ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 17 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 27, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 17

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሰኔ ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን የብጹዕ አባ ገሪማ መታሰቢያው ሆነ፣ ታላቁ አባት አባ ለትጹን አረፈ፣ ፍጹም መናኒ የሆነ የመጻተኛው ባሕታዊ ጳላሞን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ገሪማ
ሰኔ ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን የመደራው የብፁዕ አባ ገሪማ መታሰቢያው ሆነ። የዚህም ቅዱስ አባቱ የሮም ንጉሥ ነበር ስሙም መስፍንያኖስ ይባላል። የንግሥት እናቱ ስምም ሰፍንግያ ነው እርሷም መካን ስለሆነች በእናቱ በቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም አማላጅነት በመማፀን ወደ እግዚአብሔር እየለመነች ኖረች።
ከዚህ በኋላ ይህን የተባረከ ልጅ ተቀበለች ስሙንም ይስሐቅ ብላ ጠራችው። ጥቂት በአደገ ጊዜም የቤተክርስቲያን ትምህርት አስተምረው ዲቁና አሾሙት። አባቱ በሞተ ጊዜ የሮም ሰዎች በአባቱ ዙፋን ላይ አነገሡት እየፈረደና በቅን እየገዛ ሰባት ዓመት ኖረ።
በዋሻ የሚኖረው አባ ጰንጠሌዎንም በሰማ ጊዜ እንዲህ ብሎ ወደርሱ ላከ ልጄ ይስሐቅ ሆይ ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታኖችን ተዋቸው አንተ ግን ክብር ይግባውና የክርስቶስን የማያልፍ መንግሥት ትሻ ዘንድ ወደ እኔ ና።
አባ ገሪማም መልእክቱ ደርሶት በሰማ ጊዜ መንግሥቱን ትቶ በሌሊት ወጥቶ ሔደ ያንጊዜም ጌታ የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጠለት ብርሃናውያን በሆኑ ክንፎቹም ተሸክሞ የዐሥር ወር የሚሆነውን መንገድ በሦስት ሰዓት አደረሰው በአባ ጰንጠሌዎንም ደጅ አቆመው ይህም በኢትዮጵያ ንጉሥ በእልአሚድ ዘመን ነበር።
አባ ጴንጠሌዎንም ቅዱስ ይስሐቅን በአየው ጊዜ ደስ ብሎት አቅፎ ሳመው ወደ በዓቱም አስገብቶ የምንኵስና ልብስን አለበሰው።ይስሐቅም በጾም በጸሎትና በስግደት ተጠምዶ ቆዳው ከዐፅሙ እስከሚጣበቅ ሲጋደል ኖረ።
ከዚህም በኋላ መደራ ወደተባለ ቦታ ሔደ በዚያም ድንቅና ተአምር እየአደረገ በሽተኞችን በመፈወስና አጋንንትን በማስወጣት ብዙ ዘመን ኖረ። በአንዲት ዕለትም በጥዋት ሥንዴ ዘራ በሠርክም አዝመራውን ሰብስቦ አስገባ ከእርሱም መሥዋዕትን አሳረገ። በማግሥቱም በግራር ዛፍ ላይ በሮችን አውጥቶ የሥንዴውን ነዶ አበራየ ሰባ ሰባት የእንቅብ መስፈሪያም ሆነ።
ሁለተኛም የወይን አረግ በአለት ላይ ተከለ ወዲያውም በቀለች አበበችና አፈራች በእርሷም መሥዋዕትን አሳረገ። አንዲት ቀንም ሲጽፍ መሸና ፀሐይ ሊጠልቅ ተቃረበ በቦታውም እንዲቆም አዘዘው ጽሕፈቱንም እስቲጨርስ ቆመ።
ምራቁንም ትፍ ባለበት ዘንድ እስከ ዛሬ ለበሽተኞች ፈውስ ሆኖ ይኖራል። ከእጁም ብርዕ በወደቀ ጊዜ ወዲያው በቀለ አቈጥቍጦም አደገ። በአንዲት ዕለትም ሰዎች ወደ አባ ጰንጠሌዎን መጥተው ቀሲስ ይስሐቅ እኮ ከበላ በኋላ የቍርባን ቅዳሴ ቀደሰ ብለው ነገሩት አባ ጴንጠሌዎንም ወደርሱ ሒዶ ልጄ ይስሐቅ ሆይ ምሥጢር ስለ አለኝ ከአጠገባችን ሰዎችን አስገልል አለው ይስሐቅም ሰዎችን ተውና ዕንጨቶችና ድንጋዮችም ይገለሉ አለ። ወዲያውኑም ዕንጨቶችና ድንጋዮች አንድ ምዕራፍ ያህል ሸሹ። አባ ጰንጠሌዎንም ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ አለ ስለዚህም ከዚያች ጊዜ ጀምሮ ገሪማ ተባለ።
መልካም ተጋድሎውንና የቀና አካሔዱን በፈጸመ ጊዜ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍና ለሚያጽፍ ለሚያነበውና ለሚተረጉመው ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው ዳግመኛም የተራበውን ላበላ የተጠማውንም ላጠጣ እኔ የሕይወት እንጀራን እመግበዋለሁ የድኅነት ጽዋንም አጠጣዋለሁ አለው።
በቤተ ክርስቲያንህም በማኅሌት ያመሰገነውንና የጸለየውን እኔ የመላእክትን ምስጋና አሰማዋለሁ የተራቈተውንም ለሚያለብስ የብልህ እጅ ያልሠራው የብርሃን ግምጃን አለብሰዋለሁ ነፍሱም ከሥጋው በምትለይ ጊዜ የጨለማ መላእክት አይቀርቡትም። የብርሃን መላእክትንም በዚሪያው አቆማቸዋለሁ።
በስምህም ቤተ ክርስቲያን ለሠራ በሰማያት አርባ ሰባት የብርሃን ቦታዎችን እኔ እሰጠዋለሁ ለቤተ ክርስቲያንህ መባ የሚሰጠውንም እኔ በመንግሥቴ እቀበለዋለሁ። ቦታህን የሚያከብረውንም እኔ በመንግሥቴ አከብረዋለሁ ጠላቶች አጋንንትን ረግጦ የሚገዛበትንም እሰጠዋለሁ።
አባ ገሪማም ይህን ታላቅ ሀብት በቸርነትህ ብዛት የሰጠኸኝ አቤቱ ስምህ ይክበር ይመስገን ግን ጌታዬ ሆይ መታሰቢያዬን ላደረገ ገድሌንም ለጻፈ እስከ ስንት ትውልድ ትምርልኛለህ አለ። መድኃኒታችንም እስከ ዐሥራ ሁለት ትውልድ እምረዋለሁ አለው አባ ገሪማም መድኃኒታችንን ልጆች ባይኖሩትስ ምን ታደርግለታለህ አለው። መድኃኒታችንም ዐሥራ ሁለት ዕጽፍ ክብር እሰጠዋለሁ ብሎ መለሰለት።
ዳግመኛም የሞት ጥላ እንደማያገኝህ ታላቅ የምሥራች እነግርሃለሁ አለው። ይህንንም ተናግሮ ሰላምታም ሰጥቶት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ቅዱስ አባ ገሪማም በልቡ ደስ ተሰኘ ወዲያውኑም በብርሃን ሠረገላ ተነጥቆ ብሔረ ሕያዋን ገባ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ለትጹን
ዳግመኛም በዚች ቀን ታላቁ አባት አባ ለትጹን አረፈ። ይህም አባት ከብህንሳ አገር ነበር ጐልማሳ በነበረ ጊዜም “ነፍሱን ሊያድናት የሚሻ ይጣላት ነፍሱን ስለ እኔ የጣላትም ያገኛታል ለዘላለም ሕይወትም ይጠብቃታል” የሚለውን በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጻፈውን የሕያው ንጉሥን ቃል ሰማ ወዲያውኑ ልቡ ስለ እግዚአብሔር ፍቅርና ስለ ዘላለማዊ ተድላ እንደ እሳት ነደደ።
ቅዱስ ቁርባንንም ተቀብሎ እስዋሕት ወደሚባል ገዳም ሔደ በጾም በጸሎትና በስግደት ታላቅ ተጋድሎን ያለ ማቋረጥ ይጋደል ጀመር ሰባት ሰባት ቀንም ይጾም ነበረ። የእግዚአብሔርም መልአክ ተገለጸለትና የምንኵስና ልብስን ያለብሰው ዘንድ ወደ አባ ኤስድሮስ እንዲሔድ አዘዘው እርሱም መልአኩ እንዳዘዘው ሔደ አባ ኤስድሮስም በልብሱና በአስኬማው ላይ አርባ ቀኖች ጸለየ ከዚያም በኋላ ልብሱንና አስኬማውን አለበሰው በገድል መጠመድን ጨመረ።
ከዚህም በኋላ በመምህሩ ፈቃድ ወጥቶ እየተጋ እየጾመና እየተጋደለ ብቻውን ኖረ። ከእርሱም አቅራቢያ የሆነ አንድ ገዳም ነበረ የገዳሙን መነኰሳትም ይጐበኛቸው ነበር። በአንዲት ዕለትም ወደዚያ ገዳም ሔደ አበ ምኔቱንም ታሞ ለሞት ደርሶ አገኘው መነኰሳቱም በዙሪያው ሆነው ያለቅሱ ነበር። አባ ለትጹንም የሰይጣን ሠራዊትን ከበውት ደስ ሲላቸው አያቸው።
አባ ለትጹንም አባት ሆይ በአንተ ላይ የሆነው ምንድን ነው ብሎ አበ ምኔቱን ጠየቀው እርሱም መነኰሳቱን ከአጠገቡ እንዲርቁ አዘዛቸው።
ከዚህም በኋላ ያደረገውን በደሉን ሊነግረው ጀመረ እንዲህም አለው ከእኔ አስቀድሞ እንደርሱ ያለ ማንም ያልሠራው ኃጢአትን ሠርቻለሁና አባቴ ሆይ በጸሎትህ አትርሳኝ እኔ ቅስና ልሾም ፈልጌ ባልሾሙኝ ጊዜ ወደ ሌላ አገር ሔድሁ ኤጲስቆጶሱም ቅስና ሹሞኛል ብዬ በድፍረት በቁርባኑ ላይ የምቀድስ ሆንኩ። ለጠላሁትም በቍርባኑ መሥዋዕት ውስጥ መርዝ አድርጌ አሰጠዋለሁ እርሱም ይሞታል ከእናቴም ጋራ ዐሥር ጊዜ ተኝቼ አለሁ ከእኔም ፀንሳ ለመውለድ በደረሰች ጊዜ ሥራይ አጠጥቼ ሕፃኑን በሆድዋ ውስጥ ገደልሁት ኃጢአቴ ብዙ ነው ተነግሮ አያልቅም። ከበጎ ሥራም ምንም ምን የሠራሁት የለም ነገር ግን በጸሎትህ አትርሳኝ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም መውጫዬ ደርሷልና ወዲያውም በክፉ አሟሟት ሞተ ነፍሱንም አጋንንት ሲቀበሏትና በየራሱ በሆነ ሥቃይ ሲአሠቃይዋት አባ ለትጹን አያት። አባ ለትጹንም ልቅሶን አለቀሰ።
አባ ለትጹን “ስለ ወዳጆቹ ነፍሱን አሳልፎ የሚሰጥ ያለ ከሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም” የሚለውን የቅዱስ ወንጌልን ቃል አሰበ። አባ ለትጹንም ስለዚህ ኃጥእ ሰው ነፍስ ክብር ይግባውና ጌታችንን እየለመነ አምስት ጊዜ እስከሚሞት ሰውነቱን ሊአሠቃያት ጀመረ።
የመላእክት አለቃ ሚካኤልም መጥቶ አስነሣውና እንዲህ አለው ስለዚያ ኃጢአተኛ ነፍስ ንፍስህን አትግደል ምሕረት አይገባውምና እግዚአብሔር ዕውነት ፈራጅ ስለሆነ በደሉ አይሠረይለትም አባ ለትጹን ግን መሐሪ ይቅር ባይ ወደ ሆነ እግዚአብሔር ስለዚያ ኃጢአተኛ እየለመነ ራሱን ማሠቃየት አልተወም።
ከዚህም በኋላ ራሱን በባሕር አስጥሞ ሞተ ያን ጊዜም ታላቅ ነጐድጓድ ሆነ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ በባሕሩ ዳር ተቀመጠ ከባሕርም አውጥቶ ከሞት ያድነው ዘንድ ሚካኤልን አዘዘው እርሱም አድኖ ክብር ይግባውና በጌታችን ፊት አቆመው።
ጌታችንም የመረጥሁህ ለትጹን ሆይ ኃጢአቱ እጅግ ብዙ ስለ ሆነ ከኃጢአተኞች ሁሉ በደል ስለሚከፋ ምሕረት ስለማይገባው ስለዚያ ኃጢአተኛ ብዙ ጊዜ ነፍስህን ለምን ትገድላለህ አለው። አባ ለትጹንም እንዲህ ብሎ መለሰ መሐሪና ይቅር ባይ ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ ያን ኃጢአተኛ ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ ያለዚያ ነፍሴን ከእርሱ ጋራ ወደ ሥቃይ ውሰዳት።
ከዚህም በኋላ ጌታችን የዚያን ኃጥእ ነፍስ ያመጣት ዘንድ ሚካኤልን አዘዘውና አመጣት በከበሩ እጆቹም ዳሠሣት እንዳልተፈጠረችም አደረጋት። ይቺ ነፍስ አፈር ትሁን እንጂ ለሥቃይ ወይም ለሕይወት አትሁን አለ። አባ ለትጹንም ስለ ይቅርታውና ቸርነቱ ገናናነት መድኃኒታችንን ፈጽሞ አመሰገነው።
ከዚህም በኋላ ጌታችን አባ ለትጹንን የመረጥሁህ ለትጹን ሆይ በዕውነት እነግርሃለሁ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ በስምህ መባ ለሚአስገባ ወይም የተራበ ለሚያበላ የተጠማ ለሚያጠጣ የተራቆተ ለሚያለብስ ወይም ገድልህን ለሚጽፍ እኔ የሁሉንም ኃጢአታቸውን ይቅር እላለሁ ስማቸውንም በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ በጎ ዋጋቸውንም እሰጣቸዋለሁ ጌታችንም ይህንን ብሎ ወደ ሰማያት ዐረገ።
ቅዱስ አባ ለትጹንም እጅግ ደስ አለው ወደ በዓቱም ተመልሶ እየተጋደለ ብዙ ዘመን ኖረ። እግዚአብሔርንም አገለገለው። መልካም ገድሉንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ባሕታዊ ጳላሞን
በዚችም ዕለት ፍጹም መናኒ የሆነ የመጻተኛው ባሕታዊ ጰላሞን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ እርሱም ከተጋድሎው የተነሣ ሰይጣን እስከ ደከመ ድረስ በተራራ ላይ እግዚአብሔርን እያገለገለ በገድል ተጠምዶ የሚኖር ነበር። ይህ አባት በቀንና በሌሊት ያለቅስ ነበር እንጂ ከማንም ጋር ሳይነጋገርና ከቶ ሳይስቅ ለረጁምና ለብዙ ዘመናት ኖረ።
ሰይጣንም የሚአስቅ ነገርንና ጨዋታን ብዙ ጊዜ በላዩ ያመጣበት ነበር እርሱ ግን ፈገግ እንኳን አይልም ነገር ግን የሚተክዝ ነበር ክብር ይግባውና ልቡም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር የተመሠጠ ነበር።
ሰይጣንም በእርሱ ላይ ተቆጥቶ የሚአድነው ሆነ በአንዲት ቀንም አባ ጰላሞን የእጅ ሥራውን ሊሸጥ ተነሥቶ ሔደ ሲጓዝም ሰይጣን ጐዳናውን አሳተው ልቡንም መሠጠው እንጂ ያውቅ ዘንድ አልተወውም። ከሰባት ቀኖችም ፍጻሜ በኋላ አባ ጰላሞን ከረሀብና ከጥማት ብዛት የተነሣ በምድር ላይ ወደቀ ለመሞትም ደረሰ ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም እንዲጠፋ አልተወውም ነገር ግን ሰይጣንን ከእርሱ አርቆ አሳደደው።
አረጋዊ አባ ጰላሞንም በእርሱ የሆነውን በአወቀ ጊዜ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ ብሎ ጮኸ። ወዲያውኑም ጰላሞን ሆይ አትፍራ ከእንግዲህ ወዲህ ጠላት በአንተ ላይ ክፉ ሊሠራ አይችልም ነገር ግን ተነሥተህ ወደ ደቡብ ጥቂት ተጓዝ በዚያም በተራራው አጠገብ የሚኖር ስሙ ለትጹን የሚባል ሽማግሌ ጻድቅ ሰው ታገኛለህ እርሱም ስለ ስሜ ብዙ መከራ የተቀበለ ነው ያደረግኸውን ሁሉ ሰይጣንም እንዴት እንዳሳተህ ንገረው እርሱ ኃጢአትህ እስቲሠረይ ስለ አንተ ይጸልያልና የሚል ቃልን ሰማ።
ወዲያውኑም ብጹዕ አባ ጰላሞንም ተነሥቶ ከእጅ ሥራው ጥቂት ተሸክሞ አቤቱ በስምህ አድነኝ የሚለውን የዳዊት መዝሙር እስከ ፍጻሜው ዳግመኛም ስልሳ ሦስተኛውን መዝሙር እያነበበ ቃሉ ወደ አመለከተው ሔደ። ጌታችንም መርቶ ወደ ሽማግሌው አባ ለትጹን አደረሰው።
አባ ለትጹንም በአየው ጊዜ በደስታ ተቀብሎ ሰላምታ ሰጠው ወደ ተራራውም አወጣው ከጸለዩም በኋላ ተቀመጡ። አባ ጰላሞንም የመረረ ልቅሶን እያለቀሰ ሊነግረው ጀመረ ከትንሽነቱ ጀምሮ ሰይጣንም እንዳሳተው እንዲህ ብሎ ነገረው በአንዲት ዕለት የእጅ ሥራዬን ልሸጥ በግብጽ ገቢያ መንገድ ስጓዝ ሰይጣን መጥቶ ልቤን አዘነጋት መድኃኒቴ የሚሆነኝን የጌታዬ ኢየሱስንም ስም እጠራ ዘንድ አልተወኝም ዳግመኛም እንደ ንጉሥ ከተማ የታነፀች ውኃዎችና ተክሎች መልካሞች ዛፎች የአሏት ከተማን አሳየኝ የእጅ ሥራዬንም ልሸጥ ሳስብ ባሏ ብዙ ገንዘብ ትቶላት ሙቶ በምታዝን ሴት አምሳል ታየኝ። የእጅ ሥራህን እኔ እገዛሃለሁ ብላኝ ወደ ቤቷ አዳራሽ አስገባችኝ እንቅቦቹንም ከላዬ አውርዳ አኖረች እግሮቼንም አጠበች ባሮቿንም ማዕድ ያቀርቡ ዘንድ አዘዘቻቸው ከእርሷ ጋርም እበላ ዘንድ ብዙ ማለደችኝ በልተን ጠጥተንም ሰከርን።
ስንጨዋወትም ባሮቿ ሁሉም ወጡ ሁለታችን ብቻችንን ቀረን ያን ጊዜም ልቤ በዝሙት እሳት ተቃጠለ እግዚአብሔርንም መላእክቶቹንም ቢሆን አላሰብኩም በእርግጥ ከእርሷ ጋራ እንደሚተኛ ሆንኩ።
ከዚህ በኋላ በነቃሁ ጊዜ ብመለከት ምንም ነገር አላገኘሁም ሴትም ማዕድም ቤትም አታክልትም ቢሆን አላገኘሁም ነገር ግን ራሴን ከተራራው በታች አገኘሁ። እንዳልበላና እንዳልጠጣም ሆንሁ። እጅግም አለቀስሁ። ሰይጣንንም በሩቅ ቁሞ መጻተኛ ጰላሞን ሆይ ወዮልህ እንደዎፍ ላጠምድህ በአንተ ላይ በርትቻለሁና እያለ ሲዘብትብኝ አየሁት።
ነገሩንም ሰምቼ በመስቀል ምልክት በላዩ አማተብኩ ከእኔም ሸሸ። አሁንም አባቴ ለትጹን ሆይ በደሌን ይቅር ይለኝ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንድትለምንልኝ በቅድስናህ ተማፅኛለሁ ቅዱስ አባ ለትጹንም አይዞህ እግዚአብሔር ኃጢአትህን ይቅር እንደሚልህ አምናለሁ ብሎ መለሰለት።
ከዚህም በኋላ ተነሥቶ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ጸለየ ወደነርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ የታመናችሁ አገልጋዮቼ አትፍሩ ከእንግዲህ ወዲህ ጠላት በእናንተ ላይ አይበረታታም ጰላሞንም የሠራውን ኃጢአት በራሱ በሰይጣን ላይ አደረግሁ የጰላሞንን ኃጢአት ብቻ አይደለም ነገር ግን የሚፈትናቸውን ሰዎች ሁሉ ኃጢአታቸውን በሰይጣን በራሱ ላይ እመልሳለሁ።
ከዚህ በኋላ አባ ጰላሞን ከአባ ለትጹን በረከትን ተቀብሎ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ በዓቱ ሔደ ተጋድሎውንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሰኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages