ጾመ ሐዋርያት(የሰኔ ጾም) - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, June 30, 2023

ጾመ ሐዋርያት(የሰኔ ጾም)


በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት የሐዋርያት ጾም የዐዋጅ ጾም ተብለው ከሚታወቁት ከሰባቱ አጽዋማት ውስጥ አንዱ የሆነውና ከጰራቅሊጦስ (ርደተ መንፈስ ቅዱስ) ቀጥሎ እስከ ሐምሌ አምስት ቀን ድረስ የሚጾም ጾም ነው፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ዓለም ሔደው ወንጌልን ከማስፋፋታቸው በፊት ጹመዋል፡፡ ለስብከተ ወንጌል ወደ መላው ዓለም ሲሰማሩ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ሥጋት ቀርቶላቸው በመላ ሰውነታቸው የተረጋጋ ሕይወትና ሰላም ነግሦባቸዋል፡፡ በምግባር፣ በሃይማኖት ጸንተው በነገሥታት ፊት ያለዕረፍት በድፍረት ቃለ እግዚአብሔርን እያስተማሩና ግፈኞችን እየገሰፁ በጥበዐት ለሰማዕትነት ደርሰዋል ጌታችንም በዚሁ ሥራቸው አክብሮአቸዋል፡፡

ሐዋርያት የጾሙት ጾም የጌታችን አርአያነትና ምሳሌነትን መከተላቸውንም ያሳያል፡፡ ይህ ጾም ሐዋርያት ለአገልግሎት ወደየሀገረ ስብከቶቻቸው ከመሰማራታቸው በፊት ለአገልግሎትም ከመውጣታቸው በፊት እግዚአብሔር መንገዳቸውን እንዲያቃናላቸው ትዕግሥቱን ብርታቱን ማስተዋሉን፣ ጸጋውን፣ ጽባቱን እንዲሰጣቸው ብለው የጾሙት ጾም ነው፡፡
ለማገልገል አገልግለንም ከእግዚአብሔር በረከትን ለማግኘት በአገልግሎት ለመጽናት ፈተናንም ለማለፍ እግዚአብሔር የአገልግሎት ጥበብና ማስተዋልን እንዲሰጠን አገልግሎታችንን በጾም በጸሎት በንስሓ መጀመር አለብን፡፡ ምእመናንም ሐዋርያትን መሠረት አድርገው ይህን ጾም ይጾማሉ፡፡ የሐዋርያት ጾም በአብዛኛው በሰኔ ወር ውስጥ ስለሚጾም የሰኔ ጾም በመባል ይታወቃል፡፡
ሐዋርያት ከጌታ ጋር የዋሉና ያደሩ ከቃሉ ትምህርትን የተማሩ ቅዱሳን አባቶች ናቸው፡፡ ያስተማሩት ት/ትና የፈጸሙት ሥርዓትም ከእርሱ ያዩትን የሰሙትን እና የተማሩትን ነው፡፡ እኛም ዛሬ ይህንን ታሪክ ልንፈጽም ይገባል፡፡
ከክርትቲያናዊ ተግባራት በተለይም ከአገልግሎት በፊት ጾም መቅደም አለበት፡፡ ያለ ጾምና ጸሎት በአገልግሎት መጽናት፣ ፍሬ ማፍራት፣ መከራን መታገሥ፣ በትዕግሥት፣ በጽናት፣ በማስተዋል፣ በፍቅር ማገልገል አይቻልም፡፡ ሐዋርያት አገልግሎታቸውን በዚህ በመጀመራቸው በአገልግሎት ጸንተዋል፣ ምግባርና ሃይማኖትን አፍርተዋል፡፡ መከራንም እስከመጨረሻው ታግሠዋል (ማር 2፡- 20፣ ማቴ 9፡-14)፡፡
ጾም አንድን ክርስቲያን ክርስቲያን ከሚያሰኙት ሥራዎች እና በእግዚአብሔር ዘንድም እንዲወደድ ከሚያደርጉን ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እኔ ክርስቲያን ነኝ እያለ ግን ይህ ጾም የቄሶች ጾም ነው እያለ ምክንያትን የሚያቀርብ ክርስቲያን እርሱ ራሱን መፈተሽ መመርመር ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን ተግባሩ ሐዋርያትን የሚመስል መንፈሳዊ ሰው ነውና፡፡
ሐዋርት አገልግሎታቸውን በጾም በመጀመራቸው አገልግሎታቸው ውጤታማ ሆኗል፡፡ የበለጠ የእግዚአብሔርን አጋዥነት አግኝተዋል፡፡ በአንድ አሳብና ልብ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ራሳቸውን አሳልፈው ለወንጌል ሰጥተዋል፡፡ በአገልግሎት ላይም ያጋጠማቸውን መከራና ፈተናን ሁሉ በትዕግሥት፣ በእምነት እና በጽናትም አልፈዋል፡፡
ምንጭ፡- ጾም ጸሎትና የንስሓ ሕይወት ፳፻፲፫ ዓ.ም

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages