ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 7 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 7

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የእስክንድርያ ሀገር አርባ ሦስተኛ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #ቅዱስ_እለእስክንድሮስ አረፈ፣ የእስክንድርያ አርባ አምስተኛ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #ቅዱስ_ቴዎድሮስ አረፈ፣ ገዳማዊው ግብጻዊ #ጻድቅ_አብዱልማዎስ አረፉ፡፡


የካቲት ሰባት በዚህች ቀን የእስክንድርያ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት እለእስክንድሮስ አረፈ፡፡ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ሦስተኛ ነው። ይህም አባት ታሮን በሚባል ገዳም መነኰሰ ትርጓሜውም የአባቶች ገዳም ማለት ነው በጌታችንም ፈቃድ በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ እርሱ የተማረ አዋቂ ጻድቅ ሰው ነበረና።
በሹመቱ ወራትም ብዙ መከራ ደረሰበት የግብጽ ንጉሥ ልጁን ሹሞ በመንግሥቱ ላይ አሠለጠነው እርሱም በአስቄጥስ በረሀ ያለውን የመነኰሳቱን ገዳማት አፈረሳቸው። ከክፋቱና ከክህደቱ ብዛት የተነሣ ከምስር በስተሰሜን ወዳለች ገዳም ገብቶ በዚያ አምላክን የወለደች የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕሏን አየና ይች ምንድን ናት አለ እርሷም በሽልማት ሁሉ የተሸለመችና ያጌጠች ናት በልብሶቿም ላይ ያማረ የሐር ልብስ ነበረ ስዎችም የክርስቶስ እናት የሆነች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ሥዕል ናት አሉት እርሱም ተሳድቦ የረከሰ ምራቁን በፊቷ ላይ ተፍቶ ደኅና ከሆንኩ ክርስቲያኖችን ፈጽሜ አጠፋቸዋለሁ አለ ዳግመኛም በክብር ባለቤት በጌታችን ክርስቶስ ላይ የስድብ ቃልን ተናገረ።
ሌሊትም በሆነ ጊዜ የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ ታላቅ ራእይን አየ በነጋም ጊዜ ለአባቱ እንዲህ ብሎ ነገረው ዛሬ በዚች ሌሊት ታላቅ መከራና ብዙ ቅጣት ደረሰብኝ ታላቅ ዙፋንንም አየሁ በላዩ የተቀመጠበት ሰው እጅግ የሚያስፈራ የሚያስደነግጥ ነው ፊቱም ከፀሐይ ይበራል የብዙ ብዙ የሆኑ ሠራዊት የጦር መሣሪያ ይዘው በዙሪያው ቁመው ነበር እኔና አንተም እሥረኞች ሁነን በኋላው ቁመን ነበር እኔም በዙፋን ላይ የተቀመጠው ማነው ብዬ ጠየቅሁ ትላንት አንተ የዘበትክበት የክርስቲያን ንጉሥ ክርስቶስ ይህ ነው አሉኝ ከዚህም በኋላ የጦር መሣሪያ ከተሸከሙት አንዱ ወደ እኔ መጥቶ ጐኔን በጦር ወጋኝ ጦሩንም ከጐኔ ውስጥ አላወጣውም።
አባቱም ሰምቶ ደነገጠ እጅግም አዘነ ያ ልጁም ወዲያውኑ ታመመ አንደበቱም ተዘግቶ በክፉ አሟሟት ሞተ። ዳግመኛም ከአርባ ቀን በኋላ አባቱ ሞተ። በርሱም ፈንታ ሌላ ንጉሥ ተሾመ እርሱም ክርስቲያኖችን እጅግ አሠቃያቸው ይህንንም አባት ሊቀ ጳጳሳት እለእስክንድሮስን አብዝቶ አሠቃየው ከሕዝቡ ሦስት ሺህ የወርቅ ዲናር ለምኖ እስከ ሰጠው ድረስ ጌታችንም ይህን ንጉሥ ፈጥኖ አጠፋው።
ከዚህም በኋላ አሁንም ሌላ ንጉሥ ተሾመ እርሱም ሊቀ ጳጳሳቱን ይዞ እንደ ቀድሞው ሦስት ሺህ የወርቅ ዲናር እንዲሰጠው ፈለገ እርሱም ከወገኖቼ እስከምለምን ታገሠኝ ብሎ ማለደው ንጉሡም ቀጠሮ ሰጠውና ይለምን ዘንድ ወደ ላይኛው ግብጽ ወጣ።
በተራራ ላይ አንድ ገዳማዊ ሰው ነበር ከእርሱም ጋር ሁለት ደቀ መዛሙርት አሉ በተራራውም በአንድ ቦታ እንዲቆፍሩና እንዲጠርጉ አዘዛቸው ወርቅን የተመላ አምስት ማሰሮ አገኙ አንዱን ሸሽገው አራቱን ወደ ገዳማዊ መምህራቸው አመጡ እርሱም ይረዳበት ዘንድ እንዲስጡት ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ ላካቸው። እነርሱ ግን እነዚያን የወርቅ ማሰሮዎች ይዘው ተመልሰው ወደ ዓለም ገቡ የምንኵስና ልብሳቸውንም ጥለው ሚስት አገቡ በዚያም ወርቅ ወንዶችና ሴቶች ባሮችን እንስሳትንም ገዙ።
የዚያችም አገር አስተዳዳሪ ያዛቸው ገንዘብንም ከወዴት እንዳገኙ በመግረፍ መረመራቸው እነርሱም አምስት የወርቅ ማሰሮዎችን እንዳገኙ አመኑ መኰንኑም ለንጉሥ የጭፍራ አለቃ አሳልፎ ሰጣቸው እርሱም ወደ ንጉሥ አቀረባቸውና አምስት የወርቅ ማሰሮ እንዳገኙ አስረዳው ንጉሡም ጭፍሮቹን ልኮ የሊቀ ጳጳሳቱን ቤት በረበረ የአብያተ ክርስቲያናት ከሆነ ከንዋየ ቅድሳት ያገኘውን ሁሉ ወሰደ ሊቀ ጳጳሳቱንም አሠረውና ወርቅን የተመሉ አራቱን ማሰሮዎች ደግሞም ሦስቱን ሽህ የወርቅ ዲናር አምጣልኝ አለው እርሱም ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ገንዘብ ምንም ምን የለኝም አለው ወደ ሕዝቡ ልኮ ሦስቱን ሽህ የወርቅ ዲናር አምጥተውለት እስከ ሰጠው ድረስ አልተወውም ይህንንም ክፉ ንጉሥ ጌታችን አጠፉው።
ከዚህም በኋላ ከእርሱ የከፋ ሌላ ንጉሥ ተሾመ እርሱም የሐሰተኛውንና የርኵሱን ነቢይ ስም በከበረ መስቀል ፈንታ በእጆቻቸው ውስጥ እንዲአትሙ የክርስቲያንን ወገኖች አስገደዳቸው። ይችም ምልክት የመለኮትን ነገር የሚናገር ወንጌላዊ ዮሐንስ የተናገራት ትንቢት ናት ይህም ክፋ ንጉሥ ወደ ሀገሮች ሁሉ ይህን እንዲአደርጉ አዘዛቸው ሊቀ ጳጳሳቱንም እንዲሁ ያደርግ ዘንድ አዘዘው።
ሊቀ ጳጳሳትም ይተወው ዘንድ ብዙ ለመነው አልተቀበለውም ዳግመኛም እስከ ሦስት ቀን ይታገሠው ዘንድ ለመነው ከዚህም በኋላ ደግሞ እንዳይጥለውና ወደዚህ ወደረከሰ ሥራ እንዳያስገባው ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ማለደ ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ በጥቂት ደዌ ጐበኘው ወደ ቤቱ እስክንድርያ ይሔድ ዘንድ እንዲአዝዝለት ንጉሡን ለመነው።
ንጉሡም ከለከለው ሰለ እጅ ኀትመት ምክንያት ለመፍጠር ሰለ መሰለው የእግዚአብሔርም መልአክ ተገለጠለትና ነገ ታርፋለህ አለው እርሱም አርድእቱን እግዚአብሔር ነገ ስለሚጐበኘኝ አርፋለሁና መርከብን አዘጋጁ አላቸው። አንዳለውም በማግሥቱ አረፈ ሥጋውንም በመርከብ ተሸክመው ወስደው ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሥጋ ጋር ቀበሩት።
በዚህም አባት አለእስክንድሮስ ዘመን በግብጽ አገር ለሚኖሩ መለካውያን ስሙ አንስጣስዮስ የሚባል ሊቀ ጳጳሳት ነበራቸው ያዕቆባውያን ምእመናንን ይወዳቸዋል ስለዚህም ወገኖቹ መለካውያን ተጣሉት። እርሱም ነፍሱን ያድን ዘንድ አስቦ ወደዚህ አባት አለእስክንድሮስ መጥቶ ከሥልጣኑ በታች በመሆን የሚታዘዝ ሆነ እለእስክንድሮስም አንስጣስዮስን በእርሱ ፈንታ የሊቀ ጵጵስናውን ሥልጣን ይዞ መንጋውን ይመራ ዘንድ እርሱ ግን ከመነኰሳት እንዳንዱ ሁኖ በገዳም ይኖር ዘንድ እንዲተወው ለመነው።
አባ አንስጣስዮስም አልወደደም እንዲህም አለ ይህን የምሻ ከሆነ አኔ እስከ ዛሬ ሊቀ ጳጳሳት አልነበርኩምን ላንተ ደቀ መዝሙርህ ሁኜ ላገለግልህ ወደድኩ እንጂ አለ። በመካከላቸው ከተደረገው ከብዙ ልመና ከብዙ ምልልስም በኋላ ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ አንስጣስዮስ ፈቀደ በአንዲትም ሀገር ላይ ኤጲስቆጶስነትን ሾመው። መንጋውንም እንደሚገባ በጎ አጠባበቅን ጠበቀ፡፡ አባት እለእስክንድሮስም በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር የኖረው ሃያ አራት ዓመት ከስድስት ወር ነው እግዚአብሔርንም አገለገለው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት ቴዎድሮስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ አምስተኛ ነው። ይህም አባት መርዩጥ በሚባል አገር በአንድ ገዳም ውስጥ መነኰሰ የዚያም ገዳም ስም ጠንቡራ ነው። ለአንድ ፍጹም ጻድቅ የሆነ ሽማግሌ ሰው ደቀ መዝሙሩ ሆነ። እርሱም ልጁ ቴዎድሮስ በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና እንደሚሾም በመንፈስ ቅዱስ አይቶ ይህንን ለመነኰሳቱ ነገራቸው።
ይህም አባት ቴዎድሮስ በገድል የተጠመደ ሆነ መልኩም የሚያምር ነው በሰውነቱም ላይ ከውስጥ ማቅ በመልበስ በላዩ የብረት ልብስ መንቈር ይለብስ ነበር በቅንነቱና በትሕትናው ፍጹም ሆነ። በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ተመርጦ በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ። የክርስቶስንም መንጋዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ ሁልጊዜ መጻሕፍትን በማንበብ ያስተምራቸው ነበር ይልቁንም በሰንበትና በበዓላት ቀን።
የሹመቱም ዘመን ጸጥታና ሰላም ነበረ ቤተ ክርስቲያንም በሰላም ኖረች በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም ላይ ዐሥራ አንድ ዓመት ተኩል ከኖረ በኋላ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን ገዳማዊው ጻድቁ አብዱልማዎስ አረፉ። ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆኑ በበርሃ ሰው ሳያዩ ለ70 ዓመታት በቅድስና ኑረዋል:: በጊዜውም እግዚአብሔር አባ አብዱልማዎስን ወደ አባ ዕብሎይ ልኳቸው ነበር:: ሁለቱ ተገናኝተው አብረው ለ3 ቀናት ሲቆዩ ቅዱስ መልአክ እየተገለጸ አጽናንቷቸዋል:: ከሥውራን ማኅበርም ተቀላቅለው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለዋል::
አባ ዕብሎይ ሲያርፍ አንበሶች እያገዟቸው ቀብረዋቸዋል:: እርሳቸውም "እኔን የሚቀብረኝ ስጠኝ" ብለው ጸልየው ነበርና 3 ገዳማውያን መጥተውላቸዋል:: የካቲት 5 ቀን አባ ዕብሎይን ገንዘው ቀብረው በ3ኛው ቀን አርፈዋል::
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages