አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን ቅዱሳን ዮሐንስና ስሞዖን በሰማዕትነት ሞቱ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ገብርኤል አረፈ።
ቅዱሳን ዮሐንስና ስሞዖን
ሐምሌ ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን መርባስ የሚባል አገር ሰዎች የሆኑ ቅዱሳን ዮሐንስና የአባቱ ወንድም ልጅ ስምዖን በሰማዕትነት ሞቱ። የዚህ ቅዱስ ዮሐንስ እናቱ መካን ነበረች አባቱም ልጅን ይሰጠው ዘንድ ክብር ይግባውና እግዚአብሔርን ይለምነው ነበር ከዚህም በኋላ ልጁን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልጋይ ሊአደርገው ተሳለ።
መጥምቁ ዮሐንስም እግዚአብሔር ልጅን እንደሚሰጠው በራእይ ተገልጦ ነገረው። ይህን ቅዱስም በወለደው ጊዜ ዮሐንስ ብሎ ጠራው በመጥምቁ ዮሐንስም ስም ቤተ ክርስቲያን ሠራ። ከዚህ በኋላ አድጎ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ አባቱ የበጎች እረኛ አደረገው ምሳውንም ለእረኞችና ለመንገደኞች ሁል ጊዜ ይሰጥ ነበር እርሱ ግን እስከ ምሽት ይጾም ነበር።
አባቱም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ስለዚህ ሊአረጋግጥ ወደ ርሱ ሔደ አባቱንም በአየው ጊዜ ዮሐንስ ፈርቶ ሊሸሽ ወደደ። አባቱም የዛሬ ምሳህን አሳየኝ አለው ብላቴናውም ታይ ዘንድ ግባ አለው ወደ መጠለያውም በገባ ጊዜ አገልግሉን ትኩስ እንጀራን ተመልቶ አገኘው እጅግም አደነቀ ከልጃቸው የሆነውንም ለሚስቱ ነገራት።
ከዚያችም ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ አደረችበት አወቁ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲማር አደረጉት እንጂ በጎችን የሚጠብቅ እረኛ እንዲሆን አልተዉትም።
ከዚህም በኋላ አባቱ ሊአጋባው ወደደ። እርሱ ግን ይህን አልወደደም። ዐሥራ ስምንት ዓመት በሆነውም ጊዜ ቅስና ተሾመ የአባቱ የወንድም ልጅ የሆነ ስምዖንም በጎቹን ትቶ መጥቶ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆነ። እርሱም ስለ ተአምራቱ የተናገረ ነው። እግዚአብሔር በእጆቹ ላይ ድንቆችንና ተአምራቶችን ገልጧልና። ደዌ ያለባቸውንም ሁሉ ያመጡአቸው ነበር እርሱም በዘይቱ ላይ ይጸልይና ይቀባቸው ነበር ወዲያውኑም ከደዌያቸው ይድኑ ነበር። እርሱም ወደርሱ የሚመጡትን ከኃጢአት ይርቁ ዘንድ ያስተምራቸው ነበር። ይመክራቸውና ይገሥጻቸውም ነበር። ተአምራቱም የማይቈጠር ብዙ ነው። ከተአምራቱም አንዱ ይህ ነው። በአንዲት ዕለት አንድ የንጉሥ ጭፍራ አንዲት መበለት የተሸከመችውን ገብስ ቀምቶ ለፈረሱ አበላት ያችም መበለት በዚህ ቅዱስ ዘንድ ከሰሰችው ቅዱስ ዮሐንስም ረገመው ያን ጊዜም ፈረሱ ሞተች።
ዳግመኛም የንጉሥ የጭፍራ አለቃ ግብር ሊሰበስብ መጣ አንድ ዐይኑ የታወረች አንድ አገልጋይም ነበረው። ከእርሱም ተባርኮ ወዲያውኑም የታወረች ዐይኑ ተገለጠች በእርስዋም ደኅና አድርጎ አየ። ይህም ቅዱስ የሰዎችን ሥራቸውን በግልጽ ያይ ነበር ስለ ኃጢአታቸውም ንስሓ ይገቡ ዘንድ ይገሥጻቸው ነበር።
ዜናውም በንጉሥ ማርያኖስ ዘንድ ተሰማ ለእርሱም አንዲት ሴት ልጅ ብቻ ነበረችው ወደ ሆድዋም ከይሲ ገብቶ ለሞት ተቃረበች ከዚህም በኋላ ያድኗት ዘንድ ገንዘቡን ለባለ መድኃኒቶች ሰጠ ነገር ግን አልተቻላቸውም። ከዚህም በኋላ የጭፍራ አለቃው የባሪያውን ዐይን እንደ አዳነ የቅዱስ ዮሐንስን ዜና ነገረው ንጉሡም ጭፍራ ልኮ ወደርሱ ሊአስመጣው ወደደ ቅዱስ ዮሐንስም በመንፈስ ዐወቀ እርሱ ግን የመንገዱን ድካምና ባሕሩን ይፈራ ነበር ያን ጊዜም ደመና መጥታ ነጠቀችው ሰርመላስ ከሚባል አገርም ወደ አንጾኪያ ከተማ አደረሰችው። በንጉሡም ዐልጋ ላይ አቆመችው ንጉሡም ደነገጠ ቅዱስ ዮሐንስም ወደዚህ ወዳንተ ልታስመጣኝ የተመኘኸው ምስኪን ሰው እኔ ነኝ ብሎ ነገረው። አሁንም ልጅህን አምጣት አለው ልጁንም አመጣ። በላይዋም በጸለየ ጊዜ ከይሲው ሳያሳምማት ከሆድዋ ወጣ። ንጉሡም ከቤተ መንግሥቱ ሰዎች ሁሉ ጋር ከእርሱ ተባረከ። እጅግም አደነቁ ለሚፈሩት ይህን ጸጋ የሚሰጥ የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
እጅ መንሻውንም ብዙ ገንዘብ አቀረበለት እርሱ ግን ምንም አልወሰደም። ንጉሡም በእርሱ ዘንድ ሊአኖረው ወደደ ቅዱሱ ግን አልወደደም ንጉሡም እንዳይሔድበት ቀሚሱን ያዘ ያንጊዜም ንጉሡ ቀሚሱን እንደያዘ ደመና ነጥቆ ወሰደው ቀሚሱም ተቆርጦ በንጉሥ እጅ ላይ ቀረ ቅዱስ ዮሐንስም በዚያች ሰዓት ወደ ሀገሩ ደረሰ።
ንጉሡም ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ የቀሚሱን ቁራጭ በውስጧ አኖረ ቤተ ክርስቲያኒቱም እስከ ዛሬ ድረስ የፊቃር ቤተ ክርስቲያን ተባለች። የቊርባን ቅዳሴ በሚቀደስ ጊዜም ሥጋውንና ደሙን መቀበል የሚገባቸውንና የማይገባቸውን ጻድቃንና ኃጥአንን ያያቸዋል።
ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ የጣዖትን አምልኮ በአቆመ ጊዜ ለአባቱ ወንድም ልጅ ለስምዖንም ይህን አስረድቶት ወደ እስክንድርያ ከተማ ሔዱ በመኰንኑ ፊትም ቁመው ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ጽኑዕ የሆነ ሥቃይም አሠቃያቸው። ከዚህም በኋላ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቈረጣቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ ከሥጋቸውም ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ ለበሽተኞችም ታላቅ ፈውስ ተገኘ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ገብርኤል
ዳግመኛም በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባ ስምንተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ገብርኤል አረፈ። የዚህ ቅዱስ ወላጆች በእግዚአብሔር ሕግ የጸኑ ደጋጎች ፈቃዱንና ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ነበሩ።
ይህንንም ቅዱስ በወለዱት ጊዜ በፈሪሀ እግዚአብሔር አሳደጉት። በአንዲት ዕለትም ቅዱሳን መነኰሳት ወደርሱ መጡ ከውስጣቸውም መልካም ገድል ያለው አንድ አረጋዊ ነበረ። እርሱም ብዙዎች ኤጲስቆጶሳት ሕፃኑን ከበው እጃቸውን እንደሚጭኑበት እንደሚባርኩትና ይሁን ይሁን ይገባዋል እንደሚሉ ራእይን አየ።
ሽማግሌውም ይህን ራእይ በአየ ጊዜ ሕፃኑ ታላቅ እንደሚሆን አሰበ ለአባቱም ይህን ሕፃን አስተምረው ለብዙዎች ሕዝቦች አለቃ ይሆን ዘንድ አለውና አለው። አባቱም ሰምቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው ከዚህ ሕፃን ምን ይደረግ ይሆን አለ።
ሕፃኑ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ፈቃድ አባቱ አረፈ ብህና በሚባል አገርም ገድሉ የተደነቀ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ብሉያትንና ሐዲሳትንም የሚያውቅ የእናቱ ወንድም ስሙ ጴጥሮስ የሚባል ኤጲስቆጶስ ነበረ ሕፃኑንም ወስዶ አስተማረው ከተሰጠውም ጸጋና ከዕውቀቱ የተነሣ ያዩት ሁሉ ያደንቁ ነበር ዲቁናም ተሾመ።
ዐሥራ ሁለት ዓመትም በሆነው ጊዜ የምንኵስናን ልብስ ሊለብስ ወደደ ይህንም ኃላፊውን ዓለም ናቀ ኤጲስቆጶሱ አባ ጴጥሮስም በገድል ተጸምዶ ለሚኖር ለቀሲስ አባ ጴጥሮስ ሰጠው እርሱም በጥቂት ቀኖች የምንኵስናን ገድል አስተማረው ከእርሱም ብዙ ትሩፋቶች ታዩ።
ከዚህም በኋላ መምህሩ ቀሲስ አባ ጴጥሮስ በአረፈ ጊዜ ከዚያ ተነሥቶ ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ሔደ በዚያም በጾምና በጸሎት በስግደት በመትጋት እየተጋደለ ያለ ማቋረጥ ብዙ ዘመናት ኖረ።
ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወደ አባ መቃርስ ደብር ሔደ። በደብረ ማርስ ባለች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን አበምኔት አደረጉት ሕንፃዋንም አደሰ።
ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሒዶ ከቅዱሳት መካናት ተባረከ በዚያም በቅድስት ትንሣኤ በተሰየመች ቤተ ክርስቲያን በጳጳሱ በአባ ሚካኤል እጅ ቅስና ተሾመ። ከዚያም ወደ ምስር አገር ተመልሶ በማዕልቃ ባለች በእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን እየጻፈ ተቀመጠ።
በዚያም ወራት ሉቀ ጳጳሳቱ አባ ቄርሎስ አረፈ። የወንጌላዊው የማርቆስ መንበርም ያለሊቀ ጳጳሳት ነበር። ስለዚህም ኤጲስቆጶሳት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ይሾሙት ዘንድ በአንድ ምክር ተስማሙ ሰይጣን ግን ክፉዎች ሰዎችን አነሣሥቶ ተቃወሙት። ሹመቱንም አልፈቀዱም። ነገር ግን መንፈሳዊ አባት የነበረውን የከሊል ልጅ አባ አትናቴዎስን ሾሙት። እርሱም መንጋውን በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ።
እርሱም በአረፈ ጊዜ ኤጲስቆሳትና የሕዝብ አለቆች ዳግመኛ ተሰበሰቡና በእጃቸው ጽፈው አባ ገብርኤል እንዲሾም ፈቀዱ ሁለተኛም በሕዝቡ መካከል ሁከት ተነሣ ከሌሎችም ጋራ ዕጣ ያጣጥሉት ዘንድ ተስማሙ ስሞቻቸውንም ጽፈው በመንበሩ ላይ አኖሩ በላዩም እየጸለዩና እየቀደሱ ሦስት ቀኖች ሰነበቱ። ከዚህም በኋላ ታናሽ ብላቴና አምጥተው በውስጡ የአባ ዮሐንስ ስም ያለበትን ክርታስ አወጣላቸው። ያም አባ ዮሐንስ ተሾመ። ይህን አባ ገብረኤልን ግን ለማዕልቃ ቤተ ክርስቲያን ተከራካሪ አድርገው ሾሙት።
በዚያ ወራትም በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ ችግር ሁኖ ነበር። ይህ አባ ገብርኤልም ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ሒዶ በጾምና በጸሎት በስግደትም በቀንና በሌሊት ሲጋደል ኖረ። ከቅዱሳን መነኰሳትም ብዙዎች መልካም ራእይን አዩለት ከእርሳቸው በእስክንድርያ ከተማ የሊቀ ጳጳሳት ልብስን እንደሚአለብሱት ብዙዎች ከአሕዛብ የተመለሱ ክርስቲያኖችም እንደሚያጅቡት ያየ አለ። ደግሞም ይሾምባት ዘንድ ወደ አስቄጥስ ወደ አባ መቃርስ ገዳም ሲሔድ ያየለት አለ። ቁጥር የሌላቸውንም መክፈቻዎችን ሲቀበል ያዩ አሉ።
ከገዳሙም ሊወርድ ብዙ ጊዜ ይሻ ነበር ነገር ግን አልተቻለውም። ከዚህ በኋላ አባ እንጦንስ በራእይ ተገልጦ እንዲህ አለው ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ከዚህ ገዳም ትወርድ ዘንድ እኔ አልፈቅድም ጊዜው ሳይደርስ አትውረድ አለው።
ከሦስት ዓመት በኋላም አንዱ አረጋዊ የከበረ መልአክ እንግዲህስ አባ ገብርኤልን ወስደው በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና ይሾሙታል እያለ እንደሚያነጋግረው ራእይ አየ። በዚያችም ቀን የሀገረ እንጣፊ መኰንን መጣ ከእርሱም ጋር ብዙዎች መሳፍንቶች ነበሩ። አባ ገብርኤልን አምጥተው በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ የሚያዝዝ የንጉሥ ደብዳቤም ከእርሱ ጋር ነበረ።
ከዚህም በኋላ ያለ ፈቃዱ ወስደው በወንጌላዊው በማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጵጵስናን ሾሙት። በዚያችም ቀን እርሱ ለኢየሩሳሌም አንድ ጳጳስና ሌሎችንም ኤጲስቆጶሳት ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም ሾመ። ከዚህም በኋላ ሦስት ጊዜ ሜሮን አከበረ ባረከ እንደዚህም አድርጎ አንድ ዓመት ከአንድ ወር ኖረ።
በዚያን ጊዜም አባ እንጦንስ ተገልጦ እንዲህ አለው እነሆ ዕረፍትህ ቀርቦአል ከዐሥራ ስምንት ወሮች በኋላ ወደ እግዚአብሔር ትሔዳለህ የዘላለም ሕይወትንም ትወርሳለህ።
ከዚህም በኋላ በክርስቲያን ወገኖች ላይ ታላቅ መከራ ሆነ። ይህም አባት ወገኖቹን ያድን ዘንድ ወደ ጌታችን ለመነ ክብር ይግባውና ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ ሕዝቡን ይቅር አለ።
ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ ከመንበረ ሢመቱ ወጥቶ በምስር አገር ዓመት ሙሉ ተሠወረ። ከአንድ ምእመን በቀር ማንም አላወቀበትም በቀንና በሌሊት በገድል ከመቀጥቀጡ የተነሣም መልኩ ተለወጠ ሥጋውም ደረቀ።
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር እርሱን ለሚፈራው ለአንድ ምእመን ሥራውን ገለጠ። እርሱም ከዚያ ቦታ አውጥቶ በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አስቀመጠው በጸሎትና በቅዳሴ እያገለገለ ኖረ። ድኆችንም ይጐበኛቸው ነበር። የሚሹትንም ይሰጣቸው ነበር። ወደ ርሱ የሚመጡትንም ሕዝቦች ያስተምራቸውና ያጽናናቸው ነበር።
በአንዲት ዕለትም ሊቀ ጳጳሳት አባ አትናቴዎስ በግልጽ ታየው እንዲህም አለው ስለዚህ ፈጽሞ አትዘን ከዚህ ብዙ ድካምና መከራ እግዚአብሔር ያሳርፍሃልና አነሆ ምድራዊ ኑሮህን የሚፈጽም ደዌ በአንተ ላይ ይመጣል ነገር ግን ደስ ይበልህ ታላቅ የሆነ የእግዚአብሔርን ጸጋ ተቀብለሃልና። የዘላለም ሕይወትንና የማያልቅ ተድላ ደስታንም ትወርሳለህና አለው።
በዚያን ጊዜም በሚያስጨንቅ ደዌ ታሞ እየተጨነቀ ኖረ። ስለ ነፍሱም መውጣትና በእግዚአብሔር ፊት ስለ መቆሙ ይፈራና ይደነግጥ ነበር የእመቤታችን ማርያም ሥዕልም በዚያ ነበረ። ወደርሷም አዘውትሮ ይማልድ ነበረ በዚያን ጊዜም ክብር ይግባውና ራሱ እግዚአብሔር በብሩህ ገጽ ተገለጠለት መንግሥተ ሰማያትን አግኝተሃልና ደስ ይበልህ እንጂ አትፍራ እስከ ሦስት ቀንም ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ትወጣለህ በማለት አረጋጋው። ይህንንም ብሎ ከእርሱ ተሠወረ በሦስተኛውም ቀን በሰላም አረፈ። በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንም በታላቅ ክብር ተቀበረ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ
No comments:
Post a Comment