አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥር ሃያ ስድስት በዚህች ቀን #ቅድስት_አንስጣስያ አረፈች፣ የከበሩ #አረጋውያን_መነኰሳት ከንጉሥ መልእክተኛ ከልጁም ጋር በሰማዕትነት አረፉ።
ጥር ሃያ ስድስት በዚህች ቀን ከቍስጥንጥንያ ቤተ መንግሥት ታላላቆች የአንዱ ልጅ የሆነች ቅድስት አንስጣስያ አረፈች። እርሷም በላሕይዋ በደም ግባቷ እጅግ ያማረች ናት ንጉሥ ብስጥያኖስም ሊአገባት ፈለገ እርሷ ግን ይህን በልቧ አልወደደችም የንጉሡም ሚስቱ በሕይወት ነበረች ንጉሡ እንደሚሻትም ለንግሥት ሚስቱ አስረዳቻት በዚያንም ጊዜ ንግሥቲቱ ወደ ግብጽ በመርከብ አሳፍራ በሥውር ሸኘቻት ከእስክንድርያም ከተማ ውጭ ገዳም አሠራችላት በዚያም ኖረች ያም ገዳም በስሟ ተጠራ።
የከበረች እንስጣስያም በግብጽ አገር እንዳለች ንጉሥ በአወቀ ጊዜ ፈልገው ወደርሱ ያመጧት ዘንድ መልእክተኞችን ላከ ይህንንም ነገር ተረድታ ተነሣች የወንዶችንም ልብስ ለብሳ መስፍንን መሰለች ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔዳ ወደ አበ ምኔቱ ወደ አባ ዳንኤል ገባች ምሥጢሯን ሁሉ ገለጠችለት ።
እርሱም ወስዶ በዋሻ ውስጥ ለብቻዋ አኖራት እርሷም ሴት እንደሆነች ማንም አላወቀም በየሳምንቱም በእንስራ ውኃ ቀድቶ ከዚያ ዋሻ ደጃፍ እንዲያኖር አንዱን ደግ አረጋዊ አባ ዳንኤል አዘዘው ያም ሽማግሌ አያውቅም ይችም ቅድስት አንስጣስያ በጸሎት በጾምና በመስገድ በመትጋትም እየተጋደለች ሃያ ስምንት ዓመት ኖረች ።
ውኃ ሲቀዳላት የነበረ ያ ሽማግሌ በአረፈ ጊዜ አባ ዳንኤልም ያ ሽማግሌ ሲሠራ እንደ ነበረ ይሠራ ዘንድ ረዳቱን አዘዘው ቅድስት አንስጣስያም ሀሳቧን በገል ላይ እየጻፈች በበዓቷ ደጃፍ ታኖረው ነበር ረድኡም ወደ መምህሩ ወደ አባ ዳንኤል ይወስደዋል። የምትጽፈውንም ምን እንደሆነ አያውቅም ።
በአንዲት ዕለትም የጻፈችበትን ገል አመጣ አባ ዳንኤልም በአነበባት ጊዜ አለቀሰ ረድኡንም ልጄ ሆይ ተነሥ የዚያን ቅዱስ ሰው ሥጋ ሒደን እንቅበር እርሱ ከዚህ ዓለም ይለያልና አለው ። በሔዱም ጊዜ ወደ በዓቷ ገብተው ከእርሷ ተባረኩ እርሷም አባ ዳንኤልን አባቴ ሆይ ስለ እግዚአብሔር ብለህ በላዬ ካለው በቀር በምንም ልብስ እንዳትገንዘኝ አለችው ከዚህም በኋላ የከበረች አንስጣስያ ተነሥታ ጸለየች እኔ በእግዚአብሔር ዘንድ አደራ አስጠበቅኋችሁ አለችና በምድር ላይ ተቀምጣ አረፈች በላይዋም አለቀሱ ሊቀብሩዋትም አስበው ረድኡ ይገንዛት ዘንድ ሲቀርብ እንደ በለስ ቅጠሎች ደርቀው ጡቶቿን ተመለከተ። ከተጋድሎ ብዛትም የተነሣ እንዲህ ሁኗልና አባ ዳንኤልም አይቶ በማድነቅ ዝም አለ ።
ከቀበርዋትም በኋላ ወደ በዓታቸው ተመለሱ ረድኡም ወደ አባ ዳንኤል ቀርቦ ሰገደለትና እንዲህ ሲል ለመነው ስለ እግዚአብሔር ብለህ የዚችን ቅድስት ዜናዋን ንገረኝ ሴት እንደሆነች አይቻለሁና።
አባ ዳንኤልም የገድሏን ዜና ሊነግረው ጀመረ እንዲህም አለው እርሷ ከቍስጥንጥንያ አገር ከመንግሥት ታላላቅ ወገኖች ውስጥ የሆነች ስትሆን ሰውነቷን ለክርስቶስ ሰጥታ የዚህን የኃላፊውን ዓለም ክብር ሁሉ ተወች። ሰይጣንን ከተዋጋችበት ከዚህ ከታላቅ ተጋድሎዋ ለእኛ ለወንዶች መመከሪያ ሊሆነን ይገባል ከእርሷም የሴቶችን ደካማነት አርቃ የኃይለኞች ወንዶችን ብርታት ገንዘብ እስከማድረግ ደርሳ እግዚአብሔርን አገለገለችው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
፵፱ አረጋውያን ሰማዕታት
በዚህችም ቀን የጻድቅ አርቃዴዎስ ልጅ በሆነ በጻድቁ ቴዎዶስዮስ ዘመነ መንግሥት አርባ ዘጠኝ የሆኑ የከበሩ አረጋውያን መነኰሳት ከንጉሥ መልእክተኛ ከልጁም ጋር በሰማዕትነት አረፉ።
የሰማዕትነታቸውም ምክንያት ቴዎዶስዮስ ልጅ አልነበረውም በአስቄጥስ ገዳም ወደ ሚኖሩ አረጋውያን መነኰሳት ልጅን ይሰጠው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲማልዱለት እየለመናቸው መልእክትን ላከ ከውስጣቸውም ስሙ ቢስዱራ የሚባል አንድ ታላቅ አረጋዊ አለ እርሱም ወደ ንጉሥ እንዲህ ብሎ ጻፈ ከአንተ በኋላ ከሚነሡ መና*ፍቃን ጋር አንድ እንዳይሆን ልጅን ይስጥህ ዘንድ እግዚአብሔር አልወደደም። መልእክቱን በአነበበ ጊዜ ንጉሡ ደስ ብሎት እግዚአብሔርን አመሰገነው ሃሳቡንም አሳረፈ።
ዳግመኛም ግብዞች ሰዎች ሌላ ሚስት አግብቶ ከእርሱ በኋላ በዙፋኑ የሚቀመጥ ልጅን ይወልድ ዘንድ መከሩት እርሱም የትሩፋታቸው ዜና በዓለም ዳርቻ ሁሉ ደርሷልና በአስቄጥስ ገዳም ከሚኖሩ ከቅዱሳን አረጋውያን ትእዛዝ በቀር ምንም ምን አላደርግም ሲል መለሰላቸው።
ስለዚህም አረጋውያንን ይጠይቅ ዘንድ ንጉሥ መልእክተኛውን ዳግመኛ ላከ ለንጉሡም መልእክተኛ ልጅ ነበረው ልጁም በረከታቸውን ይቀበል ዘንድ ከእርሱ ጋር ወደ አረጋውያን እንዲወስደው አባቱን ለመነው መልእክተኛውም ከልጁ ጋር ወደ አረጋውያን በደረሰ ጊዜ የንጉሡን ደብዳቤ ሰጣቸው እነርሱም አነበቧት ያን ጊዜ ግን አባ ቢስዱራ ስለሞተ አልተገኘም አረጋውያንም የንጉሡን መልእክተኛ የአባ ቢስዱራ ሥጋ ወዳለበት ወሰዱትና አደረሱት ሥጋውንም አባታችን ሆይ እነሆ የንጉሥ መልእክት ወደ እኛ ደረሰ እኛም የምንመልስለትን አናውቅም አሉት። በዚያንም ጊዜ አረጋዊ አባ ቢስዱራ ተነሥቶ እግዚአብሔር ልጅን ሊሰጥህ አልፈቀደም አላልኩህምን አለ በሉት ለንጉሥ አሁንም ከዓላ*ውያን ጋር አንድ ሁኖ እንዳይረክስ ሌሎች ሴቶችንም ቢአገባ ልጅን አይሰጠውም ይህንንም ተናግሮ ተመልሶ ተኛ።
አረጋውያንም ይህን ቃል በክርታስ ጽፈው ለንጉሥ መልእክተኛ ሰጡት እርሱም ወደ አገሩ ሊመለስ በተነሣ ጊዜ እነሆ የበርበር አረ*ማውያን ደረሱ አባ ዮሐንስ የሚባል አረጋዊም ቁሞ ወገኖቹን እንዲህ አላቸው እነሆ የበርበር ሰዎች ይገ*ድሉን ዘንድ መጡ ምስክርነት የሚሻ ከእኔ ጋር ይቁም የሚፈራ ግን ወደ ግንብ ሒዶ ይሠወር አለ።
የሸሹም አሉ ከአባ ዮሐንስ ጋርም የቀሩ አርባ ዘጠኝ አረጋውያን መነኰሳት የንጉሥ መልእክተኛም ልጅ ከጎዳና ጉዞ ላይ ዘወር ሲል በአረጋውያን ሰማዕታት ራሶች አክሊላትን ሲያኖሩ መላእክትን አያቸው የዚያም ጎልማሳ ስሙ ድያስ ነው አባቱንም እነሆ በአረጋውያን ራሶች ላይ አክሊላትን ሲያኖር ረቂቃን መላእክትን አያለሁ አሁንም እንደርሳቸው አክሊልን ለመቀበል እኔ እሔዳለሁ አለው አባቱም ልጄ ሆይ እኔም ከአንተ ጋር እሔዳለሁ አለው።
በዚያችም ጊዜ አረጋውያን መነኰሳት ለአረ*ማውያን ተገለጡላቸው አረ*ማውያንም ገ*ደሏቸው የምስክርነት አክሊልንም ተቀበሉ። አረ*ማውያንም ከሔዱ በኋላ መነኰሳቱ ከተሠወሩበት ግምብ ወርደው የሰማዕታትን ሥጋቸውን ሰበሰቡ ገንዘውም በበዓት ውስጥ አኖሩዋቸው በእርሳቸውም ዘንድ ሌሊቱን ሁሉ የሚጸልዩና የሚዘምሩ ከእርሳቸውም የሚባረኩ ሆኑ የአባ ዮሐንስንም ሥጋ ሰዎች ሰርቀው ባታኑን ወደሚባል አገር ወሰዱት ከእርሳቸውም ዘንድ ጥቂት ቀኖች ኖረ ከዚህም በኋላ ቅዱሳኑ ወደቦታው መለሱት።
ሌሎችም ከሀገረ ፍዩም የጎልማሳውን ሥጋ ሰርቀው ወደ ፍዩም አገር ሲአደርሱት የእግዚአብሔር መልአክ ነጥቆ ወደ አባቱ ሥጋ መለሰው መነኰሳቱም ብዙ ጊዜ ፈተኑት የወጣቱን ሥጋ ከአባቱ ሥጋ የሚለዩት ሁነው ነበር። በጥዋትም በአንድነት ያገኙአቸዋል ከመነኰሳቱም አንዱ እንዲህ የሚለውን እስኪያይና እስኪሰማ ድረስ። "ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛ በሕይወተ ሥጋ ሳለን እርስበርሳችን አልተለያየንም በጌታችን ክርስቶስም ዘንድ አልተለያየንም እናንተ እርስ በርሳችን ለምን ትለያዩናላችሁ!" ከዚያችም ቀን ወዲህ የለያቸው የለም።
አረ*ማውያንም የአስቄጥስን ገዳም በአ*ጠፉ ጊዜ ስለ ቅዱሳን ሰማዕታት ሥጋ መነኰሳቱ ፈሩ ከቦታቸውም አፍልሰው ወስደው በከበረ አባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ጎን አኖሩዋቸው የመቃብር ቦታም ሠሩላቸው በላዩም በሊቀ ጳጳሳት ታውዳስዮስ ዘመን በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ሠሩላቸው።
ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚንም ወደ አስቄጥስ ገዳም በመጣ ጊዜ የካቲት አምስት ቀን እንዲከበር በዓልን ሠራላቸው ይኸውም ሥጋቸው የተገለጠበት ነው ቤተ ክርስቲያናቸውም እስከ ዛሬ አለች በቅብጢ ቋንቋ ብህም ብሲት በመባል የታወቀች ናት ይህም አርባ ዘጠኝ ማለት ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን
No comments:
Post a Comment