ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 8 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, April 20, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 8

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ስምንት በዚህች ዕለት የከበሩ ሦስት ሴቶች ቅዱሳት_አጋሊስ_ኤራኒና_ሱስንያ በሰማዕትነት አረፉ፣ መቶ ሃምሳ ሰዎች በፋርስ ንጉሥ እጅ በአንዲት ቀን በሰማዕትነት አረፉ።


ሚያዝያ ስምንት በዚህች ዕለት የከበሩ ሦስት ሴቶች በሰማዕትነት አረፉ። የእሊህም ስማቸው አጋሊስ ኤራኒና ሱስንያ ነው። ከተሰሎንቄ ሀገርም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመልኩ ናቸው። ወላጆቻቸው እግዚአብሔርን የሚፈሩ ነበሩ።
እሊህም ደናግል በድንግልና በንጽሕና መኖርን ወደው በአንድ ምክር ተስማሙ ጽኑዕ በሆነ ገድልም ተጠመዱ ይልቁንም ያለማቋረጥ ተግተው ይጸልዩና ይጾሙ ነበር። ወደ ገዳሙም ተመልሰው ከመነኰሳቱ ጋራ ያገለግላሉ።
ከሀዲ መክስምያኖስም በነገሠ ጊዜ የጣዖታትን አምልኮ አቁሞ የንጹሆችን ደም አፈሰሰ። እሊህም ደናግል በአዩ ጊዜ ፈርተው ወደ ተራራ ሸሹ በዚያም በዋሻ ውስጥ ተሸሸጉ በጾምና በጸሎት በመጸመድ ሳይወጡ በዋሻው ውስጥ ኖሩ።
አንዲት የክርስቲያን ወገን አሮጊት በየሰባት ቀን ትጐበኛቸውም ነበር የሚአሻቸውንም ትሰጣቸዋለች የእጅ ሥራቸውን ትሸጥላቸውና ከእነርሱ የሚተርፈውን ትመጸውታለች። አንድ ሰውም ከከተማ ወጥታ ወደ ተራራ ሁልጊዜ ስትሔድ አያት ሳታየውም ተሠውሮ በሩቅ ተከተላት ወደ ዋሻውም እስከምትገባ ተመለከተ ከዚያ እስከምትወጣም ተሠውሮ ቆየ በዚያ ቦታ ብዙ ገንዘብ ያላት መስሎታልና።
ያቺ አሮጊትም ከዋሻው በራቀች ጊዜ ያ ሰው ገባ ለክብር ባለቤት ሙሽሮቹ የሆኑ የከበሩ አዕናቍ ደናግልን ቁመው ሲጸልዩ አገኛቸው ተሰሎንቄ ከተማ እስኪያደርሳቸውም አሥሮ ጐተታቸው።
መኰንኑም ሃይማኖታቸውን በጠየቃቸው ጊዜ ስለ እሳቸው የተሰቀለ የክብር ባለቤት ክርስቶስን የሚያመልኩ ክርስቲያኖች እንደሆኑ በፊቱ አመኑ። መኰንኑም ተቆጥቶ ይገርፉአቸው ዘንድ አዘዘ የሚአሠቃይ ጽኑ ግርፋትም ገረፉአቸው ባልተሰዘዙና ወደ ክህደቱ ባልገቡ ጊዜ ወደ እሳት እንዲጨምሩአቸው አዘዘ።
በእሳትም ውስጥ በጣሉአቸው ጊዜ ነፍሳቸውን አሳለፉ በመንግሥተ ሰማያትም የሕይወትን አክሊል ተቀዳጁ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን መቶ ሃምሳ ሰዎች በፋርስ ንጉሥ እጅ በአንዲት ቀን በሰማዕትነት አረፉ።
እርሱም ለሀገሩ ቅርብ የሆነ የክርስቲያንን አገር ከበበና ብዙ የሰው ምርኮ ማርኮ ወደ አገሩ ወሰዳቸው ፀሐይን ጨረቃንና ከዋክብትንም ያመልኩ ዘንድ አስገደዳቸው አይሆንም ባሉትም ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጡአቸው ዘንድ አዘዘ። ራሶቻቸውንም ቆረጡአቸው በመንግሥተ ሰማያትም የሕይወትን አክሊል ተቀበሉ፡፡
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages