ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 21 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 27, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 21

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም


ሰኔ ሃያ አንድ በዚች ዕለት የአዳምና የዘሩ ድኅነት የተደረገባት አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የታላቁ በዓል መታሰቢያና በዓለም ሁሉ የቤተ ክርስቲያን መታነፅ መታሰቢያ ነው፣ ከምስር አገር ቅዱስ ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት ሞተ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ከላድያኖስ አረፈ፣ ሐዋርያው ቶማስ በመሸታ ቤት ባረድዋት በአንዲት ሴት ላይ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም (ህንጸተ ቤተክርስቲያን)
ሰኔ ሃያ አንድ በዚች ዕለት የአዳምና የዘሩ ድኅነት የተደረገባት አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የታላቁ በዓል መታሰቢያና በዓለም ሁሉ የቤተ ክርስቲያን መታነፅ መታሰቢያ ነው። ከሁሉ አስቀድሞ ያቺ ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት ዘመን ብቻዋን ታነፀች።
ይኸውም ጳውሎስና በርናባስ በአሕዛብ ውስጥ በሰበኩ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ከሰዎች ቤቶች በቀር ቅዱስ ቊርባንን የሚቀበሉበት ቤተ ክርስቲያንም አልነበራቸውም ነበር። ስለዚህም ወደ ጴጥሮስና ወደ ሐዋርያት ሁሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን መታነፅ ጉዳይ እየለመኑ መልእክትን ላኩ።
ሐዋርያትም እንዲህ ብለው መለሱላቸው ክብር ይግባውና ያለ ጌታችን ፈቃድ እኛ ምንም ምን አንሠራም። ነገር ግን የምንሠራውን እስኪያስረዳን ድረስ ወደ እግዚአብሔር እየጸለዩና እየማለዱ አንድ ሱባኤ ይጾሙ ዘንድ ወደ ሃይማኖት የተመለሱ አሕዛብን እዘዙአቸው እንዲህም አዘዙአቸው።
በሱባዔውም ፍጻሜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጸላቸው ሐዋርያትንም ሁሉ ከየአገሮች ሁሉ እስከ ፊልጵስዮስ በደመና ሰበሰባቸው ከእርሳቸውም ጋር ጳውሎስና በርናባስ ነበሩ ጌታችንም ባረካቸው እንዲህም ብሎ ነገራቸው "ይቺ ዕለት በእናቴ በማርያም ስም በአራቱ ማእዘነ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት እንድታንፁ የፈቀድኩባት ናት።"
ይህንንም ብሎ ከከተማዋ በስተ ምሥራቅ በኲል አወጣቸው የቤተ ክርስቲያኒቱንም ቦታና መሠረቷን ወሰነላቸው ከእርሳቸውም ጋራ የእግዚአብሔር ኃይል ነበረ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንፃዋ እስከ ተፈፀመ ድረስ ደንጊያዎች በሐዋርያት እጆች ውስጥ ይለመልሙ ነበረ ጌታችንም ነዋየ ቅድሳቷን አልባሳትዋንና መሠዊያዋን አዘጋጀ።
ከዚህ በኋላ ጌታችን እጁን በጴጥሮስ ራስ ላይ ጭኖ በአራቱ ማእዘነ ዓለም ውስጥ "አርሳይሮስ" ብሎ ሾመው ይህም "ሊቀ ጳጳሳት" ማለት ነው። ለሐዋርያት አለቃ ጴጥሮስ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የጳጳሳት አለቃ ይሆን ዘንድ ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል እያሉ ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን ሰዎች ሦስት ጊዜ አሰምተው ተናገሩ።
ከዚህም በኋላ ጌታችን ሐዋርያትን የቊርባኑን ቅዳሴ ሥርዓት ያከናውኑ ዘንድ ለሕዝቡም ሥጋውን ደሙን ያቀብሏቸው ዘንድ አዘዛቸው እንዲህም የሚል አለ ራሱ መድኃኒታችን ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን ለሐዋርያት አቀበላቸው። እንዲህም አላቸው በዚች ቀን የእጃቸውን ሥራ እንዳይሠሩ ሕዝቡን ሁሉ እዘዙአቸው ይኸውም በሰኔ ወር ሃያ አንድ ቀን ነው።
ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን ከእርሳቸው ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ከዚያችም ቀን ጀመሮ አባቶቻችን ሐዋርያት በዓለሙ ሁሉ ውስጥ አምላክን በወለደች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን የሚያሳንፁ ሆኑ።
በቂሣርያው ሊቀ ጳጳሳት በባስልዮስ ዘመን እንዲህ ሆነ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን በሠራ ጊዜ በውስጡ የእመቤታችን የማርያምን ሥዕል ይሥልበት ዘንድ ሠሌዳ ፈለገ ሰዎችም በአንድ ባለጸጋ ዘንድ ስለ አለ አንድ መልካም ሠሌዳ ነገሩት።
ቅዱስ ባስልዮስም ሠሌዳውን እንዲሰጠው ወደ ባለጸጋው ላከ ባለጸጋውም ይህ ሠሌዳ ለልጆቼ ነው አለ እንጂ ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚያም አልፎ በመድፈር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ የስድብ ቃል ተናገረ ወዲያውኑም በድንገት ወድቆ ሞተ ልጆቹም ፈሩ ያንንም ሠሌዳ ከብዙ ወርቅና እንቊ ጋራ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ አምጥተው የአባታቸውን በደል ያቃልልለት ዘንድ ለመኑት።
ቅዱስ ባስልዮስም ያንን ሠሌዳ ወስዶ የእመቤታችንን ሥዕል ይሥልበት ዘንድ ለሠዓሊ ሰጠው። እመቤታችንም ቅድስት ድንግል ማርያም በሌሊት ራእይ ለቅዱስ ባስልዮስ ተገለጸችለት ሥዕሏንም በዚያ ሠሌዳ ላይ እንዳይሥል ከለከለችው። ከዐመፀኛ ሰው እጅ ወስዶታልና። እጅግም ያማረ የእመቤታችን ሥዕሏ የተሣለበት የሁለት ደናግልም ሥዕል ያንዲቱ በቀኝ ያንዲቱ በግራ ሆኖ የተሣለበት ቀይ ሠሌዳ ያለበትን ቦታ ነገረችው።
ቅዱስ ባስልዮስም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ አመለከተችው ወደዚያ ቦታ ሔደ ያንንም ሠሌዳ አገኘው ወደዚያች ቤተ ክርስቲያንም በታላቅ ደስታ አመጣው።
ከዚህም በኋላ ዳግመኛ በአንድ ጣዖት ቤት ሁለት ምሰሶዎች እንዳሉ አስረዳቸው እነርሱንም አምጥቶ በመቅደሱ ፊት ለፊት እንዲአቆማቸው በላያቸውም ሥዕሏን እንዲያኖር አዘዘችው።
ቅዱስ ባስልዮስም እነዚያን ምሰሶዎች ያመጣቸው ዘንድ ሔደ መሠርያኑም ሊከለክሉት ፈለጉ ጌታችንም ኃይላቸውን ደመሰሰ እነዚያንም ምሰሶዎች አምጥቶ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አቆማቸው በላያቸውም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕሏን አስቀመጠ እግዚአብሔርም ከእነዚያ ምሰሶዎች በታች የውኃ ምንጭ አፈለቀ በውስጥዋም የሚታጠብ ሁሉ ከአለበት ደዌ ሁሉ የሚድን ሆነ።
እንዲሁም ከእመቤታችን ማርያም ሥዕል በሽተኞችን ሁሉ የሚፈውስ የዘይት ቅባት ፈሰሰ ይህ ሁሉ የሆነ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በከበረችበት በሰኔ ወር በሃያ አንድ ቀን ነው።
በዚያችም ቀን እንዲህ ሆነ አንዲት ሴት መጥታ ታጠበች ወዲያውኑም ሁለመናዋ በለምጽ ተሸፈነ ቅዱስ ባስልዮስም ወደርሱ አስቀርቦ በእርሷ ላይ የሆነውን ጠየቃት እርሷም የእኅቷን ባል እንደወደደችና እኅቷን በመርዝ ገድላ እንዳገባችው ነገረችው። ቅዱስ ባስልዮስም ታላላቅ ሦስት ኃጢአቶችን ሠራሽ ግን ወደ እግዚአብሔር ንስሐ ግቢ ምንአልባት በደልሽን ይቅር ይልሽ እንደ ሆነ አላት በዚያን ጊዜም ምድር ተሠንጥቃ እንደ ዳታን ዋጠቻት እርሷ የረከሰች ስትሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባትን ደፍራለችና።
እኛ ሁላችን የክርስቲያን ወገኖች አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለከበረች ድንግል ማርያም ለመታሰቢያዋ መንፈሳዊ በዓልን ልናደርግ ይገባናል ሰለ እርሷ ለአዳምና ለሁላችን ለልጆቹ ድኅነት ሆኖአልና ይህንንም በዓል ለማድረግ የሚተጋ የተመሰገነ ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት
ዳግመኛም በዚህች ቀን ከምስር አገር ቅዱስ ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ከእንዴናው ገዥ ከአርያኖስ ጭፍራዎች ውስጥ ነበር ሰው ሁሉ ጣዖታትን እንዲያመልክ የሚያዝ የዲዮቅልጥያኖስ የመልእክት ደብዳቤ በተነበበ ጊዜ ይህ ቅዱስ ከሕዝቡ መካከል ተነሥቶ የንጉሡን ደብዳቤ ወስዶ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም ብሎ የከሀዲውን ንጉሥ የመልእክት ደብዳቤ ቀደደ።
መኰንኑም ድፍረቱን አይቶ ወደርሱ ገሥግሦ ሔደና የራሱን ጠጉር ይዞ አንሥቶ በምድር ላይ ጣለው ታላቅ ድብደባም እንዲደበድቡት አዘዘ ሁለተኛም ሁለመናው እስቲደቅ እንዲደቁሱት አዘዘ እርሱም የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ እያለ ይጮኽ ነበር።
ጌታችንም ትዕግሥቱን አይቶ መልአኩን ልኮ ከሥቃዩ አድኖ ጤነኛ አደረገው ወደ መኰንኑም ቀርቦ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከአንዱ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለምና አንተ ከሀዲ እፈር አለው።
ያን ጊዜም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው በመጋዝም መግዞ ሰቀለው ከዚያም በኋላ ሥጋው እንደ ሰም ቀልጦ እንደ ውኃ እስቲፈስ በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰለው ከከተማ ውጪም ጣሉት።
ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለምንም ጉዳት አንሥቶ ጤነኛ አደረገው። ወደ መኰንኑም ተመልሶ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለምና አንተ ከሀዲ እፈር ብሎ ጮኸ። ይህንንም ድንቅ ተአምር አይተው ቁጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።
መኰንኑም ማሠቃየቱ በሰለቸው ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። የድል አድራጊነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ከላድያኖስ
በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አራተኛ የሆነው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ከላድያኖስ አረፈ። ይህም ቅዱስ በወንጌላዊው ማርቆስ እጅ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ እርሱም ዲቁናን ሾመው ደግሞም ቅስናን ሾመው የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርትና ሕግ ጠንቅቆ ተማረ።
አባ ሜልዮስም በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ዐሥራ አንድ ዓመት ያህል በቀናች ሃይማኖት እያጸናቸው በትምህርትና በምክር ሁሉ እንደሚገባ የክርስቶስን መንጋዎች ጠበቀ። ልዑል እግዚአብሔርንም አገልገሎ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ሐዋርያው ቶማስ
በዚችም ቀን ሐዋርያው ቶማስ በመሸታ ቤት ባረድዋት በአንዲት ሴት ላይ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ነው።
አንድ ጎልማሳ በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ እጅ የተባረከ እንጀራን ከሕዝቡ ጋር ተቀብሎ ሊበላ ሲል እጆቹ ፈጽመው ደረቁ፡፡ እርሱንም ያዩት ሰዎች በዚህ ጎልማሳ ላይ የሆነውን ነገር ለሐዋርያው ነገሩት፡፡ ቅዱስ ቶማስም ልጁን ጠራውና ‹‹ልጄ ሆይ! የእግዚአብሔር ቸርነት በግልጽ ዘልፎሃልና ያደረከውን ነገር ንገረኝ?›› አለው፡፡ ጎልማሳውም ከሐዋርያው እግር ሥር ወድቆ ሰገደና ‹‹መልካም ሥራ የሠራሁ መስሎኝ ክፉ ሥራን ሠርቻለሁ፡፡ ይኸውም አስቀድሜ ወደ አንዲት የጠጅ አበዛ ሴት ልጅ እገባ ነበር፡፡ አንተም በንጽሕና እንድንኖር አስተማርኸን፤ ያችም ሴት አብሬያት እተኛ ዘንድ ነዘነዘችኝ፡፡ ስለዚህም ሰይፍ አንሥቼ አረድኳት›› አለው፡፡ ሐዋርያውም ‹‹እንዴት እንዲህ ያለ ቁጣና የአውሬ ሥራን ትሠራለህ?›› ብሎ ከገሠጸው በኋላ ውኃ አስቀርቦ በላዩ ጸለየበትና ጎልማሳውን ‹‹በዚህ ታጠብ ትድናለህ›› አለው፡፡ ጎልማሳውም በውኃው በታጠበ ጊዜ የደረቁ እጆቹ ዳኑ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቶማስ ‹‹የዚያቸ ሴት በድን ወዳለበት ቦታ ምራኝ›› አለው፡፡ ጎልማሳውም መርቶ ከቦታው አደረሰው፡፡ ሐዋርያውም በድኗን ባየ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ ወደ ውጭ አውጥተው በአልጋ ላይ እንዲያኖሯት ካዘዘ በኋላ እጁን በላይዋ ጭኖ ጸለየ፡፡ ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ጎልማሳውን ‹‹ሂድ እጇን ይዘህ ‹እኔ ቀድሞ በእጄ ገደልኩሽ፣ አሁን ግን በሃይማኖት በእኔ እጅ ክርስቶስ ያስነሣሽ› በላት›› አለው፡፡ ጎልማሳውም ቅዱስ ቶማስ እንዳዘዘው ባደረገ ጊዜ ፈጥና ከሞት ተነሣች፡፡ ከአልጋዋም ፈጥና ወርዳ ከቅዱስ ቶማስ እግር ሥር ወድቃ ሰገደችለት፡፡
ቅዱስ ቶማስም ለሞተች በኋላ የት እንደነበረች ያችን በሕዝቡ ሁሉ ፊት ጠየቃት፡፡ እርሷም በሲኦል እንደነበረችና በዚያም ያሉትን ልዩ ልዩ የሆኑ እጅግ ጽኑ ሥቃዮችን ሁሉ በዝርዝር ለሕዝቡ አስረዳች፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ከዚያ የነበሩትን ‹‹ይህች ሴት ሞታ እንደነበር አይታችኋል፣ አሁንም አይታ የምትመሰክረውን ሰማችሁን? በሲኦል ያለው ሥቃይ ብቻ አይደለም ነገር ግን ከዚህ የሚከፋ አለ፡፡ እናንተም የኃጢአትን ሥራና ክፉ ሀሳብን ትታችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፡፡ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ፍቅርንና ንጽሕናን ጠብቁ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን ትቀበላላችሁ›› አላቸው፡፡ ሕዝቡም ሁሉ በክብር ባለቤት በጌታችን አመኑ፡፡ ለድኆቸም ምጽዋትን ሊሰጡ ብዙ ገንዘብ ሰብስበው አመጡ፡፡ ለድኆች ምጽዋት መስጠት ለሐዋርያው ልማዱ ነበርና፡፡ ወሬውም በሀገሩ ሁሉ ተሰማና ሕመምተኞችን ሁሉ ሰብስበው አምጥተው በፊቱ ጣሏቸው፡፡ ቅዱስ ቶማስም ሁሉንም ፈወሳቸው፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ ልመናዋ በረከቷም ወንዶችና ሴቶች ባሮቿ ከሆን ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ይኑር፣ በቅዱሰኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages