ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 29 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, April 6, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 29

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን ለእመቤታችን ለቅድስት_ድንግል_ማርያም የከበረ_መልአክ_ገብርኤል የምሥራች የነገረበት ነው፣ በመድኃኒታችን በከበረችና ልዩ በሆነች ትንሣኤው የዓለም ድኅነት ሆነ፣ የከበረ ሐዋርያ_ቅዱስ_ጳውሎስ የምድር ዳርቻ በሆነች አልዋሪቆን በምትባል አገር ደርሶ አስተማረ።መጋቢት ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የከበረ መልአክ ገብርኤል የምሥራች የነገረበት ድኅነትን የተመላች ታላቅ በዓል ናት በዚህም የከበረ ወንጌል ምስክር ሁኗል እንዲህ ሲል፦ ኤልሳቤጥ ከፀነሰች በኋላ በስድተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል የገሊላ ክፍል የሆነች ናዝሬት ወደምትባል አገር ከዳዊት ወገን ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ።
የድንግሊቱም ስም ማርያም ነው። መልአኩም ወደርሷ ገብቶ ደስተኛ የሆንሽ ደስ ይበልሽ ጸጋን የተመላሽ ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም አይታ ከንግግሩ የተነሣ ደንግጣ እንዴት እንዲህ ያለ ሰላምታ ይቀበሏል ብላ አሰበች።
መልአኩም እንዲህ አላት ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ እርሱ ታላቅ ነው የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል።
እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል ለያዕቆብ ወገንም ለዘላለም ነግሦ ይኖራል ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም።
ማርያምም መልአኩን ወንድ ሳላውቅ ይህ እንደምን ይሆናል አለችው።መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት መንፈስ ቅዱስ መጥቶ ያድርብሻል የልዑል ኃይልም ያጸናሻል ከአንቺ የሚወለደው ከሶስቱ አካል አንዱ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል።
እነሆ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ፀንሳለች ወንድልጅም አገኘች ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም እነሆኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለችው።
ያን ጊዜም ድንግል ስትሆን ረቂቅ ፅንስን ተቀበለች የእግዚአብሔር አካላዊ ቃል ወልድ ዋህድ ለኩነተ ሥጋ ወርዶአልና ይህም አንድ ባሕርይ አንድ ህልውና ሲሆን ከሦስቱ አካላት አንዱ ነው ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ የነበረ በማይመረመር ድንቅ በሆነ ተዋሕዶ እንዴትም እንደሆነ በማይታወቅ በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን አደረ ፅንስ ሆኖ ኖረ።
በዚያን ጊዜም የኋላ ኋላ መለየት ከቶ የሌለውን ፍጹም ሰውነት ነሥቶ ተዋሐደ መለኮቱ ከትስብእቱ ጋራ ያለ መለያየት አንድ ሆኖአልና። ይቺም ዕለት የበዓላት ሁሉ በኵር ናት በእርሷም የዓለም ድኅነት ተጀምሮዋልና።
ዳመኛም በዚህች እለት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽንሰት በተጨማሪ የቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ፣የቅዱሳን አብርሃ ወአጽብሐ፣ የቅዱስ ኢያሱ ነቢይ፣ የቅዱስ ላሊበላ፣ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጽንሰታቸው ታስቦ ይውላል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ደግሞ በመድኃኒታችን በከበረችና ልዩ በሆነች ትንሣኤው የዓለም ድኅነት ሆነ፡፡ በረቀቀ ጥበቡ ሠላሳ ሦስት ዓመት ያህል በምድር ላይ ሥራውን ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ በፈቃዱ ሕማማተ መስቀልን ተቀብሎ ሙቶ ከተቀበረ በኋላ በሦስተኛው በዚች ቀን በሃያ ዘጠኝ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና።
በዚች ቀን አስቀድሞ ደጅ ለሚጠኑት በዓለም ላሉ ሰዎች ሰው በመሆኑ ድኅነታቸውን አበሠራቸው እንዲሁም ደግሞ በዚች ዕለት ከሲኦል በመዳን ሙታንና ሕያዋን ደስ አላቸው።
በዚህም በጌታችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መነሣት መነሣታቸውን አረጋገጡ። የከበረ ጳውሎስ በመነሣቱ ክርስቶስ የሙታን በኵር ሆነ እንዳለ እርሱ ለሙታን በኵራቸው ነውና።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስ አልዋሪቆን ከምትባል አገር ደርሶ አስተማረ ይቺም የምድር ዳርቻ ናት። ራሱ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ አለ ከዚያም በእግዚአብሔር መልአክ ትእዛዝ ወደ ዚያች አገር ሔድኩ ሀገሪቱም እንደ ሮሜ አማሳል ታላቅ የሆነች እጅግ ውብ ናት ፍሬዋም የበዛ ነው።
በውስጡ የሚታለፍበት ስሙ ገርጋ የሚባል ባሕር ግን አግድመቱ ሦስት መቶ ምዕራፍ ነው። መጋቢት ሃያ ሰባት ቀንም መጀመሪያ ከዚያ ከባሕሩ ዳርቻ ደረስኩ ለሀገሩም ሰዎች በዓላቸው ነበር የጽጌ ረዳ አክሊልም እየታቱ በጣዖቶቻቸው ራስ ላይ ያኖራሉ ከስንዴአቸውም አዲስ እሸትን ለጣዖቶቻቸው ያቀርባሉ።
የአገር ጠባቂ የሚሉትም በጠልሰም የተቀረጸ ሥዕል በአገሩ ቅጽር ላይ ተደርጓል ወደዚያች አገር የሚመጣ እንግዳ ሰው ሲያይ በላዩ ያደረ ርኵስ መንፈስ በታላቅ ድምፅ ይጮኻል። የአገር ሰዎችም የዚያን ጠልሰም ጩኸቱን በሚሰሙ ጊዜ ወደ አገራቸው የመጣውን እንግዳ ወጥተው ይገድሉታል ሕጋቸው እንዲህ ነውና ወደ አገራቸው ይገባ ዘንድ ማንንም አይተዉም አያሰናብቱም።
እኔም ወደዚያች አገር ደርሼ ወደ ባሕሩ በቀረብኩ ጊዜ ያ ጠልሰም እነሆ እንግዳ ወደ እናንተ ደረሰ ብሎ በአገራቸው ቋንቋ ጮኸ። የአገር ሰዎችም ድምፁን ሰምተው ከንጉሣቸው ጋራ ብዙ ሰራዊት መጡ በዚያን ጊዜ ስለ በዓላቸው ተሰበስበው ነበርና ፈለገኝ እኔ ግን በአየኋቸው ጊዜ ሸሽቼ የቀበሮዎችና የእሽኮኮዎች መሸሻ ወደ ሆነ ዋሻ ገባሁ። ከዚያም ገብቼ በረሀብና በጥም ስለተሠቃየሁ አለቀስኩ። በዚያን ቀን የፀሐይ ትኩሳት ከመጽናቱ የተነሣ ሐሩር ሆኖ ነበርና በዚያም እስከ ሌሊት ቆይቼ ከዚያ ወጥቼ ከባሕሩ ውኃ ጠጣሁ ቁሜም ወደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስም ጸለይኩ።
ንጋትም በሆነ ጊዜ ከዚያ ዋሻ ወጥቼ ወደ አገር ለመግባት ፈለግሁ። ያ ጠልሰም አሁንም መምጣቴን እየገለጠ ሁለተኛ እንደታላቅ ነጐድጓድ ጮኸ ለባሕሩም ልማድ አለው ጠልሰሙ በሚጮኸ ጊዜ ይታወካል ማዕበሉም ይነሣል ያን ጊዜም ያገር ሰዎች ሊገድሉኝ መጡ።
ከሩቅ በአየኋቸውም ጊዜ ፈራሁ እንደቀድሞውም በዚያ ዋሻ ደግሜ ተሸሸግሁ ጌታ ክርስቶስንም እለምነው ዘንድ ጀመርኩ በአባት ጴጥሮስም ጸሎት የማፀንኩ በወንድሞቼ በሐዋርያትም ጸሎት። ይልቁንም ንጽሕት ድንግል በሆነች በብርሃን እናት በእመቤታችን ማርያም በአማላጅነቷ ተማፀንኩ በሌሊቱ ርዝመት ሁሉ ስጸልይ አደርኩ።
በነጋም ጊዜ ወደ ባሕሩ ዳር ወጣሁ ያም ጠልሰም እንደ ልማዱ ጮኸ ተራራዎችም እስቲናወጹ ጩኸቱን አበዛ የባሕሩም ማእበል ታወከ። ውኃውም እንደ ደም ሆነ የአገሩም ሰዎች ከሠራዊቶቻቸው ጋራ እንደ ቀድሞው ወጡ ባሕሩም መርከቦችን ተመላ እኔም ልሠወር ሮጥኩ።
በዚያን ጊዜም የብርሃን እናት እመቤታችን ድንግል ማርያምን በባሕሩ ላይ ቁማ አየኃት። ጳውሎስ ሆይ ወዴት ትሸሻለህ አምላክህ ክርስቶስ እንዲህ እንድትሸሽ አዘዘህን እርሱ ራሱ ሥጋችሁን የሚገድሉትን አትፍሩአቸው ነፍሳችሁን ግን መግደል አይችሉምና ያለ አይደለምን። አንተም በቦታህ ጸንተህ ቁም እኔም ከአንተ ጋራ አለሁ እጄንም ከአንተ አላርቅም በርታ ጠንክርም የዚችን አገር ሰዎች ሁሉንም በዚህ የባህር ውኃ እንደምታጠምቃቸው ዕወቅ በእጅህም አምነው ሙታን በሚነሡባት ዕለት ዕድላቸው ከአንተ ጋር ይሆናል ባሕሩም ቃልህን ሰምቶ ይታዘዝልሃል አለችኝ።
ምሕረትንና ርኅራኄን የተመላች እመቤቴ የብርሃን እናት ድንግል ማርያም ይህን ስትናገረኝ እነሆ በእጃቸው የጦር መሣሪያ የያዙ ኃይለኞች ሰዎችን የተሞሉ መርከቦችን በቅርብ አየኋቸው እጅግም ፈራሁ እመቤቴ ማርያምም ተሠወረችኝ። ነገር ግን ከደመና ውስጥ ጳውሎስ ሆይ ሰዎችን አጥምቅ ማጥመቅንም አታቋርጥ የሚለኝን ቃል እሰማ ነበር። እኔም በታላቅ ቃል ፈጣሪዬ ሆይ ይህን የባሕር ውኃ ለእሊህ ለተጣሉ በጎች ሰይጣንም ለማረካቸው ጥምቀትን አድርገው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በዚህ ባህር ጥምቀት እሊህን ሰዎች በሦስትነትህ ስሞች የልጅነትን ክብር የሚቀበሉ አድርጋቸው በማለት አሰምቼ ተናገርኩ።
እንዲህም ይህን እያልኩ ከባሕሩ ውኃ ዘግኜ ሰዎች በአሉባቸው መርከቦች በላያቸው ረጨሁት የሰዎቹም ቁጥራቸው አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ነው። እኔ ወደአለሁበት የባሕር ዳር በደረሱ ጊዜ ከመርከባቸው ወጥተው ፈለጉኝ እኔም እመቤቴ የብርሃን እናት እንዳዘዘችኝ በፊታቸው ቆምኩ በረድኤቷ ተማምኛለሁና አልፈራሁም። በአዩኝም ጊዜ ሁሉም በፊቴ ሰገዱ በአንድ ቃልም ቅዱስ ጳውሎስ ሆይ ፍቅር አንድነት ለአንተ ይሁን ወደአንተ ከመድረሳችን በፊት በመርከቦች ውስጥ እያለን እኛ ያየነውን አየህን አሉኝ።
እኔም አዲስ የተወለዳችሁ ልጆች ሆይ ምን አያችሁ አልኋቸው የሰማይ ደጆች ተከፍተው የቀኝ እጅ እንደ እሳት ነበልባል ተዘርግታ አየን ደግሞ የፊቷ ብርሃን ከፀሐይ ሰባት እጅ የሚበራ ሴት አየን። እርሷም ከደመና በታች የምትረጨውን ውኃ ተቀብላ በላያችን ትረጨዋለች ትስመናለች ታቅፈናለችም። በራሲቻችንም ላይ የብርሃን አክሊሎችን ታደርጋለች አሉኝ። ይህንንም በሰማሁ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለኝ በስሙ በምንሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዳለ ተረዳሁ።
ከዚህም በኋላ ሌሎች መርከቦች መጡ ኃይለኞች ሰዎችን ከጦር መሣሪያ ጋር የተመሉ ናቸው እንዲህም እያሉ ዛቱበኝ። አንተ ሥራየኛ ጥበበኞች ሕርምስና በለንዮስ ታምራት የሚያደርጉባቸው የጠልሰም መጻሕፍቶች ከእኛ ጋራ እንዳሉ ዕወቅ በማለት እኔም ቸር ፈጣሪዬ ሆይ የቀደሙትን በጎች ይቅር እንዳልካቸውና በውስጣቸው ኃይልህን እንደገለጥክ ለእነዚህም እንዲሁ ኃይልህን ግለጥ ይቅርም በላቸው አልኩ።
ከዚያም በኋላ ከባሕሩ ውኃ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥምቀትን ይሁናችሁ አልኩ ወዲያውኑ መርከቦች ከባሕሩ ዳር ደረሱ። ሁሉም ሰዎች ከመርከብ ወጥተው በፊቴ ሰገዱ የቸር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሆይ እናመሰግንሃለን አሉኝ።
ይህንንም ድንቅ ተአምር ከቀደሙት ባልንጀሮቻቸው ጋራ ተነጋገሩ ዜናዬም በዚያች አገር ንጉሥ ዘንድ ተሰማ እርሱም ከሰራዊቱ ጋር ተነሳ በመርከቦችም ተጭነው ወደእኔ መጡ። እኔም ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አቅንቼ የፈጣሪዬን ስም ጠራሁ ባሕርዋንም በመስቀል ምልክት አማተብኩባት። እንዲህም አልኳት አንቺ ባሕር በእግዚአብሔር ልጅ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ትከፈዪ ዘንድ አዝሻለሁ ምድሩም ይገለጥ መርከቦችም በየብስ ውስጥ ይቁሙ።
ነገሬንም ሳልጨርስ ባሕርዋ ተከፈለች በውስጥዋም ዐሥራ ሦስት ጎዳናዎች ተገለጡ መርከቦቹም ውኃ በሌለው ምድር ላይ ቆሙ ይህንንም አይተው ሰይፎቻቸውን መዘዙ ዕንጨቶችም ሆነው አገኙአቸው እኔም ከሕህሩ ውኃ ዘግኜ በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እያልኩ በላያቸው ረጨሁ። በዚያን ጊዜ እሊያ መርከቦች ነፋስ ተሸክሟቸው ያለ ውኃ ከምድር ከፍ ከፍ ብለው ተጓዙ ሰዎችም ከውስጣቸው ወጥተው ወደእኔ መጥተው ሰገዱ። ከእነሱም የቀደሙ ሰዎች ሰላምታ እንዳቀረቡልኝ ንጉሡም ከሀገር ሰዎች ሁሉ ጋር በፊቴ ሰገደ።
ከዚያም በኋላ ከእርሳቸው ጋር ወሰዱኝ ወደ ከተማውም በደረቅ ያለ መርከብ ገባን በምኵራባቸውም ውስጥ በጽጌ ረዳ አክሊል ጣዖቶቻቸው ተከልለው የሥንዴ እሸትም እንደ መስዋዕት ሆኖ ተጥሎ አየሁ ይህንንም አይቼ እጅግ አዘንኩ።
የአገር ሰዎችም ክብር መምህር ሆይ በዚች ዕለት ለአማልክት በዓል የምናደርግበት እንደ ነበረ ዕወቅ አሁን አንተ ለማን ታዝናለህ ለአብ እንድርገውን ወይም በወልድ ስም ወይም በመንፈስ ቅዱስ ስም በስማቸው ያጠመቅከን ስለሆነ አሉኝ። እኔም እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ የሚገባቸውን ሃይማኖትን አስተማርኳቸው መጻሕፍትንም በእጄ ጻፍኩላቸው።
በአማላጅነቷ ከርኵስ ሰይጣን ተገዥነት ስለዳኑ ያንን በዓል የብርሃን እናት በሆነች በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም እንዲያደርጉት አዘዝኋቸው ዕለቱም የእግዚአብሔርን ልጅ እንደምትፀንሰውና በሥጋ እንደመትወልደው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ያበሠረበት ስለሆነ።
እኔም አምላካዊ ትምርትን አስተማርኳቸው በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አደረግኋቸው ውኃው በተከፈለበትም ላይ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰሩ አዘዝኳቸው። በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድንቆች የሆኑ ብዙ ተአምራቶችንም አደረኩላቸው ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ዘንድ ወጥቼ መጣሁ።
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages