ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 27 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 27

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ሃያ ሰባት በዚህች ቀን #የቅዱስ_ሱርያል ሊቀ መልአክ በዓል ነው፡፡ የያሬድ ልጅ #ቅደስ_ሄኖክ_ነቢይ የተሰወረበት ነው፣ የከበረ #ቅዱስ_ሰራብዮን በሰማዕትነት ሞተ፣ የከበረ ሐዋርያ #ቅዱስ_ጢሞቴዎስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ የከበረ #ቅዱስ_ቢፋሞን በሰማዕትነት ሞተ።


ጥር ሃያ ሰባት በዚህች ቀን የሊቀ መልአክ ሱርያል በዓል ነው፡፡ እርሱም ከሊቃናት አንዱ ነው፡፡ ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም:: የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው::
በሦስቱ ሰማያት ካሉት ዘጠኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ (የሥልጣናት) መሪ (አለቃ) ነው:: መልአኩ እጅግ ርሕሩሕ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው:: ለኖኅ መርከብን ያሳራው: ከጥፋት ውኃም ያዳነው፣ ከነቢይ እዝራ ጋር የኖረ የተሠወረ ምሥጢርንም የገለጠለት ነው እና ስለ ሰው ልጆች ወደ እግዚአብሔር የሚለምን ነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው::
በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው:: ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እሥራልዩ" ይባላል:: "የእሥራኤል ረዳት" እንደ ማለት፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የያሬድ ልጅ ሄኖክን የመላልኤል ልጅ የቃይናን ልጅ የኄኖስ ልጅ የሴት ልጅ የአዳም ልጅ ኄኖክን መላእክት ይዘው አሳረጉት ይኸውም በመባርቅትና በነፋሳት ላይ ተጭኖ በመብረር ወደ ሰማይ ወስደው ከረቂቃን መላእክት ጋር አኖሩት የእግዚአብሔርም ትእዛዝ ጸሐፊ ተባለ።
እንዲህም አለ ከማደሪያው ከሚወጣው ከቅዱሱና ከገናናው በጸናች ኃይሉ ከሠራዊቱ ጋር በሲና ተራራ ከሚገለጠው ጋር በመነጋገር ተመላለስኩ። ሁሉም ይፈሩ ነበር በውኃ ዳርም ሳለሁ የልመናቸውን መታሰቢያ ጻፍኩ እስከ አንጎላቸሁና ሕልም እንደሚያይ እስከምሆን ይችም በአርሞን ግራና ቀኝ ያለች አገር ናት።
በደብር ቅዱስ ለነበሩ ለኃጢአት ለሚተጉ ለሴት ልጆች ይዘልፋቸው ዘንድ ቃል እንደጠራውና እንዳሳየው ተናገረ። እንዲህ አለ በበረድ ደንጊያ ወደ ተሠራ ታላቅ ቤት ቀረብኩ በበረድ ደንጊያ የተሠራ የዚያ ቤት ግድግዳ እንደ ሳንቃ ልዝብ ነው ከዚህ ቤት የሚበልጥም ሌላ ቤት አየሁ ደጃፉም የተከፈተ ነው በእሳት ቅጽርም የተሠራ በክብር ከሁሉ የሚበልጥ ነው።
በውስጡም ከፍ ያለ የእግዚአብሔርን ዙፋን አየሁ መልኩም እንደ ውርጭ ነው አጎበሩም እንደሚያበራ ፀሐይ ነው ከዙፋኑም በታች የኪሩቤል ድምፅ ይሰማል። ዳግመኛም ወደ ሰባት ተራራዎች ደረስኩ ሦስቱ በምሥራቅ በኵል ሦስቱ በአዜብ በኵል ናቸው የመካከለኛው ግን ሰማይ ጠቀስ ነው የመላእክትም ጌታ በላዩ አለ።
ሌሎች አራት ገጾች ኪሩቤልን አየ ስለ ክርስቶስም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ የዘመናት አለቃ ወደ ሆነው የሰው ልጅ ተጠራ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ የነበረ ሆነ ሁለተኛም ለጻድቃን የጽድቅ በትር ለአሕዛብም ብርሃን ተስፋ ለሌላቸውም አለኝታ ይሆናል አለ።
በሰማይ ገጽ ስለሚመላለሱ ብርሃናት እንዲህ አለ አንዱም አንዱ በየወገናቸው በሠለጠኑበትና በተሠየሙበት ጸንተው ይኖራሉ ስለ ነፋሳትም መውጫዎች እንዲህ ብሎ ተናገረ ሦስቱ በሰማይ ገጽ ሦስቱ በምድር ገጽ ሦስቱ በቀኝ ሦስቱ በግራ ናቸው። ስለ አዳምም እንዲህ አለ እነሆ በሬ ከምድር ወጣ ፀዓዳም ሆነ ስለ ሔዋንም ደግሞ ሴት እምቦሳ ከርሱ ወጣች አለ።
ስለ ምኵራብም ያንን አሮጌ ቤት እስከሚአሳንሰው ድረስ አየሁ አለ ምሰሶዎቹንም ከውስጡ አወጣ። ሰለ ቤተክርስቲያንም ጌታ አዲስ የበጎች ቤት አምጥቶ እስቲሠራ ድረስ አየሁ ከቀድሞውም ቤት የበለጠ ነው በጎችም ሁሉ በውስጧ ይሠማራሉ አለ። ስለ ምእመናንም የእሊህም በጎች ፀጕራቸው ንጹሕ ነጭ ነው የተበተኑትም ከአራዊት ጋራ ይሠማራሉ ሁሉም በአንድነት ተሰብስበው ገራሞች ሆነዋልና።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት ከግብጽ ደቡብ ከታችኛዪቱ ምስር አውራጃ በብኑዲ ከምትባል መንደር የከበረ ሰራብዮን በሰማዕትነት ሞተ። ለዚህም ቅዱስ ብዙ የገንዘብ ጥሪት እንስሳትም አሉት አብዝቶ መመጽወትንም የሚወድ ነው ስደትም በሆነ ጊዜ የክርስቲያን ወገኖችን ፈልጎ ያሠቃይ ዘንድ መኰንኑ ኄሬኔዎስ በየሀገሩ እንደሚዞር ሰማ ለርሱም ስማቸው ቴዎድሮስና ሁለተኛውም በግ አርቢ ሰርማ የሚባሉ ወዳጆች ነበሩት እነርሱም ተከተሉት ይህም ቅዱስ መኰንኑን ሊገናኘው ከሀገሩ ወጣ መኰንኑንም በአገኘው ጊዜ በፊቱ ቁሞ ከወገኖቹ ጋር በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ሁሉንም አሠራቸው።
የሀገር ሰዎችም በሰሙ ጊዜ ሁሉም ተሰብሰቡ መኰንኑን ገድለው ቅዱስ ሰራብዮንን ከእጁ ሊወስዱ ሽተው የጦር መሣሪያ በመያዝ ለጦርነት የተሰለፉ ሠራዊት ሁነው ደረሱ ቅዱሱ ግን ከለከላቸው እንዲህም አላቸው እኔ በጌታዬ ክርስቶስ ስም ደሜን አፈስ ዘንድ በፈቃዴ የመጣሁ አይደለምን መኰንኑም በመርከብ ተሳፍሮ ከዚያ ሔደ ቅዱሳኑም አብረውት ሔዱ።
ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰ ጊዜ የከበረ ሰራብዮንን በመንኰራኵር ውስጥ ጽኑዕ ሥቃይን እንዲአሠቃዩት ወደ እሳት ማንደጃም ይጨምሩት ዘንድ አዘዘ። ከዚህም በኋላ ከነዳጅ ድፍድፍና ቅመማቅመም ጋር በወጭት ውስጥ ቀቀሉት የሥጋውንም ሥሮች ቆረጡ በብረት ዐልጋ ላይም አስተኝተው በችንካር ቸነከሩት ይህን ሁሉ ሥቃይም የሚታገሥ ሆነ የእግዚአብሔርም መልአክ ሥቃዩን ከላዩ ይቀበልለት ነበር።
ከዚህም በኋላ ከእንጨት ላይ ሰቅለው በፍላፃዎች ነደፉት የእግዚአብሔርም መልአክ እርሱን ከተሰቀለበት አውርዶ በእርሱ ፈንታ መኰንኑን አሥሮ ሰቀለው። የከበረ ሰራብዮንም እንዲህ አለው ሕያው እግዚአብሔርን በክርስቶስ ስም የታሠሩትን ሁሉንም እስከምታወጣቸውና የሞታቸውን ፍጻሜ እስከምታዝዝ አንተ ከእዚህ ከተሰቀልክበት ዕንጨት እንደማትወርድ ዕወቅ። በዚያንም ጊዜ ሁሉንም አውጥተው ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጧቸው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ የእነዚህም ሰዎች ቊጥራቸው አምስት መቶ አርባ ነፍስ ሆነ።
ከዚህም በኋላ የከበረ ሰራብዮንን ወደ ሀገሩ ከእርሱ ጋር ወስዶ ያሠቃየው ዘንድ ከኀሳቡም ካልተመለሰ እራሱን በሰይፍ ይቆርጥ ዘንድ ኄሬኔዎስ አንዱን መኰንን አዘዘው። መኰንኑም ከርሱ ጋር በመርከብ ወሰደው ሌሊትም በሆነ ጊዜ ወደ አንድ ወደብ ደርሰው በዚያ ተኙ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ያቺ መርከብ ወደ ቅዱስ ሰራብዮን አገር ደረሰች በጥዋትም በነቁ ጊዜ የመሔጃቸው አቅጣጫ ተለውጦ አገኙ እጅግም አደነቁ ወደ ሰራብዮንም እነሆ ይቺ ሀገርህ ናት የሚል ቃል ከሰማይ መጣ ከመርከብም አውርደው ታላቅ ሥቃይን አሠቃይተው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ። መኰንኑም ልብሶቹን አውጥቶ ገንዞ ለዘመዶቹ ሰጠው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የከበረ ሐዋርያ ጢሞቴዎስ ከኤፌሶን አገር ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ የሥጋው ፍልሰት ሆነ። ጻድቁ ቈስጠንጢኖስም መንግሥትን በያዘ ጊዜ የከበሩ የሐዋርያትን ሥጋቸውን ከሰማዕታትም ብዙዎችን ከቦታው ሁሉ ወደ ቊስጥንጥንያ አፈለሳቸው ስለ ሐዋርያ ጢሞቴዎስም ሥጋ በኤፌሶን አገር እንዳለ ሰምቶ ካህናትንና ምእመናንን ላከ እነርሱም አፍልሰው ወደ ቊስጥንጥንያ አድርሰው በከበሩ ሐዋርያት ቤተ መቅደስ ውስጥ አኖሩት።
(ሙሉ ታሪኩ የጥር 23 ስንክሳር ይመልከቱ)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የከበረ ቢፋሞን በሰማዕትነት ሞተ፡፡ ይህም ከታናሽነቱ ድንግል የሆነ እግዚአብሔርን የሚወድ ለድኆችና ለችግረኞች የሚመጸውት ይህንንም ዓለም ንቆ የተወ ነው። አባቱም ከከበሩ ወገኖች የሆነ ስሙ አንስጣስዮስ የእናቱም ስም ሶስና ነው። እነርሱም መመጽወትን የሚወዱ ክርስቲያኖች ናቸው የጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን የከበሩ ሰማዕታትንም ሁሉ በዓላት ለድኆችና ለምስኪኖች ምጽዋትን በመስጠት ያከብራሉ የሚኖሩትም በምስር አውራጃ አውሲም በሚባል አገር ውስጥ ነው።
እግዚአብሔርም መልኩ እጅግ ያማረ ይህን የተባረከ ልጅ ቢፋሞንን ሰጣቸው በእርሱም ደስ ብሏቸው በጎ መሥራትንና ትሩፋትን አበዙ አድጎ ወደ ዘጠኝ ዓመትም ሲደርስ ያሰተምረው ዘንድ እግዚአብሔርን ለሚፈራ አንድ ቄስ ሰጡት እርሱም ተቀብሎ ወስዶ ጥበብን ጽሕፈትን ተግሣጽን አስተማረው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንም መጻሕፍት አጠና በቤተ ክርስቲያንም ሁል ጊዜ ያገለግላል እጅግ በመትጋትም በጾም በጸሎት በመስገድ ይጋደል ነበር።
እግዚአብሔርም በእጆቹ ብዙዎች የሆኑ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ ከእሊህ በቊስል ደዌ እጆቹንና እግሮቹን የታመመ አንድ ድኃ ነበረ የከበረ ቢፋሞንን ምጽዋትን ለመነው ሊሰጠውም እጁን ሲዘረጋ በዚያን ጊዜ ከደዌው ድኖ ጤነኛ ሆነ ሕዋሳቱም ሁሉ ጠነከሩ።
ሁለተኛም በሌላ ጊዜ በዳዊት መዝሙር ሲያመሰግን ከዚያ አንድ ጋኔን የሚጥለው ሰው ነበረ የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ ተወኝ ከዚህ ቦታ ልጥፋ በሎ ጮኸ የከበረ ቢፋሞንም ወደ ጌታችን ጸልዮ ያንን ጋኔን ያደረበትን ሰው አዳነው መምህሩም አይቶ አክብሮትን ለቢፋሞን ጨመረ። እርሱ ያለ ማቋረጥ በመንፈሳዊ ትሩፋት ሥራ የሚያድግ ሁኗልና የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማደሪያው ውስጥ የሚገለጥለት ሆነ ቅዱሳን መላእክቶቹም ከርሱ ጋር አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያምም በአንድነት ያጽናኑት ነበር በመምህሩም ዘንድ ስምንት ዓመት ኖረ።
ከዚህም በኋላ እየተጋደለ ኖረ በየሰባት ቀንም በመጾም ከሰንበት ቀን በቀር አይበላም ወላጆቹ ሚስት እንዲአገባ ጠየቁት እርሱም በዚህ በሚአልፍ ዓለም ከሴት ጋር መኖር ለእኔ ምኔ ነው ፍላጎቱ ሁሉ ያልፋልና አላቸው። ወላጆቹም በርሱ ደስ አላቸው በጎ መሥራትንም ጨመሩ። ከዚህም ነገር በኋላ በሰባተኛው ወር አባቱ አረፈ የከበረ ቢፋሞንም ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ምጻዋትን አብዝቶ ሰጠ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም የተጠመደ ሆኖ የከበረ የወንጌልን ትእዛዞች ለመፈጸም ይጋደል ነበር።
በዚያንም ወራት የፋርስ ሰዎች በሮም ሰዎች ላይ ጦርነት አስነሥተው ነበር የሮም ንጉሥም በጦርነት ሙቶ መንግሥት ያለ ንጉሥ ተቀመጠች መኳንንቱ እና የመንግሥት ታላላቆች ተሰብስበው ተማከሩ ከሁሉ አገሮችም ተዋጊዎች የሆኑ አርበኞችን ይሰበስቧቸው ዘንድ አዘዙ። ከላይኛውም ግብጽ ልበ ደንዳና የሆነ አንድ ሰው ተገኘ እርሱም ስሙ አግሪጳዳ የሚባል የሰይጣን ማደሪያ የሆነ ፍየሎችን የሚያረባ ነው ወደ አንጾኪያ ከተማም ወስደው ለመንግሥት ፈረሶች ባልደራስ አድርገው ሾሙት።
በአንዲትም ዕለት ሁለት ሸምበቆ አንሥቶ በአንድነት አሥሮ ዋሽንት ነፋባቸው በፈረሶች ሰይጣን አደረባቸውና ፈረሶችም እየጨፈሩ ያሽካኩ ጀመር የሞተውም ንጉሥ ሴት ልጅ በቤተ መንግሥት አዳራሽ ሁና በመስኮት ሲዘፍንና ዋሽንት ሲነፋ አግሪጳዳን አይታው እጅግ አማራት ሰይጣንም በልቧ የዝሙትን ፍላጎት ጨመረ ወደርሷም አስጠራችውና አገባችው ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ አሰኝታ አነገሠችው። ታናሽ እኅቷም ታላቂቱ እኅቷ ያደረገችውን በአየች ጊዜ ቀናች እርሷም መክስምያኖስ የሚባል አንድ መኰንን መልምላ አገባች ልብሰ መንግሥትም አልብሳ ንጉሥ አደረገችው መክስምያኖስና ዲዮቅልጥያኖስም በአንጾኪያና በሮም ተስተካክለው ነገሡ።
ከዚህም በኋላ ሰይጣን ተገለጠላቸውና እንዲህ አላቸው ነገሥታት እስከአደረግኋችሁ ድረስ በንጉሡ ሴቶች ልጆች የዝሙትን ፍቅር በልባቸው የጨመርኩ እኔ ነኝ። አሁንም ትእዛዜን ከሰማችሁ በምድር የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉንም በእጆቻችሁ ውስጥ አደርጋቸዋለሁ እናንተም ስገዱልኝ የወርቅና የብር ምስሎችንም ሠርታችሁ አማልክት በሏቸው ስማቸውንም አጵሎን፡ አርዳሚስ ብላችሁ ጥሩአቸው ሰዎችንም ሁሉ ዕጣን እንዲአሳርጉላቸው እንዲሰግዱላቸውም እዘዟቸው አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ ዝጉ የአማልክትንም ቤቶች ክፈቱ ትእዛዛችሁን ሰምተው ለአማልክት የማይሰግዱትን ግን በየአይነቱ በሆነ በጽኑዕ ሥቃይ አሠቃዩአቸው ራሶቻቸውንም በሰይፍ ቊረጡ።
እሊህም ሰነፎች ዲዮቅልጥያኖስና መክስምያኖስ በሰሙ ጊዜ ሰገዱለትና እኛ የአዘዝከንን ሁሉ እናደርጋለን አሉት። በዚያንም ጊዜ በግብጽ አገር ሄሬኔዎስንና አርያኖስን ሁለቱን መኳንንቶች ሾሙ ለጣዖት የማይሰግዱትን ሁሉ እንዲአሠቃዩ አዘዙአቸው። የከበረ አባ ቢፋሞንም ይህን ዜና በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ የሆነውንም እስቲረዳ ድረስ ተሠወረ ወዳጁን ቴዎድሮስንም ጠራውና በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ደማቸውን ያፈሱ ዘንድ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ ከክፉ ነገርም ሁሉ ያድናቸው ዘንድ በአንድነት ጸለዩ።
የከበረ ቢፋሞንም በጎ ሥራን አብዝቶ ይሠራ ነበር ወሬውም በንጉሥ መክስሚያኖስ ዘንድ ተሰማ እንዲህ ብለው ከሀዲዎች ነግረውታልና በምስር አውራጃ በአውሲም ከተማ ስሙ ቢፋሞን የሚባል አንድ ሰው አለ እርሱም የነገሥታትን ትእዛዝ የሚተላለፍ አማላክትን የሚረግምና የሚያቃልል ነው።
በዚያንም ጊዜ የከበረ ቢፋሞንን ለአማልክት እስከሚዐጥን ድረስ እንዲአሠቃየው ያለዚያም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጥ ንጉሥ ወደ አርያኖስ ደብዳቤ ጽፎ ላከ የእግዚአብሔርም መልአክ የሆነውን ይነግረው ዘንድ ለአባ ቢፋሞን ተገለጠለት በሰማዕትነትም እንደሚሞት እናቱም እንደምትሞት አስረዳው እግዚአብሔርም ያዘጋጀላቸውን አክሊላት አሳየው አገልጋዩን ዲዮጋኖስን ከእርሱ ጋር እንዲወስደው አዘዘው።
ያን ጊዜ ተነሣ ወደ እናቱም ገብቶ ያየውን ሁሉ ነገራት እርሷም ይህንኑ ራእይ እንዳየች ነገረችው በአንድነትም ደስ አላቸው ወደ ማደሪያውም ሒዶ እስቲነጋ ድረስ ሊጸልይ ቆመ በነጋ ጊዜ ወደ ወዳጁ ቲዎድሮስ ልኮ አስመጣው ራእይንም እንዳየ ነገረው ከዚህም በኋላ እንዲህ ብሎ አዘዘው የመከራው ወራት ካለፈ በኋላ በዚች አገር አንተ ኤጲስቆጶስነት ትሾማለህና ቤተ ክርስቲያን ሥራልኝ ይህንንም ነግሮት ሰላምታ ተለዋውጠው ተሳስመው ተለያዩ።
ከጥቂት ቀኖች በኋላ ወደ አውሲም ከተማ መኰንኑ አርያኖስ ደረሰ የሀገር ታላላቆችንም አቅርቦ ስለ ከበረ ቢፋሞን ጠየቃቸው እርሱ አማልክትን እንደሚረግም ሰምቷልና የሀገር ሽማግሌዎችም ስለ ቅዱስ ቢፋሞን አዘኑ እርሱ በእነርሱ ዘንድ ተወዳጅ ነውና። በዚያንም ጊዜ አባ ቢፋሞን ተነሥቶ ረጂም ጸሎትን ጸለየ ቤተ ሰቦቹንም ሁሉ ተሰናበታቸው ያማሩ ልብሶችንም ለብሶ በነጭ ፈረስ ተቀምጦ የአገር ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወዳሉበትም ሔደ እነርሱም በአዩት ጊዜ አክብረው ሰላምታ ሰጡት ተከትለውትም ወደ መኰንኑ ወደ አርያኖስ ሔደ አርያኖስም አባ ቢፋሞንን በአየው ጊዜ ደስ አለው ከወንበሩም ተነሥቶ ሰላም ላንተ ይሁን ብሎ ሰላምታ ሰጠው።
አባ ቢፋሞንም እንዲህ ብሎ መለሰለት ለምን ሰላም ትለኛለህ የሰላም ትርጓሜው ደስታ ነውና ለእኔ ግን በጌታዬ በፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ አለኝ ለአንተና ለባልንጀሮችህ በሰማያት ደስታ የላችሁም ብሏል መጽሐፍ። አርያኖስም እኔ ክፉ ነገርን እንድትነግረኝ አልመጣሁም ለአማልክት እንድትሠዋ በንጉሡ ደብዳቤ ታዝዤ መጣሁ እንጂ አለው::
ቅዱሱም መልሶ ይህ አይገባም ትክክለኛውስ ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ ለእርሱም እንድንሰግድ ይገባል እሊህ አማልክቶቻችሁ አፍ አላቸው አይናገሩም ዓይን አላቸው አያዩም ጆሮ አላቸው አይሰሙም አፍንጫ አላቸው አያሸቱም እጅ አላቸው አይዳስሱም እግር አላቸው አይሔዱም በአንደበታቸውም አይናገሩም በአፋቸው ውስጥ ትንፋሽ የለምና የሠሩአቸውም እንደነርሱ ይሁኑ እኔ ግን ሰማይና ምድርን በውስጣቸው ያለውን ሁሉ ከፈጠረ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለሌላ አልሰግድም አለው።
አርያኖስም ከቅዱስ ቢፋሞን አፍ ይህን ነገር ሰምቶ እጅግ ተቆጣ በየዓይነቱም ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ዳግመኛም በፈረስ ጅራት አሥሮ መላ ከተማውን አስጎተተው እናቱና አገልጋዮቹም ሁሉ ወደርሱ መጡ እነርሱንም ከከበረ የወንጌል ቃል አስተማራቸው ገሠጻቸውም በዚያንም ጊዜ በግልጽ እኛ ክርስቲያን ነን ብለው ጮኹ የመኰንኑን ወንበር ገለበጡ መኰንኑም ጒድጓድ እንዲቆፍሩላቸውና እሳትንም አንድደው በውስጡ በሕይወት ሳሉ እንዲወረውሩአቸው አዘዘ እንዳዘዘውም አደረጉባቸው ቊጥራቸውም አምስት መቶ ነው።
ምስክርነታቸውንም እስኪፈጽሙ የከበረ ቢፋሞን ያጽናናቸውና ያስታግሣቸው ነበር እናቱም ልጅዋ ቢፋሞንን በላይዋ እንዲጸልይ ለመነችው እርሱም በመስቀል ምልክት በላይዋ አማተበና በሰላም ሒጂ አላት በዚያንም ጊዜ ሰውነቷን በእሳት ውስጥ ጣለች። ከእነሱ ጋርም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለች።
የከበረ ቢፋሞንን ግን አርያኖስ ወደ ንጉሥ መክስምያኖስ ሰደደው ንጉሡም የነገሥታትን ትእዛዝ የምትተላለፍ ለአማልክት የማትሰግድ ሥራየኛው ቢፋሞን አንተ ነህን አለው። ቅዱሱም ሥራይን ግን አላውቅም ለረከሱ አማልክትም አልሰግድም አንተና አማልክቶችህ በአንድነት ወደ ገሀነም እሳት ትወርዳላችሁና አለው ንጉሡም ተቆጥቶ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ከማሠቃየትም በሰለቸ ጊዜ ወደ ኄሬኔዎስ ሰደደው እርሱም ወደ አርያኖስ ሰደደው በእነዚያ ቀኖችም ምንም አልበላም።
አርያኖስም ወስዶ በብረት ችንካሮች ቸነከረውና ለአማልክት ካልሰገድክ አጠፋሃለሁ አለው ቅዱሱም እርሱንና አማልክቶቹን ዘለፈ ረገማቸውም ከዚህም በኋላ በከተማዪቱ ሁሉ መንገድ እንዲጎትቱትና ከእንዴናው ከተማ ውጭ በእሳት እንዲአቃጥሉት መኰንኑ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት ጌታችንም ያለ ጥፋት በጤና ከእሳት ውስጥ አወጣው የከበረ ቢፋሞንም ከእሳት ውስጥ ቁሞ በነበረ ጊዜ ከእግሮቹ ብዙ ደም ፈሰሰ ከሕዝብ ጋር የቆመ አንድ ሰው ነበረ እርሱም ለምጻምና ዕውር ነበር ከደሙም ወስዶ ዓይኖቹን ቀባ ያን ጊዜ አየ ከለምጹም ነጻ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታመን ክርስቲያን ነኝ ብሎ ጮኸ ራሱንም እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘና ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
የከበረ አባ ቢፋሞንንም ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አርያኖስ አዘዘ ቢፋሞንም አገልጋዩን ዲዮጋኖስን እንዲህ ሲል ሥጋውን በሥውር እንዲጠብቅ ደሙንም በበፍታ ልብስ እንዲቀበል ገድሉንም በአውሲም አገር ላሉ ምእመናን እንዲነግር አዘዘው የመከራው ወራት ያልፍ ዘንድ አለውና ከዚህም በኋላ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ብሎ በመስቀል ምልክት አማተበ ወደ ጭፍሮችም ቀርቦ የታዘዛችሁትን ፈጽሙ አላቸው እነርሱም ወደ ሌላ ቦታ ብቻውን ወስደው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት ።
ከአንገቱም ብዙ ደም ፈሰሰ አገልጋዩ ዲዮጋኖስም ከእርሱ ዘንድ ያለውን በፍታ ዘርግቶ የቅዱስ ቢፋሞንን ደም ተቀበለበት። በዚያም ቦታ እጅግ ጣፋጭ የሆነ መዓዛ መላ ጭፍሮች እስኪያደንቁና እስኪደነግጡ ድረስ ታላቅ ፍርሀት ወረደባቸው ከዚያም ቦታ ሸሹ።
ከዚህም በኋላ ምእመናን መጥተው ሥጋውን ወሰዱ ብዙ ሽቱ አምጥተውም በመዘመር በክብር ገነዙት ከከተማም ውጭ ተሸክመው ወስደው ቀበሩት ከመቃብሩም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ አገልጋዩም ያቺን በፍታ ወስዶ ጠበቃት ወደ ሀገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜ የሚፈራ ሆነ ምን እንደሚያደርግም አሰበ የከበረ ቢፋሞንም ተገለጠለትና ለወዳጁ ለቴዎድሮስና ለሀገሩ ሰዎች ዜናውን እንዲነግር አዘዘው እግዚአብሔርም ምእመናን ሰዎችን ላከለት እነርሱም ከእርሳቸው ጋር በመርከብ አሳፍረው ወሰዱት በመርከብም ውስጥ ሳለ የክብር ባለቤት ጌታችን ከዚያች በፍታ በከበረ ቢፋሞን ደም ከታለለችው ተአምራትን ገለጠ አገልጋዩ ዲዮጋኖስም ገድሉን ነገራቸው አደነቁ ጌታችንንም አመሰገኑት እርሱንም ወደ አገሩ ወደ አውሲም አደረሱት ዲዮጋኖስም ለወዳጁ ለቴዎድሮስና ለሀገሩ ሰዎች ሁሉ የገድሉን ዜና ነገራቸው ያቺንም በደም የታለለች በፍታ ሰጣቸው ይህችም የመከራው ወራት አልፎ ደጉ ቈስጠንጢኖስ ነግሦ በሀገሮች ሁሉ በክርስቲያን ወገኖችም ላይ ሰላምና ጸጥታ እስከሆኑ ድረስ በእነርሱ ዘንድ ተጠብቃ ኖረች።
እግዚአብሔርም የከበረ የቢፋሞንን ሥጋ ለምእመናን አለኝታና መጽናኛ ለበሽተኞችም የሚፈውስ ኃይል እንዲሆን ሊገልጠው ወደደና በእርሱም በላይኛው ግብጽ በጥማ አውራጃ በቃው ከተማ በጥር ሃያ ሰባት በዚች ቀን በሰማዕትነት የሞተ ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages