አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥር ሃያ ስምንት በዚህች ቀን #ጌታችን_ተአምራትን በማድረግ ሰባት እንጀራና ጥቂት ዓሣ አበርክቶ ብዙ ሰዎችን ያጠገበበት መታሰቢያ ነው፣ የከበረ #ቅዱስ_ቀሌምንጦስ በሰማዕትነት ሞተ፣ #መነኰስ_ቅዱስ_አካውህ በሰማዕትነት ሞተ፣ የከበረ አይሁዳዊ የማኀው ልጅ የእመቤታችን ወዳጅ #ቅዱስ_ዮሴፍ አረፈ።
(ጌታችን 5 እንጀራ 2 ዓሣ አበርክቶ 5 የገበያ ሕዝብ እንደመገበ)
ጥር ሃያ ስምንት በዚህች ቀን ጌታችን ተአምራትን በማድረግ ሰባት እንጀራና ጥቂት ዓሣ ቆራርሶ አበርክቶ ብዙ ሰዎችን ያጠገበበት መታሰቢያ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገበው ይህ የጌታችን ተአምር በውስጡ ብዙ ምሥጢራትን የያዘ ነው እንጂ ስለ ሥጋዊ ምግብ ብቻ የተነገረ አይደለም፡፡ ማቴ 14፡13-23፡፡ የተመገቡትና የተቆጠሩት አምስት ሺህ ወንዶች ብቻ ናቸው እንጂ ሴቶችና ሕጻናት አልተቆጠሩም፡፡ ይህስ ለምን ነው ቢሉ ሴቶች በአደባባይ ሲበሉ በሃፍረት ዳር ዳር ስለሚሉ ነው፡፡ ሕጻናት ደግሞ ከሚበሉት የሚፈረፍሩት ይበዛልና ነው፡፡
ጌታችን ያንን ሁሉ ሕዝብ በመንደር አጠገብ ሊመግባቸው ሲችል ለምን አርቆ ወደ ምድረ በዳ ወሰዳቸው ከተባለ ስለ ሁለት ምክንያት ነው፡፡
አንድም ‹‹ጥንት አባቶቻችሁን ከመንደር (ከግብጽ) አውጥቼ አርባ ዘመን ሙሉ መና የመገብኳቸው እኔ ነኝ፤ አሁንም በሥልጣኔ በተአምራቴ መገብኳችሁ›› ሲላቸው ነው፡፡
አንድም ጌታችን ተአምራቱን ከመንደር አጠገብ አድርጎት ቢሆን ኖሮ ሁልጊዜ ክፋትንና ጠማማ ነገርን ማሰብ ለአይሁድ ልማዳቸው ነውና ‹‹ፈጣን ፈጣን ደቀ መዛሙርቱን በጎን ወደ መንደር እየላከ ያስመጣው ነው›› ይሉት ነበር፡፡ ስለሆነም ጌታችን ለጥርጥር ምክንያት እንዳይኖራቸው አድርጎ ነው ተአምራቱን የገለጠላቸው፡፡ ጊዜውም አመሻሽ ላይ ነበርና ምሽት ላይ ያደረገበትም ምክንያት ጠዋት ላይ ቢሆን ኖሮ ‹‹የበላነው ሳይጎድል ነው ያበላን›› ብለው ከማመን ይርቁ ነበር፡፡
በተጨማሪም በበረሃ ያውም በምሽት ሕዝቡን በውኃ አጠገብ በሣር ላይ አስቀምጧቸው መመገቡ ‹‹በፍጻሜው ዘመን በምቹ ስፍራ በመንግሥተ ሰማያት መንፈሳዊ ምግብ እመግባችኋለሁ፤ በውኃ (በጥምቀት) በሚገኝ ክብርም አከብራችኋለሁ›› ሲላቸው ነው፡፡ ተአምራቱን ከውኃ ዳር ማድረጉ ‹‹መታጠቢያ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን›› እንዳይሉ ነው፡፡ ሳር የበዛበት ቦታ ላይ ማድረጉም ‹‹መቀመጫ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን›› እንዳይሉ ነው፡፡
አምስቱ እንጀራ የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር ማለትም የምሥጢረ ሥላሴ፣ የምሥጢረ ሥጋዌ፣ የምሥጢረ ጥምቀት፣ የምሥጢረ ቁርባንና የምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ሁለቱ ዓሣ ደግሞ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔር ማለት እግዚአብሔር አምላክን በፍጹም ነፍስና በፍጹም ሐሳብ መውደድ ነው፡፡ ፍቅረ ቢጽ ደግሞ ባልንጀራን እንደራስ አድርጎ መውደድ ነው፡፡ አንድም ደግሞ እንጀራውና ዓሣው የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምሳሌ ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ኪራስ ከሚባል አገር ስሟ አክሮስያ የምትባል የመበለት ልጅ የከበረ ቀሌምንጦስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም የሆነ በገላትያ ነገሥት በአርአያኖስና በሉቅዮስ ዘመን ነው ከታናሽነቱም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሥርዓቷንና ሕጓንም እናቱ አስተማረችው ዕድሜውም ዐሥራ ሁለት ዓመት ሲሆነው በጾምና በጸሎት መጋደል ጀመረ አገልግሎትንም አበዛ በእሳት የበሰለ ሥጋም ቢሆን አይበላም ነበር። እንደ ሠልስቱ ደቂቅ ጥሬ ባቄላ የሚመገብ ሆነ እንጂ ዲቁናም ተሾመ ጥበብና እውቀትም ተጨመረለት።
ወሬውም በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ በተሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀርቦ ብዙ ሸነገለው ለርሱም ልጁ ያደርገው ዘንድ ቃል ገባለት ትእዛዙንም ባልሰማ ጊዜ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው እግዚአብሔርም አጸናው ያለ ጉዳትም በጤንነት አስነሣው ከሀድያንንም አሳፈራቸው።
በዚያንም ጊዜ የምስክርነቱ ተጋድሎ በዲዮቅልጥያኖስ እጅ ሰባት እስቲደርስ አንድ ተብሎ ተቈጠረለት። ማሠቃየቱንም በደከመ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስ ወደ ሮም ንጉሥ ላከው እንዲህም ብሎ ጻፈ ይህ መሠርይ ከቶ እንደርሱ ያለ መሠርይ አላየሁም ለአማልክትም ይሠዋ ዘንድ ምናልባት ልቡን መመለስ ብትችል እነሆ ወዳንተ ላክሁት።
ወደ ሮሜው ንጉሥም በደረሰ ጊዜ የወርቅ ልብሶችን አመጡለት እርሱም ወደ ልብሶች አልተመለከተም ንጉሡም በእርሱ ላይ ተቆጣ ቊጣውንም አልፈራም በዚያንም ጊዜ በመንኰራኵር ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ገረፈውም ሕዋሳቱንም አስቆራረጠ እግዚአብሔርም እንደ ቀድሞው ያለ ጥፋት በጤንነት አስነሣው ይህም ሁለተኛ ምስክርነት ነው።
ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ወደ ኒቆምድያ ከተማ ወደ መክስምያኖስ ላከው በዚያም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃዩት ጌታችንም እንደቀድሞው በጤንነት አስነሥቶት ጠላቶቹን አሳፈራቸው ይህም ሦስተኛ ምስክርነት ነው።
ከዚህም በኋላ ወደ አደገባት ወደ ኪራስ ከተማ መለሱት በዚያም አሠቃዩት ጌታችንም በጤንነት ያለሥቃይ አስነሣው ይህም አራተኛ ምስክርነት ነው።
ዳግመኛም ወደ መክስምያኖስ መለሱት በዚያም ቅዱስ ከልከላዎስንና ብዙ ሰማዕታትን አግኝቶ እርስ በርሳቸው ተጽናኑ የከበረ ቀሌምንጦስንም ጽኑ ሥቃይን አሠቀዩት ጌታችንም እንደቀድሞው አዳነው ይህም አምስተኛ ምስክርነት ነው።
ከዚህም በኋላ ወደ መኰንን ሉቅዮስ ወሰዱትና በዚያ አሠቃዩት ጌታችንም አዳነው ይህም ስድስተኛው ምስክርነት ነው።
ሰባተኛውም ምስክርነት ብዙ ከአሠቃዩት በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡ ሶፍያ የምትባል አማኒት ሴት መጥታ የቅዱሱን ሥጋ ወስዳ ገንዛ ቀበረችው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የከበረ መነኰስ አካውህ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ፍዩም ከሚባል አገር ነው በምንኵስናውም ታላቅ ተጋድሎን ሲጋደል የኖረ ነው ሰይጣንም ተገልጦ መጣበት ቅዱስ አካውህም ሰይጣንን ይዞ በራሱ ጠጉር አሠረውና ሊቀጣው ጀመረ። ሰይጣንም ትለቀኝ ዘንድ በክርስቶስ መከራዎች አምልሃለሁ ብሎ ጮኸ በዚያንም ጊዜ ሰደደው እንደ ጢስም ተበተነ።
ከዚህም በኋላ በስደት ወራት ወደ ከሀድያን አደባባይ ሔደና እኔ ክርስቲያን ነኝ ብሎ ጮኸ ከሀድያንም ጽኑ ሥቃይን አሠቃይተው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ። ከእርሱም ጋር ስምንት መቶ የሆኑ የቅዱስ አካውህ መኅበር በሰማዕትነት ሞቱ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_ዮሴፍ_አይሁዳዊ (የእመቤታችን ወዳጅ)
በዚህችም ቀን የከበረ አይሁዳዊ የማኀው ልጅ ዮሴፍ አረፈ። ይህም ቅዱስ እስራኤላዊ ነው የአይሁድንም ሃይማኖት እየተማረ አደገ መጻሕፍቶቻቸውንም ተማረ።
በአንዲትም ዕለት እየተማሩ ሳለ የክርስቲያንን ልጆች አያቸው ከእርሳቸውም ጋር ትደምረው ዘንድ እናቱን ለመናት። በደመረችውም ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ሁሉ ተማረ የክርስቶስ ሃይማኖት ፍቅርም በልቡ አደረ ከዚህም በኋላ የቤተ ክርስቲያንን ሕግ ከሚወድና ከሚጠብቅ ከአንድ ክርስቲያናዊ ወጣት ጋር ተገናኘ እርሱም በቊርባን ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰደው ዮሴፍም ሥጋውንና ደሙን ተቀበለ።
በማግሥቱም አናጉንስጢሶችና መዘምራን ከዮሴፍ ጋር ተሰበሰቡ ልብሶቻቸውንም እንደ ድንኳንና እንደ መጋረጃ አምሳል በመሥራት ከቤታቸውም ዳቦ አመጡ በጨዋታ መልክ ከውስጣቸው ሊቀ ጳጳሳትን ኤጲስቆጶሳትን ሾሙና የቊርባን ሥርዓት ሠሩ ወደሚያስተምራቸውም መምህር ቤት ሔደው ይበሉ ይጠጡ ነበር እንዲህም እያደረጉ ኖሩ።
የዮሴፍም አባት በሰማ ጊዜ ቊጣን ተመልቶ ልጁን የግንግሪት አሠረው በውስጡ እሳትን የተመላ ጉድጓድ ወዳለበት ወህኒ ወስዶ ጨመረውና በላዩ የእቶኑን በር ዘጋበት የእግዚአብሔርም መልአክ እሳቱን አቀዘቀዘው እናቱ ግን ልጅዋን በአጣችው ጊዜ በመጮህ አለቀሰች የምታደርገውንም አጣች።
ከሰባት ቀኖችም በኋላ የዮሴፍን ወሬ ወደ እሳት እንደተጨመረ ባልንጀሮቹ ሰምተው በመጮህ እያለቀሱ ስሙንም እየጠሩ መጡ ዮሴፍም ከውስጥ እንዲህ ሲል መለሰላቸው በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት በእመቤቴ ማርያም ርዳታ እኔ በሕይወት አለሁና ወንድሞቼ አታልቅሱ እርሷም ከእሳቱ በልብሷ ሸፍና አድናኛለችና ይህንንም በሰሙ ጊዜ ለሊቀ ጳጳሳቱ ነገሩት። እርሱም ወዲያውኑ ተነሣ ከካህናቱ ጋር ወንጌልን መስቀልንና ማዕጠንቶችን ይዘው ሔዱ ወደ እቶኑም በደረሱ ጊዜ ጸሎትን አድርገው ዮሴፍን ከማሠሪያው ፈትተው አወጡት።
አባቱ ማኅውም በሰማ ጊዜ መጥቶ ከሊቀ ጳጳሳቱ እግር በታች ወድቆ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አመነ የክርስትና ጥምቀትንም ያጠምቀው ዘንድ ለመነውና ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር አጠመቀው።
ዮሴፍ ግን ከዋሻ ገብቶ በየሰባት ቀን እየጾመና እየጸለየ በገድል ተጠምዶ ሃያ ስምንት ዓመት ያህል ኖረ ከዚህም በኋላ ዕረፍቱ እንደቀረበ በአወቀ ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወደሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ በቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት ቁሞ ወደ ተወዳጅ ልጅዋ ትማልድለት ዘንድ ለመናት ከሥዕሉ ውስጥም እንዲህ አለቸው ዮሴፍ ሆይ በሦስተኛው ቀን በሦስት ሰዓት ወደኔ ትመጣለህና ደስ ይበልህ በዚያችም ዕለት በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment