ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 25 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 25

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ሃያ አምስት በዚህች ዕለት ሰማዕቱ #ቅዱስ_መርቆሬዎስ በሥዕሉ ላይ አድሮ ቅዱሳን ባስልዮስንና ጎርጎርዮስን የረዳበት ዕለት ነው፡፡ በገድል የተጸመደ የከበረ #ቅዱስ_ጴጥሮስ አረፈ፣ የከበረ #ቅዱስ_ስብስትያኖስ ምስክር ሁኖ ሞተ፡፡


ጥር ሃያ አምስት በዚህች ዕለት ሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ በሥዕሉ ላይ አድሮ ቅዱሳን የሆኑ ባስልዮስንና ጎርጎርዮስን በመርዳት ከሃዲውን ንጉሥ ዑልያኖስን የገደለው በዚሁ ዕለት ነው፡፡
መርቆሬዎስ ማለት የአብ ወዳጅ ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ወላጆቹ አስሊጥ ከምትባል ሀገር ቢሆኑም እርሱ ግን ተወልዶ ያደገው በሮሜ ከተማ ነው፡፡ አያቱና አባቱ ሥራቸው አውሬ ማደን ስለነበር አንድ ቀን እንደልማዳቸው አውሬ ሲያድኑ ከገጸ ከለባት ወገን የሆኑ ሁለት ወንዶች አግኝተዋቸው የመርቆሬዎስን አያት በሉት፡፡ አባቱንም ሊበሉት ሲሉ የታዘዘ መልአክ ከለከላቸው፡፡ ዙሪያቸውንም በእሳት አጥሮ ከበባቸው፡፡ እነርሱም በተቸገሩ ጊዜ ለመርቆሬዎስ አባት ሰገዱለት፡፡ በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር ፍጥረታቸውን ወደገራምነት ለወጠውና እንደበጎች የዋሆች ሆነው አብረውት ወደ መንደር ገቡ፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ ተወለደና ስሙ ፒሉፓዴር ተባለ፡፡ የውሻ መልክ ያላቸውም በእርሱ ዘንድ ብዙ ዘመናት ኖሩ፡፡ ከዚህም በኋላ ክርስቲያኖች ሆኑ፡፡ የቅዱስ መርቆሬዎስም ወላጆች አስቀድመው አረማውያን ነበሩና የክርስትና ጥምቀትን በጸጋ ተቀበሉ፡፡ አባቱን ኖህ እናቱንም ታቦት ብለው ሰየሟቸው፡፡ ቀድሞ ፒሉፓዴር የነበረውም ስሙ ተለውጦ መርቆሬዎስ ተባለ፡፡ የውሻ መልክ ያላቸው ግን መልአኩ በተገለጠላቸው ጊዜ እንደነገራቸው ለቅዱስ መርቆሬዎስ አባት የሚታዘዙና የሚያገለግሉ ሆኑ፡፡ ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባትና የውሻ መልክ ያላቸውን ዜናቸውን ሲሰማ ወታደሮቹን ልኮ በፊቱ አቆማቸው፡፡ እግዚአብሔርም የቀድሞ ፍጥረታቸውን መልሶላቸው አራዊት አደረጋቸውና ንጉሡን እጅግ አስፈሩት፡፡ ንጉሡም የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት የአራዊት ተፈጥሮአቸውን ያርቅለት ዘንድ ለመነው፡፡ የቅዱስ መርቆሬዎስም አባት በለመነ ጊዜ ተፈጥሮአቸውን መልሶላቸው ገራሞች ሆኑ፡፡
ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባት ገዥና የሠራዊቱ አለቃ አድርጎ ሾመው፡፡ የውሻ ፊት ያላቸውም አብረው ያገለግሉት ስለነበር ሁሉም ይፈራው ነበር፡፡ ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባት ወደ ጦርነት ከላከው በኋላ ሳይመለስ ስለቀረ ሚስቱን ሊያገባት አሰበ፡፡ የመርቆሬዎስ አባትም የመርዶሳውያን አገሮች ሁሉ ገዢ በነበረው ንጉሥ ተይዞ ቢማረክም ገዥው ክርስቲያን መሆኑን አይቶ አከበረው፡፡ ቆይቶም በሀገሩ ላይ ሾመው፡፡ ሚስቱም ጠፍታ ከሀገሯ ወጥታ ሄዳ ስለነበር ከባሏ ተገናኝተው በዚያው መኖር ጀመሩ፡፡ መርቆሬዎስም አባቱና እናቱ ከሞቱ በኋላ ንጉሡ በአባቱ ፈንታ በመርዶሳውያን አገር ላይ ሾመው፡፡
መርቆሬዎስ መኰንንነት በተሾመም ጊዜ ገጸ ከለባቱ አብሮት ነበር፡፡ ለመዋጋትም በወጣ ጊዜ የቀድሞው የአራዊት የሆነ ተፈጥሮውን እግዚአብሔር ይመልስለት ስለነበር ማንም አይቋቋመውም ነበር፡፡ ለቅዱስ መርቆሬዎስ ታላቅ የድል አድራጊነት ኃይል ተሰጠውና ዜናው በሁሉም ሀገሮች ተሰማ፡፡ በሮሜ ሀገር ጣዖትን የሚያመልከው ዳኬዎስ የተባለውም ንጉሥ የበርበር ሰዎች ጋር ጦርነት ሊገጥም በወጣ ጊዜ እጅግ ሲበዙበት ፈራ፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስም በጦሩ መሀል የተሳለ ሰይፍ የያዘ የእግዚአብሔርን መልአክ ስላየ ንጉሡን እግዚአብሔር ያጠፋቸዋልና አትፍራ›› አለው፡፡ መልአኩም ሰይፉን ለቅዱስ መርቆሬዎስ ሰጠውና ‹‹ጦርነቱን ድል ባደረግህ ጊዜ እግዚአብሔርን አስበው›› አለው፡፡
ጦርነቱን ድል አድርጎ ሲጨርስም መልአኩ ድጋሚ ተገልጦለት ‹‹ለምን የፈጣሪህን ስም መጥራት እረሳህ?›› አለው፡፡ ከጦርነቱም በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረግ በዓልን አደረገ፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስም በዚያ ስላልተገኘ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረጉ እንዳልተባበረ ንጉሡ ሲያውቅ መልእክተኞችን ልኮ አስመጣው፡፡ ንጉሡም ‹‹ከእኔ ጋር ለምን አታጥንም?›› ባለው ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ ትጥቁንና ልብሱን አውልቆ ከወረወረለት በኋላ ‹‹ክብር ይግባውና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጽሞ አልክደውም፣ ለረከሱ ጣዖቶችህም አልሰግድም›› አለው፡፡ ንጉሡም ተናዶ ልዩ ልዩ በሆኑ ሥቃዮችም እጅግ አሠቃየው፡፡
ንጉሡም ስለ መርቆሬዎስ ብለው የአገሩ ሰዎች እንዳይነሱበት ፈርቶ በብረት ችንካር ቸንክሮ የቀጵዶቅያና የእስያ ክፍል ወደሆነች ወደ ቂሳርያ ከደብዳቤ ጋር ላከው፡፡ በዚያም እጅግ ካሠቃዩት በኋላ ንጉሡ ዳኬዎስ እንዳዘዘ ኅዳር 25 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነት ተጋድሎውን ፈጸመ፡፡ የሕይወትንም አክሊል ተቀዳጀ፡፡ በዓለሙ ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ታነጹለት፡፡ እግዚአብሔርም ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን በቅዱስ መርቆሬዎስ ስም አደረገ፡፡
ከብዙ ተአምራቱም አንዱ የቂሳርያውን ሊቀ ጳጳስ ባስልዮስን እረድቶ ከሃዲውን ዑልያኖስን የገደለበት ነው፡፡ ዑልያኖስ ነግሦ የክብር ባለቤት ጌታችንን ክዶ ጣዖታትን ማምለክና ክርስቲያኖችን ማሠቃየት ጀመረ፡፡ የቂሳርያው ሊቀ ጳጳስ ባስልዮስም አስተምሮ ሊመልሰው ወደ ንጉሡ ቢመጣ ክብር ይግባውና ዑልያኖስ ጌታችንን ሰድቦ ባስልዮስንም አሰረው፡፡ ባስልዮስም በእሥር ቤት ሳለ በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ፊት ጸለየ፡፡ ሥዕሉም ወዲያው ተሰወረው፡፡ ያንጊዜም ወደ ከሃዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ዘንድ ሄዶ በጦር ወግቶ ገደለውና ወዲያው ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ ከጦሩም አንገት ደም ይንጠፋጠፍ ነበር፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ከሃዲውን ንጉሥ እንደገደለው ዐውቆ ‹‹የክርስቶስ ምስክር ጌታዬ ሆይ የእውነት ፀር የሆነ ዑልያኖስን ገደልከውን?›› አለው፡፡ ሥዕሉም ያን ጊዜ አዎን እንደሚል ራሱን ዘንበል አደረገ፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ደስ ብሎት እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡
ሌላው ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በተአምሩ ከእስልምና እምነት መልሶ ክርስቲያን ያደረገው አንድ እስላም ሰው አለ፡፡ ይኸውም የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያኑ በተሠራችበት በምስር አገር የሚኖር ከመሳፍንት ወገን የሆነ ወጣት ነበረ፡፡ ከብዙ ሰዎችም ጋር ሆኖ ወደ መሐመድ መቃብር ለመሄድ እንዳሰበ ለአባቱ ሲነግረው ስንቅ ሰንቀው በሰላም ወደ መካ መዲና ሸኙት፡፡
መካ ደርሰውም ሥራቸውም ፈጽመው ወደቤታቸው እየተመለሱ ሰባት ቀን ተጓዙ፡፡ በሌሊትም ሲጓዙ ስለ ሥጋዊ ግዳጁ ያ እስላም ወጣት ከግመል ላይ ወርዶ ለመጸዳዳት ዘወር አለ፡፡ እነርሱም አብሯቸው የሚጓ መስላቸው ስለነበር ባልንጀሮቹም በበረሃው ውስጥ ትተውት ሄዱ፡፡ እርሱም ወዴት እንደሚሄድ ስላላወቀ አራዊትም እንዳይበሉት ፈርቶ እጅግ ደነገጠ፡፡
በዚያም ጊዜ በምስር አገር በአባቱ ቤት አቅራቢያ ያለች የሰማዕቱ የቅዱስ መርቆሬዎስን ቤተ ክርስቲያን አስታውሶ በልቡ ቅዱስ መርቆሬዎስን እንዲያድነው በመለመን ተሳለ፡፡ ወዲያውም ቅዱስ መርቆሬዎስ በፈረሱ ተቀምጦ ወደ እርሱ መጣና ‹‹ከወዴት ነህ? ከዚህ በረሃ ውስጥስ እንዴት ጠፋህ?›› አለው፡፡ ወጣቱ እስላምም የሆነውን ነገረው፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስም ‹‹ና በኋላዬ በፈረሱ ላይ ተፈናጠጥ›› አለውና በአየር ላይ እየበረረ በምስር አገር ወዳለች የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ዐይን ጥቅሻ አደረሰውና እንደተዘጋች በውስጧ አስገባውና ከእርሱ ተሰወረ፡፡ ይህም ወጣት በኋላ አምኖ ተጠምቆ ብዙ ሰማዕትነት ተቀብሏል፡፡ ገዳምም ገብቶ ብዙ ከተጋደለ በኋላ እንደገና ወደ አገሩ ተመልሶ ብዙዎችን ወደ ክርስትና አምጥቷል፡፡ በቅዱስ መርቆሬዎስ ስም ቤተ ክርስቲያን አሠርቶ አበ ምኔትም ሆኖ ብዙ መነኮሳትን አፍርቷል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን በገድል የተጸመደ የከበረ ጴጥሮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ቀራጭ ነበረ እርሱም ልቡ የደነደነ ርኅራሄ የሌለው ነው በዚህም ክፉ ስም ጨካኝ ርኅራሄ የሌለው ብለው ይጠሩታል።
ከዚህም በኋላ የኃጢአተኛን ሞት የማይሻ ጌታችን ከእርሱ ምጽዋት የሚለምነውን ድኃ ላከለትና ለመነው በዚያንም ጊዜ አገልጋዩ እንጀራ ተሸክሞ ደረሰ አገልጋዩ ከተሸከመው ከራሱ ላይ አንድ እንጀራ ለዚያ ደኃ ጣለለት ይህንንም ያደረገ ስለ ርኅራኄ አይደለም ከአጠገቡ እንዲሔድለትና ከቶ ወደርሱ እንዳይመለስ ነው ምስኪኑም ተቀብሎ ወደ ማደሪያው ሔደ።
በዚያችም ሌሊት ተኝቶ ሳለ በሕልሙ እንዲህ አየ ብዙዎች ሊተሳሰቡት ይሻሉ በእጆቻቸውም ሚዛኖች ተይዘዋል ብዙዎችም መልካቸው እጅግ የከፋ ጥቋቊሮች ኃጢአቱ ሁሉ ከእርሳቸው ጋር አለ በግራ በኩል ባለው ሚዛን ውስጥ አኖሩት ደግሞ ልብሶቻቸው ነጫጭ የሆኑ ከብርሃናውያን መላእክት መልካቸው ያማረ ብዙዎች ነበሩ እነርሱም ቁመው በማዘን ምንም ያገኘነው ነገር የለም በቀኝ ባለው ሚዛን ውስጥ ምን እናኖራለን ይሉ ነበር በዚያንም ጊዜ ከእርሳቸው አንዱ መልአክ ጴጥሮስ ለድኃው የጣላትን ያችን እንጀራ አምጥቶ ከዚች እንጀራ በቀር ሌላ ከበጎ ሥራ ምንም አላገኘሁለትም አለ ባልንጀሮቹ መላእክትም በእነዚህ ሁሉ ኃጢአቶቹ አንጻር ይቺ ምን ትጠቅማለች ብለው መለሱ በዚያንም ጊዜ እየፈራና እየደነገጠ ከእንቅልፉ ነቅቶ ከተኛበት ተነሣ።
ከዚያችም ዕለት ወዲህ ስለቀደመች ክፉ ሥራው ተጸጸተ እጅግም የሚራራ ሆነ ቤቱንና ጥሪቱን ሁሉ ሽጦ ለድኆችና ለምስኪኖች ሰጠ ራሱንም ሸጠ።
ብዙዎችም ከበጎ ሥራዎች ይህን ስለ ሠራ እንደሚአመሰግኑትና እንደሚያደንቁት በአወቀ ጊዜ ከዚያ በመሸሽ ወደ አስቄጥስ ገዳም ገብቶ ከአባ መቃርስ ገዳም በዚያ መነኰሰ ፍጹም በሆነ ተጋድሎም ተጠምዶ እግዚአብሔርን አገለገለው የዕረፍቱን ጊዜ አውቆ የከበሩ አረጋውያንን ጠርቶ ተሳለማቸውና በዚያን ጊዜ አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የሮም ንጉሥ ልጅ የከበረ ስብስትያኖስ ምስክር ሁኖ ሞተ እርሱንም በተግሣጽና እግዚአብሔርን በመፍራት የአሳደጉት ነው።
አባቱም ከሞተ በኋላ ዲዮቅልጥያኖስና መክስምያኖስ ነገሡ ይህንንም ቅዱስ አገረ ገዥነት ሾሙት እንደ አባቱም እጅግ አከበሩት። እርሱም በጥበብና በማስተዋል ይጓዝ ነበር በሽተኞችን ሁሉ የዕውራንንም ዐይኖች በጸሎቱ ከፈተ።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ዲዮቅልጥያኖስ በካደው ጊዜ ለጣዖት ይሰግድ ዘንድ ይህን ቅዱስ ስብስትያኖስን ግድ አለው ባልሰማውም ጊዜ ከደረቀ ግንድ ጋር አሠረው ቊጥር በሌላቸው ፍላጻዎች ይነድፉት ዘንድ አዘዘ እንደሞተም ጠርጥረው ትተውት ሔዱ ምእመናንም በሌሊት ሲመጡ በሕይወት አገኙት ፈትተውም ወደ ደሴት መካከል ወስደው በዚያ አኖሩት።
ዲዮቅልጥያኖስም ሰምቶ ወደርሱ አስቀረበውና በብረት ዘንጎች ይደበድቡት ዘንድ አዘዘ እየደበደቡትም ብዙ ቀኖች ኖሩ ከዚህም በኋላ ነፍሱን አሳለፈ ለቅድስት ውሉድስና በሕልም ተገልጦ ሥጋው ያለበትን ነገራት እርሷም ሒዳ ወደ ጴጥሮስና ጳውሎስ መቃብር ወስዳ ቀበረችው። ጌታችንም መታሰቢያውን ለሚያደርግና ስሙን ለሚጠራ የቸነፈር ሕመም እንዳይቀርበው ቃል ኪዳንን ሰጠው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎቱ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages