛት ይህንንም ለማንም አልነገረም።
በሌላዪቱም ዕለት በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ሳለ መሥዋዕትን ተሸክመው ወደ መቅደስ ሲገቡ ካህናትን አያቸው በጻሕሉም ውስጥ ነጭ በግ ተኝቶ ከበላዩ ነጭ ርግብ ሲጋርደው በቅዳሴውም ፍጻሜ ያ በግ በየመለያያው የተከፋፈለ ሆኖ ካህናቱም ከተከፋፈለው ሥጋውን ሲቀበሉ ደሙንም ከጽዋው ውስጥ ሲቀበሉ አየ እጅግም አደነቀ። በልቡም የክርስቲያን ሃይማኖት እጅግ ድንቅ ነው በእውነትም የከበረ ክቡር ነው አለ። ዳግመኛም ያ በግ ተመልሶ እንደ ቀድሞው ኑሮው ሕያው ሁኖ አየ ከዚህም በኋላ ከመቀመጫው ወርዶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ሔዶ ያየውን ሁሉ ለካህናቱ ነገራቸው እነርሱም ሰምተው ስለዚህ ድንቅ ሥራ ደስ አላቸው።
በዚያችም ሌሊት ተግቶ ሲጸልይ ሊቅ ቴዎድሮስ ተገለጠለት እርሱም በፈረሱ ላይ ተቀምጦ ነበር እንዲህም አለው እነሆ በእኔ ላይ ሥዕሌን እስከ ወጋህ ድረስ ክፉ ሠራህ በክብር ባለቤት ክርስቶስ ሥጋ ላይም ዘበትክ አሁንም ከክህደትህ ተመልሰህ በክብር ባለቤት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አለው ይህንም ብሎ ከእርሱ ተሠወረ።
በማግሥቱም በፈረሱ ላይ ሁኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱም ገብቶ ከእርሱ የሆነውን ሁሉ ነገረው ሊቀ ጳጳሳቱም ሰምቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው እርሱንም በሕዝብ ፊት አጠምቅህ ዘንድ እፈራለሁ ነገር ግን ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሒድ ጌታችን ክርስቶስም የሚያጠምቅህን ይሰጥሃል አለው።
እርሱም ሰምቶ ወደ ዮርዳኖስ ሔዶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገባ የሌሊቱም እኩሌታ ሲሆን የብርሃን እናት ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም ነጭ ሐር ግምጃ ለብሳ ተገለጠችለት ከእርሷም ጋር በንጹሕ ልብስ የተሸለመች ሴት ነበረች በእጅዋም ይዛ አነሳችውና አትዘን እኔ ካንተ ጋር እኖራለሁና አለችው።
ሲነጋም ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በሔደ ጊዜ ሁለት ገዳማውያን መነኰሳትን አገኛቸው እነርሱም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቁት። ስሙንም እንጦንስ ብለው ሰየሙት የምንኲስና ልብስ አሰኬማንም አልብሰው በሰላም አሰናበቱት ወደ ደማስቆም ሔዶ ወደ ቤቱ ገባ።
ባልንጀሮቹና ወገኖቹም በአዩት ጊዜ የለበሰከው ምንድን ነው አሉት እኔ ክርስቲያን ነኝ አላቸው በዚያንም ጊዜ ይዘው በሜዳ ውስጥ እየጐተቱ ወደ መኰንኑ እስኪያደርሱት ይደበድቡት ነበር። መኰንኑም ወደ እሥር ቤት እንዲጨምሩት አዘዘ በታላቅ ሥቃይም ዐሥራ ሰባት ሌሊት በዚያ ኖረ እነሆ በላዩ ብርሃን ወረደ እንዲህም የሚል ቃል ሰማ እንጦንዮስ ሆይ አክሊል ተዘጋጅቶልሃልና አትፍራ ብርሃንን የለበሱ ሁለት አረጋውያንም መጥተው በራሱ ላይ የብርሃን አክሊልን አኖሩ በነጋ ጊዜም ወደ አደባባይ ወስደው ራሱን በሰይፍ ቆረጡትና በዕንጨት ላይ ሰቀሉት።
በሌሊትም በላዩ ብርሃን ወረደ ጠባቆችም አይተው ከዕንጨት ላይ አወረዱት በጤግሮስም አቅራቢያ ቀበሩት ከመቃብሩም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት ከግብጽ አገር ከእስሙናይን አውራጃ የሆነ የከበረ አባት አቡፋና አረፈ። ይህም አባት ከቶ ብርሃን በሌለበት ዋሻ ውስጥ የሚኖር ሁኖ በየሁለት ቀን ይጾማል የሚበላውም የሚጠጣውም በመለኪያ ተለክቶ ነው በሌሊትም በመዓልትም አምስት መቶ ጊዜ ይጸልያል።
በአንዲትም ዕለት ወንድሞች ሊጐበኙት ወደርሱ መጡ እንጀራንም አጣ ሦስት እንጀራንም በአገኘ ጊዜ ለሃያ ሰዎች አቀረበላቸው እነርሱም በልተው ጠገቡ ተአምራትንም እያደረገ በሽተኞችንም እየፈወሰ ኖረ።
ከዚህም በኋላ እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ ወደርሱ መጣ አቡፋና ሆይ ዐሥራ ስምንት ቀረህ የከበረ አቡፋናም ዐሥራ ስምንት ዕለታት እንደሆኑ አስቦ እሊህ ዕለቶች እስቲፈጸሙ ቆመ ከዚህም በኋላ ሱባዔዎች ናቸው ብሎ ይህንንም በመቆም ፈጸመ እንደገና ወሮች ይሆናሉ ቢሆኑስ ብሎ ይህንንም በመቆም ሳያጓድል አደረሰ። ዳግመኛም እንዲህ የሚል ቃል ወደርሱ መጣ አቡፋና ሆይ ዐሥራ ስምንት ዓመት ናትና ጽና በርታ አለህ እግዚአብሔር አለው በዚያንም ጊዜ ፈጽሞ ጸና።
በዋሻው ደጃፍ የውኃ ምንጭ ነበረ ምሳርንም ወረወረበት ምሳሩም ነቢይ ኤልሳዕ እንዳደረገው በውኃ ላይ ተንሳፈፈ። የከበረች የአርባ ቀንን ጾም ከሦስት ቀኖች በቀር ሳይበላ ፈጸመ። ሲበላም ሲያንቀላፋም ግድግዳ ተጠግቶ ነው እግሮቹም እንደዝሆን እግር እስከሚሆኑ እንዲህ ተጋደለ።
በአንዲትም ዕለት ለደቀ መዛሙርቱ እነሆ ዓለም አለፈ አላቸው በጠየቁትም ጊዜ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ሞተ አለ በአንዲትም ዕለት ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር የያዘ እንግዳ በአንድ ቄስ ቤት አደረ በተኛ ጊዜ ስለ ገንዘቡ ቄሱ ገደለውና ወስዶ ከአንድ መነኵሴ ደጅ ጣለው ለቅዱስ አቡፋናም በነገሩት ጊዜ ከሟቹ ላይ እንዲጥሉበት ቆቡን ሰጣቸው ሲጥሉበትም ሟቹ ተነሣ ስለ ገንዘቡ ቄሱ እንደ ገደለው ነገራቸው እጅግም አደነቁ።
በአንዲትም ዕለት አንድ ሰው ቡራኬ ሊቀበል ወደርሱ ሲመጣ ልጁ በጉዞ ላይ ሞተ ልጁንም ተሸክሞ ወደ ቅዱስ አቡፋና ሔደ በፊቱም ሰግዶ ተባርኮ ተመለሰ ያን ጊዜ የሞተው ብላቴና ተነሥቶ አባቱን ተከተለው።
ከቆመ ጀምሮ ዐሥራ ስምንቱ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ ዕረፍቱን አውቆ ቅዱስ ቍርባንን ተቀበለ ወደ መኖሪያውም ሒዶ ራሱን ዘንበል አድርጎ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ለዘለዓለሙ ከእኛ ጋር ትሁን አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment