ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 27 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, April 4, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 27

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት 27 በዚች ቀን ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስለ ዓለም ድኅነት በሥጋ ተሰቀለ፣ የመነኰሳት ሁሉ አባት የሆነ የከበረ አባት ታላቁ_አባ_መቃርስ አረፈ፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ ሰማዕት_ገላውዲዎስ አንገቱን የተቆረጠበት ቀን ነው።
መጋቢት ሃያ ሰባት በዚችም ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ድኅነት በሥጋ ተሰቀለ። ፈጣሪዋ በዕንጨት መስቀል ላይ ተዘርግቶ ተሰቅሎ በአየችው ጊዜ ፀሐይ ጨለመች እርሱም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣትን ለባዊት ነባቢት የሆነች ነፍሱን ከሥጋው ለያት ሐዋርያ ጴጥሮስ በሥጋ ምውት ሲሆን በመለኮት ሕያው ነው እንዳለ ነፍሱ ከመለኮት ሳትለይ ከሥጋ ተለየች በዚያ ጊዜ ሥጋ ከመለኮት ሳትለይ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ነበር። እንዲሁም ነፍስ ከመለኮት ጋራ አንድ ሁና እሥረኞች ነፍሳትን ትፈታቸው ዘንድ ወደሲኦል ወረደች።
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ስለ ዓለም ሁሉ ድኅነት በሥጋ ተሰቅሏልና ሞቱን በአንክሮ እናዘክር ዘንድ የልቡናችን ዐይን ወደ ቀራንዮ እናንሳ! እነሆ ክፉዎች አይሁድ ሰይጣን ልባቸውን አስቶታልና እንደ ወረንጦና እንደ ወስፌ እንደመርፌም ያለ 300 እሾህ ያለው ስረወጽ አድርገው አክሊል ሠርተው ከፍላት አግብተው በጉጠት አንስተው ‹ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሥ ነህ ዘውድ ይገባሃል› ብለው በራሱ ላይ ደፉበት፡፡ ለአክሊለ ሦኩም 73 ስቁረት ነበረው፡፡ እራሳቸው እንደ መሮ፣ ወርዳቸው እንደ ሞረድ 4 ማዕዘን አሠርተው ቁመታቸውን ክንድ ከስንዝር፣ ስለታቸውን እንደ ወስፌ አድርገው 73 ችንካር ሠርተው በ73ቱ ስቁረት አግብተው በጌታችን በራሱ ላይ ቢመቱበት ሥጋ ለሥጋ ገብቶ መሐል ልቡን ወጋው፡፡ አክሊለ ሦኩን በራሱ ላይ አድርገው ሲያበቁ ከቤት ወደ አደባባይ እያመላለሱ ‹‹ንጉሥ ሆይ!...›› እያሉ ምራቃቸውን እየተፉበት ተዘባበቱበት፡፡ መስቀል አሸክመው ከሊቶስጥራ እስከ ቀራኒዮ ድረስ እያዳፉ ሲወስዱት 136 ጊዜ በምድር ላይ ጣሉት፡፡ ከኋላ ያሉት ‹‹ፍጠን›› እያሉ ገፍትረው ይጥሉታል፣ ከፊት ያሉት ደግሞ ‹‹ምን ያስቸኩልሃል?›› እያሉ መልሰው ገፍትረው ይጥሉታል፡፡ ከዚህ በኋላ ክፉዎች አይሁድ ቁመታቸውን ክንድ ከስንዝር ስለታቸው ደግሞ እንደ ወስፌ የሆኑ 5 ችንካሮችን ሠርተው ሳዶር በሚባለው ችንካር ቀኝ እጁን፣ በአላዶር ግራ እጁን፣ በዳናት ሁለት እግሮቹን፣ በአዴራ መሐል ልቡንና በሮዳስ ደረቱን ቸንክረው የአዳም ራስ ቅል ባለበት ቀራኒዮ አደባባይ ላይ ሰቅለውታል፡፡
ክፉዎች አይሁድ መድኃኔዓለም ክርስቶስን እንደያዙት የኋሊት አስረው አፍንጫውን 25 ጊዜ ቢመቱት ደሙ በመሬት ላይ እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ከጌቴሴማኒ እስከ ሐና ቤት ድረስ አስረው የፊተኞቹ ሲጎትቱት የኋለኞቹ እየለቀቁት የኋለኞቹም በተራቸው ሲጎትቱት የፊተኞቹ ይለቁታል፡፤ እንዲህ እያደረጉ 65 ጊዜ ከመሬት ጋር አጋጭተውታል፡፡ ሳውል በእግሩ ሲረግጠው ጌታችን ‹‹መመለስህ ላይቀር ለምን ትረግጠኛለህ?›› ቢለው ስለዚህ ንግግርህ ብሎ ሳውል 440 ጊዜ አስገረፈው፡፡
ክፉዎች አይሁድ መድኃኒታችንን በሁለት ግንዶች መካከል አድርገው 65 ጊዜ ከግንዱ ጋር አጋጩት፡፡ ቀያፋ በሚመረምረው ጊዜ ጌታችን ‹‹አምላነቴን አንተው ራስህ ተናገርኽ›› ቢለው አይሁድ በእጃቸው ሲመቱት እጃቸውን ቢያማቸው ድንጋይ ጨብጠው 120 ጊዜ ፊቱን ጸፉት፡፡ አይሁድ ወደ ጲላጦስ ዘንድ ሲወስዱት ‹‹ምናልባት ጲላጦስ ባይፈርድበት እንኳ እንዳይቆጨን›› ብለው 305 ጊዜ በሽመል ደብድበውታል፡፡ በአምላክነቱ ቻለው እንጂ የአንዱ ምት ብቻ በገደለው ነበር፡፡ በርባን የይሁዳ የሚስቱ ወንድም (አማቹ) ስለነበር እርሱ እንደፊታለትም ከዋጋው ከ30ው ብር ጋር አብሮ ተደራድሮበት ነበር፡፡
ሰይጣን ልባቸውን ለክፋት ያስጨከናቸው ክፉዎች አይሁድ በጲላጦስ አደባባይ የጌታችንን ፂሙን 80 ጊዜ ነጭተውታል፡፡ ጲላጦስ እንደ ሕጋቸው 41 ብቻ ገርፈው እንዲለቁት ቢያዝም ክፉዎች አይሁድ ግን ጌታችንን ሲገርፉት ‹‹አሠቃቂ ግርፋቱን አይተን ልባችን እንዳይራራ›› ብለው ሰንጠረዥ ገበጣ ሰርተው ሲጫወቱ አንዱ ተነስቶ እስከ 60 እና 70 ድረስ ይገርፍና ሲደክመው ‹‹ቆጠራችሁን?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ‹‹አልቆጠርንም›› ሲሉት ከድካሙ የተነሣ ‹‹እኔው ልግረፍ እንደገና እኔው ልቁጠር›› ብሎ ትቶት ሲቀመጥ ሌላኛው ይነሣና እንደዛኛው ሁሉ በተራው 60 እና 70 ይገርፈዋል፡፡ ሁሉም እንዲህ እያሳሳቱ የራሳቸውን ሕግ እየተላለፉ አይሁድ ጌታችንን ሥጋው አልቆ አጥንቱ እንደበረዶ ነጭ ሆኖ እስኪታይ ድረስ 6666 ጊዜ ጽኑ ግርፋትን ገረፉት፡፡ በእነዚህ ሁሉ ግርፋቱ ወቅት 366 ጊዜ ሥጋው ተቆርሶ መሬት ላይ ወድቋል፡፡
የመድኃኔዓለም ወገኖች ሆይ! የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ መሆኑንና የትዕግሥቱን ብዛት አይተን እናደንቅ ዘንድ ከመጻሕፍት ጠቅሰን እንነግራችኋለን፡፡ አይሁድ ጌታችን አብርሃም ሳይወለድ በፊት እርሱ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገን አምላክ መሆኑን ቢነግራቸው ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፡፡ እሱ ግን ጊዜው ገና ነበርና ተሰውሮአቸው በመካከላቸው አልፎ ሲሄድ በፍጹም አላዩትም ነበር፡፡ በቅዱስ ወንጌል ላይ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- ‹‹አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው። አይሁድም:- ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት። ኢየሱስም:- እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው። ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ፡፡›› ዮሐ 8፡56-59፡፡
ዳግመኛም በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጻፈው አይሁድ መድኃኔዓለምን ሊይዙት የጦር መሣሪያቸውን ሰብስበው ወደ ጌቴሴማኒ በመጡ ጊዜ ‹‹ማንን ትፈለጋላችሁ?›› ቢላቸው ‹‹የናዝሬቱን ኢየሱስን እንፈልጋለን›› ሲሉት ‹‹እኔ ነኝ›› ቢላቸው ከአንደበቱ የወጣውን መለኮታዊ ቃል ብቻ መቋቋም አቅቷቸው መሬት ላይ ወድቀው ተዘርረዋል፡፡ ይህም ክስተት በተደጋጋሚ ተከስቷል፡፡ (ዮሐንስ ወንጌል ላይ ምዕራፍ 18 ከቁጥር አንድ ጀምሮ ይመለከቷል፡፡) እናም የጌታችን ሞቱ በፍጹም ፈቃዱ ባይሆን ኖሮ በጌቴሴማኒ ሊይዙት የመጡት ክፉዎች አይሁድን እንደመጀመሪያው ሁሉ በተሠወራቸው ነበር አሊያም ከአንደበቱ በሚወጣው አምላካዊ ቃሉ ብቻ ባጠፋቸው ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ጌታችን ወደዚህች ምድር የመጣበትን ዓላማ ይፈጽም ዘንድ እንዲገድሉት በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ ቢሰጣቸው ያን ሁሉ እጅግ አሠቃቂ መከራ አደረሱበትና ለመስቀል ሞት አበቁት፡፡
ወዮ ለዚህ ለመድኃኒዓለም ፍጹም ትዕግስት አንክሮ ይገባል! ዓለምን በመዳፉ የያዘ አምላክ በአይሁድ እጅ እንደሌባ ተያዘ፡፡ ሠራዊተ መላእክት ለምሥጋና በፊቱ የሚቆሙለት መድኃኔዓለም እርሱ ሊፈረድበት በፍርድ አደባባይ ቆመ፡፡ በእስራት ያሉትን የሚፈታ እርሱ በብረት ችንካር ተቸነከረ፡፡ ሰማይን በከዋክብት ምድርም በአበባ ያስጌጠ እርሱ ግን የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፋ፡፡ ዓለሙን ሁሉ በቸርነቱ የሚመግብ እርሱ ተጠማሁ አለ፡፡ ወዮ የመድኃኔዓለም የማዳኑ ምሥጢር ምንኛ ድንቅ ነው!!! ለዚህ ባሕርይው አንክሮ ይገባል፡፡
በመድኃኔዓለም ክርስቶስ ሞት በአንድነት እናለቅስ ዘንድ ቅዱሳን ሁላችሁ ኑ! መድኃኒታችን ሙቷልና ፍጥረታት ሁሉ ያለቅሳሉ፤ መያዝንና መታሠርን የተቀበለ መድኃኒታችን ሙቷልና፡፡ ጥፊንና ግርፋትን የተቀበለ መድኃኒታችን ሞተ፡፡ መደብደብንና መመታትን የታገሰ መድኃኒታችን ሞተ፡፡ ሄኖክ እግዚአብሔር ‹‹በሴም ቤት ይደር›› ብሎ አብ ስለራሱ የተናገረለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ አብርሃም ቃልኪዳን የገባልህን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ይስሐቅ ከሰይፍ ቤዛ የሆነህን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ያዕቆብ በበረሃ የታገለህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኢዮብ በደመና የታየህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ሙሴ ስለ እርሱ ‹እንደእኔ ያለ ነቢይ ይነሣል› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዳዊት ‹‹እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፣ በበረሃ ዛፍም አገኘነው›› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኤርሚያስ ‹‹የክቡሩን ዋጋ ሠላሳ ብር ተቀበሉ›› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡
ኢሳይያስ ‹‹ወልድ ሰው ለመሆን ተገለጠልን፣ ሕፃን ተወለደልን፣ ድንቅ መካር ኃያል አምላክ›› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ሕዝቅኤል ‹‹አምላክ ወደ ተዘጋች ደጃፍ ገባ፣ ከተዘጋች በርም ወጣ›› ብለህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዳንኤል ነጭ ሐር ለብሶ ያየኸውን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኤልያስ ከሞት በፊት የሰወረህ በእሳት ፈረሶች ያሳረገህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ሕዝቅያስ የፀሐይ መግባቱን ያሳየህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ምናሴ ችንካሮችህን ከእግር ብረት የፈታ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኢዮስያስ ፋሲካውን ያደረግህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል ከእሳት ምድጃ ያዳናች የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ኑ፡፡ አብያና ሲላ ፌንቶስ ከመወለዱ አስቀድሞ ያመናችሁበት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ኑ፡፡ የቀድሞ አባቶች ነቢያት ሁላችሁ ከፋራን ተራራና ከቴማን ይመጣል ያላችሁት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ኑ፡፡ አሞፅ በአድማስ ቅጥር ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዘካርያስ በተራራዎች መካከል ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዕዝራ በአርፋድ በረሃ ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡
ስምዖን በክንድህ የታቀፍከውን ሕፃን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዮሴፍ እንደ አንተ የተሸጠ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ጠራቢ ዮሴፍ በትከሻህ ያዘልከው በክንድህ የተሸከምከው ሕፃን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ከሕፃንነትህ ጀምሮ በበረሃ ያለ እናት ያለ አባት ያሳደገህ መንገዱንም እንድትጠርግለት ያዘጋጀህና መለኮትን እንድታጠምቅ የመረጠህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡
ኢያቄምና ሐና ሆይ የልጃችሁን ልቅሶዋን የልቧንም መዘንጋት ታዩ ዘንድ ኑ፡፡ ከሔዋን እስከ ፋኑኤል ልጅ እስከ ሐና ያላችሁ ሁላችሁ ቅዱሳት ሴቶች የድንግልን ልቅሶዋን ታዩ ዘንድ ኑ፣ አንድ ልጇ ሙቷልና፡፡ የለመለመ የሥጋ ሞት ሕንፃ የተጀመረበት የአቤል ተከታዩ፣ ከጎኑ የፈሰሰው ደም ሔዋንን ከጥፋት ያዳናት የተገደለ መድኃኒታችን ነው፡፡ የናቡቴ ጓደኛው የተገፋው መድኃኒታችን ነው፡፡ አቤል ስለሚስቱ ሞተ፡፡ ናቡቴም ስለ ወይኑ ቦታ ሞተ፡፡ መድኃኒታችን ግን በቀኙ ያነጻት ዘንድ ስለቤተክርስቲያን ሞተ፡፡ ነፍሳችሁን ይወስዷታልና መውረዱንም አላወቁምና ስለ ወገኖቹ ኃጢአት እስከ ሞት ደረሰ ብሎ ስለ እርሱ የተናገረ አባቱን እንስማው፡፡ ሙሴም እርሱን ያውቁት ዘንድ አላሰቡትም፣ በሚመጣበት ቀንም አላወቁትም አለ፡፡ ዕዝራ በባሕር ጥልቅ ያለውን ማወቅ እንዳይችሉ ወልድንም ማወቅ እንዲሁ ሆነባቸው አለ፡፡ ጳውሎስም ብታውቁትስ ኖሮ የክብርን ጌታ እግዚአብሔርን ባልሰቀላችሁት ነበር አለ፡፡
በመሰደድ፣ ያለምንም በደልም በፍርድ አደባባይ በመቆም መከራ መስቀልን በመሸከም አብነት የሆናችሁ ሰማዕታት ሁላችሁ ኑ የመድኃኔዓለምን የሞቱን ዕለት አስባችሁ በጋራ አልቅሱለት፡፡ ሁሉ የእርሱ ከእርሱ ለእርሱ ተፈጥሮ ሳለ በምድር ላይ ምንም ሳይኖረው ራሱን እንኳን የሚያስጠጋበት ቤት ሳይኖረው አብነት የሆናችሁ ባሕታውያንና መነኮሳት ሁላችሁ ኑ በዛሬዋ ዕለት ስለሞተው አምላካችሁ መሪር ዕንባን አልቅሱለት፡፡ ሕግ ጠብቆ፣ ሥርዓት አክብሮ፣ ነዳያንን በመመገብና ያዘኑትን በማጽናናት 33 ዓመት በምድር ላይ ኖሮ አብነት የሆናችሁ እናንት በዓለም ሆናችሁ ሕግ ጠብቃችሁ፣ አሥራት በኩራቱን አውጥታችሁ፣ ድሆችን በመርዳት የምትኖሩ ክርስቲያኖች ሁላችሁ የመድኃኔዓለምን የሞቱን ዕለት ታስቡ ኑ፡፡
‹‹የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና›› ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደጻፈልን (1ኛ ጴጥ 2፡21) እርሱ ንጹሕ ባሕርይ ሲሆን ወደ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ወደ ዮርዳኖስ በመሄድ ለተጠመቅን ለእኛ ለተነሣሕያን ለሁላችን አብነት የሆነን መድኃኒታችን ስለእኛ ሞቷልና ሞቱን እናስብ ዘንድ ኑ በቤቱ ተሰብስበን እናልቅስለት፡፡ መታሰያውንም እናድርግለት፡፡ ጌታችን ሞቶ ተቀብሮ ካረገ በኋላ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለቅዱሳን አባቶቻችን ለእነ አቡነ መባዓ ጽዮን፣ ለእነ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እንደነገራቸው የሞቱን መታሰቢያ የሚያደርግ ኃጠአተኛ እንኳ ቢሆን ሲኦልን አያያትም፡፡ የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ የሚያድርግ ቢኖር ሲኦል ራሷ አፍ አውጥታ ‹‹ይህችን ነፍስ ወደኔ አታምጡብኝ›› ብላ ትጮሃለች እንጂ ችላ አትቀበለውም፡፡
የጌታችን ወዳጆቹ ዮሴፍ ኒቆዲሞስ በድርብ በፍታና በመቶ ወቄት ሽቱ ገንዘው በሐዲስ መቃብር ሊቀብሩት ቢሉ ጌታችን ያን ጊዜ ዐይኑን ክፍቶ ‹‹በሰውነቴ መዋቲ ብሆን በመለኮቴ ሕያው ነኝ እንጂ ምነው እንደ እሩቅ ብእሲ ዝም ብላችሁ ትገንዙኛላችሁን?›› አላቸው፡፡ ይህን ጊዜም ዮሴፍ ኒቆዲሞስ በታላቅ ድንዳጤ ሆነው ‹‹አቤቱ ጌታችን ሆይ! እንግዲያስ ምን እያልን እንገንዝህ?›› አሉት፡፡ መድኃኒታችንም እንዲህ እያላችሁ ገንዙኝ አላቸው፡- ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽእ በስብሐት ይኰንን ሕያዋነ ወሙታነ ተሣሃለነ እግዚኦ› እያላችሁ ገንዛችሁ ቅበሩኝ አላቸው፡፡›› ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን ለወዳጆቹ ለ12ቱ ሐዋርያት፣ ለ72ቱ አርድእት፣ ለ36ቱ ቅዱሳት አንስት ‹‹እስከ ሦስት ቀን እነሣላችኋለሁ እዘኑ አልቅሱ፣ እህል ውኃ አትቅመሱ በሏቸው›› ብሎ ለዮሴፍና ለኒቆዲሞስ አክፍሎት አስተማራቸው፡፡
ዳግመኛም መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከዕርገቱ በኋላ ለቅዱሳን ሐዋርያት የሞቱን መታሰቢያ እንዲያደርጉ ነግሯቸዋልና፡፡ ሕማሙንና ሞቱንም እንዲዘክሩ አዟቸዋልና አሁንም ያንን ሁሉ የመድኃኔዓለምን ሞቱን ያላሰበና የሞቱን መታሰቢያ በዓል ያላከበረና እርሱንም የማይወደው ቢኖር ዕድል ፈንታው ጽዋ ተርታው ከአይሁድ ጋር ነው፡፡
የአምላካችንን የመድኃኔዓለምን ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ተባብረን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ከእርሱ ለመተባበር ያብቃን!
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን በገዳም ለሚፈጸም ተጋድሎ ፋና የሆነ በአስቄጥስ ገዳም ለሚኖሩ መነኰሳት ሁሉ አባት የሆነ የከበረ አባት ታላቁ አባ መቃርስ አረፈ። ይህም የከበረ አባት በግብጽ ደቡብ መኑፍ ከሚባል አውራጃ ሳሱይር ከሚባል አውራጃ መንደር ከሚኖሩ ሰዎች ወገን ነው ።
ወላጆቹም ደጎች ዕውነተኞች ነበሩ። አባቱ አብርሃም እናቱም ሣራ ይባላሉ። እናቱም እንደ ኤልሳቤጥና እንደ ሣራ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ጸንታ የምትኖር ናት አባቱም በፈሪሃ እግዚአብሔር ሁኖ ንጽሕናውንና ቅድስናውን ጠብቆ ሁልጊዜ ቤተ ክርስቲያን በማገልገል ጸንቶ ይኖራል እግዚአብሔርም በላያቸው በረከቱን አሳድሮ በሥራቸው ሁሉ ከፍ ከፍ አደረጋቸው።
ለድኆችም የሚመጸውቱ ለሰው ሁሉ የሚራሩ ናቸው። በጾም በጸሎትም ተወስነው እንዲህ ባለገድል ሲኖሩ ግን ልጅ አልነበራቸውም። ለአብርሃምም በሌሊት ራእይ ከእግዚአብሔር ዘንድ በልጅ አምሳል ተገለጠለት በዓለሙ ሁሉ የሚታወቅ ብዙ መንፈሳውያን ልጆችን የሚወልድ ልጅን ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔር አለው ብሎ አስረዳው።
ከዚህም በኋላ ይህን የከበረ ልጅ መቃርዮስን እግዚአብሔር ሰጠው። ትርጓሜውም ብፁዕ ማለት ነው በላዩም የእግዚአብሔር ጸጋ አደረበት ለወላጆቹም ይታዘዝና ያገለግል ነበር ሊያጋቡትም አሰቡ እርሱ ግን አይሻም ነበር ፈቃዳቸውን ይፈጽም ዘንድ ግድ ብለው አጋቡት ወደ ሙሽራዪቱም በገባ ጊዜ ራሱን እንደታመመ ሰው አደረገ እንዲህም ሁኖ ብዙ ቀን ኖረ።
ከዚያም በኋላ አባቱን ተወኝ ወደ ገዳም ልሒድ ከበሽታዬ ጥቂት ጤና ባገኝ አለው እግዚአብሔር ወደሚወደው ሥራ ይመራው ዘንድ ሁልጊዜ በጾምና በጸሎት ሁኖ ይለምነው ነበር። ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ በረሀ ሔደ ከበረሀውም በገባ ጊዜ ራእይን አየ ስድስት ክንፍ ያለው ኪሩብ እጅና እግሩን ይዞ ወደ ተራራ ላይ እንደሚያወጣውና የአስቄጥስን በረሀ ምሥራቋን ምዕራቧን የዚያችን በረሀ አራት ማእዘንዋን አሳይቶ እነሆ ይቺን በረሀ መላዋን ላንተና ለልጆችህ ርስት አድርጎ እግዚአብሔር ሰጥቶሃል አለው።
ከበረሀውም በተመለሰ ጊዜ ያቺ ብላቴና ታማ አገኛት ጥቂት ቆይታ ወዲያው በድንግልናዋ እንዳለች አረፈች። የክብር ባለቤት እግዚአብሔርንም አመሰገነው። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ እናት አባቱ አረፉ የተዉለትንም ገንዘብ በሙሉ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጠ።
የሳሱይር ሰዎች ግን ዕውነተኛነቱንና ቅድስናውን አይተው ቅስና አሾሙት። ከከተማውም ውጭ ቤት ሠሩለት ሥጋውንና ደሙን ይቀበሉ ዘንድ ወደርሱ ይሔዱ ነበር።
በዚያች አገርም አንዲት ድንግል ብላቴና ነበረች ከአንድ ጐልማሳ ጋርም አመንዝራ ፀነሰች ጉልማሳውም አባትሽ ድንግልናሽን ማን አጠፋው ብሎ ሲጠይቅሽ መቃርስ የሚባለው ባሕታዊ ቄስ እርሱ ስለ ደፈረኝ ነው በዪው ብሎ መከራት።
ፅንሷም በታወቀ ጊዜ አባቷ ይህን አሳፋሪ ሥራ በአንቺ ላት የሠራብሽ ማነው ብሎ ጠየቃት። እርሷም በአንዲት ቀን መቃርስ ወደሚባለው ቄስ ሒጄ ሳለሁ በኃይል ይዞኝ ከእኔ ጋራ ተኛ ስለዚህ ከእርሱ ፀነስኩ ብላ መለሰችለት።
ወላጆቿና ቤተሰቦቿም በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቆጡ ከብዙ ሰዎችም ጋራ ወደ ቅዱስ መቃርስ ሒደው ይዘው ከበዓቱ አወጡት እርሱ ግን ምን እንደሆነ አላወቀም። ለመሞት እስቲቃረብም አጽንተው ደበደቡት እርሱም ኃጢአቴ ምንድናት እናንተ ያለ ርኅራኄ ትደበድቡኛላችሁና እያለ ይጠይቃቸው ነበር።
ከዚህ በኋላ በፍሕም የጠቆሩ ገሎችን በአንገቱ ላይ በገመድ አንጠልጥለው ወዲያና ወዲህ እየጐተቱ የልጃችንን ድንግልና ያጠፋ ይህ ነው እያሉ እንደ እብድ በላዩ ይጮኹ ጀመር።
በዚያን ጊዜ መላእክት እንደሰው ተገልጠው የሚያሠቃዩትን ሰዎች ይህ ተጋዳይ ምን አደረገ አሏቸው። እነርሱም በልጃቸው ላይ የኀፍረትን ሥራ እንደሠራ አድርገው መልሰው ነገሩአቸው። እነዚያ መላእክትም ይህ ነገር ሐሰት ነው እኛ ይህን ሰው ከታናሽነቱ ጀምሮ እስከዚች ቀን እናውቀዋለን እርሱ የተመረጠ ጻድቅ ሰው ነውና አሏቸው የታሠረበትንም ፈትተው ከላዩ ገሎችን ጣሉ እነዚያ ክፉዎች ግን ዋስ እስከሚሰጠን ድረስ አንለቀውም አሉ። እጀ ሥራውን የሚሸጥለት አንድ ሰው መጣ ለልጅቷም በየጊዜው ምግቧን ሊሰጣት ዋስ ሆነው ከዚያ በኋላ አሰናብተው ወደ በዓቱ ተመልሶ ገባ።
ከዚያቺም ቀን ጀምሮ ራሱን በራሱ መቃርስ ሆይ እንግዲህ ባለሚስትና ባለልጅ ሁነኻል ሌሊትና ቀን መሥራት ይገባሃል እያለ ያቺ ሐሰተኛ ልጅ የምትወልድበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ እንቅቦችን ቅርጫቶችን እየሠራ ለዚያ ወዳጅ ለሆነውና ለሚያገለግለው ወንድም ይሰጠውና ያም ሰው እየሸጠ ለዚያች ሐሰተኛ ልጅ እየሰጠ ኖረ።
የምትወልድበትም ቀን ሲደርስ እጅግ አስጨነቃት በታላቅ ሥቃይም ውስጥ አራት ቀኖች ያህል ኖረች። ለሞትም ተቃረበች እናቷም ከአንቺ የሆነው ምንድነው የተሠራ ሥራ አለና ንገሪኝ አለቻት። እርሷም በእግዚአብሔር አገልጋይ ላይ ዋሽቻለሁና ያመነዘርኩት ከዕገሌ ገ ልማሳ ጋር ሲሆን በዕውነት ሞት ይገባኛል አለቻት።
አባትና እናቷም በሰሙ ጊዜ ደንግጠው እጅግ አዘኑ የአገር ሰዎችም ሁሉም ተሰበሰቡ በእርሱ ላይ የሰሩትን በደል ይቅር ይላቸው ዘንድ ወደ ቅዱስ መቃርስ ሒደው ለመኑት። ያን ጊዜ በበረሀ ያየውን ያንን ራእይ አስታውሶ ይቅር አላቸው ቀድሶም ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው።
ክንፉ ስድስት የሆነ ኪሩብ ደግሞ ተገለጠለት ትርጓሜው የልብ ሚዛን ወደተባለ ወደ አስቄጥስ ገዳም እጁን ይዞ መርቶ አደረሰው። ቅዱስ መቃርስም ያንን ኪሩብ ጌታዬ ሆይ በውስጡ የምኖርበትን ቦታ ወስንልኝ አለው። ያ ኪሩብም አልወስንልህም የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ አትተላለፍ እነሆ ይህ ገዳም ሁለመናው ላንተ ተሰጥቷልና ወደፈለግህበት ሒደህ ተቀመጥ ብሎ መለሰለት።
ቅዱስ መቃርስም የቅዱሳን ሮማውያን የመኪሲሞስና የደማቴዎስ ቦታ ወደ ሆነው ከውስጥኛው በረሀ ገብቶ ኖረ። እነርሱ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ከእርሱ አቅራቢያ ኑረዋልና ከዕረፍታቸው በኋላ ግን ሒዶ በዚያ ቦታ እንዲኖር የእግዚአብሔር መልአክ አዘዘው። ይኸውም ዛሬ የእርሱ ገዳም የሆነው መልአኩ ይህ ገዳም በልጆችህ በመክሲሞስና በደማቴዎስ በስማቸው ይጠራል ስለ አለው እስከዚች ቀን ደብረ ብርስም ተብሎ ይጠራል ትርጓሜውም የሮም ገዳም ማለት ነው።
የከበረ አባ መቃርስም ታናሽ በዓት ሠራ። በውስጥዋም ሆኖ ያለ ማቋረጥ በጾም በጸሎት በስግደትም በመትጋት ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ።
ሰይጣናትም ተገልጠው የሚመጡበትና በቀንም በሌሊትም በግልጥ የሚዋጉት ሆኑ።
በጸምና በጸሎት ሲጋደል ሰይጣናት እየተዋጉት ዕረፍትን ስለ አላገኘ በልቡ አሰበ በዓለም ውስጥ ሳለሁ የቅዱስ አባ እንጦንዮስን ዜና ሰምቻለሁ የምንኵስናን ሥርዓት ያስተማረኝና ይመራኝ ዘንድ ተነሥቼ ወደርሱ ልሒድ የረከሱ ሰይጣናት የመከሩትን ምክራቸውን እገለብጥ ዘንድ እርሱ ዕውቀትንና ማስተዋልን ይሰጠኛልና አለ።
ያን ጊዜም ተነሥቶ ጸሎት አድርጎ ወደ አረጋዊ አባ እንጦንዮስ ዘንድ እስከሚደርስ ወደምሥራቅ አቅጣጫ ተጓዘ። አባ እንጦንዮስም ከሩቅ በአየው ጊዜ እነሆ ተንኰል ሽንገላ የሌለበት እስራኤላዊ አለው በታላቅ ደስታ ተቀብሎ ሳመው።
አባት ለልጁ እንደሚገልጥ ኀሳቡን ሁሉ ገለጠለት ይህ አረጋዊ አባ እንጦንዮስም የመቃርስን ራሱን ስሞ ልጄ ሆይ በዮናኒ ቋንቋ እንደ ስምህ ትርጓሜ አንተ ብፁዕ ትባላለህ። ሥራህንና ወደ እኔ መምጣትህን ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ገልጦልኛልና ስለዚህም መምጣትህን የምጠባበቅ ሆንኩ አለው።
ከዚህ በኋላ ለአባ መቃርስ የከበረች የምንኵስናን ሥርዓት ሁሉ አስተማረው መሠራቱ በሚገባ በብዙ ነገርም አጸናው። ሰይጣናት የሚዋጉት መሆናቸውን እነርሱ በሥውር በፈቲው ጦር እንዲሁም ጥፋት በሆኑ ሥራዎች ሁሉ ይዋጉህ ዘንድ አላቸው። አንተ ፍጹም ልትሆን አንተም እስከ ሞት ደርሰህ ታገሥ አሁንም እግዚአብሔር ወደ ወሰነልህ ቦታ ሒደህ ሥራህን እየሠራህ በውስጡ ታገሥ ብሎ ገለጠለት።
ከአባ እንጦንዮስ ዘንድ የምንኵስናን ሥርዓት እየተማረ ጥቂት ቀኖች ከኖረ በኋላ ከተባረከ ኤጲስቆጶስ ከአባ ሰራብዮን ጋራ በተማራቸው ሕያዋን በሚያደርጉ ትምህርቶችና ሥርዓቶች ፈጽሞ ደስ እያለው ወደ ቦታው ተመለሰ። አባ መቃርስም በአባቴ በአባ እንጦንዮስ ዘንድ በነበርኩባቸው ቀኖች ሲተኛ ከቶ አላየሁትም አለ።
አባ መቃርስም በምንኵስና ሥርዓት ተጠምዶ እየተጋደለ ብዙ ቀን ኖረ ያ ኪሩብም በግልጽ ይጐበኘው ነበር። በአንዲት ቀንም እንዲህ የሚለውን ቃል ከሰማይ ሰማ ቃሌንና ትእዛዜን ሰምተህ ወደዚህ መጥተህ በዚህ ቦታ ውስጥ ስለኖርክ እነሆ ቊጥር የሌላቸውን የብዙ ብዙ ወገኖችን ከነገዶች ከሀገሮች በቋንቋ ከተለያዩ ሕዝቦች እሰበስባለሁ ። እንርሱም በዚህ ቦታ ያገለግሉኛል የከበረ ስሜንም ያመሰግናሉ በበጎ ሥራቸውና ትሩፋታቸው ደስ ያሰኙኛል አንተም ተቀበላቸው ዕውነተኛ የድኅነት መንገድን ምራቸው። ይህንንም ቃል በሰማ ጊዜ ተበረታታ ልቡም ጸና።
በሌሊትም በጸሎት ጊዜ ቁሞ ሳለ የክብር ባለቤት ጌታችን ጆሮውን ከፍቶለት ሰይጣናትን ሲሞክሩ ሰማቸው እንዲህም አሉ ይህን ሰው በዚህ በረሀ እንዶኖር ብንተወው የብዙ ብዙ ወገኖችን ይመራቸዋል እነርሱም በዚህ በረሀ ውስጥ ነዋሪዎች ሁነው የሰማያውያን ሀገር ያደርጉታል። እነርሱ ለዘላለም ጸንቶ በሚኖር ሕይወት ይተማመናሉና። እኛንም በሚቀጣ ጸሎታቸው ቀጥተው አሠቃይተው ያሳድዱናልና ከዚህ ቦታ ልናሳድደው እስኪ እንችል እንደሆነ ኑ ዛሬ በእርሱ ላይ እንሰብስብ ሲሉ ሰማቸው። አባ መቃርስም ይህን በሰማ ጊዜ ልቡ ጸና በሰይጣናት ላይም ተበረታታ የሰይጣናት ምክራቸውን እስከሚሰማ ጀሮውን የከፈተለት እግዚአብሔርን አመሰገነ ድካማቸውንም አወቀ።
ከዚህ በኋላ ይዋጉት ዘንድ ሰይጣናት በእርሱ ላይ ተሰበሰቡ በደጁም እሳትን እያነደዱ ከእሳቱ እያነሡ ወደ በዓቱ ይጨምሩ ጀመር ያቺ እሳት ግን በጸሎቱ የምትጠፋ ሆነች።
ከዚህ በኋላ እንስሳዊ በሆነ ሥራ በፈቲው ጦር ተዋጉት በዚህም ታገሠ። ትካዜን ዓላማዊ ክብር መውደድን ትእቢትን መመካትን ታካችነትን ስድብን ሃይማኖት ማጣትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተስፋ መቁረጥን በልቡ አሳደሩበት ከዚህም ሁሉ በሚበዛ ተዋጉት የከበረ አባ እንጦንዮስ እንደነገረው።
በእሊህም አጥፊዎች በሆኑ ሥራዎች ሰይጣናት እየተዋጉት ለረጅም ጊዜ ከኖረ በኋላ ዳግመኛ ወደ አባት እንጦንዮስ ገና ከሩቅ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ በልቡ ሽንገላ በእውነት የሌለበት እስራኤላዊ ነው ልጆቼ ይህን የከበረ ሰው ታዩታላችሁን እርሱ ለብዙ ወገኖች የቀና የጽድቅ በትርና ረጅም አላማ ይሆን ዘንድ አለውና ከአሸናፊ እግዚአብሔር አፍ የተገኘ ጣፋጭ ፍሬም ይሆናልና አለ።
ወደ ቅዱስ አባ እንጦንዮስም በቀረበ ጊዜ በምድር ላይ ሰገደለት በፍጥነትም ቀና አድርጎ ሳመው ፊቱ እንደ በሽተኛ ፊት ተለውጦ አይቶታልና ይኸውም ሰይጣናት አብዝተው ስለተዋጉት ነው።
ከዚያም ጸሎት አድርገው በአንድነት ተቀመጡ አባት እንጦንዮስ ደስታ በተመላ ቃል ልጄ መቃርስ በደኅና አለህን አለው ቅዱስ መቃርስም እነሆ ከእኔ የሆነውን ሁሉ እግዚአብሔር ቀድሞ ገልጦልሃል ብሎ መለሰለት እርሱም ያን ጊዜ አስተማረው አጽናናውም እንዲህም ብሎ መከረው። መንፈሳዊ ጥበብን ለሚሹ ለብዙ ወገኖች መምህራን እንድንሆን ይቺውም ምንኵስና ናት ከጠላታችን በላያችን የሚመጣብንን መከራ ሁሉ ልንታገሥ ለእኛ የሚገባ ነው። ልጄ መቃርስ ሆይ ውኃ ለመቅዳት ስትሔድ እግዚአብሔር የነገረህን ያንን ቃል አስብ አለው።
ቅዱስ መቃርስም ሰምቶ እጅግ አደነቀ። የተሠወሩ ሥራዎቹ ለከበረ አባት እንጦንዮስ የተገለጡለት እንደሆኑ አወቀ። በእርሱ ዘንድም እየተማረና በረከትንም እየተቀበለ ብዙ ቀኖች ኖረ። ከዚያም የከበረች አስኬማን ያለብሰው ዘንድ ፈለገ አባ እንጦንዮስም በላዩ ጸለየ እርሷን አስኬማዪቱን አለበሰው ስለዚህም የከበረ እንጦንዮስ አባት ተባለ።
ዳግመኛም ወደዚህ ወደኔ መምጣትን ቸል አትበል እኔ ከጥቂት ቀኖች በኋላ ወደ እግዚአብሔር እሔዳለሁና አለው። አባ መቃርስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ተነሥቶ ሰገደለት መንፈሳዊ በረከቱን ይቀበል ዘንድ ከእርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመነው እርሱም ተቀመጥ አለውና ተቀመጠ።
ዳግመኛም አባ እንጦንዮስ ከጥቂት ቀኖች በኋላ ሰይጣናት በእኔ ላይ እንዳደረጉት በግልጥ ከተዋጉህ በኋላ ከዚህ ከክፉ አሳብ ውጊያ እግዚአብሔር ያሳርፍሃልና በርትተህ ታገሥ። እስከ ዕድሜህ ፍጻሜ ከአንተ ጋራ ሆኖ እንዲረዳህ እግዚአብሔር ያደረገውን ጠባቂህን መልአክ እንዳታሳዝነው ተጠበቅ አለው።
ከዚህ በኋላ አባ እንጦንዮስ ለአባ መቃርስ በትሩን ሰጠው በመንፈሳዊም ሰላምታ ተሰናብቶት አረፈ ሥጋውንም ማንም በማያውቀው ሥውር ቦታ ቀበረው። የከበረ አባ መቃርስም ወደ ቦታው ተመልሶ በአስቄጥስ ገዳም ተቀመጠ ዜናውም በአራቱ ማእዘን ተሰማ። እግዚአብሔርም በእጆቹ አስደናቂዎች ተአምራትን አደረገ ከእነርሱም አንዱ የአንጾኪያ ንጉሥ ርኵስ መንፈስ ያደረባትን ልጁን ወደርሱ ላካት እርሷም በጐልማሳ አምሳል ሁና ወደርሱ መጣች እርሱም አወቀ አድኖ ወደ አባትና እናቷ ሰደዳት። እርሱም ብዙ ወርቅና ብር በላከለት ጊዜ ምንም ምን አልተቀበለም። ሁለተኛውም አውሲም በሚባል አገር አንድ መነኰስ ነበር ስቶ ትንሣኤ ሙታን የለም አለ ብዙዎች ሰዎችንም አሳታቸው የአውሲም ኤጲስቆጶስም ወደ አባ መቃርስ ሔዶ የእርሱን ሕዝቦች እንዳሳታቸው ነገረው እንዲረዳውም አብዝቶ ለመነው።
አባ መቃርስም ተነሥቶ ከዚያ ኤጲስቆጶስ ጋራ ወደ ሀገረ አውሲም ደርሶ ያንን ርኵስ መንፈስ ያደረበትን ባሕታዊ መንኰስ ተገናኘው ስለ ትንሣኤ ሙታንም በተነጋገረው ጊዜ ያ ባሕታዊ የሞተ ሰው ከመቃብር ካላስነሣህ እኔ አላምንም ብሎ መለሰለት። አባ መቃርስም ወደ ክብር ባለቤት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየ ያን ጊዜም አንድ ምውት ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። ሰውየውም ከቀደሙ ከሀድያን ወገን ነው ያ ባሕታዊውም አምኖ ከስህተቱ ተመለሰ እንደርሱም የሳቱ ሁሉም ተመለሱ።
ያ ከሙታን ተለይቶ የተነሣውም የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቀው ዘንድ አባ መቃርስን ለመነው እርሱም አጥምቆ የምንኵስና ልብስ አለበሰው ሰባት ዓመትም ኑሮ አረፈ።
ከዚህም በኋላ የከበረ አባ መቃርስ ተመልሶ ከእርሱ አስቀድሞ በዚያ በረሀ ውስጥ ሰው እንዳለ ያይ ዘንድ ወደ በረሀው ውስጥ ዘልቆ ገባ። ዕራቁታቸውን የሆኑ ሁለት ሰዎችን አይቶ ፈራ የሰይጣን ምትሐት መስሎታልና እልቦት ቦሪቦን ብሎ ጸለየ ይህም አቡነ ዘበሰማያት ማለት ነው እነርሱም በስሙ ጠርተው መቃሪ ሆይ አትፍራ አሉት እርሱም በበረሀ የሚኖሩ ቅዱሳን እንደሆኑ አውቆ ወደ እርሳቸው ቀርቦ እጅ ነሣቸው። እነሱም በዓለም ስላሉ ሰዎች ስለ ሥራቸውም ጠየቁት እርሱም በቸርነቱ እግዚአብሔር በሁሉም ላይ አለ ብሎ መለሰላቸው።
እርሱም ደግሞ የክረምት ቅዝቃዜ ይቀዘቅዛቸው እንደሆነ የበጋውም ትኩሳት ያልባቸው እንደሆነ ጠየቃቸው። እነርሱም በዚህ በረሀ እግዚአብሔር አርባ ዓመት ጠብቆናል የክረምት ቅዝቃዜ ሳይቀዘቅዘን የበጋ ትኩሳት ሳያልበን ኖርን ብለው መለሱለት ደግሞ እንደናንተ መሆን እንዴት እችላለሁ አላቸው።
እነርሱም ወደ በዓትህ ተመልሰህ ስለ ኃጢአትህ አልቅስ አንተም እንደእኛ ትሆናለህ አሉት ከእነርሱም በረከትን ተቀብሎ ወደቦታው ተመለሰ።
በእርሱ ዘንድ መነኰሳት በበዙ ጊዜ ጕድጓድ ቆፍረው መታጠቢያ ሠሩለት ሊታጠብ በወረደ ጊዜ ሊገድሉት ሰይጣናት በላዩ አፈረሱት መነኰሳትም መጥተው አወጡት።
እግዚአብሔርም ከዚህ አለም መከራ ሊያሳርፈው በወደደ ጊዜ ሁልጊዜ የሚጐበኘውን ኪሩብን ወደርሱ ላከ። እርሱም እኔ ወደ አንተ መጥቼ እወስድሃለሁና ተዘጋጅ አለው ከዚያ በኋላ አባ እንጦንስንና የቅዱሳንን አንድነት ማኅበር ሰማያውያን የሆኑ የመላእክትንም ሠራዊት በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን እስከ ሰጠ ድረስ ያይ ነበር።
መላ የዕድሜው ዘመን ዘጠና ሰባት ሆነ። የቅዱስ መቃርስ ነፍስ ወደ ሰማይ ስታርግ እንዳየ በዚህ ነገር ደቀ መዝሙሩ አባ በብኑዳ ምስክር ሆነ ሰይጣናትን እንደሰማቸው እየተከተሉ መቃሪ ሆይ አሸነፍከን አሸነፍከን እያሉ ሲጮኹ እስከ ዛሬ ገና ነኝ አላቸው ወደ ገነትም ሲገባ መቃሪ ሆይ አሸነፍከን ብለው በታላቅ ድምፅ ጮኹ የክብር ባለቤት ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመስገን ስሙም ይባረክ ከእጃችሁ ያዳነኝ አላቸው ብሎ መስክሮአል።
የሥጋው ፍልሰትም እንዲህ ሆነ እርሱ በሕይወት ሳለ ሥጋውን እንዳይሠውሩ ልጆቹን አዞአቸው ነበር የሀገሩ የሳሱይርም ሰዎች መጥተው ለደቀ መዝሙሩ ለዮሐንስ ገንዘብ ሰጡ።
ይህንንም ስለ ገንዘቡ ፍቅር ይመክረውና ይገሥጸው የነበረ ገንዘብ ከመውደድ ተጠበቅ የሚለው ነው። እርሱም መርቶ የቅዱስ አባ መቃርስን ሥጋ አሳያቸው ወደሀገራቸው ሳሱይር ወሰዱት እስከ ዓረብ መንግሥት መቶ ስልሳ ዘመን በዚያ ኖረ ደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ግን ገንዘብ ስለመውደዱ ዝልጉስ ሆነ።
ከዚህም በኋላ ልጆቹ መነኰሳት ወደ ሀገሩ ወደ ሳሱይር ሔዱ የከበረ አባት የአባ መቃርስን ሥጋ ሊወስዱ ፈለጉ የአገር ሰዎችም ከመኰንኑ ጋር ተነሥተው ከለከሉአቸው በዚያቺም ሌሊት የከበረ አባ መቃሪ ለመኰንኑ ተገልጦ ተወኝ ከልጆቼ ጋራ ልሒድ አለው። መኰንኑም መነኰሳቱን ጠርቶ የአባታቸውን ሥጋ ተሸክመው ይወስዱ ዘንድ ፈቀደላቸው።
በዚያን ጊዜም ተሸከመው አክብረው ወሰዱት በብዙ ምስጋና በመዘመርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ነሐሴ ዐሥራ ዘጠኝ ቀን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከእርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ። ማለድ ብለው ሲደርሱ አርፋ አገኟት፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የኢትዮጵያ ንጉሥ ሰማዕት ገላውዲዎስ አንገቱን የተቆረጠበት ቀን ነው። ይህ ቅዱስም በተግሣጽ በምክር በፈሪሀ እግዚአብሔር አደገ አባቱ ንጉሥ ልብነ ድንግል ሃይማኖቱ የቀና ነበርና በዘመኑም የእስላም ወገን የሆነ ስሙ ግራኝ የሚባል ተነሥቶ አብያተ ክርስቲያናትን አጠፋ።
ከንጉሥ ልብነ ድንግል ጋር ጦርነት ገጠመ ንጉሡም ወግቶ መመለስ ቢሳነው አርበኞች ሠራዊትን እስከሚሰበስብ ከእርሱ ሸሸ በስደትም እያለ በድንገት ታሞ ሞተ።
ይህም አመፀኛ የኢትዮጵያን ሀገሮች እያጠፋ ዐሥራ አምስት ዓመት ያህል ኖረ። ከኢትዮጵያም ሕዝቦች የሚበዙትን ማርኮ ከቀናች ሃይማኖት አውጥቶ የእርሱ ሃይማኖት ተከታዮች አደረጋቸው በመመካትም እንዲህ አለ። ሀገሮችን ሁሉ ግዛቶቼ ስለ አደረግኋቸው ከእንግዲህ የሚቃወመኝ የለም።
ከዙህ በኋላ እግዚአበሔር ይህን ቅዱስ ገላውዴዎስን አስነሣ ከግራኝ ታላላቅ መኳንቶቹ ጋር ጦርነት ገጠማቸው ድልም አድርጎ አሳደዳቸው።
ግራኝም በሰማ ጊዜ ተቆጣ ከቱርክ አርበኞች ጋርና ከአእላፍ ፈረሰኞች ጋር መጥቶ ንጉሡን ገጠመው ጌታችንም ግራኝን በንጉሥ ገላውዴዎስ እጅ ጣለው ገደለውም። ግራኝን በመፍራት የተበተኑ ሁሉ ከተማረኩበትም ሁሉ ተመለሱ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናትም ተመልሰው ታነፁ የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስ ሃይማኖት ተቃናች።
ከዚህም በኋላ ከእስላሞች ወገን አንዱ ከብዙ አርበኞች ሠራዊት ጋር መጣ በመድኃኒታችን የስቅለት በዓል ከጥቂት ሰዎች ጋራ ተቀምጦ ሳለ በድንገት ንጉሡን ተገናኘው ሰዎቹም የጦር መኰንኖች እስቲሰበሰቡ ፈቀቅ እንበል አሉት።
እርሱ ግን የክርስቲያኖችን መማረክና የአብየተ ክርስቲያናትን መፍረስ አላይም ብሎ እምቢ አለ እንዲህም እያለ ወደ ውጊያው መካከል ገብቶ በርትቶ ሲዋጋ የኋላ ኋላ እስላሞች ሁሉም ከበቡት።
ተረባረቡበትም በጐራዴም ጨፈጨፉት በብዙ ጦሮችም ወጉት ከፈረሱም ጣሉት የከበረች አንገቱንም ቆረጡት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages