ቀዳሚት ሥዑር - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, April 14, 2023

ቀዳሚት ሥዑር

በመምህር ቸሬ አበበ

ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር አምላካችን የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሔዱትን፣ በክንፍ የሚበሩትን እና በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን፣ በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈባት ዕለት ነች፡፡ የመጀመሪያዋ ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፡፡ እግዚአብሔርን ፍጥረታትን ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ ስላረፈባት ‹ሰንበት ዐባይ› (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች፡፡ ይህቺን ዕለት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት ዐባይ) በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ እግዚአብሔር ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንዳደረገባት ዅሉ፣ የፍጥረት ርእስ የኾነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው አምላካችን ክርስቶስ በመቃብር አርፎባታል (ማቴ. ፳፯፥፷፩)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር አርፎ የዋለባት ዕለት በመኾኗ ‹ቀዳሚት ሥዑር› ወይም ‹ቀዳም ሥዑር› ትሰኛለች፡፡ ‹ሥዑር› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም (የጾም ቀን በመኾኗ) ነው፡፡ የጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እኽል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

እመቤታችንና ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን፣ በመጾምና በመጸለይ ዕለቷን እንዳከበሯት ዅሉ የተዋሕዶ ልጆችም የተቻላቸው ከሐሙስ ጀምረው በማክፈል (በመጾም) እኽል ውኃ ሳይቀምሱ ለሁለት ቀናት ያድራሉ፡፡ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡ በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸምም ካህናቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡ ምእመናን የምሥራች ቄጠማ ያድላሉ፡፡

ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ኾነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል (ዘፍ. ፱፥፩-፳፱)፡፡

ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደ ኾነ ዅሉ፣ አሁንም ‹‹በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፤›› ስትል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የኾነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ዅሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከዋዕየ ሲኦል (የሲኦል ቃጠሎ) ወደ ጥንተ ማኅደራቸው ገነት መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፦ ማህበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages