ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, June 5, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 19

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ዕለት የዓለም ብርሃን የሆነ አባ ዮሴፍ አረፈ፣ የከበረ አባት አባ ዐብየ እግዚእ መታሰቢያው ነው፣ የከበሩ አባት የሐይቁ አቡነ ብስጣውሮስ ዕረፍታቸው ነው፣በዚህችም ቀን የአቡነ ዮሴፍ ዘአክሱም ልደታቸውና ዕረፍታቸው ነው፣ ከአባ መቃርስ ገዳም ቅዱስ አባት ቀሲስ ይስሐቅ አረፈ፣ኃይለኛ ተጋዳይ ቅዱስ ኤስድሮስ በሰማዕትነት አረፈ።


አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም
ግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ዕለት የዓለም ብርሃን የሆነ በወሎ ላስታ ሰውንና ዝንጀሮን በቃልኪዳን ያስተሳሰሩትና እመቤታችን ዕጣን እየሰጠቻቸው ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥላሴን መንበር ያጠኑት የእንጂፋቱ አቡነ ዮሴፍ ዕረፍቱ ነው።
ተአምረኛው ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ዮሴፍ ዘእንጂፋት አባቱ ንጉሡ ዐፄ ዳዊት እናቱ ዳግም ሞገሳ ይባላሉ፡፡ ትውልድ ሀገሩ ወሎ መቄት እንጂፋት ነው፡፡ ሲወለድ በርካታ ሙታን ተነሥተዋል፡፡ ጻድቁ ያላየው የቅዱሳን ቦታ ያልተሳለመው ገዳም የለም፡፡ በወሎ ላስታ ሰውንና ዝንጀሮን በቃልኪዳን ያስተሳሰረ ታላቅ አባት ነው፡፡
ይህም ቅዱስ ያዩትና የሰሙት እስቲአድንቁት ድረስ በአባቱ ቤት ሳለ የዚህን ዓለም ጥበብ ሁሉ ተማረ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት ተረጐመ ከዚህም በኋላ ዲቁና ሾሙት።
የነፍሱንም ድኅነት እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ ብርሃናዊ መልአኩን ሚካኤልን ላከለትና ዮሴፍ ሆይ ይህን ኃላፊውን ዓለም ትወደዋለህን? አስጸያፊ አይደለምን በውስጡም ያለው ሁሉ አለው። ከዚያችም ጊዜ ጀምሮ እርሱ የመረጠውን መንገድ ይመራው ዘንድ እግዚአብሔርን እየለመነ ጾምና ጸሎትን ጀመረ።ከወለቃ አውራጃም ስሙ አባ ዘካርያስ የሚባል ነበረ እርሱም ለዮሴፍ ዘመዱ የሆነ በጭልታም ዮሴፍን ወስዶ የምንኲስና ልብስ አለበሰው። ወደ ትግራይ ምድርም ወሰደውና በዚያ ተግባረ እድ ለምንኲስና ሥራ የሚገባ ጽሕፈትን ስፌትን ተማረ።
ከዚህም በኋላ ወደ በረሀ ዱር ገብተው የእንጨት ፍሬ እየበሉ ከዝኆኖች ከአንበሶችና ከዘንዶዎች እየተፈተኑ በየአይነቱ በሆነ ተጋድሎ በመድከም ኖሩ። በጽድቃቸውም ኃይል ብዙ ተአምራትን አደረጉ አባ ናትናኤልም የጋለ ምንቸት በመሐል እጁ ይዞ በመነኰሳቱ ፊት ዞረ። አባ ዮሴፍም የሚያበስሉበት ማሰሮ በተሰበረ ጊዜ ወጡ ሳይፈስ አገናኝቶ እንደ ቀድሞው አደረገው።ገብር ኄርም ሕዝባዊ ሲሆን በሞተ ጊዜ ሊአጠምቁት ሲሉ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ኤጲስቆጶስነት ሹሞኛልና እኔ በእጄ አጠምቃችኋለሁ አላቸው።እሊህም ቅዱሳን የትሩፋታቸውንና የጽድቃቸውን የአማረ ሥራቸውን አሳዩ።
ከዚህም በኋላ አባ ዮሴፍን ወደ ጳጳስ ወሰዱትና ቅስና ተሾመ። አባ ዘካርያስም በአረፈ ጊዜ አባ ዮሴፍ ወደ ሌላ ገዳም ሒዶ ሳይቀመጥ ቁሞ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾመ። ከድካም ጽናትም በወደቀ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ አነሣው።
ሁለተኛም ከገደል አፋፍ እጁን ዘርግቶ ሳይሰበስብ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ቆመ። ሰይጣንም መጥቶ ወደ ቆላ ወረወረው የመላእክት አለቃ ሚካኤልም ተቀብሎ ወደ መቆሚያው መለሰው።
ደግሞም ከደንጊያ ዋሻ ውስጥ ገብቶ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ያለ መብልና ያለ መጠጥ ኖረ። ሰይጣናትም ወደርሱ እየመጡ በየራሳቸው ምትሐት በማሳየት ያስፈራሩት ነበር መላእክትም ያበረቱትና ያጸኑታል።ናላው በአፍንጫው እስቲፈስ ድረስ በየእልፍ እልፍ እየሰገደ ኖረ።
ከዚያም የትግራይን አውራጃዎች ሁሉ ዞረ። ወደ ሰሜንም ምድር ተሻግሮ ከያሬድ መቃብር ገባ በደጃፉም ላይ ተቀርጾ አግኝቶ አንቀጸ ብርሃንን ተማረ። ሲመለስም ሽፍቶች አግኝተውት በደንጊያ ወገሩት በበትርም ደበደቡት በጦርም ወግተው ጥለውት ሔዱ። አምላክን የወለደች እመቤታችንም ቅድስት ድንግል ማርያም ወደርሱ መጥታ አዳነችው። አንዲት ቀንም የሴት በድን አግኝቶ በላይዋ ባማተበ ጊዜ ተነሣች።
ወደ ኢየሩሳሌምም ሦስት ጊዜ ሒዶ ከከበሩ ቦታዎች ተባርኳል ወደ አባቶቻችን ሐዋርያት መቃብርም እስከ ሀገረ ባርቶስና ሕንደኬ ደረሰ። ውኃው ከመላበት ወንዝም በሚደርስ ጊዜ በላዩ አማትቦ እንደ የብስ በእግሩ እየረገጠ ይሻገረዋል።
አንበሶችና ነብሮች ይከተሉታል ምግብ በአጡ ጊዜ ደንጊያውን ባርኮ ሥጋ አድርጎ ይሰጣቸዋል። ከዚህ በኋላም ወደ አባታችን ተክለሃይማኖት ገዳም ደብረ ሊባኖስ ሔደ። ከአባ ተወልደ መድኅንም እጅ አስኬማ ተቀበለ አባ ተወልደ መድኅንም ሊፈትነው ወዶ ሰባት የጽድ ቅርንጫፍ ሰብሮ ትከለው ብሎ ሰጠው በተከላቸውም ጊዜ ወዲያውኑ በቅለው አደጉ እስከ ዛሬም አሉ።
ብዙዎችም ወደርሱ መጥተው በእርሱ እጅ መነኰሱ በእግዚአብሔር አብና አምላክን በወለደች በእመቤታችን ድንግል ማርያም ስም በአነፃቸው አብያተ ክርስቲያን በአንድነት ኖሩ። በአንዲት ዕለትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕጣንን ሰጠችውና ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋራ የአሸናፊ እግዚአብሔርን መንበር አጠነ።
ብዙ ጊዜም ወደርሱ ሐዋርያት እየመጡ ይባርኩታል። በአንዲት ዕለትም ነብር ከእናቱ እጅ ሕፃንን ነጥቆ ወሰደ በአባ ዮሴፍም ስም በአማጸነችው ጊዜ በሦስተኛው ቀን መለሰላት። ለልጆቹም ገንዘብም ሆነ የእንስሳ ጥሪት እንዳያደርጉ ሥጋ እንዳይበሉ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ ትሕትናን ቅንነትን እንዲማሩ ከንቱ ነገር ቧልትን እንዳይናገሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳይስቁ ይህ ሁሉና የመሳሰለውን ሥርዓትን ሠራላቸው።
ከዚህ በኋላም ሩጫውን በፈጸመ ጊዜ በሰላም በፍቅር አረፈ ደብረ ታቦር ብሎ በሰየማት ቤተ ክርስቲያንም ተቀበረ ከእርሱም ቁጥር የሌላቸው ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ጻድቁ አባ ዐብየ እግዚእ
በዚችም ዕለት የከበረ አባት አባ ዐቢየ እግዚእ መታሰቢያው ነው። አባታቸው ያፍቅረነ እግዚእ እናታቸው ጽርሐ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ሁለቱም ሃይማኖታቸው የቀና ምግባራቸው ያማረ በእግዚአብሔር የተወዱ ናቸው፡፡ በወርቅ በብር የከበሩ ቢሆኑም ልጅ ግን አልነበራቸውም፡፡ በእመቤታችን ስም ለተቸገሩ ምጽዋትን በመስጠት ዘወትር ይማጸኑ ነበር፡፡
አንድ ቀን ድንቅ የሆነ ራእይ አየና ፈቃደ እግዚአብሔርን ሲጠባበቁ ነሐሴ 7 ቀን ጽርሐ ቅዱሳን ፀነሰችና ግንቦት አንድ ቀን እንደ ፀሐይ የሚያበራ ልጅ ወለደችና በ40 ቀኑ ሲጠመቅ ስሙን ዓቢየ እግዚእ አሉት፡፡ ያጠመቁትም የአክሱሙ ሊቀ ጳጳስ መተርጉም ሰላማ ሲሆኑ እሳቸውን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሕጻኑን እንዲያጠምቁት በማዘዝ በክንፎቹ ተሸክሞ ከአክሱም ወደ ተንቤትን ምድረ መረታ አመጣቸውና አጠመቁት፡፡
እርሳቸውም ‹‹ይህ ሕጻን ድውይ የሚፈውስ ሙታንን የሚያነሣ ቅዱስ ይሆናል›› ብለው ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ያፍቅረነ እግዚእ እና ጽርሐ ቅዱሳን እንግዳን መቀበል ልማዳቸው ነበርና አንድ ቀን ሦስት አጋንንት በሽማግሌ አምሳል ሆነው በእንግድነት እቤታቸው ገቡና ‹‹ልጃችሁን የሐዋርያትን መጻሕፍትን መዝሙረ ዳዊትንና አርጋኖንን እንድናስተምርላችሁ ስጡን›› አሏቸው፡፡ ወላጆቹም ገና ሕጻን መሆኑን በመናገር ሲከራከሩ ቅዱስ ሚካኤል ደርሶ እነዚያን አጋንንት አጠፋቸው፡፡ አጋንንቱም ይህንን ዘዴ ተጠቅመው ሕጻኑን ዓቢየ እግዚእ ወስደው ሊገድሉት ነበር ምክንያቱም በእርሱ ምክንያት ነፍሳት እንደሚድኑ ዐውቀዋልና፡፡
ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ የእግዚአብሔርን ከጠሩበት ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይልም ነበር፡፡ ከልጆችም ጋር ሲጫወቱ ልጆቹ ‹‹ስለ እግዚአብሔር ብለህ ይህን አድርግልን…›› ሲሉት ያደርግላቸዋል፡፡ በእረኝነት ሳሉ ምሳውንም ሆነ እራቱን ለምስኪኖች ይሰጣል፡፡ ለእግዚአብሔር ስም እጅግ ቀናተኛ ስለነበሩ ስሙን ይፈሩ ስለነበር ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው ‹‹ይህን ክፉ ነገር በራስህ ላይ አድርግ›› ባሏቸው ሰዓት እንኳን በራሳቸው ላይ አንዳች ክፉ ነገር ወይም አደጋ ለማድረስ ወደኋላ አይሉም ነበር፡፡ ይህንን ሊፈትኗቸው ብለው አንድ ቀን ስለታማ ጦር አምጥተው ‹‹ስለ እግዚአብሔር ብለህ እስቲ ራስህን በዚህ ስለታማ ጦር ትወጋ ዘንድ ና›› ባሏቸው ጊዜ አብርሃም ልጁን ይስሃቅን ሊሠዋ በኅሊናው እንደወሰነ እርሳቸውም በቁርጥ ኅሊና ሆነው ራሳቸውን በጦሩ ሊወጉ ሲሉ ዘለው ያዟቸው፡፡ በሌላም ጊዜ እንዲሁ ሊፈትኑት በጭነት ምክንያት ጀርባው የቆሰለ አህያ አምጥተው ‹‹ዓቢየ እግዚእ ስለ እግዚአብሔር ብለህ የዚያችን አህያ ቁስሏን ላስ›› አሉት፡፡
እርሱም ያን ጊዜ ‹‹ርኩስን ብስም ኃጢአት ይሆንብኛል፣ አይሆንም ካልኳቸው ደግሞ ስመ እግዚአብሔርን ጠርተንበት እምቢ አለ ስለሚሉ የፈጣሪዬን ስም መዳፈር ይሆንብኛል ብሎ በልቡ አሰበና ያን ጊዜ ይስም ዘንድ ተመለሰ፡፡ ባልንጀሮቹም በቁርጥ ኅሊናው እንደወሰነ ባወቁ ጊዜ ሊያደርገውም ሲሄድ ተመልከተው ቶሎ ብለው ሮጠው ከኋላው ያዙት፡፡ እርሱም ‹‹እኔስ የፈጣሪዬን ስም እፈራለሁ ስሙን ተደፋፍሬ በምድር በሕይወት ከምኖር ሞት ይሻለኛል›› አላቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ወላጆቹ ለመምህር ዘርዐ ሚካኤል ሰጡትና ብሉያት ሐዲሳት መጻሕፍትን
ሌሎችንም አስተማረው፡፡ ከዚህም በኋላ መምህሩንና ዓቢየ እግዚእን ቅዱስ ሚካኤል ነጥቆ ወስዶ አክሱም አደረሳቸውና ዓቢየ እግዚእ ከአባ ሰላማ መተርጉም እጅ ዲቁናና ቅስና ተቀበሉ፡፡ ከብዙ ዘመንም በኋላ የሃሌ ሉያው አባ ሳሙኤል ቆብንና አስኬማን ሰጠው፡፡ ለአባታችን አንበሶችና ነብሮች አራዊትም ሁሉ እንደ ጓደኛ ሆነው ታዘዙለት፡፡
ቶራዎችም በሰው አንደበት ያናግሩታል፡፡ ቶራዎቹም ከነብሮች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል፡፡ እርሱም እህልን ሳይቀምስ በቤት ጣሪያም ውስጥ ገብቶ ሳይቀመጥ ተጋድሎውን በማብዛት ብዙ ደከመ፡፡ የመላእክት ክንፍ ተሰጥቶት በሦስት ሰዓት ውስጥ የሕያዋንን መኖሪያ አይቶ ይመለሳል፡፡ በዋልድባ ገዳም ስውር ቤተ ክርስቲያን አለ ነገር ግን የሚያገኘው አልነበረም፡፡ አባታችን ዓቢየ እግዚእ ግን 40 ቀንና 40 ሌሊት ከጾመ ከጸለየ በኋላ አራዊት ተሸክመውትና አጅበውት እዚያች ስውር ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ደረሰ፡፡
በውስጧም የሚንቀሳቀስ ብርሃን አየ ይኸውም የዚህ ዓለም ብርሃን አይደለም፡፡ በውስጧ ያሉ ስውራን ቅዱሳንንም አገኛቸውና ከእነርሱ ተባረከ፡፡ ከዚህም በኋላ የተለያዩ አስደናቂ ተአምራትን እየሠራ ወንጌልን በመስበክ ብዙ አገለገለ፡፡ የተከዜን ባሕር ለሁለት ከፍሎ በመሻገር በአካባቢው ያሉ ኢስላሞችን በተአምራቱ አሳመናቸው፡፡ ከደረቅ ጭንጫም ላይ ውኃን አፈለቀ፡፡ በተሰጠውም ክንፍ ብሔረ ሕያዋንና የጌታችን መካነ መቃብር ዘንድ እየሄደ ከቅዱሳን ጋር ጸሎት ያደርጋል፡፡ ደቀ መዛሙርቶቹም ‹‹እገሌ ሞቷልና የት እንቅበረው? ባሉት ጊዜ እርሱ ግን ከጸለየ በኋላ ከሞት ያስነሣዋል፡፡ የሐማሴኑ መስፍንም እንዲሁ በጦርነት ወቅት ሞቶ ባለሟሎቹ አስክሬኑን ተሸክመው ወደ ሀገሩ ሲወስዱት ሰላምጌ ከምትባል የላስታ ምድር ደረሱና በመንገድ አባታችንን አገኛቸውና ‹‹ይህን በድን ወዴት ትወስዱታላችሁ?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ሐማሴን ይባላል በንጉሡ ትእዛዝ ወደ ጦርነት ዘምተን ሳለ እርሱ ሞቶ ወደ ሀገሩ እየወሰድነው ነው›› አሉት፡፡ አባታችንም ያስቀምጡት ዘንድ አዘዛቸውና ውኃ አምጡልኝ አላቸው፡፡ ስመ እግዚአብሔርንም ጠርቶ ከጸለየና በውኃው ካጠመቀው በኋላ ሐማሴንን ከሞት አስነሣው፡፡ ሐማሴንንም ስለ አሟሟቱ ሲጠይቁት ‹‹መልአከ ሞት ወስዶ ለፍርድ ሳያቆመው በፊት ይህ ጻዲቅ መነኩሴ ስለ እኔ ሲለምን አየሁት፤ በጸሎቱም እግዚአብሔር ማረኝና ነፍሴን ወደ ሥጋዬ እንድትገባ አዘዘ›› ብሎ የሆነውን ሁሉ በዝርዝር ነገራቸው፡፡ አባታችንም ሐማሴንን ‹‹በሰላም ወደ ሀገርህ ሂድ›› ብሎ አሰናበተው፡፡ ያ ሹም ግን ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች መጽውቶ ወደ አባታቸን ዘንድ መጣ፡፡ የአባታችንን ጽድቁንና ትሩፋቱን የሰሙ ሁለት ሺህ ሰዎችም አብረውት ከሹሙ ጋር መጡና አባታችንን ‹የምንኩስና ልብስ ልንለብስ እንወዳለን›› ባሉት ከፈተናቸው በኋላ አመነኮሳቸው፡፡ ያንንም መስፍን ፍኖተ ሕይወት-የሕይወት መንገድ ብሎ ሰየመው፡፡
የአባታችንም ያችን ደብር ሰጠውና አበ ምኔት ሆኖ ብዙ አገልግሎ ዘመኑን ጨረሰ፡፡ ዳግመኛም አባታችንን በደብረ መድኃኒት በምትባል ደብር ሳለ ስሟ ቡሩክት ማርያም የምትባል ልጁ ሞታ አባታችን አለቀሰላት፡፡ ተነሥቶም ወደ ዋሻ ገብቶ በሩን ዘግቶ አመድ ነስንሶ ደረቱን እየደቃ እየጸለየ ሳለ ቡሩክት ማርያም ከሞት መነሣቷን ደቀ መዛሙርቱ ሮጠው መጥተው ነገሩትና ሄዶ አገኛት፡፡ ‹‹ምን አየሽ?›› ቢላት እርሷም ‹‹‹ስለአገልጋዬ ዓቢየ እግዚእ ልቅሶና መቃተት ይህች ነፍስ ወደ ሥጋዋ ትመለስና እስከምታረጅ ትኑር› የሚል ቃል ሰማሁ›› አለችው፡፡ እርሷም አባታችን ካረፉ በኋላ በምድረ ዠመዶ ኖራ በኋላ በሰላም ዐረፈች፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ብፁዕ አባታችን ከ6 መነኮሳት ልጆቻቸው ጋር ይሰግዱ ዘንድ ሲሄዱ ርዝመቱ 120 ስፋቱ 12 ክንድ የሆነ ዐይኖቹ እንደሚነድ እሳት የሆኑ ከአፉም ነበልባል የሚወጣ እንደንስርም ክንፍ ያለው ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ መጠኑም ተራራ የሚያክል አውሬ በቁጣ ሊውጣቸው አፉን ከፈተ ምላሱን አውለበለበ፡፡
መነኮሳቱም እጅግ ደንግጠው ሳለ አባታችን ግን በስመ ሥላሴ አማትበው በአውሬው ላይ
የተገለጠውን ያንን ከይሲ ለሁለት ሰነጠቁት፡፡
አንዲት እናት ወደ አባታችን መጥታ ‹‹የአንተን የጸሎት ውኃ ስጠኝ?›› አለችው፡፡ አባታችንም ‹‹ምን ልታደርጊው ነው?›› ሲላት ‹‹ልጠጣው ነው›› አለችው፡፡ እርሱም ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ‹‹…አቤቱ ይህንን የጸሎት ውኃ ለሚጠጣው ሁሉ የሚያድን አድገው…›› ብሎ ጸልዮ በስመ ሥላሴ አማትቦ ሰጣት፡፡ እርሷም ወደቤቷ ወስዳ ሌላኛዋን ሴት ‹‹ይህንን የጸሎት ውኃ እጠመቅ ዘንድ በላየ ላይ አፍሽልኝ›› አለቻት፡፡ ሁለተኛዋም ሴት በላይዋ ልታፈስ ውኃውን አነሣች፣ ከፍም አደረገችው፡፡ ነገር ግን ውኃው የረጋ ደም ሆነ፣ አልፈሰሰምም፡፡ እነዚያም መበለታት እጅግ ደንግጠው ‹‹በኃጢአታችን ውኃው ደም ሆነ፣ ወደ አባታችን ሄደን አንንገረው›› ተባብለው ሄደው ነገሩት፡፡ አባታችንም ‹‹ያደረጋችሁት ምንድነው?›› ሲላቸው ሴቷ ‹‹በራሴ ላይ አፍስሽልኝ ከማለቴ በስተቀር ምንም ያደረግነው የለም›› አለችው፡፡ አባታችንም ‹‹ቃልን ከመለወጥ በላይ ሌላ ኃጢአት ምን የለም፣ ቃልሽን ስለለወጥሽ ደም ሆነ፣ እኔን ‹የምጠጣው የጸሎት ውኃ ስጠኝ› አልሽኝ እኔም እንዳልሽኝ ሰጠሁሽ›› አላት፡፡ እርሱም ‹‹አምጭው›› አላትና ሰጠችው፡፡ ተቀብሎ በስመ ሥላሴ ሦስት ጊዜ ቢባርከው ያንጊዜ እንደቀደሞው ንጹሕ ውኃ ሆነ፡፡ ያችንም መበለት ‹‹ልትጠጪ ከወደድሽ ውሰጂ›› አላት፡፡ እነዚያም መበለታት ከምድር ላይ ወድቀው ‹‹ይቅር በለን›› ሲሉት እርሱም እጁን አንሥቶ ባረካቸው፡፡
አባታችን አንድ ቀን ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገብቶ ሳለ ገዳማውያኑ ‹‹አንድ መነኮስ ብናገኝ ሥጋወደሙ በተቀበልን…›› ሲባባሉ አገኛቸውና ባረካቸውና ‹‹ዛሬ የተዘጋጀ ቁርባን አለን?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አዎን›› አባሉት ጊዜ አዘጋጂተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ አዘጋጅተው አመጡና አባታችንን ‹‹ገብተህ ቀድስ›› አሉት፡፡ እሱም ‹‹ባርኩኝ›› አላቸውና ‹‹እንደ መልከጼዴቅ፣ እንደ አቤል መሥዋዕትህን ይቀበልልህ…›› ባሉት ጊዜ ሚመጠን አለ፡፡ ይህንንም ባለ ጊዜ ኅብስትና ጽዋ ከፃሕል ጋር ተዘጋጅቶ ከላይ ከሰማይ ወረደ፡፡
ይህንንም ያዩና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ ‹‹ይህ ኅብስትና ጽዋ ከየት መጣ›› እያሉ አደነቁ፡፡ አባታችንም የሐዋርያትን ቅዳሴ ቀድሶ አቆረባቸው፡፡ አባታችንም ወጣና ደመናውን ጠቅሶ በደመና ተጫነ፡፡ እነርሱም ‹‹አቤቱ ስለ እግዚአብሔር ብለህ ስምህን ንገረን›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹ስሜ ዓቢየ እግዚእ ይባላል የምንኩስና ስሜ የመረታ ሀገር እንጦንስ ነኝ›› አላቸውና ባረኳቸው ሄደ፡፡ ያም ፃሕልና ጽዋ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ ቅዱስ አባታችን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የተለያዩ አስደናቂ ተአምራትን እየሠራ ወንጌልን በመስበክ እገዚአብሔርን ካገለገለ በኋላ ከፈጣሪው ታላቅ ቃልኪዳን ተቀብሎ በግንቦት 19 ቀን በክብር ዐርፏል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ ብስጣውሮስ ዘሐይቅ
በዚህችም ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከጳውሎስ ሳምሳጢን ጀምሮ እስከ ንስጥሮስንና ልዮን ድረስ ያስተማራትን የክህደት ትምህርት ከሀገራችን ያጠፉልን የሐይቁ አቡነ ብስጣውሮስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ሙሉ ስማቸው ዓቃቤ ሰዓት አቡነ ብስጣውሮስ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን የትውልድ ሀገራቸው መቅደላ ነው፡፡ አባታቸው ፍተ ድንግል እናታቸው ጽዮን ሞገሳ የሚባሉ ደጋግ ቅዱሳን ናቸው፡፡ አቡነ ብስጣውሮስ በ17ኛው ምእት ዓመት የነበሩ ታላቅ ጻድቅ ሲሆኑ የታላቁና የጥንታዊው ትምህርት ቤትና የሥርዓተ ገዳም ተቋም የደብረ ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ገዳም አበምኔት ነበሩ፡፡ በልጅነታቸው ትምህርት ቤት ገብተው የሐዋርያትን ሥርዓትና የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜ በሚገባ ተምረዋል፡፡
በዘመናቸው የሃይማኖት ስደት ስለነበር አባታቸው ፍተ ድንግል ስለ ሃይማኖታቸው በዐላውያን ሰማዕት ሆነው ሲገደሉ አቡነ ብስጣውሮስ የአባታቸውን ዐፅም ይዘው በመሸሽ ወደ ላስታ ሄደው በእመቤታችን ስም በተሠራች ገዳም በደብረ ዠመዶ ወስደው ቀበሯቸው፡፡ በኋላ በዐፄ ፋሲል ዘመን ሃይማኖት ሲመለስ ዐፅማቸውን አፍልሰው አምጥተው አገራቸው ቀብረዋቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ እናታቸው በግድ ሚስት አጭተውላቸው የነበረ ቢሆንም ብዙ ሳይቆዩ ሚስታቸው ስለሞተች ቀድሞም የተመኙትን የምንኩስና ሕይወት ለመኖር ወኑ፡፡ አንድ ቀን አንዱ የደብረ ሐይቅ መነኩሴ የገዳሙን ምርት ገበያ ለመሸጥ ይዘው እንደሄዱ አንድ ቀማኛ ወንበዴ አግኝቶ ሊቀማቸው ሲል አቡነ ብስጣውሮስ ደርሰው አዳኑት፡፡ መነኩሴውንም ወደ ቤታቸው ወስደው በመልካም መስተንግዶ አሳደሯቸው፡፡
መነኩሴውም በዚያች ሌሊት ስለ አቡነ ብስጣውሮስ ብዙ ነገር ከተመለከቱ በኋላ አቡነ ብስጣውሮስን ስለ ምንኩስና አስተማሯቸው፡፡ መነኩሴው በማግስቱ ሲሄዱ ወደ ሐይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ገዳም መጥተው እንዲጎበኟቸውና እንዲባረኩ ነግረዋቸው ሄዱ፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም እግዚአብሔር መንገዳቸውን ይመራቸው ዘንድ ብዙ ከጸለዩ በኋላ ወደ ሐይቅ ገዳም ገቡ፡፡ በገበያ ያገኘውና በቤቱ ያሳደረውም መነኩሴ ሲያያቸው ደስ ተሰኝነቶ የገዳሙ አበምኔት ዓቃቤ ሰዓት አባ ዘወልደ ክርስቶስ ዘንድ ወሰዳቸው፡፡ አበምነቱም አቡነ ብስጣውሮስን ገና እንዳዩአቸው ጸጋ እግዚአብሔር እንዳደረባቸው አይተው በጣም ደስ ተሰኙ፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም መመንኮስ እንደሚፈልጉ ለአበምኔቱ ሲነግሯቸው አበምኔቱ ‹‹የምንኩስና ሥራ ቀላል አይምሰልህ፣ ብዙዎች ወደ እኛ መጡ ነገር ግን መታገስ ተስኗቸዋል…›› በማለት የምንኩስና ሕይወት ከባድ ፈተና እንዳለበት ነገሯቸው፡፡
የእግዚአብሔር ሰው ብስጣውሮስም ‹‹በልዩ ልዩ ዓይነት ፈተናዎች ፈትኑኝና ሥራዬን ካዩ በኋላ ያመነኩሱኛል›› አሏቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ብስጣውሮስ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት እየተጋደሉ ገዳሙን በጉልበት ሥራ ብዙ ካገለገሉ በኋላ ከገዳሙ አበምኔት ከዓቃቤ ሰዓት አባ ዘወልደ ክርስቶስ እጅ ምንኩስናን ተቀበሉ፡፡ ተጋድሎአቸውንም ከበፊቱ ይበልጥ በማብዛት መኖር ጀመሩ፡፡
እናታቸው የልጃቸውን መመንኮስ ሰምተው ወደ ሐይቅ መጡ ነገር ግን አቡነ ብስጣውሮስ እናታቸውን ወጥተው ላለማየት ተሠወሩ፡፡ አበምኔቱም በብዙ ፍለጋ አግኘተዋቸው ‹‹ልጄ እናትህ አንተን ለማየት ከሩቅ ሀገር መጥታለችና ሄደህ አግኛት›› ሲሏቸው አቡነ ብስጣውሮስም ‹‹አባቴ ሆይ ጌታችን በወንጌል ያለውን አያስታውሱምን? ‹እነሆ እናትና ወንድሞችህ በውጭ ቆመዋል ባሉት ጊዜ ጌታችን በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ ከሚፈጽም በቀር እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?› ብሎ ተናግሮ የለምን? ስለዚህ ወደ እናቴ አልሄድም›› ብለው ለአበምኔቱ መለሱላቸው፡፡ አበምንቱም ‹‹ከመንገዱ ርቀት የተነሣ እናትህ በብዙ ድካም መጥታለችና ልታያት ይገባል›› ብለው ግድ አሏቸው፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም ሄደው እናታቸውን ካገኟቸው በኋላ እናታቸውም በዛው መንኩሰው በባሕሩ ዙሪያ ካለው ከሴቶች ገዳም ገብተው ማገልገል ጀመሩ፡፡
አቡነ ብስጣውሮስ ከመልካም የጉልበት ሥራ ጋር ቀን ቀን የዳዊትን መዝመር፣ የነቢያትን መጻሕፍትና መኅልየ መኅልይን ሲደግሙ ይውላሉ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ገብተው እጅግ አብዝተው ሲጸልዩ የብርሃን ዓምድ ተተክሎ ይታይ ነበር፡፡ ጸሎታቸውንም ሲጀምሩ ሰማያት ይከፈቱ ነበር፡፡ ቅዱሳን መላእክትንም ሲወጡ ሲወርዱ ያዩአቸዋል፡፡ አቡነ ብስጣውሮስ በእንደዚህ ዓይነቱ ተጋድሎ ብዙ ሲያገለግሉ ዜና ትሩፋታቸው በሁሉ ዘንድ በዓለም ተሰማ፡፡ አስተዳዳሪው ዓቃቤ ሰዓቱ አቡነ ዘወልደ ክርስቶስም እርጅና ሲጫናቸው ማኅበሩን ሰብስበው ‹‹በእኔ ቦታ አባት የሚሆናችሁን ምረጡ›› አሏቸው፡፡ እነርሱም ‹‹እግዚአብሔር ያመለከተህን አንተ ሹምልን›› አሏቸው፡፡ አባ ዘወልደ ክርስቶስም በጸሎት ከጠየቁ በኋላ ‹‹እግዚአብሔርና እኔ አባት ይሆኑላችሁ ዘንድ አቡነ ብስጣውሮስን መርጠንላችኋል›› አሏቸው፡፡ ቀጥሎ አበምኔቱ ስለ አቡነ ብስጣውሮስ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናገሩ፡- ‹‹እርሱ ሃይማኖቱ የቀና ምግባሩ ያማረ በተጋድሎም የጸና በጸሎቱ ሀገርን ይጠብቃል፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በነገሥታቱና በመኳንንቱ ፊት ያደርጋል›› እያሉ ለማኅበሩ በነገሯቸው ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኙ፡፡ አቡነ ብስጣውሮስ ግን ይህን ሲሰሙ የመረረ ልቅሶን አለቀሱ፤ ከእነርሱም ዘንድ ይሸሹ ዘንድ ወጥተው በመርከብ ተጭነው ሄዱ፡፡ ነገር ግን ደርሰው ይዘው በእግዚአብሔር ፈቃድ ይሾሟቸው ዘንድ ይዘው አሰሯቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ከሰማይ ‹‹ብስጣውሮስ የአባትህን የአበምኔቱን ቃል አታስተሐቅር›› የሚል ቃል ተሰማ፡፡ ማኅበሩም ይህንን ከሰማይ የመጣውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደስተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ብስጣውሮስን እንደ ሕጋቸውና እንደ ሥርዓታቸው የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም አበምኔትና ዓቃቤ ሰዓት በማድረግ ሾሟቸው፡፡
አቡነ ብስጣውሮስም በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ወንበር በተቀመጡ ጊዜ የተሰወረውን ሁሉ የሚያዩ ሆኑ፡፡ ፊታቸውም እንደ ጨረቃ የሚያበራበት ጊዜ ነበር፣ ለአገልግሎትም ወደ ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት ክንፋቸውን እየጋረዱ ይቀበሉት ነበር፡፡ ጻድቁ ጸሎተ ዕጣን ሲያሳርጉ እያለቅሱ ነበር፤ የጌታችንን መከራ እያሰቡ ሰውነታቸውን በድብቅ ይገርፋሉ፤ ድኆችንና ጦም አዳሪዎችን ሁሉ የሚንከባከቧቸው አባት ሆኗቸው፡፡ ገዳሙንም አፍርሰው ሊዘርፉ የመጡትን ወራሪዎች አባታችን ወደ መቅደስ እየገቡ በጸሎት እያሰሯቸው አሳፍረው ይመልሷቸው ነበር፡፡ አቡነ ብስጣውሮስ በእንዲህ ዓይነት ተጋድሎ ገዳሙንና ሀገራችንን እየጠበቁ ሲኖሩ በመሀል የቅብዐት እምነት ነገር በገዳሙ ተነሣ፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንን አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹ከትስብእት ጋር ከተዋሐደ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ተቀባ፣ በዚህም ቅብዐት በጸጋ ልጅ፣ ንጉሥም፣ ነቢይም፣ ሊቀ ካህናትም ተባለ›› የሚሉ ከሃዲያን ተነሡና የእግዚአብሔር ሰው ብፁዕ አባታችን ብስጣውሮስ ይህንን የክሕደት ትምህርት ሰምተው እጅግ እያዘኑና እያለቀሱ የካዱትን ሰዎች በብዙ ምሳሌ እያደረጉ ማስተማር ጀመሩ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዐት በጸጋ ልጅ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን በባሕርይው የአብ ልጅ እንደሆነ፣ እርሱ ራሱ ቅብ፣ እርሱም ራሱ ቀቢ፣ እርሱ ራሱ ተቀቢ እንደሆነ በብዙ ምሳሌ እያደረጉ የቀደሙ የአባቶቻችንንም ትምህርት ሁሉ እየጠቀሱ አስተማሯቸው፡፡ ነገር ግን ሰይጣን አንድጊዜ አስክዷቸዋልና አንዳንዶቹ እምቢ አሏቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ሐዋርያት ከመሠረቷት አንዲት ቤተ ክርስቲያን አውግዘው ለዩአቸው፤ ቤተ ክርስቲያንም ሰላም ሆነች፡፡ በዚህም አባታችን ከሃድያንን የሚዘልፉ ዳግማዊ ቄርሎስ ተባሉ፡፡ ይህም ክህደት መጀመሪያ ሰይጣን ለጳውሎስ ሳምሳጢን ያስተማረው ነው፡፡ ጳውሎስ ሳምሳጢን በገዳም ቅጠል እየበላ የሚኖር ተሐራሚ መናኝ ነበር፡፡ በጾም በጸሎት ሲኖር ሰይጣን ራሱን ሰውሮ መጥቶ ተገለጠለትና ‹‹ጸሎትህ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰምቶልሃል፤ ነገር ግን አምላክ ያለሩካቤ በድንግልና የተወለደ አይምሰልህ በሩካቤ ተወለደ እንጂ፤ ይህም ልጅ ደግ ሰው ሆነ፣ በ30 ዘመኑ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፣ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል በራ ላይ ተቀመጠ፣ ያን ጊዜም ይህ ሰው በጸጋ የሥላሴ ልጅ ሆነ›› ብሎ አስተማረው፡፡ ጳውሎስ ሳምሰጢንም ሰይጣን የነገረውን ነገር በልቡ አምኖ ለደቀ መዝሙሩ ለተያስሮስ አስተማረው፡፡ ተያስሮስም ለድያድርስ አስተማረው፡፡ ድያድርስም ለንስጥሮስ አስተማረው፡፡ ንስጥሮስም ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንን አምላካችንን ‹‹መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ ነው›› ብሎ ለልዮንና ለመርቅያን አስተማራቸው፡፡
ንስጥሮስ ይህን አዲስ የክህደት ትምህርት እንዳመጣ በሰሙ ጊዜ 200 ኤጲስ ቆጶሳት በቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ መሪነት በኤፌሶን ተሰብስበው ሲያስተማሩት እምቢ ቢላቸው አውግዘው ለዩት፡፡ ንስጥሮስም ሰውነቱ መግሎ ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡ በኋላም መርቅያን ሲነገሠና ልዩንም የሮም ሊቀ ጳጳስ ሲሆን ሁለቱም አባታቸው ንስጥሮስ ያስተማራቸውን ሃይማኖት ማስፋፋት ቻሉ፡፡ እነ ልዮንም ንስጥሮስ በተወገዘበት ጉባዔ ላይ የነበሩትና አሁን ለሥጋቸው የፈሩ አባቶችን ይዘው ከንስጥሮስ ክህደትና ከቅዱስ ቄርሎስ ትምህርት አወጣጥተው የራሳቸውን የረከሰ ሃይማኖታዊ ድንጋጌ አወጡ፡፡ ‹‹ክርስቶስ ሁለት አካል ነው፣ አንዱ የማርያም ልጅ አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ በመቀራረብ አንድ ሆኑ ያለውን አውጥተው ከቅዱስ ቄርሎስም ቃልና ከንስጥሮስ ክህደት ቀላቅለው መለኮት የመለኮትን ሥራ ይሠራል፣ ትስብእትም የትስብእትን ሥራ ይሠራል፤ በሁለት መንገድ አንዱ ተአምራትን ያደርጋል ሁለተኛው መከራን ይቀበላል ስለዚህም ትስብእት ከመለኮት ያንሳል›› ብለው ጻፉ፡፡ ይህንንም የክህደት ጽሕፈታቸውን ለቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላኩለት፡፡ እርሱም ሄዶ ከክህደታቸው እንዲመለሱ አስተማራቸው፡፡ ‹‹በአንዱ ክርስቶስ ላይ ለምን የሁለትነት ነገር ትናገራላች? ወደ ሠርግ ቤት ተጠርቶ የሄደው ውኃውንም የወይን ጠጅ ያደረገው እርሱ አንዱ ክርስቶስ ነው…›› እያለ በብዙ ምሳሌ ካስተማራቸው በኋላ ልዮንንና መርቅያን የጻፉትን የክህደት ጽሕፈት በፊታቸው ቀደደው፡፡ እነርሱ ግን አንድ ጊዜ ክደዋልና የቅዱስ ዲዮስቆሮስን ፂሙን ነጭተው ጥርሱን አውልቀው ብዙ አሠቃዩት፡፡ እርሱም የነጩትን ፂሙንና ያወለቁትን ጥርሱን ሰብስቦ ‹‹እነሆ የሃይማኖቴን ፍሬ ተቀበሉ›› ብሎ ለእስክንድርያ ክርስቲያኖች ላከላቸው፡፡ ከሃዲያኑም ወደ ጋግራ ደሴት አጋዙትና በዚያው ዐረፈ፡፡
ሰይጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ለጳውሎስ ሳምሳጢን ያስተማራትን ያችን ክህደት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሰይጣን የሚያድርባቸው ሰዎች እየተቀባበሏት እስከ ንስጥሮስንና እስከ ልዮን ድረስ ከደረሰች በኋላ የልዮን ልጅ በሆነው በአውፍንስ አማካኝነት በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ገባች፡፡ አውፍንስም ክህደቱን ለሁለት የሀገራችንን መነኮሳት አስተማራቸው፡፡ ለአንደኛው ‹‹ወልድ ሦስት ልደት አለው፣ በመጀመሪያ ከአብ ተወለደ ዳግመኛም በመንፈስ ቅዱስ ሥጋ ከድንግል ተወለደ ሦስተኛም በቤቴልሔም ተወለደ›› ብሎ ካስተማረውና ካስካደው በኋላ ስሙን ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› ብሎ ጠራው፡፡ ሁለተኛውንም መነኩሴ ለብቻው ጠርቶት ‹‹ልጄ ሆይ ስማኝ ልብ አድገህም ዕወቅ፣ ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዐት የከበረ ነው፣ ይኸውም ሳይዋሃድ ማደር ነው›› ብሎ ካስተማረውና ካስካደው በኋላ ስሙን ‹‹ኤዎስጣቴዎስ›› ብሎ ጠራው፡፡ እነዚህም የካዱ ሁለቱ መነኮሳት በየሀገሩና በየአውራጃው እየዞሩ ሀገራችን ኢትዮጵያን በክህደት ትምህርታቸው አጥፍተዋት ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህን ክህደት በትምህርታቸውና በተአምራታቸው እንዲገታ አድርገውታል፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም እነዚያን ከሃዲዎች አውግዘው ለዩአቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ከሃዲያኑ አባታችንን ከሰሷቸውና ከጎንደሩ ንጉሥ ጋር አጣሏቸው፡፡ ንጉሡም የእነዚያን ካሃዲዎች እምነት አምኖ ተቀብሎ ነበርና አባታችንን ወደ ጎንደር እንዲያመጧቸው ጭፍሮቹን ላከ፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም ነገሩን አውቀው ስለ ቀናች ሃይማኖት ይመሰክሩ ዘንድ አንደበት እንዲሆናቸው ጌታችንን በጸሎት ሲጠይቁ ጌታችንም ‹‹ልጄ ብስጣውሮስ ሆይ አይዞህ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ እኔ ስለመሠረትኳት አንዲት ሃይማኖት ጽና›› አላቸው፡፡ አባታችንም ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄዱና ንጉሡ ሰዎቹን ስለማውገዙ ጠየቃቸው፡፡ አባታችንም ንጉሡን ስለ ቀናች ሃይማኖት እየመሰከሩለት አስተማሩት፡፡ ንጉሡም በብዙ ስጦታና ሽንገላ ሊያታልላቸው ሞከረ ነገር ግን አባታችን አጥብቀው ተቃወሙት፡፡ ንጉሡም ዕውቀታቸውንና ጽናታቸውን ባየ ጊዜ
አባታችንን በእግር ብረት አሳስሮ አሥር ቤት ውስጥ ጣላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ የእግር ብረቱ እንደሰም ቀልጠ፡፡ ወታደሮቹም ይህንን ተአምር አይተው ፈርተው ሄደው ለንጉሡ ነገሩት፡፡
ንጉሡም ሰምቶ ደነገጠ፤ እየፈራና እየተንቀጠቀጠ ወደ አባታችን መጥቶ ሰገደና ‹‹አባቴ ሆይ ይቅር በሉኝ የሃይማኖትንም ነገር እንደገና አስተምሩኝ›› አላቸው፡፡ እሳቸውም አስተምረው ባረኩት፡፡ በመከራቸውም ታግሰው ለልጆቻቸውና ለእኛም የሐዋርያትን ሃይማኖት አጸኑልን፡፡ ዕድሜአቸውም 90 ዓመት በሆነው ጊዜ ዕረፍታቸው እንደደረሰ ዐውቀው የቀናች ሃይማኖት በሀገራችን ለዘለዓለም ጸንታ ትኖር ዘንድ ጌታችንን አጥብቀው ለመኑት፡፡ ጌታችንም በደሙ የመሠረታት የቀናች ሃይማኖት በሀገራችን ጸንታ እንደምትኖርና ሌላም የምሕረት ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ግንቦት 19 ዐረፉ፡፡
በዚያችም ዕለት ሐይቅ አለቀሰች፤ የሐይቅም ባሕር ሦስት ዓመት በኃይል ስትታወክ አቡነ አላኒቆስ ይህ ሁሉ የሆነው ስለ አባታችን ስለ ብስጣውሮስ ማረፍ መሆኑን ዐውቀው ወደ ንጉሡ ሄደው የአባታችንን ዐፅም እንዲሰጣቸው ጠየቁት፡፡ ንጉሡ ግን ‹‹በረድኤታቸው ይጠብቁኛልና አልሰጥም›› አላቸው፡፡ ንጉሡ ስለከለከላቸው አቡነ አላኒቆስም ቁስቋም ወደምትባል በወርቅና በከበረ ዕንቁ ወደተሸለመች ወደ እመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ሄደው በእመቤታችን ሥዕል ሥር ወድቀው አለቀሱ፡፡ ሥዕሏም በሰው አንደበት አናግራ ካጽናናቻቸው በኋላ የአባታችን ዐፅም ከመሠዊያው በስተቀኝ በኩል እንደሚገኝ ነገረቻቸው፡፡ አቡነ አላኒቆስም ዐፅማቸውን አፍልሰው ወደ ሐይቅ በተመለሱ ጊዜ የመዓዛው ሽታ የንጉሡን አገር ሁሉ መላው፤ መቃብሩ በነበረበት ቦታም የብርሃን ዓምድ ተተክሎ ታየ፡፡
ንጉሡም መነኩሴው የአባታችንን ዐፅም እንደወሰዱ ባወቀ ጊዜ መነኩሴውን ይዘው ከአባታችን ዐፅም ጋር ያመጡለት ዘንድ ብዙ ፈረሰኛ ወታደሮቹን ላካቸው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በጥበቡ ሰውሯቸዋልና አቡነ አላኒቆስን ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ አቡነ አላኒቆስም የቅዱስ አባታችንን ዐፅም ወስደው በሐይቅ በመሠዊያው በስተቀኝ በኩል በቀበሩት ጊዜ በፊት ያስቸግር የነበረው የበሐሩ ኃይለኛ ንውጽውጽታ በአንድ ጊዜ ጸጥ አለ፡፡ ሌላም ብዙ ተአምራት ተደርገው ታዩ፡፡ ይኸውም ፍልሰተ ዐፅማቸውም የካቲት 8 ቀን ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ ዮሴፍ ዘአክሱም
በዚህችም ቀን የአቡነ ዮሴፍ ዘአክሱም ልደታቸውና ዕረፍታቸው በተመሳሳይ ግንቦት 19 ቀን ነው፡፡ ልጅ ሆነው እየተጫወቱ ሳለ መልአክ መጥቶ ለወላጆቻቸው የዓለም ሰው እንዳልሆነ ስለነገራቸው ወስደው ለሊቀ ጳጳሱ ሰጧቸው፡፡ በአክሱም ሲማሩ አድገው በ22 ዓመታቸው መንኩሰዋል፡፡ አንጋፋ ከተባሉት የኢትዮጵያ ቅዱሳን አንዱና ዋነኛው ናቸው፡፡
ጻድቁ በጸሎት ላይ እንዳሉ ጌታችን ተገልጦላቸው እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ትወደኛለህን?›› ብሎ ሲጠይቃቸው ‹‹ጌታዬ ባለወድህማ ኖሮ መች ዓለምን ንቄ እከተልህና ገዳም እገባ ነበር›› አሉት፡፡ ቀጥሎም ጌታችን ‹‹ከወደድከኝስ ለእናቴ ዓሥራት የሰጠኋት፣ ለወዳጄ ለጊዮርጊስ ዓሥራት የሰጠኋት፣ ለባለሟሌ ለገብረ መንፈስ ቅዱስ ዓሥራት የሰጠኋት ይህችን ቅድስት ሀገር ያሬድንና ጊዮርጊስን ያፈራችውን ኢትዮጵያን ጠብቅ›› ብሏቸው ተሰወረ፡፡ ጻድቁም ጌታችን ይህን ከነገራቸው በኋላ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ስለ ሀገራችን ቆመው ጸልየዋል፡፡ ሸዋ ቡልጋ ፈጠጋር ውስጥ ለሚገኙት ወንድማቸው ለታላቁ ጻድቅ ለአቡነ ዘካርያስም ስለ ኢትዮጵያ አብዝተው እንዲጸልዩ መልእክት ስለላኩባቸው አቡነ ዘካርያስም ዕድሜ ልካቸውን የጸለዩአት ጸሎት ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ ማር›› የምትል ነበረች፡፡ የአቡነ ዘካርያስ ገዳም ቡልጋ ውስጥ ይገኛል፡፡ አቡነ ዮሴፍ ዘአክሱም የሀገራችንን ሊቃውንትና ሕዝቡንም ለብቻ ሰብስበው የሮማውያን የሀሰት ትምህርት ነፍስን ለሲኦል የሚዳርግ ፍጹም ክህደት መሆኑን አጥብቀው አስተምረዋል፡፡ ጻድቁ በአንድ ወቅት ርሀብ በሆነ ጊዜ የገዳሙን ድንጋዮች ባርከው ዳቦ አድርገው ሕዝቡን የመገቡ ታላቅ አባት ናቸው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ይስሐቅ ገዳማዊ
በዚህች ቀን ከአባ መቃርስ ገዳም ቅዱስ አባት ቀሲስ ይስሐቅ አረፈ። ይህም አባት ከምሥር ከታናናሽ ቦታዎች ከአንዲት ቦታ ነው ወላጆቹም ድኆች ሲሆኑ ግን በበጎ ስራ ባለጸጎች ናቸው።
አረጋውያን መነኰሳትም የእጅ ስራቸውን ሊሸጡ ወደ ምሥር በሄዱ ጊዜ ተከትሏቸው ወደ አስቄጥስ ገዳም መጥቶ ሲአገለግላቸው ኖረ። በቀንበራቸውም ተጠምዶ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ በዘመኑም ሁሉ ከቶ ምንም ጥሪት አላደረገም።
እንደ አባቶቻችን ሁለት ልብሶችን ለምን አልገዛህም ሲሉት እርሱም እኔ እስከ ዛሬ ሕዝባዊ ነኝ በዓለም ሳለሁም ሁለት ልብስ የለኝም ነበር ብሎ ይመልስላቸዋል።
ሁለተኛም አባቶቻችንም እኮ ሰሌንና ማቅ ይለብሳሉ ለእኛም አንድ ልብስ ይገባናል ይህ አይበቃንምን አላቸው። ሁልጊዜ የሚያለቅስ ሆነ ለምን ታለቅሳለህ ብለው በጠየቁት ጊዜ ወላጆቼ ሙተውብኝ ድኃ አደግ አድርገውኛልና ይላቸዋል።
ከምግቡም የማዕጠንት አመድ ጨምሮ እየበላ ብዙ ዘመናት ኖረ። ከዚህ በኋላ ጭንቅ በሆነ ደዌ ተይዞ በታመመ ጊዜ ከወንድሞች አንዱ ምግብ ሰርቶ አመጣለት። እርሱም ከቶ አልቀመሰም ያም ወንድም ይህ ጥሩ ምግብ ነው ለበሽታህም መድኃኒትነት አለውና ብላ ብሎ ብዙ ለመነው።
እርሱም ወንድሜ ሆይ እመነኝ እኔ በዚህ ደዌ ውስጥ ሠላሳ ዓመት እኖር ዘንድ እወዳለሁ ብሎ መለሰለት። በዕድሜውም በሸመገለ ጊዜ ትሩፋቱና ጽድቁም በበዛ ጊዜ ቅስና ይሾሙት ዘንድ አረጋውያን ተሰብስበው ተማከሩ።
እርሱም ከእርሳቸው ሸሽቶ ከተዘራ ማሳ ውስጥ ገብቶ ተሠወረ። እርሱንም እየፈለጉ ዞሩት አላገኙትም ያቺንም ማሳ አልፈው ከዳርዋ ተቀመጡ ጥቂት ሊያርፉ። ከእርሳቸውም ጋር አህያ ነበረ ወደ ማሳውም ሩጦ ገብቶ ይህ አባት በተሸሸገበት ቦታ ቆመ፡፡ አህያውን ሊያስወጡትም በገቡ ጊዜ ያንን አባት አገኙት። ደግሞ እንዳይሸሽ ሊአሥሩት ፈለጉ አሁንስ ዐውቄዋለሁ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ አላቸው ከዚያም አብሮአቸው ሒዶ ቅስና ሾሙት።
ከዚህ በኋላም ተጋድሎውንና ለአረጋውያን መታዘዙን ጨመረ ወጣቶችንም በጎ ሥራ ያስተምራቸዋል ሰምታችሁ የምትታዘዙ ሁኑ ከትሩፋት ሁሉ ይህ ይበልጣልና አላቸው።
የሚያርፍበትም ጊዜ ሲደርስ ከእርሱ በኋላ የሚሠሩትን እንዲአስተምራቸው በዚያ ገዳም ያሉ ጎልማሶች በጠየቁት ጊዜ እንዲህ አላቸው። በገዳሙ ውስጥ ጸንታችሁ እንድትኖሩ እኔ ስሠራ ስታዩኝ እንደነበረ እናንተም እንዲሁ በፈቃዳችሁ ሥሩ። እኛ አባቶቻችን በአረፉ ጊዜ አዝነን አልቅሰን ነበር እንደሚሠሩትም በሠራን ጊዜ ከእነርሱ በኋላ ተጽናንተን በገዳም የምንኖር ሆን። ይህንንም እያለ በፍቅር በሰላም አረፈ የሕይወት አክሊልንም አገኘ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን ኃይለኛ ተጋዳይ ቅዱስ ኤስድሮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ ከእስክንድርያ አገር ከከበሩ ከቤተ መንግሥት ወገኖች ውስጥ ነው አባቱም በብዙ ሠራዊት ላይ የተሾመ መኰንን ነው። ስሙም በደላዖን ነው የእናቱም ስም ሶፍያ ነው ሁለቱም ከክርስቲያን ወገን ናቸው ይህንንም ቅዱስ በወለዱት ጊዜ ኤስድሮስ ብለው ሰየሙት።
ከብዙ ወራት በኋላም ከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ የሚያደርገውን የኃጢአትና የበደልን ብዛት በአየ ጊዜ እርሱ ከመንግሥት ታላላቆች ውስጥ ስለሆነ ምስፍናውን ትቶ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋራ ገለል አለ። ስለ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጻተኞች በመሆን ከዚህ ዐላዊ ንጉሥ ፊት ሸሽተው ሳሙኤል ከሚባል ሰው ዘንድ ተሰባስበው በገዳም ተቀመጡ።
ከዚህ በኋላም ለጣዖታት እንዳይሰግዱ ከንጉሡ ሸሽተው ስለተሠወሩ ከሀድያን መጥተው በንጉሡ ዘንድ ነገር ሠሩባቸው። ወዲያውኑ አምስት መቶ ጭፍራ ልኮ ከፊቱ አስቀረባቸው።
ከእርሱ ዘንድ በመገለላቸውም ንጉሥ ጠየቃቸው እነርሱም እንዲህ አሉት። የክብር ባለቤት ክርስቶስን በተውከው ጊዜ ተውንህ ታላቅ ስንፍና አድርገህ ስተሃልና። በሰማ ጊዜም ተቆጥቶ የበደላዖንን አንገት ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም አገኘ። ቅዱስ ኤስድሮስን ግን ይመከር እንደሆነ ብሎ አሠረው ያንጊዜ ዐሥራ ሁለት ዓመቱ ነበር።
ከጥቂት ቀን በኋላም በአንገቱ የብረት ዛንጅርና ገመድ አስገብተው ከንጉሥ ፊት አቀረቡት። ንጉሡም አልፈራህምን ልብህስ ለመመለስ አልመከረምን ብሎ ጠየቀው። እርሱም እኔ የቀናች ሃይማኖቴን ትቼ ወደ ስሕተት አልመለስም አለው።
ያን ጊዜ አራቁተው ከምሰሶ ላይ ሰቅለው ደሙ እንደ ውኃ እስቲወርድ እንዲጨምቁት ንጉሥ አዘዘ። እናቱ ሶፍያም ከደሙ ወስዳ በንጉሡ ፊት ላይ ረጨች። እንዲህም አለችው ከሰው ሁሉ አንተ የተረገምክ ነህ እንዲሁ እኅቱ አፎምያም ደንጋዮችን አንሥታ ንጉሡንና መኳንንቶቹን ወረወረችባቸው። ንጉሥም ተቆጣና ከወገባቸው መካከል እንዲቆርጧቸው አዘዘ ቆርጠዋቸውም ምስክርነታቸውን ፈጸሙ አክሊልንም አገኙ።
ቅዱስ ኤስድሮስም ተሰቅሎ ሳለ በእናቱና በእኅቱ ላይ የሆነውን ይመለከት ነበር በወገቡም ላይ የእሳት ፍም ደፉበት ደግሞም ሆዱን ሠንጥቀው አንጀቱን አወጡ። በተራራ ላይም ጣሉት የሰማይ ወፎችና የዱር አራዊት አልቀረቡትም። መድኃኒታችንም ከሞት አስነሥቶ እንደ ቀድሞ ሕያው አደረገው።
ከዚያም ሒዶ በንጉሡ ፊት ቆመ ንጉሡም ከብረት ዐልጋ ላይ አውጥተው ከበታቹ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ። ሁለተኛም በብረት ላይ አስተኝተው አንጀቱ እስቲፈስ ድረስ ፈጩት ከዚህም መድኃኒታችን አስነሣው። ደግሞም ሁለተኛ ከስምንት መቶ ነፍስ ጋር ሰቀሉት ያንጊዜም መድኃኒታችን አድኖ አስነሣው።
ንጉሡም አይቶ በበሬ ቅርጽ በተሠራ ብረት ውስጥ አሥረው በላዩም ድኝና ዝፍት ጨምረው ከበታቹ እሳት እንዲአነዱ አዘዘ። ከጥቂት ቀን በኋላ ራሱን እንዲቆርጡት አዝዞ ቆረጡት ያንጊዜም ጌታችን ከሞት አነሣው እነሆ ሲያስነሣው ሦስተኛው ነው።
ደግሞ ከዚህ በኋላ እጅግ ከባድ የሆነ ደንጊያ በአንገቱ አሥረው ወደ ባሕር ጣሉት ወዲያውኑ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል አውጥቶ ከንጉሡ ፊት አደረሰው። ንጉሡም በከተማ መካከል እንዲሰቅሉት አዘዘ እንደዚህም ተሰቅሎ ሞተ። የክብር ባለቤት ጌታችንም አስነሣው ይህም ሲያሥነሣው አራተኛ ጊዜ ነው።
ከዚህም ለአንበሶች ጣሉት እግዚአብሔርም ነቢይ ዳንኤልን እንዳዳነ አዳነው። ከዚህም በኋላ በየጥቂቱ ቆራርጠው እንዲከትፉትና በእንቅብ ሰብስበው ወደ ባሕር እንዲጥሉት አዘዘ አሽከሮቹም እንዱሁ አደረጉ።
ያን ጊዜም የክብር ባለቤት ጌታችን ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋራ መጥቶ በባሕሩ ዳር ቆመ ከዚያም አውጥቶ አስነሣው። ያለ ምንም ጉዳት ይህም ከሞት ሲያስነሣው አምስተኛ ነው።
ንጉሡም በአፈረና የሚያደርገውም በተሳነው ጊዜ ከወገኖቹ ጋራ ተማክሮ በዚያ ያሠቃዩት ዘንድ እጅና እግሩን አሥሮ ወደ ሰሎንቅያ ሀገር ላከው። የሰሎንቅያ አገር ገዥም አስቀድሞ ስለ ሚያውቀው ከቅዱስ ኤስድሮስ ጋራ ቸርነትን ርኅራኄን አደረገ።
ንጉሡም ሰምቶ ተቆጣ ያንን መኰንንም እንዲአመጡት አዘዘ። ቅዱስ ኤስድሮስንም ወደ እርሱ መልሶ በእሥር ቤት በረኃብና በጽምዕ አኖረው ቅዱሱም በእሥራቱ መጠን ታላላቅ ድንቆች ተአምራትን እያደረገ በሽተኞችን ሁሉ አዳነ።
በዚችም በግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ ቀን በስድስት ሰዓት ከከተማ ውጭ እንዲሰቅሉት ንጉሥ አዘዘ። አየርም መላእክትን ተመላች የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብዙዎች ቃል ኪዳኖችን ከእርሱ ጋራ አደረገ። ያን ጊዜም ነፍሱን አሳለፈ። በማይጠፋ መንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊላትን ተቀበለ በተጋድሎ የኖረባቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመቶች ናቸው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages