አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ከዚህም በኋላ ገበታው የወርቅ የሆነ ወንጌልን ያሠራለት ዘንድ አባቱን ለመነው አባቱም እንደፈለገው አሠራለት ሁል ጊዜም ያነበው ነበር። በሚያነብ ጊዜም አባቱና እናቱ ደስ ይላቸው ነበር።
በዚያም ወራት ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዝ መነኵሴ ወደ እነርሱ መጣ በእነርሱም ዘንድ አደረ ከቅዱስ ዮሐንስም ጋራ ተነጋግሮ የምኵስናን ሥራ አመሰገነለት ይህን ዓለም እስከ ናቀና እንደ እርሱ መነኰስ ይሆን ዘንድ እስከ ወደደ ድረስ ልቡን ማረከው።
ያን ጊዜም ያ መነኰስ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ ሁለተኛም ተመልሶ እንደ ልማዱ በእነርሱ ዘንድ አደረ። ቅዱስ ዮሐንስም መነኵሴው ወደ ገዳሙ ይወስደው ዘንድ ፈለገ መነኲሴውም አባትህን እፈራዋለሁ ልወስድህ አይቻለኝም አለው። ቅዱስ ዮሐንስም ከእርሱ ጋራ እንዲወስደውና ነፍሱን እንዲያድን አማለው።
ከዚህም በኋላ በስውር ወሰደው በመርከብም ተጭነው ያ መነኰስ ወደሚኖርበት ገዳም ደረሱ የገዳሙም አበ ምኔት የወጣቱን ዮሐንስን መልኩን አይቶ አደነቀ። ቅዱስ ዮሐንስም የምንኵስናን ልብስ ያለብሰው ዘንድ አበ ምኔቱን ለመነው አበ ምኔቱም ልጄ ሆይ የምንኵስና ሕግ እጅግ ጭንቅ ናት እኮ አለው። አብዝቶም በለመነውና ግድ ባለው ጊዜ ራሱን ላጭቶ አመነኰሰው።
ከዚህም በኋላ ከጾም ከትጋትና ከኀዘን የተነሣ ሥጋው ደርቆ አጥንቶቹ እስከሚታዩ ድረስ በብዙ ተጋድሎ ተጸመደ። አበ ምኔቱም ልጄ ሆይ ለሰውነትህ እዘን ድካምህንም ቀንስ መነኰሳቱም ሁሉ እንደሚሠሩት ሥራ እያለ ያጽናናውና ይመክረው ነበር።
በዚህ ተጋድሎም ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜ ከእነርሱ በረከትን ትቀበል ዘንድ ከመሞትህ በፊት ወደ አባትህና እናትህ ሒድ የሚል ራእይ አየ። ይህንንም ራእይ በሦስት ሌሊቶች ውስጥ አየ ለአበ ምኔቱም እንዴት እንዳየ ነገረው አበ ምኔቱም ይህ ራእይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ሆነ ልትሔድ ይገባሃል አለው። ከገዳሙም በወጣ ጊዜ አንድ ምስኪን ሰው ጨርቅ ለብሶ አገኘ። የእርሱንም ልብስ ሰጥቶት ጨርቁን ወሰደ።
ወደ አባቱ ቤትም በደረሰ ጊዜ በትንሽ ጎጆ ውስጥ በአባቱ ደጅ በጾም በጸሎትና በስግደት እየተጋደለ ባሮች ከአባቱ ማዕድ የሚጥሉለትን ፍርፋሪ እየተመገበ ሰባት ዓመት ኖረ። እናቱም በአንጻሩ ስታልፍ የሚከረፋ ሽታው ያስጨንቃት ነበር። ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰባት ቀን በኋላ ከዚህ ዓለም ትወጣለህ ብሎ ነገረው።
ያን ጊዜም ወደ እናቱ ልኮ ልመናውን ልትሰማ ወደ እርሱ መጣች ልጅዋም እንደሆነ ፈጥኖ አልነገራትም ነገር ግን በዚያች በታናሽ ማደሪያ ውስጥ በላዩ ባለ ጨርቅ እንድትቀብረው የለበሰውንም ጨርቅ እንዳትለውጥ አማላት። ከዚህም በኋላ ያንን የወርቅ ወንጌል ሰጣት። እንዲህም አላት ይህን መጽሐፍ አንብቡ እኔንም አስቡኝ።
አባቱም በመጣ ጊዜ ያንን የወርቅ ወንጌል አሳየችው እርሱም ለልጁ ያሠራለት ወንጌል እንደሆነ አወቀ። አባቱና እናቱም ወደ እርሱ ሔደው ስለ ልጃቸው ጠየቁት እርሱም ከዚህ ጨርቅና ከዚህ ትንሽ ማደሪያዬ ውስጥ በቀር በሌላ እንዳትቀብሩኝ ማሉልኝ አላቸው።
በአማላቸውም ጊዜ እርሱ ልጃቸው እንደሆነ ነገራቸው ያን ጊዜም ጮኹ መሪር ልቅሶንም አለቀሱ የሮሜ ከተማ ሽማግሌዎችና ሕዝቡ ሁሉ ተሰበሰቡ ሰባቱ ቀንም ሲፈጸም ቅዱስ ዮሐንስ አረፈ። እናቱም መሐላዋን ረስታ አስቀድማ ለሠርጉ ያዘጋጀቻቸውን ያማሩ ልብሶች አውጥታ ገነዘችው። በዚያችም ጊዜ ታመመች አባቱ ግን መሐላውን አስታውሶ እነዚያን ያማሩ ልብሶች አስወገደ በጨርቆቹም ገነዙት በዚያ በትንሹ ማድሪያም ውስጥ ቀበሩት ከሥጋውም በሽተኞች የሚፈወሱበት ታላቅ ድኅነት ተገኘ።
ከዚህም በኋላ በስሙ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ሥጋውን በውስጧ አኖሩ። ከእርሱም ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ
No comments:
Post a Comment