ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 12 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, July 25, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 12

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሐምሌ ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ አባ ሖር በሰማዕትነት ሞተ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል
ሐምሌ ዐሥራ ሁለት በዚህች ቀን የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ የሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። በዚች ቀን የፋርስ ንጉሥ ወደ ሆነ ወደ ሰናክሬም ሠራዊት እግዚአብሔር ላከው ከሰናክሬም ሠራዊትም መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ አርበኞች ወንዶችን ገ*ደለ።
ይህም እንዲህ ነው ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን በከበባት ጊዜ ሕዝቅያስንና ፈጣሪው እግዚአብሔርን እየዘለፈ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ እንዲህም አለ እግዚአብሔር ያድናችኋል እያለ ሕዝቅያስ አያስታችሁ ከእጄ የሚያድናችሁ ማን ነው።
የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስም እጅግ አዘነ ወገኖቹንና ሀገሩ ኢየሩሳሌምንም ያድን ዘንድ ማቅ ለብሶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። እግዚአብሔርም ልመናውን ተቀብሎ ወደ ፋርስ ንጉሥ ወደ ሰናክሬም ሠራዊት የመላእክት አለቃ ሚካኤልን ላከለት። ድንቅ ሥራንም ሠርቶ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ሰዎች ሁሉ አዳናቸው።
ስለዚህም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ የሚካኤልን በዓል መታሰቢያ በዚች ቀን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ሖር
በዚህችም ቀን ስርያቆስ ከሚባል አገር አባ ሖር በሰማዕትነት ሞተ፡፡ አባቱም አንጠረኛ ነበር አንዲት እኅትም ነበረችው። ጐልማሳም በሆነ ጊዜ ሰማዕት ይሆን ዘንድ ወደ ሀገረ ፈርማ ሔደ በመኰንኑም ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ከሥቃዩም ድኖ ተነሣ።
መኰንኑም በእጁ ላይ ጌታችን ያደረገውን ይህን ተአምር አይቶ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋራ አመነ። በሌላ መኰንን እጅም ከሚስቱና ከልጆቹ ጋራ በሰማዕትነት ሞተ።
ቅዱስ አባ ሖርን ግን ወደ እንዴናው ላከው በዚያም በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ አሠቃዩት በመንኰራኵሮችም አበራዩት ዘቅዝቀውም ሰቅለው በእሳት በአጋሉት የብረት በትር ደበደቡት።
መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነትን አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages