ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 17 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, July 25, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 17

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሐምሌ ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን ቅድስት አውፎምያ በሰማዕትነት ሞተች። የቅዱስ ዮስጦስ የከበረች ዐፅሙ በክብር ተገኘች፣ ታላቁ ነቢይ ዮናስ ከዓሣ አንበሪ ሆድ ለወጣበት መታሰቢያው ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስት አውፎምያ
ሐምሌ ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን ቅድስት አውፎምያ በሰማዕትነት ሞተች። ይቺንም ቅድስት በርሴፎስ የሚባል ከዲዮቅልጥያኖስ መኳንንቶች አንዱ አሠቃያት። የታሠሩ ሰማዕታት በሚያልፉ ጊዜ በአንገታቸው የሚከብዱ ሰንሰለቶች ነበሩ። እንደ ውሾችም ይጐትቷቸው ነበር። ግፋቸውንም ባየች ጊዜ ይቺ ቅድስት አለቀሰች ልቡናዋም ክብር ይግባውና በክርስቶስ ፍቅር ተቃጠለ ዲዮቅልጥያኖስንና የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመች። ያንንም መኰንን እንዲህ ብላ ዘለፈችው ርኅራኄ የሌለህ ልብህ እንደ ደንጊያ የሆነ ለእኒህ ቅዱሳን ሰዎች አትራራምን ፈጣሪያቸውስ እንዳያጠፋህ አትፈራምን።
መኰንኑም ሰምቶ ወደርሱ ያቀርቡአት ዘንድ አዘዘ። ስለ ሃይማኖቷም ጠየቃት እርሷም ክርስቲያን እንደሆነች በፊቱ አመነች። በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ በግርፋትና በስቅላት ታላቅ ሥቃይን አሠቃያት።
ከዚህ በኋላ በእሳት ምድጃ ውስጥ ጨመሩዋት ነገር ግን ከሥቃዩ የተነሣ ምንም ጉዳት አልደረሰባትም። በዚያን ጊዜም በእሳቱ መካከል ቆማ ጸለየች ፊቷንና መላ ሥጋዋንም በመስቀል ምልክት አማትባ ነፍሷን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የቅዱስ ዮስጦስ
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የቅዱስ ዮስጦስ የከበረች ዐፅሙ በክብር ተገኘች፡፡ በሰማዕትነት ያረፈው የአንጾኪያው ንጉሥ የኑማርያኖስ ልጅ ነው፡፡ ታላቁ የአንጾኪያ ንጉሥ ኑማርያኖስ በጦርነት ውስጥ በሞተ ጊዜ ልጁ ቅዱስ ዮስጦስም በሌላ ቦታ በጦርነት ውስጥ ስለነበር መንግሥትም ያለ ንጉሥ ቀረች፡፡
የቴዎድሮስ በናድልዮስ አባት ሲድራኮስና ቅዱስ ፋሲለደስ ዲዮቅልጥያኖስ ነግሦ ሃይማኖቱን እስከካደ ድረስ የመንግሥቱን አስተዳደር ይመሩ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ታላቁ የአንጾኪያ ንጉሥ ኑማርያኖስ የፋርስና የቁዝ ሰዎች በጦር በርትተው በመጡበት ጊዜ ቅዱስ ፋሲለደስንና ህርማኖስን ጠርቶ ‹‹እነሆ እኔና የተረፉት ሠራዊት ሄደን የቁዝን ሰዎች እንዋጋለን እናንተ ቤተ መንግሥቱን ጠብቁ፣ ልጆቼን ለእናንተ አደራ ሰጥቻለሁ›› አላቸው፡፡ ንጉሡም የመንግሥቱን ልብስ አውልቆ ዘውዱን ጥሎ ተራ ልብስ ለብሶ ሲዋጋ በጦር ተወግቶ ሞተ ነገር ግን የቁዝ ሰዎች አላወቁትም ነበር፡፡
ጦርነቱም ባለቀ ጊዜ የሮም መንግሥት ያለንጉሥ ብቻዋን ቀርታ አንድ ዓመት ሙሉ ቅዱስ ፋሲለደስና ህርማኖስ የመንግሥት ሕጓንና ሥርዓቷን እየጠበቁ ቆዩ፡፡ የቁዝ ሰዎችም የሮም መንግሥት ያለ ንጉሥ መሆኗን ሲያውቁ ዳግመኛ ሊያጠፏቸው በጦር በርትተው መጡ፡፡ የሮም ሰዎችም ተሰብስበው ቅዱስ ፋሲለደስን ‹‹በስራችን ወዳሉ ግዛቶች ወደ ግብጽም ተዋጊ አርበኞችን ይልኩልን ዘንድ እንጠይቃቸው›› አሉት፡፡ መኳንንቱም ወደ ግብጽ ወርደው በጦር ኃይለኛ የሆኑ ሰዎችን ይዘው ተመለሱ፡፡ ከግብጽ ካመጧቸው ኃይለኛ ሰዎች ውስጥ ከላይዕላይ ግብጽ ስሙ ከርቢጣ የሚባል ፍየል የሚጠብቅ አንድ ኃይለኛ ሰውን ወደ አንጾኪያ አመጡ፡፡
ቅዱስ ፋሲለደስና ህርማኖስም ይህ ሰው የሚያስፈራ በሥራውም ኃይለኛ ጉልበቱ የጸና ጨካኝ መሆኑን አይተው በንጉሡ ፈረስ ላይ ባልደራስ ወይም ሹም አድርገው ሾሙት፡፡ ከጥቂት ወራትም በኋላ ታላቂቱ የንጉሡ ልጅ ከቤተ መንግሥት ሆና በመስኮት በኩል ሆና ሲወጣ ባቱን ሲገባ ደረቱን አይታ በሀፀ ዝሙት ተነድፋ እጅግ ወደደችው፡፡ እርሱንም ሰይጣን ከልጅነቱ ጀምሮ ይከተለው ነበር፡፡ የንጉሡም ሴት ልጅ ወስዳ አገባችውና ስሙን ዲዮቅልጥያኖስ ብላ አነገሠችው፡፡ ይኽም ዲዮቅልጥያኖስ ከካደ በኃላ ሰይጣን ማደሪያው አድርጎት ከ470,000 (አራት መቶ ሰባ ሺህ) በላይ የሚሆኑ ክርስቲያኖችን በግፍ በሰማዕትነት የገደለ ነው፡፡
የንጉሡ ልጅ ቅዱስ ዮስጦስ ጦርነቱን አሸንፎ በድል ወደ ቤተ መንግሥት በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስ ጌታችንን ክዶ ጣዖታትን ሲያመልክ ቢያገኘው እጅግ አዝኖ ሰማዕት ይሆን ዘንድ ተመኘ፡፡ የሀገሩም ሰዎች ወደ ዮስጦስ ዘንድ ቀርበው ‹‹እኛ ዲዮቅልጥያኖስን እንገድለዋለን አንተ በአባትህ ዙፋን ተቀመጥ›› አሉት፡፡ እርሱ ግን ከምድራዊው መንግሥት ይልቅ ሰማያዊውን መንግሥት መርጧልና እሺ አላላቸውም፡፡ በጌታችንም ስም ሰማዕት ይሆን ዘንድ መረጠ፡፡ በንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስም ዘንድ ቀርቦ ስለ ጌታችን ክብር መሰከረ፡፡
ንጉሡም ገና ሲያየው እጅግ ፈርቶና ደንግጦ ‹‹ጌታዬ ዮስጦስ ሆይ! ይህን ታደርግ ዘንድ ያስገደደህ ማነው?›› አለው፡፡ ቅዱስ ዮስጦስም ከሃዲውን ንጉሥ ‹‹በምስክርነቴ ደሜን እንዳፈስ ካልጻፍክ ሕዝቡን በአንተ ላይ አስነስቼ ከመንግሥትህ እንደማስወጣህ በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እምልልሃለሁ›› አለው፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም እየፈራ የዮስጦስን ፈቃድ ይፈጽምለት ዘንድ ከሚስቱ ከታውክልያና ከልጁ ከአቦሊ ጋር ወደ ግብፅ እንዲወስዷቸው አዘዘ፡፡ እንዲያባብለውም ለእስክንድርያው መኮንን ጻፈለት፡፡
የእስክንድርያውም ገዥ እጅግ ፈርቶ ዮስጦስን ‹‹ጌታዬ ዮስጦስ ሆይ! እንዲህ አታድርግ ለአንተ ክብርህ ይሻልሃል…›› እያለ ሊያግባባው ሲሞክር ቅዱስ ዮስጦስ ግን ‹‹የመንግሥትህን ክብር እንዳታጣ ሰማዕትነቴን ፈጸምልኝ›› አለው፡፡ እርሱም ፈርቶ ወደ ላይኛው ግብፅ ወደ እንዴናው ገዥ ላከው፡፡ ከአገልጋዮች ጋራ ሚስቱን ቅድስት ታውክልያን ፃ ወደምትባል አገር ሲልካት ልጁን አቦሊን ደግም ወደ ሀገረ ብስጣ ላከው፡፡ ከአገልጋዮቹም ውስጥ እንዲያገለግሏቸው በማለት አንድ አንድ ሰጣቸው፡፡ ሚስቱ ቅድስት ታውክልያም ሰማዕትነቷን በድል ፈጽማ የክብርን አክሊል ተቀዳጀች፡፡
ቅዱስ ዮስጦስንም የእንዴና ከተማ ጣዖት አምላኪዎች ብዙ ካሠቃዩት በኋላ የካቲት 10 ቀን በሰይፍ ራሱን ቆርጡትና የተመኘውን ሰማዕትነቱን በድል ፈጸመ፡፡ ከሥጋውም ብዙ ድንቅ የሆኑ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡ ለሕሙማንም ታላቅ ፈውስ ሆነ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ታላቁ ነቢይ ዮናስ
በዚህች ቀን ታላቁ ነቢይ ዮናስ ከዓሣ አንበሪ ሆድ ለወጣበት መታሰቢያው ነው። ይህም እውነተኛ ነቢይ ዮናስ የሲዶና ክፍል በምትሆን ስራጵታ በምትባል አገር ለምትኖር መበለት ልጅዋ የሆነ ነቢይ ኤልያስም ከሙታን ለይቶ ያሥነሣው ኤልያስንም ያገለገለውና የትንቢት ጸጋ የተሰጠው ነው።
ከዚህም በኋላ ስሙ ከፍ ከፍ ያለና የተመሰገነ እግዚአብሔር ወደ ነነዌ አገር ሒደህ ሀገራቸሁ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ትጠፋለች ብለህ አስተምር ብሎ አዘዘው።
እግዚአብሔርም ይህን በአለው ጊዜ ዮናስ በልቡ እንዲህ ብሎ አሰበ እግዚአብሔር ሊአጠፋቸው ቢወድ ኖሮ ሒደህ አስተምር ብሎ ባላዘዘኝ ነበር እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ሲምራቸው እኔ በእነርሱ ዘንድ ሐሰተኛ ነቢይ እንዳልባል እፈራለሁ ከቶ ትምህርቴን አይቀበሉኝም ወይም ይገድሉኛል ወደዚያች አገርም ሒጄ እንዳላስተምር ከእግዚአብሔር ፊት ብኰበልልና ብታጣ ይሻለኛል።
ወንድሞች ሆይ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ፊት ለፍጡር ማምለጥ ይቻለዋልን። ይህስ ዮናስ የእስራኤልን ልጆች ከሚያስተምሩ ነቢያት ውስጥ ሲሆን ይህን አያውቅምን ነገር ግን አግዚአብሔር በረቀቀ ጥበቡ ይህን አደረገ እንጂ የዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት አድሮ መውጣት መድኃኒታችን በመቃብር ሆድ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት አድሮ ከዚህ በኋላ ከሙታን ተለይቶ ለመነሣቱ ምልክት ይሆን ዘንድ ነው።
ዮናስም ከዓሣ አንበሪ ሆድ ያለ ምንም ጥፋት እንደመጣ እንዲሁ መደኃኒታችን ያለመለወጥ ተነሥቷልና።
እንዲህም ሆነ ከእግዚአብሔር ፊት ዮናስ ሸሽቶ ወደ ተርሴስ አገር ሊሔድ ተነሣ ወደ ኢዮጴ አገርም ወርዶ ወደ ተርሴስ አገር የሚሔድ መርከብን አግኝቶ በገንዘቡ መርከቡን ተከራየ።
ከእግዚአብሔር ፊት ኰብልሏልና ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሔድ ዘንድ ወደ መርከቡ ወጣ እግዚአብሔርም ታላቁን ነፋስ ወደ ባሕር አመጣ የባሕሩም ማዕበል ከፍ ከፍ አለ መርከባቸውም ሊሰበር ቀረበ። ቀዛፊዎችም ፈርተው ወደ ጣዖቶቻቸው ጮኹ መርከባቸውም ይቀልላቸው ዘንድ ገንዘባቸውን፣ ዕቃቸውን አውጥተው ወደ ባሕር ጣሉ። ዮናስ ግን በዚያን ጊዜ ወደ ከርሠ ሐመሩ ወርዶ ተኝቶ ያንኰራፋ ነበር።
መርከቡንም የሚቀዝፍ ቀዛፊ ወደ ርሱ ወርዶ ምን ያስተኛሃል እንዳንሞት እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ ተነሥተህ የፈጣሪህን ስም ጥራ አለው። ይህች መከራ ያገኘችን ስለማናችን ኃጢአት እንደ ሆነ እናውቅ ዘንድ እርስ በርሳቸው ኑ ዕጣ እንጣጣል ተባባሉ በተጣጣሉም ጊዜ ዕጣ በዮናስ ወጣበት። እነርሱም ይህች መከራ ያገኘችን በማናችን ኃጢአት እንደሆነ ንገረን አንተስ የምታመልከው ምንድንነው ከወዴትስ መጣህ አገርህስ የት ነው ወዴትስ ትሔዳለህ ወገንህስ ማንነው አሉት።
ዮናስም እኔስ የእግዚአብሔር ባርያው ዕብራዊ ነኝ ፈጣሪዬም ምድርንና ሰማይን ባሕሩንና የብሱን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው አላቸው። እነዚያም ሰዎች ታላቅ ፍርሀትን ፈርተው ምን አድርገሀል አሉት እሱ ነግሮአቸዋልና ከእግዚአብሔር ፊት ኰብልሎ እንደሔደ እነርሱም አወቁት።
ባሕሩ ይታወክ ነበርና ታላቅ ማዕበልም ተነሥቶ ነበርና ባሕሩ ይተወን ዘንድ እንግዲህ ምን እናድርግህ አሉት። ዮናስም አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ ባሕሩም ይተዋችኋል ይህ ታላቅ የማዕበል ሞገድ የመጣባችሁ በእኔ ምክንያት እንደ ሆነ አውቃለሁ አላችው።
ባሕሪቱ ትታወካለችና ማዕበሊቱም በእነሣቸው ትነሣለችና እነዚያ ሰዎች ወደ ምድር ሊመለሱ ወደዱ ነገር ግን ተሳናቸው። ሁሉም አንድ ሁነው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ አቤቱ ስለዚህ ሰው በእውነት ልታጠፋን አይገባህም አቤቱ እንደ ወደድክ አድርገሃልና የጻድቅ ሰው ደም አታድርግብን አሉ። ከዚህም በኋላ ዮናስን አንሥተው ወደ ባሕር ጣሉት ባሕርም ድርጎዋን ተቀብላ ጸጥ አለች። እነዚያም ሰዎች እግዚአብሔርን ፈሩት ለእርሱም መሥዋዕትን ሠዉ ስእለትንም ተሳሉ።
እግዚአብሔርም ታላቅ ዓሣ አንባሪን ዮናስን ይውጠው ዘንድ አዘዘው ዮናስም በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ኖረ። ዮናስም በአንበሪ ሆድ ውስጥ ሳለ ጸሎትን ጸለየ ከዚህም በኋላ በነነዌ አገር በኩል ያ ዓሣ አንበሪ ዮናስን ወደ የብስ ምድር ተፋው።
የእግዚአብሔርም ቃሉ ዳግመኛ ወደ ዮናስ መጣ ቀድሞ አስተምር ብዬ እንደ ነገርኩህ ወደ ታላቂቱ የነነዌ አገር ተነሥተህ ሒደህ አስተምራቸው አለው።
ዮናስም እግዚአብሔር አስተምር ብሎ እንደ ነገረው ተነሥቶ ወደ ነነዌ ሔደ። ነነዌ ግን ለእግዚአብሔር ታላቅ አገር ናት በዙሪያዋ ያለ ቅጽርዋም ከበር እስከ በር ድረስ በእግር የሦስት ቀን ጐዳና ነው። ወደ ከተማም ሊገባ ደርሶ ያንድ ቀን መንገድ ሲቀረው ነነዌ እስከ ሦስት ቀን ትጠፋለች ብሎ አስተማረ።
የነነዌም ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል አመኑ ጾምን እንጹም ብለው አዋጅ ነገሩ የክት ልብሳቸውንም ትተው ማቅ ምንጣፍ ትልቁም ትንሹም ለበሱ። የነነዌ ንጉሥም ይህን ሰምቶ ከዙፋኑ ተነሣ ልብሰ መንግሥቱንም ትቶ ማቅ ለበሰ በአመድ በትቢያ ላይም ተቀመጠ።
ሰዎችም ቢሆኑ ከብቶችም ምንም ምን አይብሉ ትልልቆችም ትንንሾችም አይጠጡ እንስሶችም ወደ ሣር አይሠማሩ ውኃም አይጠጡ ብሎ አዋጅ ነገረ። እግዚአብሔርም ከክፉ ሥራቸው እንደ ተመለሱ አይቶ በእነርሱ ላይ ያደርገው ዘንድ ከተናገረው ክፉ ነገር ተመለሰ በእነርሱ ላይም ክፉ ጥፋትን አላደረገም።
ዮናስም ጽኑ ኀዘንን አዘነ ወደ ፈጣሪው እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ለመነ ጥንቱን በአገሬ ሳለሁ እንዲህ ብዬ የተናገርሁ አይደለሁምን አንተ ይቅር ባይ ርኅሩኅም ከመዓት የራቅህ ቸርነትህ የበዛ እውነተኛ የሆንክ ክፉ ነገርን ከማምጣት እንደምትመለስ አውቃለሁ ስለዚህ ከአንተ ኮብልዬ ወደ ተርሴስ ሔድሁ።
ነቢየ ሐሰት እየተባልኩ ከመኖር ሞት ይሻለኛልና አቤቱ አሁን ነፍሴን ከሥጋዬ ለያት አለ። እግዚአብሔርም ዮናስን በዚህ ነገር አንተ እጅግ ታዝናለህን አለው እርሱም አዎን አዝናለሁ አለ። ከዚህም በኋላ ዮናስ ከከተማ ወጥቶ ከከተማው ውጭ ተቀመጠ ጎጆም ለራሱ ሠራ በአገር ላይ የሚደረገውን ነገር እስኪያይ ድረስ ከጥላዋ ሥር ተቀመጠ።
ይበቅል ዘንድ በዮናስ ራስ ላይ ይሸፍነው ዘንድ እግዚአብሔር ቅልን አዘዘ ቅሉም በዚያን ጊዜ በቅሎ የዮናስን ራስ የፀሐይ ትኩሳት እንዳያሳምመው በዮናስ ራስ ላይ ሸፈነው ዮናስም በቅሊቱ መብቀል ታላቅ ደስታ አደረገ።
እግዚአብሔርም በማግሥቱ ትሉን ይምጣ ቅሉንም ይምታ ብሎ አዘዘ ቅሊቱንም ቆረጣት እርሷም ደረቀች እግዚአብሔርም ፀሐይ በወጣ ጊዜ የሚያቃጥል ሐሩር ያለበት ነፋስ ይምጣ ብሎ ዳግመኛ አዘዘ። ነፋሱም መጥቶ የዮናስን ራስ አሳመመው እርሱም አእምሮውን እስከማጣት ደርሶ በልቡናውም ተበሳጭቶ ከመኖር ሞት ይሻለኛል አለ።
እግዚአብሔርም ዮናስን በቅሊቱ መድረቅ እጅግ አዘንክን አለው እርሱም አዎን ልሙት እስከ ማለት ደርሼ አዘንኩ አለ። እግዚአብሔርም አንተስ በአንድ ሌሊት በቅላ በአንድ ሌሊት ለደረቀች ውኃ ላላጠጣሃት ላልደከምክባት ቅል ታዝናለህ። ቀኝና ግራቸውን ላልለዩ ከዐሥራ ሁለት እልፍ የሚበዙ ሰዎች እንዲሁም ብዙ እንስሶች ላሉባት ታላቅ አገር ለሆነች ነነዌ እኔ አላዝንላትምን ከበደሉ ተመልሶ ንስሐ ለሚገባ እኔ መሐሪና ይቅር ባይ ነኝና አለው።
ከዚህም በኋላ ዮናስ ተነሥቶ ወደ አገሩ ተመልሶ በሰላም አረፈ መላው ዕድሜውም መቶ ሰባ ነው። የነቢዩ የዕረፍት በዓል መስከረም 25 እንደሚከበር ስንክሳሩ ያስረዳናል።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages