ግልጽ የአደባባይ ጥያቄ ከመምህር ፋንታሁን ዋቄ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, June 16, 2023

ግልጽ የአደባባይ ጥያቄ ከመምህር ፋንታሁን ዋቄ

 ግልጽ የአደባባይ ጥያቄ ከመምህር ፋንታሁን ዋቄ (ምእመናን ሁሉ አንዲማሩበት መልሱንም በአደባባይ እንዲሰጥ በትሕትና እለምናለሁ)



ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የፍትሐ ነገሥት፥ የሐዲሳት፥ የቤተክርስቲያን ታሪክ ሊቃውንት ሁሉ ትድረስልኝ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።
ጉዳዩ፦ የግንቦት ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፥ በተለይ በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የተወሰነው ውሳኔን ይመለከታል፦
የሚከተሉት 12 ጥያቄዎች በምእመናን የሚጠየቁና ለእኔም ጥያቄዎች በመሆናቸው፥ በቤተክርስቲያን ሕግና ሐዋሪያዊ አስተምህሮ፥ ትውፊትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳትሆን መላው የአኀት አቢያተክርስቲያናት ከሚመሩበት ሥርዓትና ዶግማ አንፃር ምላሽ በመስጠት ልባችንን እንድታሳርፉልን በእግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ፦
1. በትግራይ ገዳማት ሲፈርሱ ዝም ያለው ሲኖዶስ ዛሬም ጥንታውያንገዳማት በዐቢይ መድፍ ሲፈርሱ ቆሞ መመልከቱን የሚመለከት ምእመን ጳጳሳቱ ካማን ወገን አድርጎ መመልከት ይጠበቅበታል?
2. ሲኖዶሱ የሊቃውንቱን ፣የካህናቱን እና የምእመናን ድምጽ የማይሰማ እና የማያሳትፍ ከሆነ አሁን ያላው ሲኖዶስ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ አባቶች አይደሉም ወደ ማለት የሚያሸጋግር ፈተናን በምእመናን አእምሮ የመፍጠር እድሉ ምን ያህል ነው?
3. ደርግ እግዚአብሔር የለም ሲል ዝም ያለው፤ ሕወሐትና ኦነግ ክርስቲያኖችን በሰፈር ተካፍለው ከጥምቀት ልጅነት ቤተስብነታቸው ሲለዩአቸው በዝምታ የተመለከተ፥ ብልጽግና/ኦሮሙማ የፖለቲካ ማንነት ከእምነቶች ሁሉ ይበልጣል ብሎ ሲያውጅ፥ የጫካ ሲኖዶስ ሲመሠርት በቀጥታ የማውገዝና ምእመናን እንዳይከተሉት ጥሪ ማድረግ ያልቻለ ሲኖዶስ አረኝነቱን በምን ይመዘናል?
4. የኢአማኒያን ዘንዶ ሁሉንም ሊውጥ አፉን በከፈተበት፥ ምእመናን በሚሳደዱበትና እንደቅጠል በገዛ መንግሥታቸው ጦርና ጫካ በተቀመጠው አጥፊ በሚረግፉበት በዚህ ወቅት ጉንዳኑ ንክሻ መጨነቅ፥ የጵጵስና ክብሩን ሽቶ ኃላፊነቱን መሸሽ/መርሳት የሚበዛው ኪሣራው ነው ወይስ ትርፉ?
5. ስለ መንጋው እራሱን የሚሰጥ እንጂ በጎቹ ተሰውተው ክብሩን/ምቾቱን የሚጠብቁለት ጳጳስም ካህንም በቤተክርስቲያን ታሪክ ታይቶ ይታወቃል?
6. የሐዋርያት ጉባኤ ያወገዘውን፤ የሠለስቱ ምእት ጉባኤ የደነገገውን ሃይማኖታዊ ቀኖና በሆደ ሰፊነት፥ በታጋሽነት ስም ማፍረስ ይቻላል?
7. በሐዋርያት ጉባኤ፤ በሰለስቱ ምእት ጉባኤ የተወገዙ የተለዩና ጸያፍ የሆኑ ይሁዳዊነት፤ ሲሞናዊነት፤ ዴማሳዊነት ጸረ ክርስትና ጠባያትን የሚታገስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ነው ብሎ መቀበል ለምእመናን ክርስቲያናዊ ግዴታቸው ሊሁን ይችላል?
8. ከዚህ ከግንቦቱ የቤተክርስቲያናችን የሲኖዶስ ጉባኤ ውሰኔ በመነሳት ሐውርያው አትናቴዎስ በስደት የተንገላታው፤ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጥርሱ የወለቀው፤ ጺሙ የተነጨው በስደት ያረፈው ፤ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በስደት በግዞት የተንገላታው እና ያረፈው እና ሌሎችም ሰማዕታተ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በስለት እና በእሳት የተሰቃዩት፤ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ በጣሊያን መትረጊስ የተጨፈጨፉት ሆደ ሰፊ መሆን አቅቷቸው እና ትእግሥት የለሽ ስለሆኑ ነው ብለን መደምደም እንችላለን?
9. የሊቃውንት ጉባኤ ያቀረበውን ሐሳብ ውድቅ አድርጎ በጠ/ሚ ቀኖና እና ትእዛዝ ቤተ ክርስቲያንን ማቅ ያለበሷትን ከቀኖና ውጭ በድርድር መቀበል ከኦርቶዶክሳዊት ቅደስት ቤተክርስቲያን የቅድሰትነት ባሕርይ ጋር ይስማማል?
10. ወደ 10 ሺ ምእመናን ሂደቱን በፊርማቸው ተቃውመው፥ ሊቃውነቱ ሂደቱ ስሕተት መሆኑን እየተናገሩ፥ ሲኖዶሱ ራሱ በአቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ የተሰራውን የኤጲስ ቆጶሳት ማስመረጫ ደንብ አልቀበልም ብሎ ቁጥር አንድ ወንጀለኛውን ‘አቡነ’ ሳዊሮስን አስመራጭ ኮሚቴ አድርጎ በመምረጥ ሂደቱን በልበ ድንዳነት ማስቀጠሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ሀብት እና ንብረት ብቻ እንደሆነች አያስቆጥርም?
11. አሁን የተቋቋመውን አስመራጭ ኮሚቴ እንደገና በመስፈርቱ መሠረት ማስተካከል ባለመፈለግ የሂደቱ ውጤት በሗላ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚያፈርስ፥ አገርን ለመካፈል ላሰፈሰፉት የአብይ ኦሮሙማ ፖለቲካና ለሕወሐት በር በመክፈት ለሚፈጠር አደጋ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት የሚወስዱት ኃላፊነት ምንድ ነው?
12. ዛሬ እንደትናንቱ ነገሮችን በመሸፋፈን፥ በትወናና በማስመሰል ማሳለፍ በማይቻልበት ሁኔታ ምእመናን ሂደቱ ኢቀኖናዊና የሐዋሪያትን መንገድ የለወጥ መሆኑን በመዋቅ በዚህ ተሰነካክለው ከእምነታው ለሚወድቁት ነፍሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ተጠያቂነታቸው ምን ያህል ነው?
ለማስተማር ለማይታክታችሁ መምህራን በቅድሚያ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages