ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 18 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 27, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 18

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሰኔ ዐሥራ ስምንት በዚች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ድምያኖስ አረፈ፣ የሰማዕቱ ቅዱስ ኤስድሮስ መታሰቢያው ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ድምያኖስ
ሰኔ ዐሥራ ስምንት በዚች ቀን ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ቁጥር አርባ አምስተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ድምያኖስ አረፈ።
ይህም አባት በአስቄጥስ በአባ ዮሐንስ ሐጺር ገዳም ከታናሽነቱ ጀምሮ መነኰሰ ዓሥራ ሰባት ዓመት ያህልም እየታጋደለ ኑሮ ዲቁና ተሾመ።
ከዚህም በኋላ በታርን ወደተባለ ገዳም ሔደ ይኸውም የአባቶች ገዳም ማለት ነው እርሱም በእስክንድርያ ምዕራብ ያለ ነው። እንደ ገዳማውያንም ገድል በውስጡ ተጠምዶ እየተጋደለ ኖረ።
ከእርሱ አስቀድሞ የነበረው አባ ጴጥሮስም ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ በሊቀ ጵጵስናው ሥራ የሚራዳውና በሥራው ሁሉ የሚአማክረው ስለ ቤተ ክርስቲያን ጥበቃ አዋቂ ሰው ፈለገ።
ይህንንም አባ ድምያኖስን ሰዎች በበጎ ሥራ ሁሉና በዕውቀቱ ያመሰግኑታል። ስለዚህም ወደርሱ ወሰደውና በሊቀ ጵጵስናው ሥራ እየተራዳው ከእርሱ ጋራ እንዲቀመጥ አደረገው እርሱም ትእዛዙን ተቀብሎ ከእርሱ ጋር ተቀመጠ ሰዎችም ሁሉ ወደዱት።
አባ ጴጥሮስም በአረፈ ጊዜ ኤጲስቆጶሳትና አዋቂዎች ሊቃውንት በአንድ ምክር ተስማምተው በእስክንድርያ ከተማ ይህን አባ ድምያኖስን ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ለአገልግሎትም ፅሙድ ሆነ በመልካም ሥራ ሁሉ ጸንቶ ኖረ።
ሁልጊዜም ድርሰቶችንና መልእክቶችን እየጻፈ ወደ ሀገሩ ሁሉና ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ይልክ ነበር።
በአስቄጥስም ገዳም በአባ መቃርስ ደብር ከነጣቂው ከሀዲ ወገን የሆኑ አርሲሳን የሚሉአቸው መናፍቃን ነበሩ እነርሱም በሚቈርቡበት ቀን በሌሊት ወይን ይጠጣሉ በማግሥቱም ቅዱስ ቊርባንን ይቀበላሉ።
እነርሱ ጌታችን በመጀመሪያ ኅብስቱን ከመፈተቱ በፊት በኋላም ኀብስቱን ከሰጣቸው በኋላ ሁለት ጊዜ ጽዋን እንደሰጣቸው በሉቃስ ወንጌል ተጽፎ ያለውን ምክንያት ያደርጋሉና።
ይህም አባት አባ ድምያኖስ ስሕተታቸውን ገለጠላቸው የፊተኛው ጽዋ የአለፈው የኦሪቱ ፋሲካ ምሳሌ እንደ ሆነም አስረዳቸው አዲሱ የአባቶቻችን ሐዋርያት ቀኖና ሕግ ግን የመድኃኒታችንን ሥጋውንና ደሙን የሚቀበል ሁሉ ከመብልና ከመጠጥ ይጠበቅ ዘንድ ከቊርባንም አስቀድሞ ምንም ምን እንዳይቀመስ ያዝዛል።
ከእርሳቸውም ውስጥ ከስሕተታቸው ተመልሰው ንስሐ የገቡና የታዘዙለት አሉ ያልተመለሱትን ግን አውግዞ ከምእመናን አንድነት ለይቶ አባረራቸው።
በዚህ በአባ ድምያኖስ ዘመንም የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎድሮስ አረፈ። በእርሱ ፈንታም የሥላሴን ስም ፈጽሞ የማያወሳ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ይላል እንጂ በልዩ ሦስትነት የማያምን መናፍቅ ሰው ተሾመ የከፋች ሃይማኖቱንም የምትገልጽ መልእክት ወደዚህ አባት ድምያኖስ ላከ።
አባት ድምያኖስም በአነበባት ጊዜ እጅግ አዘነ በመልእክቱ ውስጥ እግዚአብሔር አንድ ገጽ ብቻ እንደ ሆነ ያወሳል እንጂ የልዩ ሦስትነትን ስም የሚያወሳ አላገኘምና። ይህም አባት ድምያኖስ የሥላሴን በመለኮት አንድነታቸውን በገጽ፣ በአካልና በግብር ሦስትነታቸውን ከቅዱሳት መጻሕፍትም ጠቅሶ ለዚህም መናፍቅ መልእክት ጻፈለት ደግሞም እንዲህ አለው ለእግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ የነበረ ጥንትና ፍጻሜ የሌለው አካላዊ ቃል አካላዊ ሕይወት አለው።
ይህችም ምስጢርንና ዕውቀትን የተመላች መልእክት ለአንጾኪያ ሊቀ ጵጵስና ወደ ተሾመ ወደዚያ መናፍቅ በደረሰች ጊዜ ትርጓሜዋን ያውቅ ዘንድ የልቡ ድንቁርናና የአእምሮው ጉድለት አለቀቀውም። ነገር ግን በክህደቱ ጸና።
አባ ድምያኖስም ከዚህ መናፍቅ አንድነት ተለየ ማኀበሩንም በቅዳሴና በጸሎት ጊዜ ይህ ከሀዲ እስኪሞት ድረስ ለሃያ ዓመት ስሙን እንዳይጠሩ አዘዛቸው።
ይህም አባት ድምያኖስ በተግሳጾቹና በመልእክቶቹ መንጋውን እየጠበቀ አርባ ሦስት ዓመታት ያህል ከኖረና ወደ በጎ እርጅና ከደረሰ እግዚአብሔርንም ከአገለገለ በኋላ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
በዚችም ቀን የሰማዕቱ ኤስድሮስ መታሰቢያው ነው። ይህም ቅዱስ ከእስክንድርያ አገር ከከበሩ ከቤተ መንግሥት ወገኖች ውስጥ ነው አባቱም በብዙ ሠራዊት ላይ የተሾመ መኰንን ነው። ስሙም በደላዖን ነው የእናቱም ስም ሶፍያ ነው ሁለቱም ከክርስቲያን ወገን ናቸው ይህንንም ቅዱስ በወለዱት ጊዜ ኤስድሮስ ብለው ሰየሙት።
ከብዙ ወራት በኋላም ከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ የሚያደርገውን የኃጢአትና የበደልን ብዛት በአየ ጊዜ እርሱ ከመንግሥት ታላላቆች ውስጥ ስለሆነ ምስፍናውን ትቶ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋራ ገለል አለ። ስለ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጻተኞች በመሆን ከዚህ ዐላዊ ንጉሥ ፊት ሸሽተው ሳሙኤል ከሚባል ሰው ዘንድ ተሰባስበው በገዳም ተቀመጡ።
ከዚህ በኋላም ለጣዖታት እንዳይሰግዱ ከንጉሡ ሸሽተው ስለተሠወሩ ከሀድያን መጥተው በንጉሡ ዘንድ ነገር ሠሩባቸው። ወዲያውኑ አምስት መቶ ጭፍራ ልኮ ከፊቱ አስቀረባቸው።
ከእርሱ ዘንድ በመገለላቸውም ንጉሥ ጠየቃቸው እነርሱም እንዲህ አሉት። የክብር ባለቤት ክርስቶስን በተውከው ጊዜ ተውንህ ታላቅ ስንፍና አድርገህ ስተሃልና። በሰማ ጊዜም ተቆጥቶ የበደላዖንን አንገት ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም አገኘ። ቅዱስ ኤስድሮስን ግን ይመከር እንደሆነ ብሎ አሠረው ያንጊዜ ዐሥራ ሁለት ዓመቱ ነበር።
ከጥቂት ቀን በኋላም በአንገቱ የብረት ዛንጅርና ገመድ አስገብተው ከንጉሥ ፊት አቀረቡት። ንጉሡም አልፈራህምን ልብህስ ለመመለስ አልመከረምን ብሎ ጠየቀው። እርሱም እኔ የቀናች ሃይማኖቴን ትቼ ወደ ስሕተት አልመለስም አለው።
ያን ጊዜ አራቁተው ከምሰሶ ላይ ሰቅለው ደሙ እንደ ውኃ እስቲወርድ እንዲጨምቁት ንጉሥ አዘዘ። እናቱ ሶፍያም ከደሙ ወስዳ በንጉሡ ፊት ላይ ረጨች። እንዲህም አለችው ከሰው ሁሉ አንተ የተረገምክ ነህ እንዲሁ እኅቱ አፎምያም ደንጋዮችን አንሥታ ንጉሡንና መኳንንቶቹን ወረወረችባቸው። ንጉሥም ተቆጣና ከወገባቸው መካከል እንዲቆርጧቸው አዘዘ ቆርጠዋቸውም ምስክርነታቸውን ፈጸሙ አክሊልንም አገኙ።
ቅዱስ ኤስድሮስም ተሰቅሎ ሳለ በእናቱና በእኅቱ ላይ የሆነውን ይመለከት ነበር በወገቡም ላይ የእሳት ፍም ደፉበት ደግሞም ሆዱን ሠንጥቀው አንጀቱን አወጡ። በተራራ ላይም ጣሉት የሰማይ ወፎችና የዱር አራዊት አልቀረቡትም። መድኃኒታችንም ከሞት አስነሥቶ እንደ ቀድሞ ሕያው አደረገው።
ከዚያም ሒዶ በንጉሡ ፊት ቆመ ንጉሡም ከብረት ዐልጋ ላይ አውጥተው ከበታቹ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ። ሁለተኛም በብረት ላይ አስተኝተው አንጀቱ እስቲፈስ ድረስ ፈጩት ከዚህም መድኃኒታችን አስነሣው። ደግሞም ሁለተኛ ከስምንት መቶ ነፍስ ጋር ሰቀሉት ያንጊዜም መድኃኒታችን አድኖ አስነሣው።
ንጉሡም አይቶ በበሬ ቅርጽ በተሠራ ብረት ውስጥ አሥረው በላዩም ድኝና ዝፍት ጨምረው ከበታቹ እሳት እንዲአነዱ አዘዘ። ከጥቂት ቀን በኋላ ራሱን እንዲቆርጡት አዝዞ ቆረጡት ያንጊዜም ጌታችን ከሞት አነሣው እነሆ ሲያስነሣው ሦስተኛው ነው።
ደግሞ ከዚህ በኋላ እጅግ ከባድ የሆነ ደንጊያ በአንገቱ አሥረው ወደ ባሕር ጣሉት ወዲያውኑ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል አውጥቶ ከንጉሡ ፊት አደረሰው። ንጉሡም በከተማ መካከል እንዲሰቅሉት አዘዘ እንደዚህም ተሰቅሎ ሞተ። የክብር ባለቤት ጌታችንም አስነሣው ይህም ሲያሥነሣው አራተኛ ጊዜ ነው።
ከዚህም ለአንበሶች ጣሉት እግዚአብሔርም ነቢይ ዳንኤልን እንዳዳነ አዳነው። ከዚህም በኋላ በየጥቂቱ ቆራርጠው እንዲከትፉትና በእንቅብ ሰብስበው ወደ ባሕር እንዲጥሉት አዘዘ አሽከሮቹም እንዱሁ አደረጉ።
ያን ጊዜም የክብር ባለቤት ጌታችን ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋራ መጥቶ በባሕሩ ዳር ቆመ ከዚያም አውጥቶ አስነሣው። ያለ ምንም ጉዳት ይህም ከሞት ሲያስነሣው አምስተኛ ነው።
ንጉሡም በአፈረና የሚያደርገውም በተሳነው ጊዜ ከወገኖቹ ጋራ ተማክሮ በዚያ ያሠቃዩት ዘንድ እጅና እግሩን አሥሮ ወደ ሰሎንቅያ ሀገር ላከው። የሰሎንቅያ አገር ገዥም አስቀድሞ ስለ ሚያውቀው ከቅዱስ ኤስድሮስ ጋራ ቸርነትን ርኅራኄን አደረገ።
ንጉሡም ሰምቶ ተቆጣ ያንን መኰንንም እንዲአመጡት አዘዘ። ቅዱስ ኤስድሮስንም ወደ እርሱ መልሶ በእሥር ቤት በረኃብና በጽምዕ አኖረው ቅዱሱም በእሥራቱ መጠን ታላላቅ ድንቆች ተአምራትን እያደረገ በሽተኞችን ሁሉ አዳነ።
በዚችም በግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ ቀን በስድስት ሰዓት ከከተማ ውጭ እንዲሰቅሉት ንጉሥ አዘዘ። አየርም መላእክትን ተመላች የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብዙዎች ቃል ኪዳኖችን ከእርሱ ጋራ አደረገ። ያን ጊዜም ነፍሱን አሳለፈ። በማይጠፋ መንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊላትን ተቀበለ በተጋድሎ የኖረባቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመቶች ናቸው።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሰኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages