ስንክስር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 29 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክስር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 29

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን #የጌታችንና_የመድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ #ከእመቤታችን_ከከበረች_ድንግል_ማርያም ተወለደ፣ #ጻድቁ_ካህኑ_ንጉሥ_ቅዱስ_ላሊበላ ተወለደ፣ ከኤፍሬም ወገን #መስፍኑ_ኢያሱ ተወለደ፣ #ጻድቅ_ንጉሥ_አቃርዮስ አረፈ፣ ገመላዊው #ቅዱስ_ቆሪል አረፈ፣ #የአክሚም_ሰማዕታት መታሰቢያቸው ነው።


ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን የከበረና የተመሰገነ ታላቅ የልደት በዓል ሆነ የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከከበረች ድንግል ማርያም የተወለደባት ዕለት ከበዓላት ሁሉ ተለይታ ከፍ ከፍ ያለች ናት።
የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን የከበረ የልደትን በዓል በሁለት ቀኖች ያከብሩ ዘንድ በምክራቸው ተስማሙ ከወደኋላ ባለ በሃያ ስምንት ሌሊቱ የልደት በዓል ነው በሃያ ዘጠኝ መዓልቱ ጳጉሜን ስድስት በሆነ ጊዜ በዚያች ዓመት የልደት በዓል በሃያ ስምንት በመዓልት ይከበራል። ጳጉሜን አምስት ከሆነ ግን በሃያ ዘጠኝ ይሆናል ስለዚህ የበዓላት ሁሉ ራስ የሆነ የከበረ የልደት በዓል በሁለቱ ቀኖች እንዲከበር አዘዙ ወሠኑ።
የበዓላት ራስ ስለሆነ ስለ ከበረ የልደት በዓል የከበረ ወንጌል እንዲህ አለ። በንጉሡ በኄሮድስ ዘመን በይሁዳ ዕፃ በቤተልሔም ጌታ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ እነሆ የፍልስፍና ሰዎች ከምሥራቅ መጥተው ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። ኮከቡን በምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናልና የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው እያሉ።
እሊህ ፈላስፎች ከበለዓም ወገን ናቸው እነርሱም በከዋክብት የሚፈላሰፉ ናቸው በመጽሐፋቸው በበለዓም መጽሐፍም የአይሁድ ንጉሥ ሊወለድ እንዳለው ተጽፎአል እርሱ በለዓም ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ከእስራኤልም ንጉሥ ብሎ ነበርና።
ይቅር ባይ እግዚአብሔርም በረቀቀ ጥበቡ አለበማቸው በሚያምኑበትም ሳባቸው እነርሱ ከዋክብትን በመጠባበቅ የሚፈላሰፉ ናቸውና ይህንንም ኮከብ ገለጠላቸው በአዩትም ጊዜ ደስ አላቸው መልኩ በብዙ አይነት ልውጥ ነውና። ሕፃን የታቀፈች ድንግል ብላቴናን ይመስላል እርሱም በቀን ይጓዛል በሌሊትም ይሠወራል ከሰውም ሲገናኙ ይሠወርና ሲቆሙ በሌላ አንጻር ይገለጥላቸዋል።
እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ያ ኮከብ ተሠወራቸው እጅግ አዘኑ የሚያደርጉትንም አላወቁም ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ገብተው ስለተወለደው ንጉሥ ጠየቁ። የእሊህም ሰዎች ቊጥራቸው ሠላሳ ሽህ ነው ነገሥታቱ ሦስት ናቸው ለየእንዳንዱ ንጉሥ ዐሥር አሥር ሽህ ሠራዊት አለው።
ንጉሡ ኄሮድስም በሰማ ጊዜ ደነገጠ ኢየሩሳሌምም በመላዋ ከእርሱ ጋር ደነገጠች። የካህናት አለቆችና የሕዝቡን ጸሐፊዎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ በየት ይወለዳል ብሎ ጠየቃቸው። በይሁዳ ዕፃ በቤተልሔም ነው አሉት በነቢይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና።
የኤፍራታ ዕፃ ቤተልሔም አንቺም ከይሁዳ ነገሥታት አታንሺም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ካንቺ ይወለዳልና። ከዚህም በኋላ ኄሮድስ ሰብአ ሰገልን በጭልታ ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከነሱ ተረዳ።
ሒዳችሁ የዚያን ሕፃን ነገር እርግጡን መርምሩ ያገኛችሁትም እንደሆነ እኔም መጥቼ እሰግድለት ዘንድ በኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ ብሎ ወደ ቤተልሔም ሰደዳቸው። የነገራቸውንም ሰምተው ከንጉሡ ሔዱ እነሆ በምሥራቅ ያዩት ከከብ ወደ ቤተልሔም እስኪያደርሳቸው ይመራቸው ነበር ሕፃኑ ካለበትም ዋሻ ላይ ደርሶ ቆመ።
ኮከቡንም ባዩ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር አገኙት ወድቀውም ሰገዱለት ሣጥናቸውንም ከፍተው ወርቅ ከርቤ ዕጣን እጅ መንሻ አቀረቡለት።
በእግዚአብሔርም ፈቃድ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕፃኑ ጌታ ኢየሱስም በዚያች ዕለት ወደ ቤተልሔም መጡ ስለዚህም ሰብአ ሰገል አገኙአቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ናዝሬት በሌላ ቦታ አላደገምና ከተወለደም ዕድሜው ሁለት ዓመት ሆኖት ነበር።
አምላክ ነውና ስለ መንግሥቱ ወርቅን ገበሩለት ክህነትም ገንዘቡ ነውና ዕጣንን ገብሩለት ማሕየዊ ለሆነ ሞቱ ምልክትም ከርቤን ገበሩለት። ወደ ኄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ነገራቸው በሌላ መንገድም ወደ አገራቸው ተመልሰው ገቡ። አምላክ በሥጋ ስለመገለጡ ዓዋጅ ነጋሪዎችና ሰባኪዎች ሆኑ።
ይችም ዕለት ነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት ስለርሷ የተናገረላት ናት እንዲህ ብሎ እነሆ ድንግል ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም ዐማኑኤል ትለዋለች ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው።
ስለዚችም የከበረች ድንግል ነቢይ ሕዝቅኤል እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ እግዚአብሔርም አለኝ ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች አትከፈትም የሚገባበትም የለም የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር እንደተዘጋች ይገባባታልና ተዘግታ ትኑር አለ።
ነቢዩ ዳንኤልም አለ ሌሊት በራእይ አየሁ እነሆ ታላቁ እንደ ሰው ልጅ በሰማይ ደመና መጣ ዘመኑን ወደ ሚያስረጅ ደረሰ ከፊቱም አቀረቡት የዘላለም አገዛዝ ጌትነት መንግሥት ተሰጠው ሕዝቡና አሕዛቡ ሁሉ መንደር መንድረው የሚኖሩትና ነገዱም ነገሥታቱም ሁሉ ይገዙለታል አገዛዙም የዘላለም አገዛዝ ነው መንግሥቱም የማያልፍ የማይጠፋ ነው።
ዳግመኛም ኢሳይያስ እግዚአብሔር እንደ እኔ የሥጋ መጋረጃ በመጋረድ ተገለጸልኝ አለ። አሁንም ደግሞ አዲስ ሰማይ አዲስ ምድር እሠራ ዘንድ አለኝ አለ ሁለተኛም ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች ከእርሷም ጽጌ አበባ ይወጣል አለ። ዳግመኛም ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶልናልና ይኸውም ሥልጣን በጫንቃው የሆነ ክርስቶስ ነው። ስሙም ድንቅ መካር የዘላዓለም አባት የሰላም አለቃ ይባላል አለ።
ኤርምያስም አለ እግዚአብሔር እንዲህ አለ በዚያን ወራት ለዳዊት ብርሃንን አወጣለሁ በምድርም የቀና ፍርድን ያደርጋል እግዚአብሔርም ያመኑበትን ያድናቸዋል።
ኤልሳዕም እንዲህ አለ።እ ግዚአብሔር ከሰማይ ይወርዳል በእስራኤል ልጆች አደባባይም በመመላለስ ለሕዝቡ ዕውነትን ያስተምራቸዋል ከአብርሃም ልጅነት ልዩ ከሆኑ ወገኖች በቀር አሕዛብ ሁሉ ይታዘዙለታል። ናሆም ነቢይም እንዲህ አለ። እግዚአብሔር በእኔ አርአያ ይመጣል ልብሱም እንደልብሴ ነው።
ነቢዩ ኢዩኤልም እንዲህ ተናገረ የእግዚአብሔር ዙፋን የሆነች ብላቴና ድንግልን አየሁ እርሷም እንደ እሳት ያልባት ነበር ስለርሷም ይቺ ማን ናት ብዬ ኪሩብን ጠየቅሁት ከአዳም ልጆች የተመረጠች የእግዚአብሔር ዙፋን ይህች ድንግል ናት በርሷም የተጐሳቈሉ አሕዛብ ይድናሉ ለአመነባትም ረድኤትና መጠጊያ ናት።
ዳዊትም በመዝሙሩ እንዲህ አለ እግዚአብሔር አንተ ልጄ ነህ ዛሬም በተዋሕዶ ወለድኩህ አለኝ። ለምነኝ አሕዛብን ርስት አድርጌ እሰጥሃለሁ ግዛትህም በመላው ዓለም ነው። ዳግመኛም አብ አለ ቀዳማዊ ወልድ በኃይል ቀን ካንተ ጋራ ሳለሁ ከአጥቢያ ኮከብ በፊት ከሆድ ወለድኩህ እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለሙ አገልጋይ ካህን ነህ ብሎ እግዚአብሔር ማለ ከማለም አይጸጸትም።
ቤዛ ይስሐቅ በግዕ ከኅቱም ዕፀ ሳቤቅ እንደተገኘ ለእስራኤልም በበረሀ ውስጥ ከኅቱም አለት ውኃ እንደ ፈለቀ የደነቀች የአሮን በትርም እንደለመለመችና እንደ አፈራች። በሶምሶንም እጅ ውስጥ ከአህያ መንጋጋ ዐጥንት ውኃ እንደ ፈሰሰ።
እንዲሁ የጌታችን ልደት በኅቱም ድንግልና ሆነ። በዕፀ ጳጦስ ውስጥ እሳት እንደ ነደደች ዕፂቱም እንዳልተቃጠለች እንዲሁ የመለኮቱ እሳት ድንግልን አላቃጠላትም።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት ቅዱስ ላሊበላ ከአባቱ ከዐፄ ዛን ስዩም ከእናቱ ከልዕልት ኪሪዮርና በ1101ዓ.ም ታኅሣሥ 29 ቀን በቤተ መንግሥ ተወለደ። ዐፄ ዛን ስዩም ከመንገሡ በፊት የዋግ ሹም ሆኖ ሲያስተዳድር ዑጽፍት ወርቅ የምትባል ሴት አግብቶ ንጉሥ ቅዱስ ገብረ ማርያምና ዮዲት የምትባል ልጅ(ርብቃም) የሚሉ አሉ ከወለደች በኋላ ዑጽፍተ ወርቅ ሞተች። ከዚህ በኋላ የክፍለአገር ገዥ ከሆነው ረዳኢ ከተባለው የተወለደችውን ኪሪዮርናን አግብቶ ቅዱስ ላሊበላን ወለደው። ቅድስት ኪሪዮርና ማለት ቤተ ክረሰስቲያን ማለት ነው።
ቅዱስ ላሊበላ በተወለደ ጊዜ ነጫጭ ንቦች ሰፍረውበት እንደማር ሲልሱት እናቱ ስታይ በመደንገጥ "ላል ይበላል" በማለት ተናገረች። ይህም በአገውኛ ቋንቋ ልጄን ንብ በላው ማለት ነው። በዚህ መሰረቴ ላልይበላል ተብሎ እየተጠራ እንደሠ ከጊዜ ብዛት ላሊበላ ተብሏል። በነገራችን ላይ የተሳሳተ ትርጉም የያዙ አላዋቂዎች ላሊበላ ማለት ለማኝ እንደሆነ አድርገው በአንዳንድ አካባቢዎች ይናገራሉ። ላሊበላ ማለት ግን ጣፋጭ የንስሃ ጋሻ የጽድቅ አባት ማለት ነው እንጂ ለማኝ ለፍላፊ ማለት አይደለም።
ከዚህም በኋላ እናትና አባቱ ልጃቸው ወደፊት ንጉሥ ሆኖ ብዙ ሰራዊት የሚከተለው ትልቅ ሰውና መንፈሰ እግዚአብሔር ያደረበት መሆኑን በንቦች መክበብ በመረዳታቸው በ40 ቀኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሰራዊትና ካህናት ታጅበው በእልልታና በደስታ ዐፄ ካሌብ በአሰሩዋት ማይ ማርያም በተባለችው ቤተ ክርስቲያን የክርስትናውን ሥነ-ሥርዓት አስፈጽመዋል። የክርስትና ስሙም ገብረ መስቀል ተብሏል። ቅዱስ ላሊበላ በቤተ መንግሥት ውስጥ ለነገሥታት ልጆች እንደሚሰጥ እንክብካቤና ሥነ-ሥርዓት በጥበብና በሞገስ አደገ። ዕድሜውም ለትምህትተ ሲደርስ መምህር ተቀጥሮለት ከፊደል እስከ ዳዊት የሚሰጠውን ትምህርት ያለማዳገም ከፈጣሪ በተሰጠው ፀጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተማረ። በዚህም ላይ እንዳለ የበለጠ ፈጣሪውን ማገልገል በመፈለጉና በመምረጡ ቤተ መንግሥቱን ትቶ ትምህርቱን ለማሻሻል ወደ ምድረ ጎጃም ሄዶ አሉ ከተባሉ መምህራን በተለይም መምህር ኬፋ ከተባሉ ምሁር አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምሮ ወደ ደብረ ሮሃ ተመልሶ ሥርዓተ መንግሥትን ወንድሙ ቅዱስ ገብረ ማርያም እያስተማረው ሳለ ለምቀኝነት የሚያርፈው ሰይጣን በንጉሥ ባለሟሎች(አማካሪዎች) ላይ አድሮ የሁለቱን ፍቅር በጠሰው። ሰዎቹ ወደ ንጉሥ ቀርበው "ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ንገሥ እነሆ ላሊበላ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን በማግኘቱ አስተባብሮ ንጉሥነትዎን መንግሥቱ ሊቀማዎት ነውና እወቁበት" በማለት ነገሩት። ንጉሡም በነገሩ እጅግ ተቆጥቶ ወደ ማረፊያ ቤቱ ገብቶ እንጀራ አልበላም ውሃም አልጠጣም ብሎም እንደ ንጉሥ ዓክአብ ተጨንቆ ተጠቦ ሳለ እህቱ "ንጉሥ ሆይ ልብህ አይዘን አትጨነቅ ነገሩን ለእኔ ተወው" ብላ አረጋጋችው። ላሊበላ ግን ይህን ሁሉ ነገር አላወቀም ነበርና በንጹህ ልቦናው በቤተ መንግሥቱ እንደ ተቀመጠ ከዕለታት አንድ ቀን ኮሶ ታይቶት መድኃኒት እንድታጠጣው ቂመኛ እህቱን ጠየቃት እሷም የምታጠምድበትንና የምትገድልበትን ስታስብና ስትፈልግ ስለ ነበር ይህን አጋጣሚ በማግኘቷ ሀሳቡን ደስታ ተቀብለችውና ኮሶውን አዘጋጅታ መርዝ ቀላቅላ አቀረበችለት። ከእርሱ ጋራ የሚኖር የማለየው አንድ ዲያቆን ነበር። በባህሉም መሠረት ዲያቆኑ ቀምሶ ስለሚሰጥ ያንን ሲቀምሰው አስታወኮት ሞተ። የዲያቆኑንም ትውኪያ አንድ ውሻ በመላሱ ሞተ። ከዚህም በኋላ ላሊበላ መንፈሱ ታወከ። ከባድ ሀዘንም አደረበት። "እናንተ ንጹሐን ለእኔ በታዘዘው መቅሰፍት በመሞታችሁ እኔም የእናንተን መንገድ እከተላለሁ እንጂ ወደ ኋላችሁ ቀርቼ ነፍስ ገዳይ አልሆንም" አለና በውስጡ ፍቃደ እግዚአብሔር ስላለበት ፈጣሪ ሚስጥር ሊገልጽለት በመፍቀዱ በጽዋው የተረፈውን መርዝ አንስቶ ጠጣው። እርሱም ወዲያው ተዘረረና ወደቀ። በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት መጥተው ነፍሱን ወደ ፈጣሪ ወስዷት። ሥጋው ግን ሙቀት ስላልተለየው ሰዎች ለመቅበር ቢሞክሩ እንደእሳት እየፈጃቸው ሦስት መዓልትና ሌሊት በሚደንቅ ሁኔታ ተቀመጠ።
ቅዱሳን መላእክት ሰባቱን ሰማያት አንድ በአንድ እያሳዩ ወደ ፈጣሪ ነፍሱን ከአቀረቧት በኋላ እግዚአብሔር አምላክ "ወዳጄ ላሊበላ ሆይ የጠራሁህ እኔ ነኝ በማለት ወሰን የሌለውን ፍቅሩን ከገለጸለት በኋላ ሀይሉንና ጥበቡን በእርሱ ላይ አሳድሮ "ከከርሰ ምድር አብያተ ክርስቲያናትን እንደሚያንጽና በኢትዮጵያ አገር ላይ አርባ ዓመት እንደሚነግሥ ሕዝበ እግዚአብሔር ድንቅ ሥራውን በመመልከት ድኅነትን፣ በረከትን፣ ፀጋን፣ እንደሚያገኙ በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኢየሩሳሌምን ለማየትና ለመሳለም ሲሔዱ የሚደርስባቸው መከራና ሞት ደማቸው ከፊቴ በመጮሁ በእርሱ ሥራ ኢየሩሳሌምን እንደሚያንፅና ለምን እንደሚሰራ ጥቅሙን በመግለጽ ይሰራ ዘንድ መመሪያ ሰጠው። ቅዱስ ላሊበላ ግን ይህን ማድረግ እንማይቻለው ቢገልጽም አምላክ ከእርሱ ጋራ እንደሚሆን ብቻ "ስሙ በአንተ ይሁን እኔ ነኝ የምሰራው" በማለት ገለጸለት። ከላይ እንደተገለጸው በድኑ መንፈስ ቅዱስ ሳይለየው እንደ እሳት ሰዎችን እየፈጃቸው ተጨንቀው ተጠበው በሁኔታው በመገረም ለሦስት ቀንና ሌሊት እንዳሉ በሦስተኛው ቀን ነፍሱ ከሥጋው ተዋሕዶ ተነሳ።
ቅዱስ ላሊበላም ከሰው ተለይቶ ከዘመድ ርቆ የሰው ድምጽ ከማይደርስበት ቦታ ሄዶ ሌት ከቀን በመጸለይ በጾምና በጾሎት ተወስኖ ከአምላኩ ጋር በበለጠ ግንኙነቱን እያጠናከረ እንዳለ አንድ ቀን ፈጣሪ ቅዱስ ገብርኤልን ላከውና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ላሊበላን "የእግዚአብሔር አገልጋይ ላሊበላ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን እንሆ እግዚአብሔር አምላክ በኢትዮጵያ ላይ ካህንና ንጉሥ ሆነህ ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማያት የምታበቃ ነህና በህገ አብርሃም ትወሰን ዘንድ ወዳንተ መጣሁ ስለሆነም ነገ በአሁኑ ሰዓት የምትመጣ በድንቅ ሥራዋ አምላክን ያስደሰተች አንዳንተ የተመለጠች ቅድስት ሴት ትመጣለችና እርሷን አግብተህ ልጅ ትወልዳለህና በሚያስደስት ቃል ተቀበላት" አለው። ቅዱስ ላሊበላ ግን ፍቃዱ እንዳልሆነ ቢገልጽም የእግዚአብሔር ትዕዛዝ እንደሆነ በድጋሚ ሲነግረው ቃሉን ተቀበለው። እንደተባለውም በማግስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ እንደ ብርቱካን፣ መዝ፣ የመሳሰሉትን ፍራፍሬዎች ይዛ ወደ ቅዱስ ላሊበላ ሄደች እርሱም በደስታ ተቀበላት። ከዚያም ነገረ እግዚአብሔርን ተነጋግረው ወደ ቤተሰቦቿ ወሰደችው። ለቤተሰቦቿ መላኩ በህልም ነግሯቸው ስለነበር በደስታ ተቀበሉት። በዚያም በፈቃደ እግዚአብሔር በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጋብቻቸውን ፈጽመው በጾምና በጸሎት ተወስነው በመኖር ላይ ሳሉ ለምቀኝነት የማያርፈው ሰይጣን አሁንም ፈተናውን አዘጋጅቶ ሶስናን በሐሰት ዝሙትን ፈጽማለች ብለው እንደወነጀሏት ሁሉ ቅዱስ ላሊበላንም "ከቤተ መንግሥት ጠግቦ ወጥቶ የሰው እጮኛ ያባልጋል" በማለት ለንጉሡ ሹክተኞች ነገሩት። ንጉሡም ወታደሮችን ልኮ አስመጣውና ቀኑም ዐርብ ቀን በመሆኑ እንዲገረፍ አዝዞ ወደ ቅዳሴ ሄደ። ዘጠኝ ሰዓት ላይ ወደ ቤቱ ሲሄድ የጅራፍ ጽምጽ በመስማቱ "ምንድነው? የሚሰማው" ብሎ ባለሟሎቹን ሲጠይቃቸው "ቅዱስ ላሊበላ እየተገረፈ ነው" አሉት ንጉሡም ወዲያውኑ እንዲያመጡለት አዘዘ። ሲመለከተውም በሰውነቱ ላይ ምንም የግርፈት ምልክት አላየበትም ንጉሡም ጻጽቅና እውነተኛ መሆኑን ፈጣሪም ከግርፋትና ከጥፍት ከልሎታልና "እንኳን ስ ሊሞት ግርፋቱ አልተሰማውም" በማለት እጅግ አደነቀ። ከባድ ሀዘንም ተሰማው። አምላኬን በድያለሁ የማይገባ ሥራ ሰርቻለሁ "ብሎ ቅዱስ ላሊበላ በሕዝቡ መካከል "ከዛሬ ጀምሮ መንግሥት ለአንተ ይገባል በግፍ አስገርፌሀለሁ በድዬሀለሁም ይቅር በለኝ" በማለት ከጫማው ወድቆ ይቅርታ ከጠየቀው በኋላ መንግሥቱን አስረክቦ መንኖ ለመሔድ ወሰነ። የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ቅዱስ ላሊበላም "ለይቅር ይቅር ብብያሁ ነገር ግነ መንግሥት የእግዚአብሔር ገንዘብ ናትና መንግሥትህን የምቀበለው ከእግዚአብሔር እንጂ ከአንተ አይደለም አንተም በዙፋንህ መቆየት አለብህ እኔ ግን መልካም ፈቃድ ከአምላኬ እስካገኝ ድረስ እጠይቃለሁ" ብሎ የዐፄ ገብረ ማርያም ጫማ ስሞ በፍቅር ተሰናብቶ ወጣ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡና "መንግሥትን ያህል ነገር እንደ ቀላል ነገር ቆጥሮ አልነግሥም ብሎ በመሄዱ እንዴት የእግዚአብሔር መንፈስ ቢያድርበት ነው?" በማለት በችሎት ተቀምጦ ሁኔታውን በግብር ሲከታተል የነበረው ሁሉ እያለቀሰ ቅዱስ ላሊበላን ተከትሎ ወጣ። ቅዱስ ላሊበላ ግን በአላማው ፀንቶ በሰዎቹ ፍቅር ሳይታለል እግዚአብሔር የሰጠውን ረዳቱን ቅድስት መስቀል ክብራን ይዞ ወደ አክሱም ሄደ።
በአክሱም አካባቢ በአባ ጰንጠሌዎን ገዳም በጾምና በጸሎት ተወስነው ፈጣሪያቸውን እየተማፀኑ ሳለ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ "ሰማያዊ ኢየሩሳሌምን እንዳየህ ምድራዊት ኢየሩሳሌምንም አይቶ ህንፃ ቤተ መቅደሱን በሰማያዊትና በምድራዊት ኢየሩሳሌም አምሳል ያንፅ ዘንድ ኢየሩሳሌም ሔዶ የተወለደበት ቤተልሔም፣ የተጠመቀበትን ዮርዳኖስ፣ የተሰቀለበትን ቀራንዮ፣ የተቀበረበትን ጎልጎታን፣ ደብረ ታቦርን ምስጢረ መለኮቱን የገለጸበትን አጠቃላይ ብዙ ተአምራት ያደረገበትን ሁሉ እንዲያይና እንዲሳለም መልአኩም እንደሚመራው መስቀል ክብራ ግን በዚሁ ከደናግሎች ጋር እንደምትቀመጥና ቅዱስ ሚካኤል እንደሚያጽናናት እንደሚጠብቃት መታዘዙን ነገረው።
በዚህም መሠረት ቅዱስ ላሊበላ ወደ ኢየሩሳሌም በፈቃደ አምላክ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ጠባቂነት በሱዳንና በግብጽ አድርጎ ኢየሩሳሌም ገባ። በዚያም ከላይ የተጠቀሱትን ቅዱሳን መካናትንና ሌሎችንም ቅዱሳት ስፍራዎች ለዐሥራ ሦስት ዓመታት በመዘዋወር ተመለከተ። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ላሊበላ የጉብኝቱንና የተፈቀደለትን ጊዜ ሲፈጸም አሁንም መልአኩ ተገልጾ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሄደ መንግሥትን ከዐፄ ገብረ ማርያም ተረክቦ የታዘዘውን እንዲሰራና በመንገድ በግብጽ ምድር የተበተኑትን ወገኖችን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ እንዲሄድ የታዘዘ መሆኑን ገለጸለት። ቅዱስ ላሊበላም በፈቃደ አምላክ በግብጽ ያሉትን ክርስቲያኖች ሰብስቦ በጊዜው የነበረው የግብጽ መንግሥት የእስላም ሃይማኖት ተከቲይ በመሆኑ እንዴት አድርጎ እንደሚያስተዳድራቸው ጠየቃቸው። ክርስቲያኖቹም እግዚአብሔርን ማምለክ እንደተከለከሉና በሀዘን በሰቀቀን የሚኖሩ መሆናቸውን ገለጹለት። በዚህ ዘመንም በመካከለኛው ምሥራቅ 3ኛው የመስቀል ጦርነት በመኖኑ ግብጻውያን ፊታቸውን ወደዚያ አዙረው ስለነበር ቅዱስ ላሊበላ በፈቃደ አምላክ በርካታ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ መጣ።
ዐፄ ገብረ ማርያም ወንድሙ ቅዱስ ላሊበላ ሕዝበ ክርስቲያንን ይዞ የኢትዮጵያ ምድር እንደረገጠ በሰማ ጊዜ በክብር የሚቀበሉት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰራዊት አሰልፎ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲመጣ ላከበት። ቅዱስ ላሊበላም ከባለቤቱ ጋር እና ከሕዝቡ ጋር በአክሱም ስለነበር የእግዚአብሔር ፍቃድ እንደሆነና ጊዜም እንደደረሰ በማወቁ ልዋል ልደር ሳይል ወደ ቤተ መንግሥቱ መጥተ ከዐፄ ገበረ ማርያም ጋር ተገናኘ። ንጉሡ ዐፄ ገብረ ማርያም ቅዱስ ላሊበላ ወደ እርሱ መምጣቱን በሰማ ጊዜ በፍቅር እንባ ተቀበለውና ሕዝቡን ሰብስቦ አዋጅ ነግሮ "እንሆ የአምላክ ፈቃድ ደርሷል መንግሥት ለዚህ ቅዱስ ሰው ይገባል ብሎ ዙፋኑን ለቅዱስ ላሊበላ አስረክቦ ተሰናብቶ ዛሬ ቅዱስ ሐርቤ እየተባለ ወደሚጠራው ገዳም ዘግቶ በጾም፣ በጸሎት፣ በቀኖናና በንስሐ ሰውነቱን ለፈጣሪው አስገዝቶ በክብር የካቲት16 ቀን ዐርፎአል።
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ላሊበላ ንጉሥ ነኝ ብሎ ሳመካ ስልጣኑን ለሕዝቡ በመስጠት ሕዝቡን ይመራ ነበር። ሕዝቡም የቅዱስ ላሊበላን የሃይማኖት ጽናትና ደግነት እያየ "ይህን ጻድቅ ንጉሥ ዕድሜውን አርዝምልን" እያሉ ይጸልዩለት ነበር። የቅዱስ ላሊበላን ደግነት በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ በውጭም ያሉ ነገሥታትና ሕዝብ ጭምር ያውቁ ነበር በዚህም መሰረት እስላሙም ክርስቲያኑም ቅዱስ ላሊበላን አንስተው አይጠግቡም ነበር። በቅዱስ ላሊበላም ዘመነ መንግሥት ጊዜ ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ያላት ግንኙነት የሰላም፣ የፍቅር፣ የክብርና የደስታ ግንኙነት ነበራት ለዚህም ነበር 1189ዓ.ም አካባቢ ሳላህ አዲን የተባለው የእስላም ንጉሥ በሦስተኛው የመስቀል ጦርነት ኢየሩሳሌምን በያዘ ጊዜ ከክርስቲያን ቅርሶች ዋና ዋናዎቹን በጎልጎታ በሚገኘው በጌታችን መቃብር አጠገብ ያለውን ዕሌኒ ንግሥት ቅዱስ መስቀሉን ያስወጣችበት ዋሻና በቤተልሔም ጌታ የተወለደበትን ጎል (በረት) ለቅዱስ ላሊበላ በስጦታ ያበረከተው።
የቅዱስ ላሊበላ ቤተ መቅደሶች አሰራርና ፍጻሜ፦ ቅዱስ ላሊበላ በዘመኑ ይህን ድንቅ ሥራ የሰራው ጮማ በመቆራረጥ ጠጅ በማማረጥ ልብስ መንግሥትን ለብሶ በመሽሞንሞን አልነበረም። ለአንዲት ደቂቃ መንፈስ እግዚአብሔር ያልተለየው ቅዱስ አባት ነበር። ፈጣሪው የሚመሰገንበትን የእርሱም ስም ለዘላለም የሚጠራበትን ቤተ መቅደስ ለማነፅም ሱባኤ ገብቶ ቦታው የት እንደሆነ ተረዳ። ነገር ግን የተገለጸለት ቦታ ቀይት የምትባል ባላባት ትኖርበት ነበር። ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሌላ ቦታ ሰጥቶ መጠቀም ይችል ነበር። ግን የትሕትና አባት ነውና መብቷን ሳይነካ እራሱን ዝቅ አድርጐ "ቦታውን ለሥራ ፈልጌዋለሁና በገንዘብ ሽጭልኝ" አላት። እርሷም እጅግ ከፍ ያለ ገንዘብ ጠየቀችው። ይኸውም አርባ ጊደር ላም መግዛት የሚችል ገንዘብ ነበር የጠየቀችው እርሱም ምንም ምን ሳይል ወርቁን ከፈላት። ቀይትም ገንዘቧን ተቀብላ ሔደችና እንደገና ተመልሳ "የምኖርበት ቦታ ስጠኝ" አለችው። እርሱም "ወደፊት ሌላ ቦታ እስክሰጥሽ በዚህ ቆይ" ብሎ ዛሬ ቆይታ የምትባለውን ቦታ ሰጣት ከዚህም የተነሳ ከግዜ ብዛት የቦታው መጠራያ ስም ቆይታ ተባለች። ይህች ቦታ የምትገኘው ከላሊበላ ከተማ በስተ ምሥራቅ በግምት ሁለት ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው። ለዚህ ነበር አባቶቻችን ንጉሥ ላሊበላ በአንጡራ ገንዘቡ የገዛውን ቦታ ስለሆነ በቦታው የሃይማኖት ሸቃጮች የሃይማኖት ሸቀጥ አያካሂዱበትም በማለት ለመስዋዕትነት የተዘጋጁት አሁንም ቢሆን ወደፊትም በዚህ ዙሪያ ላይ መናፍቅ ቦታ እንደሌለው ሊያውቅ ይገባል።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ላሊበላ የህንፃ ሥራውን ለመጀመር ቦታው ጫካ ስለነበር በሰፊው የማጽዳት ዘመቻ ካካሄደ በኋላ የት ቦታ መጀመር እንዳለበትና የማንን ቤተ መቅደስ መጀመሪያ እንደሚሰራ እንደገና በሱባኤ ለፈጣሪው ጥያቄ አቀረበ። በጥያቄው መሠረትም ቅዱስ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ እንዳየው የወርቅ መሰላል ከሰማይ እሰከ ምድር የብርሃን አምድ ተተክሎ ዛሬ ቤተ ማርያም ካለችበት ቦታ አርፎ መላእክት ሲወጡበት ሲወርዱበት ቅዱስ ላሊበላ አየ።
ቅዱስ ላሊበላ ሥራውን ከዚህች ቦታ እንደሚጀምርና መጀመርያ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን እንደሚሰራ አወቀ በዚህም መሰረት በመጀመርያ ደረጃ ቤተ ማርያም ሠራ። ከዚያም ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ መስቀልን፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ ጊዮርጊስ፣ቤተ ገብርኤል ወቤተ ሚካኤል፣ ቤተ መርቆሬዎስ፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ አባ ሊባኖስ። እነዚህን ቤተ መቅደሶች መንፈስ ቅዱስ ጥበብን ገልፆታልና ግድግዳውን፣ ጣራውን፣ በሩንና መስኮቱን፣ አእማዱን ቅኔ ማህሌቱን ልዩ ልዩ ቅርፅ እያመጣ እያስጌጠና እያሳመረ ከመላዕክት ጋር አመቤታችን እየተራዳችው በ23 ዓመት በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ እነዚህን አስደናቂ ቤተ መቅደሶች ሰርቶ አጠናቀቀ።
ቅዱስ ላሊበላ የአነፃቸው አብያተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ በውጭም አገር ብዙ እንደሆኑ ታሪኩ ይገልጻል። ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን እንደ ምሳሌ ብንመለከታቸው፦ አዲዲ ማርያም፣ አሸተ ማርያም ጀምሮ ነበር፣ ሶማርያ መቅደስ ማርያምን (መቃዲሾ ውስጥ) ብዙ የተጀመሩና ተሰብስበው አገልግሎት የሚሰጡ በኢትዮጵያ ብቻ 23 እንደሚደርሱ ታሪክ ያወሳል።
ቅዱስ ላሊበላ መዋዕለ ዘመኑን በሰላም፣ በፅኑ፣ በእምነት፣ በፍቅርና በአንድነት ከአሳለፈ በኋላ ንግስናውን ለወንድሙ ልጅ እንዲሁም ለአሳደገውና በረከቱን ለሰጠው ለቅዱስ ነአኵቶ ለአብ አስረክቦ በጾም በፀሎት ተወስኖ ኖረ። ከዚህም በኋላ የሚያርፍበት ጊዜ ሲደርስ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በብርሃን ሠረገላ ተቀምጦ የሚአስፈራ መብረቅን ተጐናጸፎ አእላፋት ሠራዊቶቹ ዙሪያውን ሁነው ወደርሱ መጥቶ እንዲህ አለው "ወዳጄ ላሊበላ ሆይ ሰላም ይሁንልህ እኔ በማይታበል ቃሌ እነግርሃለሁ ማደሪያህ ክብርር ሁሉ ከከበሩ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያቶቼ ጋራ ይሁን። በጸሎትህና በቃልኪዳንህ ለሚታመን እምነቱ እንደ ቅዱሳን ጴጥሮስኔ ጳውሎስ ደም መፍሰስ ይሆንለታል።
ወደ ቤተ መቅደስህም የሔደ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደሴ እንደ ሔደ ይሆንለታል መቃብርህንም የተሳለመ የሥጋዬን መቃብር እንደ ተሳለመ ይሆንለታል በዓመታቱ ወሮች ሁሉ የተራቡትን እያጠገበ፣ የተጠሙትንም እያጠጣ መታሰቢያህን የሚያደርግ እኔ የተሠወረ መና እመግበዋለሁ የሕይወት ጽዋንም አጠጣዋለሁ። በመታሰቢያህ ቀንም ዕጣን ወይም ስንዴ የሚያገባውን እኔ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በውስጠኛው መጋረጃ አስቀምጬ ከተቆረሰው ሥጋዬ አቆርበዋለሁ፤ በአማላጅነትህም እየታመነ የገድልህንና የቃል ኪዳንህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ያንተ ስም በተጻፈበት ቦታ እኔ ስሙን እጽፋለሁ፣ በፍጹም ልቡ ለሚያምን ይሁን የማይታበይ ቃል የተናገርኩ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ" አለው።
ቅዱስ ላሊበላም ይህን ቃል ኪዳን ስለ አጸናለት ክብር ይግባውና ጌታችንን እያመሰገነ በምድር ላይ ወድቆ ሰገደ። ጌታችንም ሰላምታ ሰጥቶት በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ። ከዚህም በኋላ ጥቂት ሕማም ታሞ ሰኔ12 ቀን በ1197ዓ.ም በ96 ዓመቱ በሰላም ዐረፈ። ሲያርፍም ደገኛው ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር ነገራተ እግዚአብሔርን እየተነጋገሩ እንዳለ ድንገት እንደ እንቅልፍ ሸለብ አድርጎት እንደሆነ ታሪኩ ይገልፃል። ነፍሱንም የብርሃን መላእክት ተቀብለው የዘላለም ሕይወት ማደሪያ ወደሆነ ማረፊያው አስገቡት። (የሰኔ12 ስንክሳርና ቅዱሳንና ድንቅ ሥራቸው የአራቱ ቅዱሳን ነገሥታት ታሪክ ከሚለው መጽሐፍ።)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ከኤፍሬም ወገን መስፍኑ ኢያሱ ተወለደ እርሱም ለእስራኤል ልጆች ከጠላት ሰልፍ መድኃኒት ሁኖ ያዳናቸው ነው። የጌታችንም መወለድ ለአዳምና ለልጆቹ መድኃኒት ሆናቸው። የርሱም የቀድሞ ስሙ ሆሴዕ ነበረ እስራኤልን ከአማሌቅ ጦርነት በራፌድ በአዳናቸው ጊዜ ኢያሱ ተብሎ ተጠራ ይህም አዳኝ ማለት ነው።
ሙሴም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር መረጠውና ለእስራኤል መስፍን አድርጎ ሾመው ልዩ ከሆኑ አሕዛብም ጦርነት አዳናቸው ርስታቸውንም አወረሳቸው ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የሮሀ ንጉሥ አቃርዮስ አረፈ የርሱም ግዛቱ በሶርያ አገር ሰርሜን በምትባል ክፍል ነው እርሷም ሮሀ ናት።
ጣዖትን የሚያመልክ ሆኖ ኖረ መፃጉዕም ነበረ ለባለ መድኃኒቶችም ገንዘቡን ሁሉ ሰጥቶ ሊአድኑት አልቻሉም። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሽተኞችን በማዳን አጋንንትን በማስወጣት የዕውሮችን ዐይኖች በመግለጥ ሙታንን በማስነሣት የሚሠራውን ድንቅ ተአምራቱን በሰማ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደርሱ ላከ።
የሰውን ሥጋ ለብሰህ በኢየሩሳሌም የተገለጥክ የእግዚአብሔር ልጅ ምስጋና ይድረስህ ከእርሱ ሳትለይ ወደታች ለላከህ ለቸር አባትህም ምስጋና ይድረሰው አንተ የምትስተካከለው ክርስቶስ እንደሆንክ በሕሊናየ ለገለጠልኝ መንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይሁን። ያለወንድ ዘር በድንግልና ለወለደችህም እናትህ ምስጋና ይሁን ለሚያምኑብህ ሁሉ ሰላምታ ይድረሳቸው።
እኔም በአንተ አምኜ ከንቱ ጣዖትን ከማምለክ አንተን ወደ ማምለክ ተመለስኩ በኔ ላይም ንጉሥ ትሆን ዘንድ ሀገሬንም ትባርክ ዘንድ ከበሽታዬም ታድነኝ ዘንድ ከኃጢአቴም ታነጻኝ ዘንድ ወደኔ ና ጌታዬ ሆይ የከበረ ስምህን አይሁድ ሲጠሉ ለአንተ በኢየሩሳሌም መኖር ምን ያደርግልሃል። በከንቱ ለምን ትደክማለህ መካር ያጡ ወገኖች ናቸውና በቀድሞ ዘመንም ድንቆች ተአምራቶችን በማድረግ ከግብጽ አገር በአወጣኻቸው ጊዜ አላመኑብህም በበረሀም አርባ ዓመት መናውን በመገብካቸው ጊዜ ተቆጥተህ ለጥፋት እስከ አደረስካቸው በአንተ ላይ ምን ያህል አጒረመረሙብህ በሚራብና በሚጠማ ምድራዊ ሥጋማ ሲያዩህ እንዴት ነዋ ኀሳባቸው ከዚህ የተለየ ይመስልሃልን አንተ ከጥንት ጀምሮ የተሠወረውን ታውቃለህና። ይኸንንና ይህን የመሰለውን ጽፎ ደብዳቤ ወደርሱ ላከ።
የንጉሥ መልክተኞችም ወደ ጌታችን በደረሱ ጊዜ ሳይነግሩት የሰመጡለትን መልእክት አውቆ ነጭ ልብስ አነሥቶ ፊቱን አሸበት የፊቱም መልክ ወደ ልብሱ ገባ ከደቀ መዝሙሩ ከታዴዎስ ጋር እንዲህ ብሎ ላከለት ይህን የኔ መልክ የሆነውን ሥዕል ተቀበል እርሱም የምትሻውን ሁሉ ይፈጽምልሃል ከበሽታህም ይፈውስሃል ሀገርህንም ይባርካል መንግሥትህንም ያጸናል ይህ ሥዕል እኔን ነውና ይለወጥ እንደሆነ በውኃ በእሳት ፈትነው።
መልክተኞችም ወደ ንጉሥ አቃርዮስ በደረሱ ጊዜ ያንን ሥዕል ሰጡት በእሳትና በውኃም ፈተናውና ምንም ምን ጥፋት አልደረሰበትም የሮሀ አገር ሰዎችም ከንጉሣቸው ጋር በጌታችን የመለኮት ሥልጣን አመኑ ይህ ሥዕል ቊጥር የሌለው ብዙ ድንቅ ተአምራትን አደረገ ንጉሡንም ከበሽታው ፈወሰው ከዚህም በኋላ ዕድሜውን ሲፈጽም በዚች ዕለት አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ሰምኑድ ከሚባል አገር ገመላዊው ቅዱስ ቆሪል አረፈ። እርሱም በጾም በጸሎት ተወስኖ የሚኖር ነው እግዚአብሔርም የተሰወሩ ምሥጢራት ማወቅን ሰጠው የሚገለገልባቸው ከማሳም ተልባ የሚጭንባቸው ሦስት ግመሎች አሉት።
ፈራጉን በሚባል አገር ለእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ካህናት የሆነ አንድ ሰው ነበረ ቤተ ክርስቲያኒቱም ነገሥታትና መኳንንት በየጊዜው የሰጧት ብዙ ገንዘብ አላት በሊቀ ካህናቱም ዘንድ የዕቃው ሣጥን በሥውር ይኖር ነበር የዚያንም ዕቃ ቊጥር ኤጲስቆጶሱ ያውቃል ያ ሊቀ ካህናት በእርሱ ሥልጣን ሥር ነበርና ከዚህም በኋላ የዕቃው ሣጥን ያለበትን ለልጁ ሳይነግር ያ ሊቀ ካህናት በድንገት ሞተ።
ኤጲስቆጶሱም የሊቀ ካህናቱን ሞት በሰማ ጊዜ ወደዚያች ቤተ ክርስቲያን መጥቶ ከልጁ ገንዘቧን ፈለገ ያም ልጅ አባተ በድንገተኛ ሞት ስለተነጠቀና ስለ አልነገረኝም ዕቃው ያለበትን አላወቅሁም አለው። ኤጲስቆጶሱም ሰምቶ ተቆጣ ሊአሠቃየውም ፈለገ ያም ልጅ ኤጲስቆጶሱን ዕቃው ያለበትን ቦታ እስከምፈልግ ድረስ ቆየኝ ባላገኘሁትም ጊዜ የወደድከውን ታደርግብኛለህ ብሎ ለመነው እርሱም ጊዜ ሰጠው።
ወደ ቤቱም በገባ ጊዜ ችግሩን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት። እርሷም በእግዚአብሔር ታምነህ በአባ መቃርስ ገዳም ወዳሉ አባቶች መነኰሳት ወደ ጎረቤቶቻቸውም ሒድ እነርሱ ይነግሩሃልና አለችው። ወደዚያም ሲደርስ ችግሩን ይፈጽሙለት ዘንድ ለመነኰሳቱ ነገራቸው የሚነግረውም አጥቶ ተስፋ ቆረጠ። አንድ ባሕታዊም ጠቀሰውና እንዲህ አለው ሰምኑድ ወደሚሉት አገር ሒደህ ስለ ባለ ገመሉ ቆሪል ጠይቅ በእርሱም ዘንድ እደር እርሱም ይነግርሃል አለው።
ወደ ሰምኑድ መንደርም ደርሶ ስለርሱ ስለቆሪል ጠየቀ ሰዎችም ነገሩት ያለበትንም አመለከቱት በሔደ ጊዜም ከመኖሪያው አገኘው ሦስቱ ግመሎቹም ከእርሱ ጋር ነበሩ አባ ቆሪልም ፍላጎቱን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ወደ ማደሪያው አስገብቶ መብልን አቀረበለት አባቴ ሆይ ችግሬን ሳትፈጽምልኝ እኔ አልበላም አለው ቆሪልም ችግርህ በጊዜው ጊዜ ይፈጸማልና አሁመን ብላ አለው።
ከራትም በኋላ በየመኝታቸው ተኙ የሌሊቱም እኩሌታ ሲሆን ያ ሰው ቆሪልን ከግመሎቹ ጋር ቁሞ አየው ሲሰግድ ይሰግዳሉ ሲቆምም ይቆማሉ። በነጋ ጊዜም ተልባ ይጭንባቸው ዘንድ ወደ ማሳ ወሰዳቸው ያም ሰው ሊራዳው አብሮ ሔደ ወደ ማሳውም በደረሱ ጊዜ ቆሪል በገመል ላይ መጫን ጀመረ ያም ሰው ሁለተኛውን ገመል ወስዶ ያለ አቅሙ ሸክሙን አክብዶ ጫነው ገመሉም መንቀሳቀስ ተሳነው ሊመታው ፈልጎ በትር አነሣ። ገመሉም አባቴ ቆሪል ሆይ በላዬ ጉዳት እንዳያደርስ ይህን ሰው አታሰናብተውም እርሱ ያለ ችሎታዬ አሸክሞኛልና ብሎ በሰው አንደበት ጮኸ ቆሪልም መጥቶ ሸክሙን አቀለለለት ያንንም ሰው ልጄ ሆይ በማይችለው መጠን ለምን አሸከምከው አንተ የምትአዝነው ልትሸከመው የማትችለውን ሸክም በላይህ ስለ አመጡብህ አይደለምን አለው።
ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ያ ሰው ስለ ችግሩ የዕቃውን ቦታ ይገለጥለት ዘንድ አባ ቆሪልን ለመነው እርሱም ለሌላ እንዳይናገር ከአማለው በኋላ ገለጠለት እንዲህም አለው በዚያች ቤተ ክርስቲያን በስተምሥራቅ ታናሽ ዋሻ አለ ዕቃውም በዚያ አለ።
ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ለሚስቱ ነገራት በአንድነትም ወደዚያ ቦታ ሔዱ ከነገሥታት መዛግብት እንኳ የሚመስለው የሌለ መዝገብን አገኙ ከዚህም በኋላ ለኤጲስቆጶስ ነገረው ኤጲስቆጶስም ይጠብቅ ዘንድ ለርሱ ስጠው። ይህም ጻድቅ ሰው ቆሪል ብዙ ተጋድሎን ከተጋደለ በኋላ በመልካም ሽምግልና አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የአክሚም ሰማዕታት መታሰቢያቸው ነው። እነርሱም በከበረ የልደት በዓል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቊርባን ቅዳሴ አድርገው ተሰብስበው ሳሉ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሠዊያው ላይ ሥጋውንና ደሙን ለሕዝቡ ሲያቀብላቸው አዩት።
በዚህም ታላቅ ደስታ ውስጥ እያሉ መኰንኑ አርያኖስ መጥቶ ከበባቸው ወደ ቤተ ክርስቲያንም ገብቶ ስማቸው በሕዋፋና ወኒን የሚባል ሁለቱን የሀገር አለቆች ይዞ ራሳቸውን በሰይፍ ቆረጠ ከዚህም በኋላ ቀሳውስትን ዲያቆናትን ንፍቀ ዲያቆናትን መምህራንን የቤተ ክርስቲያንን ሹማምንት ገደለ ደማቸው ከቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ ወጥቶ ሃያ ክንድ ያህል እስቲጎርፍ ወንዶችን ሴቶችንና ልጆችንም ምንም ሳያስቀር አሳረዳቸው።
ኤጲስቆጶሱን አባ ብኑድያኖስን ዲዮስቆሮስን ሰከላብዮስን ከኤጲስቆጶሱ ጋር ያሉ መነኰሳትንም እነርሱን እንደታሠሩ አርያኖስ ከእርሱ ጋር ወሰዳቸው እነሆ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ጥር አንድ ቀን ተፅፎአል።
ለእርሱም ከቸር አባቱ ከማሕየዊ መንፈስ ቅዱስ ጋር ጌትነት ክብር ምስጋና ሰጊድ ከርሱ ጋር በትክክልነት ይገባል፤ እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages