ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 26 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, April 4, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 26

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ፣ የሐዲስ ኪዳንንም የቊርባን ሥርዓት አሳያቸው፣ የከበረችና የተመሰገነች ድንግሊቱ_ኢዮጰራቅስያ አረፈች።


መጋቢት ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ እንዲህም አላቸው። እናንተም ለባልንጀሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉ።
ደግሞ የሐዲስ ኪዳንን የቊርባን ሥርዓት አሳያቸው። አሁንም በዚች ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችንን ለአይሁድ ይሁዳ አሳልፎ ሰጠው።
ነቢያት ትንቢት እንደተናገሩ የሽያጩን ዋጋ ሠላሳ ብር ተቀበለ። ይቅርታው ቸርነቱ ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋር ለዘላለሙ ይኑር አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የከበረችና የተመሰገነች ድንግሊቱ ኢዮጰራቅስያ አረፈች። ይችም የተቀደሰች ብላቴና የንጉሥ አኖሬዎስ ዘመዱ ለሆነ በሮሜ ከተማ ከቤተ መንግሥት የአንድ ታላቅ መኰንን ልጅ ናት።
የሚሞትበትም ቀን በደረሰ ጊዜ እርሷን ልጁን ለንጉሥ አኖሬዎስ ይጠብቃት ዘንድ አደራ ሰጠው። አባቷም ካረፈ በኋላ ለአንድ ታላቅ መኰንን ልጅ ንጉሥ አኖሬዎስ አጫት።
በዚያም ወራት እናቷ የመሬቷን ግብር ልትቀበል በሏ የተወላትን የአትክልት ቦታዎቿም ያፈሩትን ይችንም ቅድስት ብላቴናዋን ከእርሷ ጋር ወሰደቻት። ዕድሜዋ ዘጠኝ ዓመት ሁኖ ሳለ አስከትላት ወደ ግብጽ ሔደች።
ወደ ግብጽ አገርም በደረሱ ጊዜ ሥራቸውን እስከሚፈጽሙ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ኖሩ። በዚያ ገዳም ውስጥ የሚኖሩ ደናግል ለገድል የተጸመዱ ናቸው። የሥጋ መብልን ቅባትም ቢሆን ጣፋጭ ፍሬዎችንም ምንም ምን አይበሉም ወይንም ቢሆን ከቶ አይቀምሱም ያለ ምንጣፍም በምድር ላይ ይተኛሉ።
ኢዮጰራቅስያም በዚያ ገዳም ውስጥ መኖርን ወደደች ገዳሙን ከምታገለግል መጋቢዋ ጋር ተፋቅራለችና። መጋቢዋም አንቺ ከዚህ ገዳም ወጥተሽ ተመልሰሽ እጮኛሽን ላትፈልጊ ቃል ግቢልኝ አለቻት ኢዮጰራቅስያም በዚህ ነገር ቃል ገባችላት።
እናቷ ሥራዋን በፈጸመች ጊዜ ወደ አገርዋ ልትመለስ ወደደች ልጅዋ ግን እኔ የዚህን የኃላፊውን ዓለም ሙሽርነት ስለማልሻ ራሴን ለክብር ባለቤት ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰማያዊ ሙሽራ ሰጥቻለሁ ብላ ከእርሷ ጋር መመለስን አይሆንም አለች።
ብላቴናዋ ከእርሷ ጋር እንደማትመለስ በተረዳች ጊዜ ገንዘቧን ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች መጽውታ ከልጁዋ ጋር በዚያ ገዳም ብዙ ዘመን ኑራ ከዚያ በኋላ አረፈችና በዚያው ቀበርዋት።
ንጉሥ አኖሬዎስም የኢዮጰራቅስያ እናቷ እንደሞተች ሰምቶ ለአጫት ያጋባት ዘንድ ኢዮጰራቅስያን እንዲአመጧት መልእክተኞችን ላከ። ቅድስቲቱም ንጉሥ ሆይ እወቅ የክብር ባለቤት ለሆነ ለሰማያዊ ሙሽራ ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ራሴን ሰጥቻከሁና ቃል ኪዳኔን መተላለፍ አይቻለኝም ብላ ወደ ንጉሡ ላከች።
ንጉሥ አኖሬዎስም መልእክቷን በሰማ ጊዜ አደነቀ ስለርስዋም አለቀሰ እርስዋ በዕድሜዋ ታናሽ ብላቴና ናትና። ይህች የከበረች ኢዮጰራቅስያ ግን ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለች ለመንፈሳዊ ሥራ እጅግ የተጠመደች ሆነች በየሁለት ቀን ሁለት ሁለት ቀን እያከፈለች መጾም ከዚያም በየሦስት ቀን ሦስት ሦስት ቀን ትጾም ጀመር ከዚያም በየሰባት ቀን ሰባት ሰባት ቀን የምትጾም ሆነች።
በተለየች በከበረች አርባ ጾም ምንም ምን የምትበላ አልሆነችም። ሰይጣንም በእርሷ ላይ ቀንቶ አስጨናቂ በሆነ አመታት እግርዋን መታት ብዙ ቀኖችም በሕማም ኖረች ከዚያም እግዚአብሔር ራርቶላት ከደዌዋ አዳናት በሽተኞችንም ታድናቸው ዘንድ በሽተኞችን የምትፈውስበትን ሀብት ሰጣት።
ለእመ ምኔቷና ለእኀቶቿ ደናግል በመታዘዝ ታገለግላቸው ነበር በእኀቶች ደናግል ሁሉ ዘንድ የተወደደች ናት። በአንዲት ዕለትም እመ ምኔቷ አክሊላትንና አዳራሾችን እንደ አዘጋጁ ራእይን አየች እርሷም እያደነቀች ከልጆቼ ለማን ይሆን ይህ የሚገባት ስትል እሊህ አክሊላትና አዳራሾች የተዘጋጁላት ለልጅሽ ለኢዮጰራቅስያ ነው እርሷም ወዲህ ትመጣለች አሏት።
ይህንንም ራእይ ለደናግሎች ነገረቻቸው እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም መከራ ሊያሳርፋት እስከ ወደደበት ቀን ለኢዮጰራቅስያ እንዳይነግሩዋት አዘዘቻቸው።
ከዚህ በኋላ በሆድ ዝማ ሕማም ጥቂት ታመመች ሁሉም ደናግል ከእመ ምኔቷ ጋር ወደ እርሷ ተሰበሰቡ ያቺ ቃል ኪዳን ያስገባቻት የምትወዳት መጋቢዋም መጣች በእግዚአብሔርም ዘንድ እንድታስባቸው ለመንዋት እርሷም በጸሎታቸው እንዲአስቧት ለመነቻቸው ከዚያም አረፈች ።
የተቀደሰችና የተከበረች እርሷን እኅታቸውን አጥተዋታልና ደናግሉ እጅግ አዝነው አለቀሱ። ከዚህም በኋላ የምትወዳት የገዳሙ መጋቢ የነበረች አረፈች ከእርስዋም በኋላ እመ ምኔቷ ጥቂት ቀን ታመመች ደናግሎችንም ሰብስባ በላያችሁ የምትሾሙትን እመ መኔት ምረጡ ስለ እኔ ኢዮጰራቅስያ ለምናለችና እኔ ወደ ጌታዬ ኢየሱስ እሔዳለሁ አሁን ግን ደጁን በላዬ ዘግታችሁ ሔዱ አለቻቸው እነርሱም እነዳዘዘቻቸው አደረጉ። በማግሥቱም ማለድ ብለው ሲደርሱ አርፋ አገኟት፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages