ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት ፳27 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, March 5, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት ፳27

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት 27


" ቅዱስ አንስጣስዮስ ሊቅ "
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የካቲት ሃያ ሰባት በዚች ቀን በታላቁ ንጉሥ በቈስጠንጢኖስ ዘመን የከበረ አባት የአንጾኪያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ትምህርቱ በዓለም የመላ አንስጣስዮስ አረፈ።
የከበሩ አባቶችም በኒቅያ ከተማ የአንድነት ስብሰባ በአደረጉ ጊዜ በዚህ ጉባኤ ከተሰበሰቡት ሊቃውንት አንዱ እርሱ ነው በዚህም ጉባኤ ተስማምተው አርዮስን ከባልንጀሮቹ ጋር አውግዘው ለይተውታል ባልንጀሮቹም የቂሣርያ አውሳብዮስ የኒቆምድያ አውሳብዮስና አርናሲስ ናቸው። እሊህም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ታውቀዋል።
እሊህም የከበሩ አባቶች ሥርዓትን ሠርተው ወደየሀገራቸው በተመለሱ ጊዜ እሊህ ከኤጲስቆጶስነት ሹመት የተሻሩት ወደ ኢየሩሳሌም የሚሔዱ መስለው ወጡ ወደ አንጾኪያም ከተማ ገብተው ከአንዲት አመንዝራ ሴት ዘንድ ተሰበሰቡ ብዙ ገንዘብም ሊሰጧት ቃል ገቡላት ወደ ቤተክርስቲያን እንድትገባ ይህ አባት ከእርሷ ጋር እንዳመነዘረ የወለደችውም ልጅ የእርሱ እንደሆነ በዚህ ቅዱስ አባት አንስጣስዮስ ላይ ለካህናቱና ለሕዝቡ እንድትናገር አስተማሩዋት።
ሕዝቡም እንዲህ አሏት አንቺ ሐሰተኛ ነሽ በዚህ ቅዱስ አባትም ላይ ሐሰትን ተናግረሻል በከበረ ወንጌል ካልማልሽ በቀር ቃልሽን አንቀበልም አሏት እርሷም ስለ ገንዘብ ፍቅር በሐሰት ማለች። ከዚህም በኋላ ለንጉሥ ነግረው ከመንበረ ሢመቱ ወደ አጥራክያ ደሴት አሳደዱት በስደትም ሳለ በርሷ አረፈ።
ነገር ግን ለእሊህ ከሀድያን ወዮላቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ከመለኮቱ ባሕርይ ለይተው ፍጡር ነው ብለውታልና ይህንንም ንጹሕ አባት ሰይጣን አባታቸው እንዳስተማራቸው ከአመንዝራ ጋር አንድ ሁነው በተንኰል ከመንበረ ሢመቱ አውጥተውታልና።
እግዚአብሔር ግን ቸለል አላለም ይህን አባት ከአሳደዱት በኋላ ያቺ አመንዝራ ሴት ጭንቅ በሆነ ደዌ ተይዛ ብዙ ተሠቃየች ለሞትም ተቃረበች ያን ጊዜም ይህ ሁሉ የደረሰባት በከበረ ወንጌል በሐሰት ስለማለች እንደሆነ ተገነዘበች። በአንጾኪያም ሰዎች ሁሉ ፊት በደሏን አመነች እንዲህም አለቻቸው ይህ ቅዱስ አንስጣስዮስ ከዝሙት ንጹሕ ነው እነዚያ ከሀድያን ብዙ ገንዘብ ሰጥተውኝ በእርሱ ላይ ሐሰት እንድናገር በከበረ ወንጌልም በሐሰት እንድምል አደረጉኝ እንጂ።
የአንጾኪያ አገር ሰዎችም ኃጢአቷን ማመኗን በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ ካህናቱም በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜ ስሙን የሚያነሱ ሆኑ ዮሐንስ አፈወርቅም አመሰገነው በመታሰቢያውም ቀን ስለ ርሱ ብዙ ቃላትን ደረሰ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
፨፨፨
አርኬ
ሰላም እብል አንስጣስዮስሃ ፍጹመ። ትምህርታቲሁ ዘመልዐ ኵሎ ዓለመ። እኩያን ዕደው እለ ተዓጽፋ መርገመ። ነገረ ሐሰት ላዕሌሁ እንዘ ይነቡ ሕሱመ። ኅበ ሰደድዎ አዕረፈ ወኖመ።
፨፨፨
በዚችም ዕለት የመድኃኒታችን የስቅለቱ መታሰቢያ ነው ይቅርታውና ቸርነቱ ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

የካቲት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አንስጣስዮስ ርቱዓ ሃይማኖት (ዘአንጾኪያ)

ወርኀዊ በዓላት
1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
5.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
6.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
7.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
የተጠራችሁለት ለዚህ ነው:: ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና:: እርሱም ኃጢአት አላደረገም:: ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም:: ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም:: መከራንም ሲቀበል አልዛተም . . . እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ:: (1ጴጥ. 2፥21-25)
፨፨፨፨
ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።
፨፨፨፨
ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።
ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።


No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages