ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 30 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 30

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ሠላሳ በዚች ቀን በአባ መቃርስ ገዳም በአስቄጥስ አበ ምኔት የሆነ የከበረ አባት #አባ_ዮሐንስ አረፈ፣ የትንቢትና በሽተኞችን የመፈወስ ሀብት ተሰጠው የተመሰገነ #የአባ_ዮሐንስ_ብጹዕ አረፈ፣ #ቅዱሳን_ኮርዮንና_ፊልሞና ከእነርሱም ጋር አርባ ወታደሮች በሰማዕትነት ሞቱ፣ ተጋዳይ የሆነ #አባ_ዘካርያስ_ገዳማዊ አረፈ፡፡


ታኅሣሥ ሠላሳ በዚህች ቀን በአባ መቃርስ ገዳም በአስቄጥስ አበ ምኔት የሆነ የከበረ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ።
ይህም አባት በተሾመ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በራች ለብዙ ቅዱሳንም አባት ሆነ ከእርሳቸውም ውስጥ ታላላቅ ከዋክብት የሆኑ አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም የሀገረ ተሙዝ ኤጲስቆጶስ አባ ሚናስ የሀገረ ስሐ አባ ዘካርያስ ለብዙ ሰዎች ነፍሳት ወደብ የሆኑ እነርሱን የመሰሉ ሌሎች ብዙዎች አሉ። ለሕዝቡ ቅዱስ ቊርባንን በሚያቈርብ ጊዜ ኃጢአተኛውና ጻድቁ ይገለጥለታል ከቅዱሳን መላእክቶቹ ጋር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንም በመሠዊያው ላይ ብዙ ጊዜ አየው።
በአንዲትም ዕለት ሥራው የከፋ አንዱን ቄስ ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጣ አየው ከእርሱም ጋር ያሉ ብዙዎች ርኩሳን የረቀቁ አጋንንት ከበውት አፉ ውስጥ ልጓም አድርገዋል ወደ ቤተ ክርስቲያንም ከመግባቱ በፊት የእግዚአብሔር መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ በእሳት ሰይፍ ከእርሱ ከቄሱ መናፍስትን አሳደዳቸው ቄሱም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ መቀደሻውን የክህነት ልብስ ለበሰ ሁለመናውም እንደ እሳት ሆነ ቀድሶም ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው።
ልብሰ ተክህኖውንና የመቀደሻውን ሽልማት ከላዩ አውልቆ ወደ ውጭ በወጣ ጊዜ እንዚያ የጠቆሩ መናፍስት ርኩሳን ተቀብለው እንደቀድሞው አደረጉበት።
አባ ዮሐንስም ይህን ነገር ለመነኰሳቱ ሲያስረዳ እንዲህ አላቸው በቅዳሴ አገልግሎት ጊዜ ለኃጢአተኛውና ለጻድቁ ቄስ ልዩነት የለም ስለ ሕዝቡ እምነት ያ ኅብስት ተለውጦ የክርስቶስን ሥጋ ይሆናልና ወይኑም የከበረ ደሙን ይሆናልና።
ዳግመኛ በምሳሌ እንዲህ አላቸው በብረት በወርቅና በብር ላይ እንደሚቀረጽ እንደ ንጉሥ ማኅተም ነው። ማኅተሙም አይለወጥም እንዲሁ ከካህናትም የክህነት ጸጋ አይለወጥም እርሱ እግዚአብሔር በጊዜው ጊዜ ለሁሉም ለየአንዳንዱ እንደሠራው ይከፈለዋል እንጂ።
ይህንም የከበረ ዮሐንስ ታላቅ መከራ ደርሶበታል አረማውያን በርበር ማረከው ወደ አገራቸወደ ወስደውታልና እያሠቃዩትም በእነርሱ ዘንድ ብዙ ዘመን ታሥሮ ኖረ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ገዳሙ መለሰው።
ከመሞቱ በፊት የሚሞትበትን ጊዜ አውቆ መነኰሳቱን ሰበሰባቸውና የወንጌልን ትዕዛዝ ይጠብቁ ዘንድ በሰማያዊ መንግሥት በጎ ዕድልን ርስትንም ከእርሳቸው ጋር ይቀበሉ ዘንድ እንደ ቅዱሳን አባቶች አካሄድ እንዲጓዙ አዘዛቸው።
ከዚህም በኋላ ጥቂት ታመመ ነፍሱን ሊቀበሉ የቅዱሳንን አንድነት ሲመጡ አያቸውና ፈጽሞ ደስ አለው ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ መነኰሳቱ ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን ተሸክመው ወስደው በመዘመርና በታላቅ ምስጋና ገንዘው ቀበሩት እርሱንም ከመውደዳቸው የተነሣ ከተገነዘበት ልብስ ቆርጠው በእነርሱ ዘንድ አኖሩት ለሚታመም ሁሉ የሚፈውስ ሆነ የዚህም አባት ዕድሜ ዘጠና ዓመት ሆነ በግቢግ የሚልዋት መኖሪያው እስከ ዛሬ አለች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ደግሞ የተመሰገነ የአባ ዮሐንስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ይህም ተጋዳይ የምንኲስና ልብስን ከለበሰ ጀምሮ የትንቢትና በሽተኞችን የመፈወስ ሀብት ተሰጠው ዜናውም በሀገሩ ሁሉ ተሰማ።
ይህን አባ ዮሐንስን ሁል ጊዜ የሚጐበኘው አንድ መኰንን ነበረ የመኰንኑም ሚስት ወደ አባ ዮሐንስ ዘንድ እንዲወስዳት ባሏን ታምለውና ታስገደድው ነበር እርሱም የከበረ አባ ዮሐንስ ከአርባ ዓመት ጀምሮ የሴቶችን ፊት አላየም አላት። ከዚህም በኋላ መኰንኑ ሒዶ ሚስቱ ያለችውን ለአባ ዮሐንስ ነገረው አባ ዮሐንስም በእግዚአብሔር ፈቃድ የፈለገችውን እፈጽምላታለሁ አለው።
በዚያችም ሌሊት የከበረ ዮሐንስ ለዚያች ሴት በሕልም ተገልጾ እንዲህ አላት ጻድቅ ያልሆንኩ ወይም ነቢይ የኔን ፊት ታዪ ዘንድ የምትሺ አንቺ ሴት ከእኔ ምን አለሽ እኔስ ካንቺ ምን አለኝ እንግዲህስ ፊቴን ማየት አትሺ ይህንንም ብሎ በላይዋ ጸልዮ ባረካት።
በማግሥቱም የከበረ አባ ዮሐንስ በመንፈስ እንደታያት ለባሏ ነገረችው። መልኩንና አምሳያውን አመለከተችው ከዚህም በኋላ ከብዙ ሙገሳና ምስጋና ጋር ባሏን ወደ አባ ዮሐንስ ላከችው።
የከበረ ዮሐንስም ባሏን በአየው ጊዜ ፈገግ ብሎ የሚስትህ ምኞቷ የተፈጸመላት አይደለምን በዚች ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ አግኝታኛለችና አለው መኰንኑም ሰምቶ ከትሩፋቱና ከደግነቱ የተነሣ እጅግ አደነቀ።ይህም አባ ዮሐንስ ጭንቅ በሆነ ተጋድሎ ዘጠና ዓመት ያህል ኖረ ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የመኰንኑ አርያኖስ የጭፍሮቹ ታላላቆች ኮርዮንና ፊልሞና ከእርሳቸውም ጋር ካሉ አርባ ወታደሮች ጋር በሰማዕትነት ሞቱ።
የሰማዕትነታቸውም ምክንያት የአክሚም ታላላቆች ከሆኑ ከሰማዕታት ዲዮስቆሮስ ከሰከላብዮስና ከብኑዲያስ የተደረገውን ተአምራት በአዩ ጊዜ የወታደርነት የማዕረግ ሽልማታቸውን ጣሉ በመኰንኑ አርያኖስም ፊት ቁመው እኛ በእውነተኛ አምላክ በክርስቶስ የምናምን በግልጥ ክርስቲያን ነን ብለው ጮኹ። መኰንኑም ከእሳት ማንደጃ ውስጥ ይጥሏቸው ዘንድ አዘዘ ራሳቸውንም ሲወረወሩ ብዙዎች አዩአቸው ገድላቸውንም እንዲህ ፈጸሙ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ተጋዳይ የሆነ ዘካርያስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከመመንኰሱ በፊት በጐዳና ሲጓዝ አረማውያን በርበር ተነሡበትና ያዙት ሊያርዱትም ወደዱ በእግዚአብሔርም ፈቃድ የገዳሙ አለቃ በዚያት ጐዳና ሲያልፍ በላያቸው ጮኸ እነርሱም ሠራዊት እንደደረሰባቸው ተጠራጠሩ ፈርተውም ሸሹ ሲሸሹም ከባሕር ገብተው ሰጠሙ።
ዘካርያስም ከመገደል በዳነ ጊዜ ይሸጥ ዘንድ ገንዘባቸውን ይዞ ወደ ከተማ ገባ የሀገሩም ገዥ ያዘው ሌባ እንደ ሆነ አስቦ ሊገለው ወደደ ግን ሥራውን በአወቀ ጊዜ ተወው።
ከዚህም በኋላ ወደ አባ ጳኩሚስ ገዳም ሒዶ የምንኲስናን ልብስ ለበሰ ሰይጣንም እስከ ቀናበት ድረስ በጾምና በጸሎት ተጠመደ ከዚህም በኋላ በአባቱ ተመስሎ በሕልም ታየውና መሞቻዬ ጊዜ ደርሷልና ትቀብረኝ ዘንድ ና አለው ቅዱሱም እውነት እንደሆነ አስቦ ወደ አባቱ ሔደ ግን በጤንነት አገኘው። የሰይጣን ተንኰልም እንደሆነ አውቆ ወደ መኖሪያው ተመለሰ ሰይጣንንም ድል እስከአደረገው ድረስ በሩን ዘግቶ እየተጋደለ ኖረ።
በሆሣዕናም ዕለት ወደ አበ ምኔቱ ሒዶ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ ፈቃድ ለመነው ፈቀደለትም በማግሥቱም ፊታቸው የሚያባራ ሦስት ሰዎች ሲጠብቁት አገኛቸውና አብሮዋቸው ሔደ።
ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱ የአባ ዘካርያስን ቤት ሊጎበኝ ሔደ ሦስት ታላላቅ ዘንዶዎችም በምድር ላይ ሲርመሰመሱ አግኝቶ በአያቸው ጊዜ ፈራቸው እነርሱም በስሙ ጠሩት ወደነርሱም ዘወር ሲል አባት ሆይ ሲመግበን የነበረ ጌታችን ዘካርያስ ከዚህ ወደየት ሔደ ብለው በሰው አንደበት ተናገሩት። አበ ምኔቱም ሰምቶ አደነቀ መብልንም ሰጣቸው።
አባ ዘካርያስም ወደ መኖሪያው ተመልሲ በብዙ ተጋድሎ ኖረ። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages