ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 21 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, May 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 21

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ሃያ አንድ በዚህች ቀን የከበረ አባት_ብሩታዎስ አረፈ፣ ዕለት የሐዋርያት አምሳል ሃይማኖትን የሚሰብክ ዕጨጌ_ዕንባቆም መታሰቢያው ነው፡፡


ሚያዝያ ሃያ አንድ በዚህች ቀን የከበረ አባት ብሩታዎስ አረፈ፡፡ ይህም አባት የአቴና አገር የሆነ ከምሁራን ጥበበኞች አንዱ ነው እርሱም ደግሞ ደራስያን ከሆኑ ከአረጋውያን መምህራን ጋራ የተቆጠረ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስንም ተገኝቶት ስለ ቀናች ሃይማኖት ተከራከረው። የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት የቀናች እንደሆነች ተረድቶ አመነ በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እጅ ተጠምቆ የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት ተማረ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ በአቴና አገር ቅስና ሾመው። በታላቂቱ አገር በአቴና የመምህራን አለቃ ከሆነ ዘመደ ላሕም አብሮባ ከተባለ ከከበረ ዲዮናስዮስ ጋራ ተገናኘ። እርሱም የክብር ባለቤት ስለሆነ ጌታ ኢየሱስ ሃይማኖት ብዙ ገለጠለት ከውስጡ ሥውር የሆነበትንም ተረጐመለት እጅግም ዐዋቂ ሆነ።
ይህም አባት አምላክን የወለደች እመቤታችን የከበረች ድንግል ማርያም በዐረፈችበት ቀን ደርሶ በሐዋርያት መካከልም ቆመ በደረሰው ማኅሌትና ዝማሬ ጣዕም ባለው በመሰንቆ በዜማ ድምጽም አጽናናቸው። ከአይሁድና ከአሕዛብም ብዙዎቹን መልሶ ወደ ክብር ባለቤት ወደ ጌታ ክርስቶስ እምነት አስገባቸው። በተሰጠችውም ጸጋ ነግዶ ታላቅ ትርፍ አስገኘ።
ሐዋርያትም ኤጲስቆጶስነት ሊሾሙት በፈለጉ ጊዜ ጌቶቼ ይቅርታ አድርጉልኝ እኔ ለዚች ለከበረች ሹመት አልበቃሁምና የቅስናንም አገልግሎት ልፈጽም አልቻልኩምና ተውኝ ብሎ ማለዳቸው። በዕውቀቱና በሥራው ሰማያዊ ሀብትን ተቀብሎ ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔር ሔደ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚኽች ዕለት የሐዋርያት አምሳል ሃይማኖትን የሚሰብክ ዕጨጌ ዕንባቆም መታሰቢያው ነው፡፡ እርሱም በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ወንበር ለመሾም እስከተገባው ድረስ እግዚአብሔር ከእስልምና እምነት መርጦ ያመጣውና በደብረ ሊባኖስ ገዳም በዕጨጌነት ተሹሞ ቤተ ክርስቲያንን ያገለገለ ብዙ ሰማዕትነትንም የተቀበለ ታላቅ አባት ነው፡፡
አባ ዕንባቆም ዕጨጌ ዘደብረ ሊባኖስ፡- የሐዋርያት አምሳያቸው የሆኑ ሃይማኖትን የሚሰብኩ ዕጨጌ ዕንባቆም ሚያዝያ 21 ዓመታዊ መታሰቢያ በዓላቸው መሆኑን ስንክሳሩ ይጠቅሳል፡፡ እርሳቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ወንበር ለመሾም እስከተገባቸው ድረስ እግዚአብሔር ከእስልምና እምነት መርጦ ያመጣቸው ታላቅ ሐዋርያ ናቸው፡፡ የመናዊው እጨጌ ዕንባቆም በዐረብ ምድር በየመን የተወለዱ ሲሆን አስቀድመው እስላም ነበሩ በኋላ ግን መጻሕፍትን መርምረው ዕውነትን ፈልገው በማግኘት በጌታችን በክርስቶስ አምነው ተጠምቀው ከመነኮሱ በኋላ በደብረ ሊባኖስ በአቡተ ተክለ ሃይማኖት ወንበር ተሾመው እስከማገለግል የደረሱ ታላቅ አባት ናቸው፡፡
አባ ዕንባቆም በ1416 ዓ.ም አካባቢ የመን ውስጥ ነው የተወለዱ፡፡ አባታቸው እስላም ሲሆን እናታቸው ግን አይሁዳዊት ነበረች፡፡ አባታቸው በሕጋቸው መሠረት ሁለት ሚስት አግብቶ ከአንደኛዋ 7 ልጆችን ሲወልድ ከአንዷ ደግሞ 2 ልጆችን ወልዷል፡፡ ከሁለቱ አንዱ አባ ዕንባቆም ነበር፡፡ እርሱም ቁርአንን እና ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን በሚገባ እየተማረ አደገ፡፡ ለእስልምና ሃይማኖቱ ቀናተኛ የነበረው ዕንባቆም የክርስትና ስም ሲነሳበት አይወድም ነበር፡፡ 114ቱንም የቁርአን ምዕራፎች (ሱራዎች) በቃሉ ይዞ ቀን ከሌሊት ይጸልይባቸው ነበር፡፡ አንድ ቀን በቁርአን ላይ ስለመሞትና መነሣት የተጻፈውን ሲያነብ ኅሊናው ታወከ፡፡ ወዲያውም ወደ ቁርአን ሊቅ ዘንድ ሄዶ ትርጉሙን ጠየቀ፡፡ ነገር ግን የተሰጠው ምላሽ ‹‹ለምን አነበብከው?›› የሚል ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ ቁርአኑን ከዐረብኛ ቋንቋ ውጭ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም እንደሌለበትና በእርሱ ላይ ስለተጻፉት ነገሮች ጥያቄ መጠየቅ ክልክል እንደሆነ ቁርአኑ ለራሱ ከለላ የሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡)
ዕንባቆምም ለጥያቄው መልስ በማጣቱ ይልቁንም ስለጠየቀ በቁጣ ስለተገሠጸ በእስልምና ላይ የነበረው ፍጹም እምነት ወደ ጥርጣሬ ተቀየረ፡፡ በዚያም ዘመን የኢትዮጵያ ንጉሥና የአዳል ንጉሥ ጦርነት ገጥመው አዳሎች አሸነፉና ንጉሡ 51 የኢትዮጵያ ምርኮኞችን ለአባ ዕንባቆም አባት ላከለት፡፡ ምርኮኞቹም ዕንባቆም በሃይማኖት ምክንያት ከወገኖቹ ጋር አለመስማማቱን አይተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄድ መከሩት፡፡ እርሱም አብሯቸው በመካ በኩል ዳህላክን አቋርጦ ከነጋዴዎች ጋር ወደ ኢትዮጵያ ወደብ ደረሰ፡፡
ዕንባቆምም መጀመሪያ ካገኘውና አብሮት ከመጣው ወሰንጌ ጋር በመርሐ ቤቴ ተቀመጠ፡፡ በዚያም ትምህርተ ሃይማኖትን መማር ጀመረ፡፡ በግእዝ ንባብ የጀመረውም ትምህርት ተአምረ ማርያም ላይ ሲደርስ የእመቤታችን ፍቅሯ ስላደረበት ወደ ክርስትናው ሃይማኖት ይበልጥ ተሳበ፡፡ የዕንባቆም የዘወትር ጸሎት ‹‹ወደ ዕውነተኛው ሃይማኖት ምራኝ›› የሚል ሆነ፡፡ አንድ ቀንም በክረምት ወደ ዠማ ወንዝ ወርዶ ሳለ በአንድ ጎልማሳ የተመሰለ ቅዱስ ተገለጠለትና የውኃውን ሙላት በተአምራት አሻግሮ ‹‹በዚህች መንገድ ሂድ›› ብሎ ካሳየው በኋላ ተሰወረው፡፡ ዕንባቆምም መንገዱን ይዞ ሲጓዝ ደገኛው አባ ጴጥሮስ ካለበት ገዳም ደረሰ፡፡ በገዳሙም ማረፊያ ሰጥተውት በዚያ ተቀመጠና ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተማረ፡፡ ከዚህም በኋላ መጠመቅ እንደሚፈልግ ለአባ ጴጥሮስ ነገራቸውና አጥምቀው ስመ ጥቀቱን ዕንባቆም አሉት፡፡ ዳግመኛም በዚሁ ገዳም መነኮሰ፡፡ አባ ጴጥሮስም ከጳጳሱ ከአቡነ ማርቆስ በተገናኙ ጊዜ ስለ አባ ዕንባቆም ነገሯቸው፡፡ ጳጳሱም አባ ዕንባቆምን አስጠርተው በዐረብኛ ቋንቋ የተጻፈን ወንጌል እንዲያነብላቸው ሰጡት፡፡ እርሱም በድንብ አነበበላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ዲቁና ሰጡትና በቤታቸው አስቀመጡት፡፡ በዚህም ጊዜ ለጳጳሱ የሶርያን፣ የቅብጥን፣ የዕብራይስጥንና የአርመንን ቋንቋዎች ከነጽሕፈታቸው አስተማራቸው፡፡ ጳጳሱም ቆይተው ቅስና ሾሙት፡፡ አባ ዕንባቆም አንዱን የካቶሊክ እምነት ተከታይ ተከራክሮ ሲያሳምነው ጳጳሱ ተመልክተው በዚህ ደስ ተሰኝተው ከአንግብጦን ወረዳዎች ጢቆ በምትባል አገር ላይ ሾመው ላኩት፡፡ እርሱም በዚያ በእመቤታችን ስም የተዋበች ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ስሟን ቤተልሔም አላት፡፡ ዜናውም በሁሉ ዘንድ መሰማት ጀመረ፡፡ የአባ ዕንባቆም የዘወትር ጸሎት መዝሙረ ዳዊት፣ መኅልየ ሰሎሞን፣ ወንጌለ ዮሐንስ፣ ውዳሴ ማርያምና አርጋኖን ነበሩ፡፡ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳት ራእይ ተገልጦላቸው አባ ዕንባቆምን ‹‹የደብረ ሊባኖስ አለቃ ትሆናለህ ነገር ግን መነኮሳቱ ከንጉሡ ጋር ያጣሉሃል›› ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ከዚህ ሹመትና የሰይጣን ፈተና ሸሽቶ ወደ ምድረ ግብጦን ሄዶ የሐብላሽ በምትባል ገዳም ተቀመጠ፡፡ ‹‹አቤቱ የገዳም አስተዳዳሪ ከመሆን ጠብቀኝ›› እያለ በመጸለይ በዚህች ገዳም 3 ዓመት ተቀመጠ፡፡ ነገር ግን የትሩፋቱ ዜና በእንደግብጦንና በዳሞት ተሰማ፡፡ ወደ ላሊበላም ተጉዞ ከዋልድባ መነኮሳት ጋር በመገናኘት ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቁርጥ አሳብ አድርጎ ሳለ መነኮሳቱ ‹‹ይህ አይሰምርልህምና ወደ ደብርህ ተመለስ›› ብለው መከሩት፡፡ እርሱ ግን ሳይመለስ ቅጻ ወደምትባል ሥፍራ ሄዶ በአንድ ገዳም ተቀምጦ የተለያዩ ተአምራትን እያደረገ ተቀምጦ ሳለ በደዌ ተያዘ፡፡ በቤተ ክርስቲያንም ሳለ የታዘዘ መልአክ ተገለጠለትና ‹‹ወደ ደብርህ ሂድ›› አለውና ደብረ አንጎት አደረሰው፡፡ በዚያም አባ በትረ ማርያምን አገኛቸው፡፡ እርሳቸውም ወደ ደብሩ እንዲመለስ ስለመከሩት ወደ ደብረ ሊባኖስ ተጉዞ ከአባ ጴጥሮስ ጋር በድጋሚ ተገናኘ፡፡ እርሳቸውም ‹‹ከእንግዲህስ ወዲህ ወዲያ አትበል፣ የሞቴም ጊዜ ደርሷልና አንተ በመንበሬ ተተክተህ ትሾማለህ፡፡ እንደእኔም ለብዙዎች አባት ትሆናለህ ነገር ግን መነኮሳት በከንቱ ወንጅለውህ ንጉሡ ያሥርሃል፣ ትሰደዳለህም›› ብለው ትንቢት ነገሩት፡፡
አባ ጴጥሮስም ባረፈ በ40ኛው ቀን መነኮሳቱ ተሰብስበው ዕጣ ቢጥሉ ለአባ ዕንባቆም ስለወጣ በእጨጌነት ሾሙት፡፡ ወዲያውም ሴቶችና ወንዶች መነኮሳትን በመልክ እንኳን እንዳይተያዩ በማድረግ እያስተማረ አገልግሎቱን ሲያከናውን ፈቃደ ሥጋቸውን ማሸነፍ የተሣናቸው መነኮሳት ‹‹ክብርህን ያሳንሳል፣ ስለአንተም አይጸልይም፣ እንዲያውም ‹ንጉሡ በአሳርና በመከራ ይሞታል› እያሉ ይናገራሉ›› ብለው በሐሰት ለንጉሡ በመንገር አጣሏቸው፡፡ ክፉዎችም በወጠኑት ሴራ ጻድቁ በንጉሡ ፊት ለፍርድ ቀረቡና ብዙዎቹ ‹‹ይገደሉ›› ብለው ፈረዱባቸው፡፡ ነገር ግን የዐፄ ልብነ ድንግል እንደራሴ ‹‹ከምንገድላቸው አስረን በግዞት ጉንጭ ወደሚባለው ቦታ እንውሰዳቸውና በዚያ ከሞቱ ይሙቱ›› ብሎ ሌላ ሀሳብ አቀረበ፡፡ ንጉሡም በዚህ ተስማምተው አቡነ ዕንባቆምን እጅና እግራቸውን አስረው እየደበደቡ አጋዟቸው፡፡
አቡነ ዕንባቆምም በግዞት ሆነው ሳለ ውኃ ሳይቀምሱ አንድ ዓመት ተቀመጡ፡፡ ከዚህም በኋላ እስከጎጃም ድረስ እየተዘዋወሩ ወንጌልን ሰበኩ፡፡ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትንም አነጹ፡፡ እስከ ምድረ ቢዘን ድረስም ወረዱ፡፡ በዚህም ጊዜ ግራኝ አህመድ ተነሥቶ ክርስቲያኖችን በግፍ መግደል አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል ጀመረ፡፡ አቡነ ዕንባቆም ለግራኝ በዐረብኛ ቋንቋ ደብዳቤ ጻፉለት፡፡
‹‹ክርስቲያኖችን አትግደሉ ተብሎ በቁርአን ተጽፎ እያለ አንተ ግን ለምን ትገድላለህ? አብያተ ክርስቲያናትንስ ለምን ታቃጥላለህ?›› ብለው ጻፉለት፡፡ ግራኝ አህመድም ደብዳቤአቸውን ካነበበ በኋላ ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ክርስቲያኖችን እንዳልገድል ቤተ ክርስቲያኖችንም እዳላቃጥል ከሚወጉኝ በቀር በክርስቲያን ላይ ክፉ እንዳልሠራ በአላህና ከሚስቶቹ በሦስቱ ጠለቅ ማልሁ›› ብሎ ተናገረ፡፡ ለአቡነ ዕንባቆምም ‹‹የክርስቲያን ሃይማኖት ከቁርአን የሚለይበትን መንገድ ትገልጽልኛለህና መጥተህ እየኝ›› ብሎ ልኮባቸው ነበር ነገር ግን አቡነ ዕንባቆም መንፈስ ቅዱስ ሳይፈቅድላቸው ቀርቶ ሳያገኙት ቀሩ፡፡ ዐፄ ልብነ ድንግል ሞቶ ልጁ ገላውዴዎስ ሲተካ አቡነ ዕንባቆምን ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ መልእክተኛ ላከባቸውና ሲመጡ ‹‹ስለ አህመድ ግራኝ ምን ባደረግ ይሻላል?›› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹የሥልጣንህ ሰይፍ ከአንገቱ ላይ ሆናለች፡፡ እኔም ወደ ጎጃም እሄዳለሁ፣ እከተልሃለሁ፣ በደንቢያ ላይም እንገናኛለን፡፡ ሐነፋውያን (የግራኝ ዘሮች) በእጅህ ይጠፋሉ፡፡ አንተም በመጨረሻ በእነርሱ እጅ በሰማዕትነት ታልፋለህ›› ብለው ይመጣ ዘንድ ያለውን ሁሉ በትንቢት ነገሩት፡፡
በትንቢታቸውም መሠረት ዐፄ ገላውዴዎስ ግራኝን ካጠፋው በኋላ በሌላ ጊዜ የግራኝ ተከታይ ኢማም ኑር ገላውዴዎስን ገደለው፡፡ የንጉሡ እኅት ወለተ ጊዮርጊስም ወደ አቡነ ዕንባቆም መጥታ ያመነኩሳት ዘንድ ስለለመነችው ሥርዓተ ምንኩናን ፈጸመላት፡፡ ከገላውዴዎስ ቀጥሎ ዐፄ ሚናስ ሲነግስ አቡነ ዕንባቆምን መጥተው እንዲባርኩት ለመናቸው፡፡ እርሳቸውም ከባረኩት በኋላ ወደ ደብረ ሊባኖስ እንዲመለሱ ለመናቸው፡፡ እርሳቸውም እምቢ ቢሉትም ከብዙ ልመና በኋላ እሺ ብለውት ወደ ደብረ ሊባኖስ ሲሄዱ ልጆቻቸው በደስታ ተቀበሏቸው፡፡ እርሳቸውም እያስተማሩና መልካም አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ አንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ በ137 ዓመታቸው ሚያዝያ 21 ቀን 1553 ዓ.ም በሰላም ዐረፉ፡፡ በአባቶቻቸውም መቃር ተቀበሩ፡፡ ዐፄ ሠርፀ ድንግልም በ1580 ዓ.ም የአቡነ ዕንባቆምን ገድል አጻፈላቸው፡፡ ይህ ታሪካቸውም ከዚሁ ገድላቸው ላይ የተቀዳ መሆኑን የ1990 ዓ.ም የካቲት/መጋቢት እትም ሐመር ትገልጻለች፡፡
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages