ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 16 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 27, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 16

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሰኔ ዐሥራ ስድስት በዚች ዕለት የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገለጠለት ሕፃኑንና እናቱንም ይዞ ወደ እስራኤል አገር እንዲመለስ አዘዘው፣ የከበረ በገዳም የሚኖርና በገድል የተጠመደ አባት የላይኛው ግብጽ ሰው አባ አቡናፍር አረፈ፣ የቅዱሳን አበው ባሕታውያን መታሠቢያ ናት::
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ተዝካረ ሚጠታ ለእግዝእትነ ማርያም
ሰኔ ዐሥራ ስድስት በዚች ዕለት የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገለጠለት ሕፃኑንና እናቱንም ይዞ ወደ እስራኤል አገር እንዲመለስ አዘዘው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ አቡናፍር ገዳማዊ
በዚች ዕለት መልካም ሽምግልና ያለው ስም አጠራሩ የከበረ በገዳም የሚኖርና በገድል የተጠመደ አባት የላይኛው ግብጽ ሰው አባ አቡናፍር አረፈ። የዚህንም አባት ገድል የተናገረ አባ በፍኑትዮስ ነበር እርሱ ቁጥሩ ከገዳማውያን ነውና።
አባ በፍኑትዮስም ወደ በረሃ ውስጥ በገባ ጊዜ አንዲት የውኃ ምንጭና አንዲት የሰሌን ዛፍ አግኝቶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ ዘመን ኖረ።
በአንዲት ዕለትም አባ በፍኑትዮስ ወደርሱ ሲመጣ አባ አቡናፍርን አየው ፈርቶም ደነገጠ የሰይጣን ምትሐት የሚያይ መስሎታልና ይህም አባት አቡናፍር ልብስ አልነበረውም ጸጉሩና ጽሕሙ ሥጋውን ሁሉ ይሸፍናሉ አባ በፍኑትዮስንም በላዩ በመስቀል ምልክት አማትቦ አጽናናው በፊቱም አቡነ ዘበሰማያትን ጸለየ ከዚህም በኋላ አባ በፍኑትዮስ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው አለው ይህንንም በማለቱ ከእርሱ ፍርሃቱን አራቀለት።
ከዚህ በኋላ ሁለቱም በአንድነት ጸለዩ የእግዚአብሔርንም ገናናነት እየተነጋገሩ ተቀመጡ። ከዚህም በኋላ ወደዚህ በረሀ ከዓለም አወጣጡ እንዴት እንደሆነ ከዚያም በረሀ አኗኗሩ እንዴት እንደሆነ ይነግረው ዘንድ አባ በፍኑትዮስ አባ አቡናፍርን ለመነው።
አባ አቡናፍርም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ ደጋጎች ዕውነተኞች መነኰሳት በሚኖሩበት በአንድ ገዳም እኖር ነበር የገዳማውያንን ልዕልናቸውን ሲናገሩ ሲያመሰግኑአቸውም ሰማሁ እኔም ከእናንተ የሚሻሉ አሉን አልኳቸው እነርሱም አዎን እነርሱ በበረሀ የሚኖሩ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበሩ ናቸው እኛ ለዓለም የቀረብን ስለሆን ብንተክዝና ብናዝን የሚያረጋጋን እናገኛለን ብንታመም የሚጠይቀንና የፈለግነውን ሁሉ እናገኛለን በበረሀ የሚኖሩ ግን ከዚህ ሁሉ የራቁ ናቸው አሉኝ።
ይህንንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልቤ እንደ እሳት ነደደ መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ የፈቀደውን ይመራኝ ዘንድ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ተነሥቼ ጸለይኩ። ትንሽ እንጀራም ይዤ ተጓዝኩ አንድ ጻድቅ ሰውም አግኝቼ የገዳማውያንን ገድላቸውንና ኑሮአቸውን እያስተማረኝ በእርሱ ዘንድ ኖርኩ።
ከዚህም በኋላ ወደዚህ ደረስኩ እግዚአብሔርም ያዘጋጀልኝን ይቺን ሰሌን አገኘኋት በየዓመቱም ዐሥራ ሁለት ዘለላ ታፈራለች ለየወሩም የምመገበው አንዱ ዘለላ ይበቃኛል ውኃም ከዚች ምንጭ እጠጣለሁ በዚችም በረሀ እስከ ዛሬ ስልሳ ዓመት ኖርኩ ከቶ ያላንተ የሰው ፊት አላየሁም አለኝ።
ይህንንም ሲነጋገሩ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እነርሱ ወረደ ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም ሰጣቸው። ከዚያም በኋላ ከሰሌን ፍሬ ጥቂት ምግብ ተመገብን። ያን ጊዜም የቅዱስ አባ አቡናፍር መልኩ ተለወጠ እንደ እሳትም ሆነ በእግዚአብሔርም ፊት ተንበርክኮ ሰገደ ለአባ በፍኑትዮስም ሰላምታ ሰጠው ያን ጊዜም ነፍሱን በጌታ እጅ ሰጠ። ቅዱስ በፍኑትዮስም በጸጉር ልብስ ገንዞ በዚያች ቦታ ቀበረው።
ከዚህም በኋላ አባ በፍኑትዮስ በዚያች ቦታ ይኖር ዘንድ አሰበ በዚያን ጊዜ ያቺ የሰሌን ዛፍ ወደቀች የውኃውም ምንጭ ደረቀ። ቅዱስ አባ በፍኑትዮስ ወደ ዓለም ተመልሶ የገዳማውያንን ዜና ይልቁንም የቅዱስ አባ አቡናፍርን ዜና ይሰብክ ዘንድ ይህ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አበው ቅዱሳን ባሕታውያን
ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱሳን አበው ባሕታውያን መታሠቢያ ናት። ከሰው (ከዓለም) ርቀው፣ ንጽሕ ጠብቀው፣ ዕጸበ ገዳሙን፣ ግርማ አራዊቱን፣ ጸብዐ አጋንንትን ታግሠው የኖሩ ስማቸውን የምናውቀውንም ሆነ የማናውቃቸውን እንድናከብራቸው ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና በዓል ሠርታለች።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይህን እኛንም ስለ እናቱ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መከራና ስደት ይቅር ይበለን ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages