አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ይህም ከእስራኤል ልጆች ከቢንያም ነገድ ነው ወላጆቹም የኦሪትን ሕግ የሚጠብቁ ናቸው እርሱም ሥራዎቹን በአየ ጊዜ ትምህርቶቹንም በሰማ ጊዜ ጌታችንን ተከተለው።
ድንቅ የሆኑ ተአምራቶችን እየተመለከተ ጥቂት ቀን ተቀመጠ ጌታችንም በሀገረ ናይን የመበለቲቱን ልጅ በአስነሣው ጊዜ ከዚያ ነበረ። ይህን አይቶ ወዲያውኑ አመነ ሌላ ምልክት አልሻም ብልጭ ብልጭ ሲል የነበረ የአይሁድ የሕግ ፋና ትቶ ወደ ዕውነተኛ ፀሐይ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርቦ ደቀ መዝሙሩ ሆነው እንጂ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዐረገ በኋላ በጽዮን አዳራሽ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋራ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብሎ ሐዋርያትንም በመከተል በብዙ አገሮች ውስጥ አስተማረ።
ሐዋርያትም በሀገረ አቴና ኤጲስቆጶስ አድርገው ሾሙት በውስጥዋም ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን አሳመነ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው በትምህርቱና በምክሩ ዕውቀት እንዲአድርባቸው አደረጋቸው በትምህርቱም ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ፈወሳቸው።
ተጋድሎውንም በፈጸመ ጊዜ በሰላም አረፈ በድል አድራጊነትም የክብር አክሊል ተቀበለ።
መላ ዘመኑ ሰባ ዓመት ነው በአይሁድ ሕግ ሃያ ዘጠኝ ዓመት በክርስትና ሕግ አርባ አንድ ዓመት ኖረ። እነሆ የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም በመልእክቶቹ አስታውሶታል ሰላምታም አቅርቦለታል።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment