ስንክሳር ዘወርኀ ሚያዝያ 1 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, April 8, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሚያዝያ 1

  "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።




"የተባረከ የሚያዝያ ወር ቀኑ ዐሥራ ሦስት ሰዓት ሲሆን ከዚያም ይጨምራል" ።
ሚያዝያ ፩ (1) ቀን።
እንኳን ለካህኑ ለቅዱስ አሮን (ለሊቀ ነቢያት ለቅዱስ ሙሴ ወንድሙ) ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል፣ ለከበረ አባት የሲዖል ሥቃይ አይቶ "ወደዘላለም ጨለማ ሊወስዱኝ ዛሬ የዚህን የኃላፊውን ዓለም ብርሃን ማየት አልሻም" እያለ ፊቱን በቆብ ሽፍኖ ዕድሜው ሙሉ ሲያለቅስ ለነበረ ለአባ ስልዋኖስ ለዕረፍት በዓልና ለቅድስት መጥሮንያ ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከአበከረዙንም ጋር በሰማዕትነት ከዐረፉ ከቅዱስ ዮስጦስና ከሚስቱ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
በዚች ቀን በእስክንድርያ ከተማ በሚገኝ በግብጻውያን መጽሐፍ እንደ ተጻፈ በላዕላይ ግብጽ ያለ ግብጻዊውም እንደተጻፈ ለእንበረም ልጅ ለቅዱስ ሙሴ ወንድሙ ለሆነ የካህኑ ቅዱስ አሮን የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ ይላሉ።
በኦሪቱ መጽሐፍ የተጻፈው ግን እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በሁለተኛው ወር በሦስተኛው ቀን ዐረፈ ይላል። ይኸውም ግንቦት ስምንት ነበር የእስራኤል ወሮች በጨረቃ እየተቈጠሩ ዓመቱን ስለሚዞሩ በዚያች ዓመት ሚያዝያ አንድ ቀን ሁኖ ስለተገኘ።
በእኛ(በኢ.ኦ.ተ) ዘንድ ግን የኦሪት ዘኊልቊ መጽሐፍ በአምስተኛው ወር መባቻ ስለሚል መታሰቢያውን ነሐሴ አንድ ቀን እናደርጋለን።
ካህኑ_ቅዱስ_አሮን፦ ይህም ሰው የነቢያት አለቃ ለኦሪት ሕግ መምህር ለሆነ ለሙሴ ለነቢዪት ማርያምም ወንድም ነው እርሱም ከሌዊ ነገድ ነው።
እግዚአብሔርም በግብጽ ምድር ብዙ አስደናቂ ተአምራትን በእጆቹ አደረገ። እግዚአብሔርም እርሱንና ልጆቹን መርጦ ካህናቶቹ አድርጎ ከእስራኤል ልጆች ከገንዘባቸውና ከመሥዋዕታቸውም ዓሥራትን ሰጣቸው። የቆሬም ልጆች በጠላትነት በተነሡበት ጊዜ እግዚአብሔር ፈርዶ አጠፋቸው ምድርንም አዘዛት አፍዋንም ከፍታ ዋጠቻቸው።
በበጎ ተጋድሎውና የኦሪትንም ሕግ በመጠበቅ እግዚአብሔርን ከአገለገለ በኋላ የክብር ባለቤት ወደሆነ እግዚአብሔር ሔደ። የካህኑ የቅዱስ አሮን ጸሎቱ በረከቱ ከእኛ ጋር ለዘላለም ትኑር አሜን።
አባ_ስልዋኖስ፦ ይህም አባት በአስቄጥስ ገዳም ከከበረ አባ መቃርስ ዘንድ በታናሽነቱ መነኰሰ በጠባብ መንገድ ሁሉ ተጋደለ በብዙ ጾምና ጸሎት በመትጋት በትሕትና በፍቅር ተወስኖ ኖረ ታላቅ አባትም ሆነ።
የክብር ባለቤት ጌታችንም አምላካዊ ራእይን ይገልጽልት ነበር ድንቅ የሆኑ ነገሮችንም ይነግረዋል። ይህም እንዲህ ነው በአንዲት ዕለት ልቡ ተመስጦ በምድር ላይ በግምባሩ ተደፍቶ ብዙ ጊዜ ቆየ ከዚያም በኋላ ነቅቶ ራሱን ቀና አደረገ። ከእርሱ ዘንድ ያሉ ወንድሞች መነኰሳትም በእርሱ ላይ የደረሰበትን ይነግራቸው ዘንድ ለመኑት ዝም ብሎ መሪር ልቅሶ ያለቅሳል እንጂ ሊነግራቸው አልወደደም። ከእርሱ የሆነውን ያስረዳቸው ዘንድ ግድ ባሉት ጊዜ እንዲህ አላቸው "ተድላ ወዳለበት ገነት አውጥተውኝ በዚያ የጻድቃንን መኖሪያ አየሁ ደግሞ የሥቃይ ቦታዎችንም። ሁለተኛም ብዙዎች መነኰሳትን ወደ ገሀነም ብዙዎች ምዕመናን ወደ መንግሥተ ሰማያት ሲወስዷቸው አየሁ እንግዲህ እኔ ለነፍሴ የማላለቅስ ለምድንድነው" አላቸው። ከዚያች ቀንም ጀምሮ "በኋላ ወደዘላለም ጨለማ ሊወስዱኝ ዛሬ የዚህን የኃላፊውን ዓለም ብርሃን ማየት አልሻም" እያለ ፊቱን በቆብ ሽፍኖ የሚያለቅስ ሆነ።
ይህም አባት በመንፈሳዊ ሥራ የተጠመደ ሆነ ደቀ መዛሙርቱንም ለምግባቸው የሚሆን ሥራን ከመሥራት እንዳያቋርጡ ከዕለት ምግባቸው የሚተርፈውንም እንዲመጸውቱ ያዛቸዋል።
በአንዲት ቀንም አንድ ታካች የሆነ መነኰስ ወደርሱ መጣ ሽማግሌውን አባትና ደቀ መዛሙርቱን ሲሠሩ አይቷቸው "ለኃላፊ ምግብ ትሠራላችሁ ትደክማላችሁ የዘላለም ሕይወት ለሚሆን ምግብ ሥሩ ድከሙ እንጂ ይህ በከበረ ወንጌል የተጻፈ አይደለምን "ማርያምም የማይቀሟትን በጎ ዕድል ትምህርትን አንደመረጠች" ብሎ ጠቀሰ። ሽማግሎው አባ ስልዋኖስም እንዲህ ሲናገር በሰማው ጊዜ ደቀ መዝሙሩን እንዲህ ሲል አዘዘው "ይህን መነኰስ ከእንግዳ ማሳረፊያ ቤት አስገብተህ የሚያነበው መጽሐፍ ስጠው በሩንም በላዩ ዝጋ በእርሱ ዘንድም ለመብል የሚሆን ምንም ምን አትተው "። ረድኡም ሽማግሌው መምህሩ እንዳዘዘው አደረገ። ዘጠኝ ሰዓትም ሲሆን መነኰሳቱ ተሰበሰቡ ከሽማግሌው አባትም ጋር ጸሎት አድርገው ምግባቸውን ተመገቡ። ያን እንግዳ መነኰስ ግን አልጠሩትም እርሱም ቢጠሩኝ ብሎ ወደ ደጃፍ እየተመለከተ ይጠብቅ ነበር። በረኃብም በተቃጠለ ጊዜ ከበዓቱ ወጥቶ ወደ አባ ስልዋኖስ ሒዶ "አባቴ ሆይ መነኰሳቱ ራታቸውን በሉን" አለው ሽግሌውም "አዎን በሉ" ብሎ መለሰለት። ሁለተኛ ደግሞ "እኔ እንግዳ ስሆን ለምን አልጠራችሁኝም" አለ የከበረ አባት ስልዋኖስም "አንተማ ሥጋዊ መብል የማትሻ መንፈሳዊ ሰው ነህ በጎ ዕድልን ስለመረጥክ እኛ ግን ሥጋዊያን ሰዎች ለሥጋዊ መብል የምንሠራ የምንደክም ነን ስለዚህም ለምግባች የሚሆነውን በእጃችን እንሠራለን" ብሎ መለሰለት። ያ መነኰስም በንግግሩ እንደበደለ አወቀ። አባ ስልዋኖስንም "አባቴ ሆይ እኔ በድያለሁና ይቅር በለኝ" ብሎ ሰገደለት።
አባ ስልዋኖስም " ማርታ በመሥራት እንደ ደከመች እንድከም እንሥራ ከማርያም ይልቅ ማርታ የተዘጋጀች ሁናለችና" ብሎ መለሰለት። ያ ታካች የነበረ መነኰስም በዚህ አባት ትምህርት ተመክሮና ተገሥጾ ሁልጊዜ የሚሠራና ከእርሱ የሚተርፈውንም ለድኆች የሚመጸውት ሆነ።
ይህም አባት ስለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ጥቅም ያላቸው ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ።
ዕድሜውም በመልካም ሽምግልና በተፈጸመ ጊዜ የሚያርፍባትን ሰዓት እግዚአብሔር ነገሮት በእርሱ አቅራቢያ ያሉ መነኰሳትን ጠርቶ ከእርሳቸው በረከትን ተቀበለ። በጸሎታቸውም እንዲያስቡት ለመናቸው እርሱም በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲያስባቸው ለመኑት እርስበርሳቸውም ተሰነባበተው በፍቅር በሰላም ሚያዝያ 1 ዐረፈ። የአባ ስልዋኖስ ጸሎቱ በረከቱ ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

በዚች ቀን ደግሞ በላይኛው ግብጽ ያሉ ዐረቦች ተሰብሰበው በአስቄጥስ ያሉ አድባራትናንና ገዳማትን የአባ መቃርስንም ቤተ ክርስቲያን ከበቡ በአድባራቱና በገዳማቱ ያለውንም ዕቃ ሁሉ ማረኩ። መነኰሳትም ተሰበሰቡ በከበረ አባቶችም ስም ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ማለዱ።
የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚያን ዓረቦች አስደግጦ አሳደዳቸው ያንጊዜም ማንም የተከተላቸው ሳይኖር ድል ሁነው ሸሹ። ከክብር ባለቤት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል በቀር ማንም የተከተላቸው ሳይኖር ነው። ይቅር ብሏቸዋልና ጌታችንን አመሰገኑት ለእርሱም ክብር ምስጋና ገንዘቡ ይሁን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ 1 ስንክሳር።
ሚያዝያ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አሮን ካህን (የሊቀ ነቢያት ሙሴ ወንድም)
2.አባ ስልዋኖስ ጻድቅ
3.ቅዱሳን መነኮሳት
4.ቅድስት መጥሮንያ ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
"ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል:: እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም::"
(ዕብ. 5:3)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages