አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሰኔ አራት በዚህችም ዕለት ሐራቅሊ ከሚባል አገር ቅዱስ አባት ዮሐንስ አረፈ፣ ተጋዳይ የሆነች ቅድስት ሶፊያ በሰማዕትነት አረፈች፣ በልኪም ከሚባል አገር ቅዱስ ሳኑሲ በሰማዕትነት ሞተ፣ የአርቃድዮስ የዲሙናስያ የአሞኒና የሚናስ የገድላቸው ፍጻሜ ሆነ።
ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ
ሰኔ አራት በዚህችም ዕለት ሐራቅሊ ከሚባል አገር ቅዱስ አባት ዮሐንስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ አባት ስሙ ዘካርያስ ነው እርሱም የጳንጦስና የአብልያ ሀገሮች ገዢ ነበር የእናቱም ስም ኤልሳቤጥ ነው እነርሱም ይህን የተባረከ ልጅ በተሰጡ ጊዜ ስሙን ዮሐንስ ብለው ጠሩት እርሱ ከአባቱና ከእናቱ ጀምሮ ከመጥምቀ አምላክ ዮሐንስ ጋራ በስም አንድ ሁኗልና በተግሣጽና በፈሪሀ እግዚአብሔር አሳደጉት የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ሂሣቦችንና ጥበቦችን ሁሉ አስተማሩት እናቱም በዘመኗ ሁሉ ከእግዚአብሔር መንገድ እንዳይወጣ ታማፅነው ነበር። አባቱም እንዲሁ ይመክረውና ያስተምረው ነበር።
ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ የሃያ ዓመት ልጅ ሲሆን መስፍን ሆነ የጳንጦስና የሐራቅሊ ሌሎችም አገሮች ሁሉ ተገዙለት።
እንዲሁም እያለ የመልአክ አምሳል ሰይጣን ታየው እንዲህም አለው አንተ ትነግሥ ዘንድ ወደ አንጾኪያ ሒደህ የንጉሥ ኑማርያኖስን ልጅ አግባ ብሎ ጌታ አዝዞሃል አለው ቅዱሱም በውኑ ይህ መልአክ ነውን ግን ከአፉ የእግዚአብሔር ስም ከሰማሁ አንጾኪያ እሔዳለሁ አለ።
ከዚህ በኋላም ወደ አንጾኪያ ከተማ ሔደ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስንም ተገናኘው ንጉሡም በአየው ጊዜ አከበረው እጅግም ወደደው። በማግሥቱም በምሳ ላይ ከእርሱ ጋራ እያለ ከሃድ ድዮቅልጥያኖስ አጵሎንን ያመጡት ዘንድ አዘዘ ያንንም ጣዖት ባመጡት ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ አቃለለው ስለዚህም ሥራ ንጉሡን ረገመው ሰደበውም።
ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም ቅዱስ ዮሐንስ ያደረገውን በአየ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ በእሥር ቤት አሠረው። በእሥር ቤትም ሳለ ክብር ይግባውና ጌታችን በብርሃን ሠረገላ ላይ ሁኖ ታየዉ ከእርሱ ጋራም መላእክት አሉ። ይዞም ሳመው ብዙዎች ቃል ኪዳኖችንም ሰጠው። በማግሥቱም ንጉሡ ልኮ ከእሥር ቤት አወጣዉ ወደ ርሱም አቀረበውና ለአጵሎንና ለአርዳሚስ ስገድ አለው ቅዱሱም የሰው እጅ ለሠራው እንዴት እሰግዳለሁ አለው ንጉሡ ግን ከእርሱ ጋር መታረቅ ሽቶ ብዙ የሽንገላ ነገርን ተናገረው።
ከዚህም በኋላ ግብርን ያስገብር ዘንድ ከሹመት ጋራ ወደ ግብጽ አገር ላከው ወደ ግብጽ ገዢ ወደ ስርያቆስም ስለ ርሱ እንዲህ ሲል ጽፎ ላከ እነሆ ለዮሐንስ ዘሐራቅሊ ግብር በማስገበር የአማልክትንም ቤቶች አፍርሶ አዲስ እንዲአሠራ ከግብጽና ከኢየሩሳሌም እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁ።
ቅዱሱም ይህን ምክንያት ይዞ የጣዖታትን ቤቶች አፍርሶ ተዋቸው። በዚያም ወራት ወኰንኑ ስርያቆስ የሰማዕታትን ራስ መቆረጥን ሊያዝዝ በፍርድ አደባባይ ተቀመጠ በዚያን ጊዜ ከስዒድ ዲዮስቆሮስ፣ ቢፋሞን፣*አሕራጋኖስ፣ ኪሮስ፣ ዮልዮስ፣ እለእስክንድሮስ፣ ዮሴፍ ፣ይስሐቅና፣ እስጢፋኖስ የሚሉአቸው ሰዎች መጥተው እሊህ ሁሉም እኛ ክርስቲያኞች ነን እያሉ በግልጥ ጮኹ ያን ጊዜ መኰንኑ ይዞ ያለርኅራኄ ያሠቃያቸው ጀመረ።
ቅዱስ ዮሐንስም ይህን በአየ ጊዜ የሹመቱን ሥራ ትቶ እኔ ክርስቲያን ነኝ ብሎ በግልጥ ጮኸ መኰንኑም ተቆጥቶ በእግር ብረት እንዲአሥሩትና ወደ እንድና አገር ወደ መኰንኑ አርያኖስ እንዲወስዱት አዘዘ እርሱም ስለሆነው ሁሉ መረመረው ከቃሉ መልስም የተነሣ ተቆጣ በባላ እንጨት ላይ ሰቅለው በመንኰራኲር አጣብቀው እንዲጨምቁት ከዚያም ከባላው አውርደው ሥጋው እስኪቀልጥ ሆዱ ላይና ራሱ ላይ በቀጭኔ እንዲደበድቡት አዘዘ ምድሪቱም በደሙ ተመላች ከዚያም ወደ እሥር ቤት አስገቡት።
ከጥቂት ቀኖች በኋላም በማረጃ ቢላዋ ቆዳውን ገፈው ቁስሉን በማቅ ያሹት ዘንድ ዳግመኛም አመድ ጐዝጉዘው በላዩ የእሳት ፍም ከጐኑ በታች አድርገው በላዩ እንዲአስተኙት አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት።
ሁለተኛም በእሳት የጋሉ የብረት ችንካሮችን አምጥተው በፊቱ ላይ በጀሮዎቹም ላይ እንዲያኖሩዋቸው አዘዘ እንዲህም አድርገው ከወህኒ ቤት ጨመሩት። በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾለት ሰላምታ ሰጥቶ አጸናው። በማግሥቱም ከወህኒ ቤት አውጥተው በጋሉ ብረት ዘንጎች ደበደቡት።
ከዚህም በኋላ ግንባሩን ወደ ምድር ደፍተው እጆቹንና እግሮቹን ከፈረስ ጭራ ላይ በገመድ አሠሩ። ከዚህ በኋላም ባለ ሰይፍ ወጥቶ እግሮቹንና እጆቹን ራሱንም ቆረጠ እንዲህም የምስክርነቱን ተጋድሎ ፈጽሞ የድል አክሊልን ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ሶፊያ ሰማዕት
በዚህችም ዕለት በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን ተጋዳይ የሆነች ቅድስት ሶፍያ አንገቷን በመቆረጥ በሰማዕትነት አረፈች። የዚች ቅድስት ወላጆቿ ክርስቲያን ነበሩ በወለዱዋት ጊዜም በመልካም አስተዳደግ እግዚአብሔርን በመፍራት የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት የአባቶቻችን ሐዋርያትንም ሕግና ሥርዓት ሁሉ እያስተማሩ አሳደጓት።
ከዚህ በኋላም በአደገች ጊዜ ወላጆቿ ለአንድ መስፍን ልጅ ሊአጋቧት ፈለጉ ቅድስቲቱም ይህን በመንፈስ ቅዱስ ዐውቃ ከተቀመጠችበት ተነሥታ ፊቷን ወደ ምሥራቅ መልሳ መቶ ስግደትን ሰገደች ቆማም ረጅም ጸሎትን ጸለየች በጸሎቷም ውስጥ እንዲህ አለች የክብር ባለቤት የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ወዳንተ የምደርስባት የከበረችና የቀናች መንገድህን ለእኔ ለባርያህ ለሶፍያ ምራኝ ወደ ጥፋት በሚወስድ በጠማማ መንገድ እንድንከራተት አትተወኝ የሚጠፋውንም ዓለም ያስብ ዘንድ ልቤን አትተወው ወላጆቼ በሚመክሩብኝም በረከሰ በሥጋ ፍትወት ውስጥ የኃጢአት ባሪያ እንድሆን አቤቱ አትተወኝ የከበደ የዓለማዊ ፍላጎት ሸክምን ተሸካሚ አታድርገኝ ቀላልና ልዝብ የሆነ ቀንበርህን ይሸከም ዘንድ ትክሻዬን ዘንበል አድርገው እንጂ።
ጸሎቷንም ከፈጸመች በኋላ በዐልጋዋ ላይ ተቀመጠች ጥቂትም ቆይታ እንዲህ የሚል ሃሳብ መጣባት ተነሥቼ በሥውር ልውጣ ወደ ሩቅም ሒጄ ከበረሀ ውስጥ ገብቼ ለልዑል አምላክ ላገልግል።
ከዚህም በኋላ ወላጆቿ የሰጧትን የምታገለግላትን ብላቴናዋን ጠራች ወይን አምጥታ እንድታጠጣትም አዘዘቻት በአመጣችላትም ጊዜ እርሷ ጥቂት ቀምሳ ያመጣችው ወይን እስቲያልቅ ትጠጣ ዘንድ ብላቴናዋን አዘዘቻት። ከስካርም የተነሣ ልቧ በተሰለበ ጊዜ ልብስሽን አምጪ የእኔንም ልብስ ወሰጂ አለቻትና ሰጠቻት የወይኑ ስካር አእምሮዋን ነሥቷታልና ተኚ አለቻት በላይዋም እንቅልፍ በከበዳት ጊዜ ማንም ሳያያት ቅድስት ሶፍያ በሥውር ወጣች ከወላጆቿ ማደሪያ የራቀ ነበርና።
ርቃ በሔደችም ጊዜ በተራራና በዋሻዎች ውስጥ ሊሠወሩ ፈልገው በሃይማኖት ምክንያት ከከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ፊት የሚሸሹ ሰዎችን አገኘች እናንተ ከወዴት ናችሁ ብላ ጠየቀቻቸው የየአንዳንዳቸውን አገራቸውን ነገሩዋት ደግማ ወዴት ትሔዳላችሁ አለቻቸው እነርሱም ስለሃይማኖት ከዲዮቅልጥያኖስ የሆነውን ሁሉ ነገሩዋት።
ይቺ መንገድ ወደ ዲዮቅልጥያኖስ ታደርሰኛለችን አለቻቸው አዎን ታደርስሻለች አሏት። ከዚያም ጥቂት ተጉዛ ቁማ ረጅም ጸሎትን ጸለየች ወደ ዲዮቅልጥያኖስም ደርሳ ክብር ይግባውና ክርስቶስን የምታመልክ ክርስቲያን እንደሆነች በፊቱ ታመነች። ዲዮቅልጥያኖስም የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስን ስም በሰማ ጊዜ ቁጣን ተመላ ወደርሱም እንዲአቀርቧት አዘዘ በቀረበችም ጊዜ ለአጵሎን ስገጂ አላት የሰው እጅ ለሠራው ለረከሱ የአጋንንትም ማደሪያ ለሆነው እንዴት እሰግዳለሁ አለችው።
ይህንንም ከእርሷ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ከብረት በተሠራ ጅራፍም እንዲገርፏት አዘዘ ሁለተኛም በአንገቷ ከባድ ደንጊያ አሥረው ሥጋዋ ተቆራርጦ እስቲወድቅ ድረስ በከተማው ጥጋጥግ እንዲጎትቷት አዘዘ ይህንንም አድርገው ወደ ወህኒ ቤት አስገቧት።
በማግሥቱም ያመጧት ዘንድ አዘዘ በመጣችም ጊዜ በክፉ አሟሟት እንዳትሞቺ ለአጵሎን ሠዊ አላት እርሷም ክፉ ሞትስ ለአንተ ነው የእኔስ ከአንተ የሚገኘው ሞት በፈጣሪዬ ዘንድ ሕይወት ነው አለችው እርሱም ከገደልኩሽ በኋላ ድነሽ ትነሺአለሽን አላት አንተ ሰነፍ የእኔን ተወውና ለአንተም የደይን ትንሣኤ አለህ አለችው።
ይህንንም በሰማ ጊዜ ዐጥንቶቿ ሁሉም እስቲሰበሩ በብረት በትሮች እንዲደበድቧት አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉባት። ዳግመኛም በብረት ዐልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቿ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ ቀኑ በመሸ ጊዜ ወደወህኒ ቤት እንዲአስገቧት አዘዘ በዚያችም ሌሊት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ገላዋን በመዳሠሥ አዳናት።
በማግሥቱም ያመጡአት ዘንድ አዘዘ እርሷም ምንም ሕማም እንዳላገኛት ሁና በእግርዋ መጣች ከመታጠቢያ ቤት ታጥባና ተቀብታ የወጣች ትመስል ነበር ንጉሡም ደኅንነቷን አይቶ አደነቀ የዚችን ክርስቲያን ሴት የሥራይዋን ጽናት እዩ ትላንት በእሳት አሠቃይተናት ነበር ዛሬ ድናለች አለ። እርሷም ሥራይንስ አላውቅም ነገር ግን ፈጣሪዬ ሥራይን የሚሽር ነው አለችው።
ከዚህም በኋላ እሽ ያሰኛት ዘንድ ሊሸነግላት ጀመረ እምቢ በአለችውም ጊዜ ራስዋን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ሊቆርጧትም ይዘዋት ሲሔዱ ክብር ይግባውና ጌታችን ተገለጸላት ብዙ ቃል ኪዳኖችንም ሰጣት በማይታበል ቃሉም መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ በስምሽም የሚመጸውተውን የገድልሽንም መጽሐፍ የሚጽፈውን ሁሉ እቀበለዋለሁ መንግሥተ ሰማያትንም አወርሰዋለሁ አለ። ከዚህ በኋላም አንገቷን በሰይፍ ቆረጡ በጌታችንም ዘንድ የድል አክሊልን ተቀበለች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ሳኑሲ ሰማዕት
በዚህች ቀን በልኪም ከሚባል አገር ሳኑሲ በሰማዕትነት ሞተ። ይህ ቅዱስ በልጅነቱ የአባቱን በጎች ሲጠብቅ ምሳውን ለእረኞች ሰጥቶ እርሱ ሁልጊዜ እስከ ማታ ይጾም ነበር ዘመዶቹም የሚሠራውን አያውቁም ነበር። የታመሙ በሽተኞችንም ይጐበኛቸው ነበር።
በአንዲት ሌሊትም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ሳኑሲ ሆይ የክብር አክሊልን ትቀበል ዘንድ ተነሥተህ ወደ መኰንኑ ሒድ ክብር ይግባውና በፈጣሪህ ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመን አለው። በነቃም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ እንደተገለጸለትና እንዳዘዘው ለእናቱ ነገራት እርሷም አዘነች አለቀሰችም ነገር ግን ትከለክለው ዘንድ አልተቻላትም።
ከዚህ በኋላ ስብራ በሚባል አገር ስሟ ማርያ የሚባል ድኆችንና መጻተኞችን የምትቀበልና የምትመግባቸው የተቀደሰች ሴት እንዳለች ስለርሷ ሰምቶ ወደርሷ ሔደ። በሰማዕትነትም ይሞቱ ዘንድ ከርሷ ጋራ ተስማማ።
አርሳኖስ ወደ ሚባልም መኰንን በአንድነት ሔዱ በምስር ወደብ በመርከብ ውስጥ ሁኖ አገኙትና እኛ ክርስቲያኖች ነን ብለው በፊቱ በግልጥ ጮኹ በየራሱ በሆነ ሥቃይም እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ ቅድስት ማርያም በሥቃዩ ውስጥ ሳለች ነፍሷን አሳልፋ ሰጠች የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለች።
ቅዱስ ሳሉሲ ግን ክብር ይግባውና በላዩ በአደረው በጌታችን በኢየሱስ ኃይል የሚታገሥና የሚጸና ሆነ። መኰንኑም ማሠቃየቱን በሰለቸው ጊዜ ወደ እንዴናው መኰንን ከብዙዎች እሥረኞች ሰማዕታት ጋራ ላከው እርሱም ያሠቃየው ጀመረ ተረከዙንም ሠንጥቀው ገመድ አግብተው በከተማው ውስጥ እንዲጐትቱት አዘዘ። እንዳዘዛቸውም አደረገ ግን ምንም ጉዳት አልደረሰበትም ።
ሁለተኛም ሥራየኛ አመጣለትና መርዝ በተመላ ጽዋ ሥራዩን አድርጎ ጠጣ ብሎ አዘዘው። ቅዱሱም በላዩ በመስቀል ምልክት አማትቦ ጠጣው ምንም ምን ጉዳት ሳይደርስበት ቀረ።
ከማሠቃየትም በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡት አዘዘና የከበረች ራሱን ቆረጡት የድል አክሊልንም ተቀበለ መሠርዩም አምኖ በሰማዕትነት ሞተ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አርቃድዮስና ባልንጀሮቹ
በዚህችም ቀን የአርቃድዮስ የእኅቱ የዲሙናስያ የግብጻውያኑ የአሞኒና የሚናስ የንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ጭፍሮችም የገድላቸው ፍጻሜ ሆነ። እሊህን ቅዱሳን በእሳት ምድጃ ውስጥ ከአባ ብሶይ ጋራ በጨመሩዋቸው ጊዜ የመላእክት አለቃ ገብርኤል መጥቶ ከነበልባሉ መካከል አወጣቸው።
ወደ ንጉሡም ደርሰው ረገሙት እንዲህም አሉት የምስክርነት ሞት ፍጻሜያችንን የማትጽፍ ከዕለት ወደ ዕለት ለምን ትከፋለህ። ንጉሡም ሰምቶ ተቆጣ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡና ሥጋቸውን በእሳት እንዲያቃጥሉ አዘዘ እንደዚህም የምስክርነታቸውን ተጋድሎ ፈጽመው የክብር አክሊልን ተቀበሉ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን። በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ
No comments:
Post a Comment