ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, July 25, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 19

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ እና እናቱ ቅድስት ኤየሉጣ በሰማዕትነት መከራ ተቀበሉ፣ ቅዱሳን ሶርስ ኀርማን ያኑፋና ስንጣርያ የሚባሉ የእስና ሀገር ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ፣ ብልህ የሆነ ቅዱስ በጥላን በሰማዕትነት ሞተ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ እና እናቱ ቅድስት ኤየሉጣ
ሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ ተቀበሉ። ይህም ሕፃን ዕድሜው ሦስት ዓመት ሲሆነው ከሮሜ አገር ወደሌላ ሀገር እናቱ ይዛው ሸሸች በዚያም የሸሸችውን መኰንን አገኘችው።
ሰዎችም ነገር ሠሩባት ወደርሱ አስቀረባትና ስለ አምልኮ ጠየቃት እርሷም መኰንን ሆይ ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነው ሕፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ አለችው።
ሕፃኑም ወደአለበት ጭፍራውን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ አለው። ሕፃኑም መልሶ አዎ ለእኔ ደስታ ተጠብቆልኛል ላንተ ግን ኀዘንና ልቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው መጽሐፍ ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏልና አለው እግዚአብሔር ኃይልና ንግግርን ሰጥቶታልና ብዙ ተናገረ በዚያም ያሉትን እስከ አስደነገጣቸው ድረስ ንጉሡን መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው ከብርታቱም የተነሣ አደነቁ።
መኰንኑም በአፈረ ጊዜ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ ታላላቆች የማይችሉትን ታላቅና አስጨናቂ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው እናቱንም ከርሱ ጋር እንደ እርሱ አሠቃያት እግዚአብሔርም ያለምንም ጉዳት ያነሣቸው ነበር። ብዙዎች አሕዛብም ይህን አይተው አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ።
በሕፃኑ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት። ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችንም አደረገ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳናቸው።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ በታላቅ የናስ ጋን ውስጥ ውኃ ጨምረው በእሳት ያፈሉት ዘንድ አዘዘ የፍላቱም ድምጽ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ሆነ ያን ጊዜም ፍርሀትና የሃይማኖት ጉድለት በእናቱ ላይ ደረሰባት ሕፃኑም ስለ እናቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
ያን ጊዜ ጌታችን ልቧን ወደ ሰማይ አሳርጎ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁ የብርሃን ማደሪያዎችን አየች ከዚህም በኋላ ጸናች እግዚአብሔርንም አመሰገነችው ልጅዋንም ልጄ ሆይ ከእንግዲህ አንተ አባቴ ነህ እኔም ልጅህ ነኝ አለችው።
ያቺ ከኔ የተወለድክባትም ቀን የተባረከች ናት አለች ወደዚያ ወደ ጋኑ ውስጥ በገቡ ጊዜም የውኃው ፍልሐት እንደ ንጋት ጊዜ ውርጭ ቀዘቀዘ ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የእሳቱን ኃይል አቀዝቅዞታልና።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ሥጋቸው ተቆራርጦ እስከሚወድቅ ድረስ በመቃጥን ውስጥ አድርገው እንዲጐትቷቸው አዘዘ ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ አዳናቸው መኰንኑም በታላቅ ሥቃይ ያሠቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ በወህኒ ቤት ዘጋባቸው።
ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕፃኑ ቂርቆስ ወርዶ አጽናናው አረጋጋውም። ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱሳን ሶርስ ኀርማን ያኑፋና ስንጣርያ
በዚህች ቀን ስማቸው ሱርስ፣ ኀርማን፣ ያኑፋ፣ ስንጣንያ የሚባሉ የእስና ሀገር ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ። የሰማዕትነታቸው ምክንያትም እንዲህ ነው መኰንኑ አርያኖስ ወደ እስና ከተማ ሦስት ጊዜ ደረሰ። በመጀመሪያ የተባረከች መስተጋድልት የሆነች ዳላዢን ገደላት። ስማቸውን አስቀድመን የጠራናቸው አራቱን ልጆቿንም ገደላቸው። የሰማዕትነታቸውም ፍጻሜ ግንቦት ሰባት ቀን ሆነ።
በሁለተኛም ጊዜ ስማቸው አውሳፍዮስ፣ ታማን፣ ኀርማን፣ ባኮስ የሚባል አራቱን መኳንንት ገደላቸው። የሰማዕትነታቸውም ፍጻሜ ሰኔ ሰባት ቀን ሆነ። በሦስተኛም ጊዜ በቤቷ ውስጥ በዐልጋዋ ላይ ተኝታ የነበረችውን አሮጊት የአርያኖስ ወታደሮች ስለ እነዚህ ቅዱሳን ከጠየቋት በኋላ ገደሏት።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ከክርስቲያን ወገን ያገኙትን ሁሉ እንዲገድሉ የተክል ማጠጫ በተባለች በከተማዋ ምዕራብም መግደልን እንዳያቋርጡ አዘዘ ወደ ከበረ አባት ወደ ባሕታዊ ይስሐቅም እስኪደርሱ ድረስ በመንገድ ብዙ ሕዝብን አገኙ።
ያን ጊዜም ጠባቂያቸው እንዲህ እያለ ያጽናናቸውና ያረጋጋቸው ነበር። ወደ ሰማያዊት መንግሥት እንድትገቡ ጸንታችሁ ታገሡ። እንዲህም ሲወስዷቸው መኰንኑ ደረሰ በአዩትም ጊዜ ሁሉም በአንድ ቃል እኛ ክርስቲያን ነን እያሉ በግልጽ ጮኹ መኰንኑም ሁሉንም እንደበግ ያርዷቸው ዘንድ አዘዘ።
ጭፍሮች ግን በላያቸው በሰይፎች አጋና ተጫወቱ። በዚችም በሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ ቀን የእስናን ከተማ ሰዎች ከታናሾቻቸው እስከ ታላቆቻቸው ሴቶችንና ወንዶችን ጨረሷቸው። የመላእክት ሠራዊትም ነፍሶቻቸውን ይቀበሉ የብርሃን አክሊሎችንም ያቀዳጁአቸው ነበር።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ከዚያ ወደ እስዋን ከተማ ሔደ ሁለተኛም ወደ እስና ከተማ ተመልሶ ሦስት ገበሬዎችን የእርሻ ዕቃቸውን ተሸክመው አገኘ። መኰንኑንም በአዩት ጊዜ እኛ ክርስቲያን ነን ብለው በግልጥ ጮኹ መኰንኑም ሰምቶ ይገድሏቸው ዘንድ አዘዘ በእርሻ መሣሪያቸውም ገደሏቸው የእነዚህም ስማቸው ሱሩፋስ፣ አንጣኪዮስ፣ ስሐድራ ይባላል የሰማዕትነታቸውም ፍጻሜ መስከረም ዐሥራ አንድ ቀን ነው።
ይህንንም ቅዱስ አባት ኤጲስቆጶስ ይስሐቅን መኰንኑ አሥሮ ለጣዖት እንዲሠዋ አስገደደው። እምቢ ባለውም ጊዜ ወደ እሳት እንዲወረውሩት አዘዘ የሰማዕትነቱም ፍጻሜ ታኅሣሥ ዐሥራ አራት ቀን ነው ምእመናንም ሥጋውን ወስደው ገንዘው ቀበሩት። የስደቱ ወራትም ከአለፈ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በስሙ አከበሩዋት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ በጥላን
በዚህችም ቀን ትዕማዳን ከምትባል ከተማ ብልህ የሆነ ቅዱስ በጥላን በሰማዕትነት ሞተ። አባቱም አረማዊ ነበረ ስሙም አውሱጢኪዮስ ነበር እናቱ ግን አማኝ ነበረች ስሟም ኤልያና ነበር። በአደገ ጊዜም አባቱ ጥበብን ሁሉ አስተማረው እጅግም አዋቂ ሆነ።
በበጥላን ቤት አቅራቢያም አንድ ቄስ ይኖር ነበር። በጥላንም በፊቱ ሲያልፍ መልኩንና ዕውቀቱን ብልህነቱንና አሰተዋይነቱንም ይመለከት ነበር ከሀዲ ስለመሆኑም ስለርሱ ያዝን ነበር። ቄሱም በጥላንን መንገድ መርቶ ወደ ቀናች ሃይማኖት ያስገባው ዘንድ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው።
ስለ በጥላንም ልመናውን በአዘወተረ ጊዜ በጥላን በእርሱ እጅ ያምን ዘንድ እንዳለው ጌታችን በራእይ ገለጠለት ቄሱም ደስ አለው ሁልጊዜም በፊቱ ሲያልፍ በጥላንን ያነጋግረውና ሰላምታ የሚሰጠው ነበር። ስለዚህም በመካከላቸው ፍቅር ጸና።
ከዚህም በኋላ በጥላን ወደ ቄሱ ቤት ይገባና ስለ ሃይማኖት ይነጋገር ነበር። ቄሱም ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ምን ያህል ክብር እንዳላት ለሚያምኑበትም ሁሉ ዕውቀትና ማስተዋል እንደሚሰጣቸው ድንቆችና ታላላቅ ተአምራቶች እንደሚደረግላቸው ታላቅ ፈውስም እንደሚያደርጉ ገለጠለት።
በጥላንም ክብር ይግባውና በክርስቶስ የሚያምኑ ተአምራትን እንደሚያደርጉ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት በዚያ ቄስ ትምህርት በጌታ አመነ ቄሱም ሁልጊዜ የሃይማኖትን ትምህርት ያስተምረው ጀመር።
በአንዲትም ዕለት ቅዱስ በጥላን በከተማው አደባባዮች ሲያልፍ እባብ የነደፈውን አንድ ሰው ሲጨነቅ አየው እባቡም በርሱ ዘንድ ቆሞ ነበር በልቡም የመምህሬን ቃል ልፈትን ክብር ይግባውና በክርስቶስ ከአመንክ በስሙ ታምራት ታደርጋለህ ብሎኛልና አለ። እባብ ወደ ነከሰውም ሰው ቀርቦ ኃይሉን ይገልጽለት ዘንድ እባቡንም ይገድለው ዘንድ ሰውዬውን ያድነው ዘንድ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ረጅም ጸሎትን ጸለየ ያን ጊዜም ሰውዬው ያለ ምንም ጉዳት ድኖ በጤና ተነሣ ከይሲውም ወደቀ ወዲያውም ሞተ። የበጥላንም ሃይማኖቱ ተጨመረለት።
ከዚህም በኋላ በጥላን ወደ ቄሱ ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ ሁልጊዜም ወደ ቄሱ እየመጣ ይማር ነበር። በአንዲት ቀንም ያድነው ዘንድ አንድ ዕውር መጣ። የቅዱስ በጥላን አባትም ባየው ጊዜ ዕውሩን ከውጭ መልሶ ሰደደው በጥላንም አባቱን ማነው የፈለገኝ ብሎ ጠየቀው አባቱም ልታድነው የማትችል አንድ ዕውር ነው አለው።
እርሱም አባቱን የእግዚአብሔርን ክብር ታይ ዘንድ አለህ አለው ይህንንም ብሎ ዕውሩን ጠራውና ዐይኖችህ ቢገለጡ ያዳነህን ታመልከዋለህን አለው ዕውሩም አዎን አምናለሁ አለ ቅዱስ በጥላን በዕውሩ ላይ ረጅም ጸሎትን ጸለየ እጆቹንም በዕውሩ ዐይኖች ላይ አኑሮ እንድታይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እመን አለው ወዲያውኑም ዐይኖቹ ተገለጡ።
አባቱም ይህን ድንቅ ሥራ በአየ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታ በኢየሱስ ከዕውሩ ጋር አመነ ቅዱስ በጥላንም ወደ ቄሱ ወሰዳቸውና የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው። ከዚህም በኋላ ባሮቻቸውን ነፃ አወጡ ገንዘባቸውንም ለድኆችና ለችግረኞች አከፋፈሉ።
ቅዱስ በጥላንም ጥበብን ያደርግ ነበር። ያለ ዋጋም ሰዎችን ያድናቸው ነበር። ነገር ግን ክብር ይግባውና በክርስቶስ እንዲያምኑ ይሻ ነበር። ስለዚህም ጥበበኞች ሰዎች በእርሱ ላይ ተነሡ ወደ ንጉሥም ሒደው ከቄሱ ጋራና ከአዳነውም ዕውር ጋራ በጌታችንም ከአመኑ ከብዙዎች ጋራ ከሰሱት። ወደ ንጉሡም በቀረቡ ጊዜ ንጉሡ ተቆጥቶ ለአማልክት ሠዉ አላቸው ባልታዘዙለትም ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቆረጠ። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ በጥላንን የጸና ሥቃይን አሠቃየው። ከእርሱም ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ በእጁም ብዙ ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን አመኑ። በሰማዕትነትም ሞቱ። ንጉሡም አይቶ በበጥላን ላይ ተቆጣ። ለአንበሳም አስጣለው አንበሳውም እግሩን ላሰው እንጂ ክፉ አላደረገበትም። ሁለተኛም ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ በዚህም ምስክርነቱን ፈጽሞ በመንግሥተ ሰማያት አክሊልን ተቀበለ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages