ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 27, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 19

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሰኔ ዐሥራ ዘጠኝ በዚች ቀን ሐዲስ ጊዮርጊስ ሰማዕት ሆነ፣ ሰማዕት በመሆን አባ ብሶይ አኖብ አረፈ፣ አምስቱ ቅዱሳን አርሶፎኒስ፤ ጴጥሮስ፤ አስኪርዮን፤ አርጌንዮስና፤ ቢልፍዮስ በሰማዕትነት ሞቱ
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ሐዲስ ጊዮርጊስ ሰማዕት
ሰኔ ዐሥራ ዘጠኝ በዚች ቀን ሐዲስ ጊዮርጊስ ሰማዕት ሆነ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም መዛሕዝም ነው ትርጓሜውም ድንገተኛ ማለት ነው። እርሱም እስላም ነበር ከግብጽ ደቡብ ድምራ ከሚባል አገር ክርስቲያን ሴት አግብቶ ከእርሷም ሦስት ልጆችን ወለደ ከሦስቱም አንዱ ይህ ቅዱስ ነው።
ከእናቱም ጋራ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሔድ ነበር ቅዱስ ቍርባንንም ይቀበል ዘንድ እናቱን ለመናት እርሷም ማንም የክርስትናን ጥምቀት ሳይጠመቅና ንጹሕ ሳይሆን ቍርባን ሊቀበል አይችልም አለችው።
ከዚህ በኋላም ከተረፈ መሥዋዕቱ ሰጠችው በጎረሳትም ጊዜ ጣዕሟ በአፉ ውስጥ እንደ ማር ሆነ የዚች የቁራሿ ጣዕም በአፌ ውስጥ እንዲህ የሆነ የዋናው የቍርባኑ ኅብስት ጣዕም ምን ያህል ይሆን ብሎ በልቡ አሰበ ከዚያች ጊዜ ጀምሮ ክርስቲያን ይሆን ዘንድ ወደደ።
በአደገም ጊዜ ክርስቲያን ሴት አገባ ክርስቲያን ይሆን ዘንድ መፈለጉንም ነገራት እርሷም ወደ ሌላ ሀገር ሒዶ የክርስትናን ጥምቀት እንዲጠመቅ መከረችው እርሱም ወደ ሌላ አገር ሔዶ ተጠመቀ ስሙንም ለውጦ ጊዮርጊስ ተባለ። እስላሞችም በአዩት ጊዜ ይዘው ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት ከዚያም አምልጦ ላፍጥ ወደሚባል አገር ሸሸ በዚያም ሦስት ዓመት ኖረ።
ወሬውም በተገለጠ ጊዜ ቀጡር ወደ ሚባል አገር ሒዶ የልዳዊው ሰማዕት የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን እያገለገለ ኖረ። ከዚህም በኋላ ወደ ሀገሩ ድምራ ተመለሰ እስላሞችም ሰሙ ይዘውም ለመኰንኑ ሰጡት የመኰንኑም ሚስት ክርስቲያን ነበረች ለመኰንኑም አታሠቃየው አለችው መኰንኑም አሥሮ በወህኒ ቤት ዘጋበት።
እስላሞችም ተሰበሰቡ የወህኒ ቤቱንም ደጅ ሰብረው ታላቅ ግርፋት ገረፉት አካላቱንም ቆራርጠው በሕይወትና በሞት መካከል ጣሉት ። ሲነጋም ክርስቲያኖች የሞተ መስሏቸዋልና ሊቀብሩት መጡ ነገር ግን በሕይወት አገኙት።
ከዚህም በኋላ እስላሞች ተሰብስበው ከዚህ ምክርህ ካልተመለስክ እኛ ጽኑ ሥቃይ አሠቃይተን እንገድልሃለን አሉት የመዛሕዝም ልጅ የከበረ ጊዮርጊስም ሰማይና ምድርን የፈጠረ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም የፈለጋችሁትን አድርጉ አላቸው። እጅግም ተቆጡ በመርከብ ምሰሶ ላይም ሰቅለው ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት መኰንኑም ከስቅላት አውርደው በእሥር ቤት እንዲአሥሩት አዘዘ እንደዚሁም አደረጉ።
ሚስቱም ታጽናናውና እንዲታገሥ ታደርገው ነበር ሰይጣንም እንዳያስተውና የደከመበትን ዋጋ እንዳያጣ በልቡ ወደ ክርስቶስ ያስብ ዘንድ ትመክረው ነበር። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸለትና አረጋጋው አበረታታውም ከሰማዕታትም ጋራ እንደ ተቈጠረ በማግሥቱም ራሱን በሰይፍ እንደሚቆርጡት ነገረው። በነጋም ጊዜ እስላሞች ወደ መኰንኑ ተሰብስብው ጊዮርጊስን ይሰጣቸው ዘንድ ፈለጉ መኰንኑም የወደዱትን ያደርጉበት ዘንድ እንዲሰጧቸው አዘዘ።
ከዚህም በኋላ ከእሥር ቤት አወጡት ድምራ በምትባል አገር በከበረ የመላእክት አለቃ በሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ራሱን በሰይፍ ቆረጡ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ከዚህ በኋላ በዚያች ቀንና በዚያች ሌሊት በሥጋው ላይ እሳትን አነደዱ እሳቱም በላዩ እየነደደ ምንም ምን አልነካውም ወስደውም በገቢያ ውስጥ ጣሉት ከዚያም አንሥተው በባሕር ውስጥ ጣሉት በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደ ደሴቱ ወደብ ዳር ደረሰ እናቱም ጠብቃው ነበረና ወስዳ ገነዘችው ለጥቂት ወራትም በቤቷ ውስጥ ሸሸገችው።
ከዚህም በኋላ ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠሩለት ሥጋውንም በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ታላላቅና ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ብሶይ አኖብ
ዳግመኛም በዚች ዕለት ሰማዕት በመሆን አባ ብሶይ አኖብ አረፈ፡፡ ትርጓሜውም የጠራ ወርቅ ማለት ነው። ይህም ቅዱስ ከድምያጥ አውራጃ ስሟ ባኖስ ከሚባል አገር ከአቅራብ መኰንን ከቆጵርያኖስ ጭፍሮች ውስጥ ከከተማዋ ታላላቅ ሰዎች ልጆች ወገን ነበር።በዚህም ቅዱስ በመኰንኑ ዘንድ ነገር ሠሩበት። ቅዱሱም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በፊቱ ታመነ።
ወደ አንዴናውም ወሰዱት በመኰንኑ አርያኖስም ፊት ቁሞ በጌታችን ታመነ አርያኖስም በእርሱ ላይ ተቆጣ ለአማልክትም ሠዋ አለው አልታዘዘለትም ሥቃዩንም አልፈራም መኰንኑም ወስዶ ጽኑዕ ሥቃይ አሠቃየው ከዚያም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡት አዘዘ ወደሚገድሉበት ቦታም ሊወስዱት አወጡት ብዙ ሕዝብም ይከተሉት ነበር እነሆ ከዚያም የአርያኖስ መኰንን አንበሶች ነበሩ። የሚጠብቃቸውም ሰው ነበር እነርሱም በብረት ሰንሰለት ታሥረው ነበር ከእነርሱም አንዱ አንበሳ የብረት ሰንሰለቱን በጥሶ ሩጦ ወደ ቅዱሱ ደረሰ። የእግዚአብሔርም መልአክ ቅዱሱን በአንበሳው ጀርባ ላይ አወጣውና ዐይነ ፀሐይ ወደሚባል አገር እስከሚያደርሰው በረረበት ቅዱሱ ግን ዐይኑን ሸፍኖ ስለ ነበረ ወዴት እንዳለ አላወቀም በዚያም ራሱን በሰይፍ ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱሳን አርሶፎኒስ፤ ጴጥሮስ፤ አስኪርዮን፤ አርጌንዮስና፤ ቢልፍዮስ
በዚችም ቀን አምስት ጭፍሮች በሰማዕትነት ሞቱ እሊህም አርሶፎኒስ፣ ጴጥሮስ፣ አስኪርዩን፣ አርጌንዮስና ቢልፍዮስ በዲዮስጲልዪስም ቅጽር ውስጥ ይኖሩ ነበር። መኰንኑም ለጣዖታት እንዲሠዉ በአስገደዳቸው ጊዜ እኛስ የንጉሣችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ እንፈጽማለን ለእርሱም እንሠዋለን አሉት መኰንኑም ሰምቶ ተቆጣ በአንድ ቤት ውስጥም እንዲዘጉባቸውና እስከ ሁለት ቀን እህል ውኃ እንዳይሰጧቸው አዘዘ።
ከዚያም በኋላ እንዲያመጧቸው አዘዘ በፊቱም በቆሙ ጊዜ ለአማልክት ሠዉ አላቸው እነርሱም በአንድ ቃል እኛስ ለፈጣሪያችን ለክርስቶስ እንሠዋለን ለረከሱ አጋንንት ግን አንሠዋም አሉት። አንገታቸውንም አሥረው ወደ ሌላ አገር ይወስዱአቸው ዘንድ አዘዘ።አርጌንዮስም ወንድሞቹን እኔ እውነትን እነግራችኋለሁ የእግዚአብሔር መልአክ አምስታችንንም በስማችን ሲጠራን ሰምቼዋለሁና አላቸው።
ዳክስ ወደሚባል መኰንንም በአደረሷቸው ጊዜ መኰንኑ አስቀድሞ አርሶፎኒስን ወስዶ ለአማልክት ሠዋ አለው እምቢ በአለውም ጊዜ በፈረስ ጅራት ላይ አሥረው በከተማ ውስጥ እንዲጐትቱትና እንዲአዞሩት አዘዘ። በመለሱትም ጊዜ በውሽባ ቤት ማንደጃ ውስጥ ፊቱን እንዲአጠወልጉት አዘዘ ሁለተኛም እስከ ሚጨነቅ ድረስ በሠረገላ ውስጥ አሥረው ቍልቍል ሰቀሉት ሃይማኖቱንም ጠብቆ ክብር ይግባውና ለጌታችን ነፍሱን ሰጠ።
ሁለተኛም ጴጥሮስን አቀረቡት ዳክስም ለአማልክት ሠዋ አለው ትእዛዙንም ባልተቀበለው ጊዜ እንዲአሠቃዩትና እንጨት ተክለው ዘቅዝቀው እንዲሰቅሉት አዘዘ ሁለተኛም ምድሩን ቆፍረው ከትከሻው በታች ቀብረው በቅሎዎችን በላዩ እንዲነዱበት አዘዘ ይህንንም እግዚአብሔር እየረዳው ታገሠ ከጉድጓዱም በእወጡት ጊዜ ከሥቃዩ ብዛት የተነሣ ሥጋው ጠወለገ መናገርም ተሣነው በግንድ ውስጥም አሥረው ጣሉት ።
ከዚህም በኋላ አርጌንዮስን እቀረቡት ዳክስም ለአማልክት ሠዋ አለው እምቢ ባለውም ጊዜ እስከሚገድሉት ድረስ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ ያለ መብልና መጠጥም በተበሳ ግንድ ውስጥ አሥረው ዘቅዝቀው ሰቀሉት።
ዳግመኛም እስኪርዪንን አቀረቡት ዳክስም ለራስህ እዘን በክፉ አሟሟትም እንዳትሞት ለአማልክት ሠዋ አለው እምቢ ባለውም ጊዜ እንዲያሠቃዩት እንዲሰቅሉትና ሥጋውን እንዲሰነጥቁት አዘዘ ወታደሮችም ተረከቡትና በጽኑ ሥቃይ አሠቃዩት በትዕግሥቱም በአሸነፋቸው ጊዜ ለመኰንኑ ነገሩት በረኃብና በጽምዕ ይሞት ዘንድ በግንድ ውስጥ አሥረው በባዶ ቤት እንዲዘጉበት አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት።
ደግመው ዲያቆን ቢልፍዮስን አቀረቡት መኰንን ዳክስም እንዳትሞት ለአማልክት ሠዋ አለው ባልሰማውም ጊዜ እስከሚገድሉት ድረስ እንዲአሠቃዩት አዘዘ ሥጋውን ሠነጣጥቀው በከተማው አደባባይ ጐተቱት እንጨት ተክለውም ቍልቍል ሰቀሉት በአንገቱም ከባድ ደንጊያ አንጠለጠሉ ከሃይማኖቱም ባልተናወጸ ጊዜ በረኃብና በጽምዕ እንዲሞት በግንድ ውስጥ አሥረው በላዩ መዝጊያ ሠርተው ዘጉበት።
በየዕለቱም ወንድሞች ምእመናን ከውጭ ሆነው ይጐበኙት ነበር ጳሔን የተባለው የሰኔ ወር በባተ በሠላሳ ጴጥሮስ ነፍሱን ሰጠ።እርሱንም አውጥተው ደጁን በሌሎቹ ላይ ዘጉ። የከበረ አርጌንዮስም ከአምስት ቀን በኋላ አረፈ እርሱን አውጥተው በቀሩት ላይ ደጁን ዘጉ። ብፁዕ አስኪርዮንም ከዐሥራ ሁለት ቀን በኋላ አረፈ። እርሱንም አውጥተው በቅዱስ ቢልፍዮስ ላይ ደጃፍ ሠርተው ዘጉበት እርሱም የሚያርፍበት ቀን ስትደርስ ወንድሞቼ ታገሡኝ በዚች ሌሊት እወጣለሁና አላቸው። ከዐሥራ ዘጠኝ ቀን በኋላም በዚያች ሌሊት ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሰኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages