ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 27 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, July 16, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 27

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሰኔ ሃያ ሰባት በዚች ቀን ከተመረጡ አርድእት ውስጥ ሐዋርያው ሐናንያ አረፈ ቅዱስ ቶማስ ሰንደላት በሰማዕትነት ሞተ፣ የድሃው አልዓዛር መታሰቢያው ነው፣ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ልደቱ ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ሐዋርያው ሐናንያ
ሰኔ ሃያ ሰባት በዚህች ቀን ከተመረጡ አርድእት ውስጥ ሐዋርያው ሐናንያ አረፈ። ይህንንም ቅዱስ ሐዋርያት በደማስቆ ከተማ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት። በውስጧም ሕይወት ሰጭ የወንጌልን ትምህርት አስተማረ ዳግመኛም በቤተ ገብርኤል ውስጥ ሰብኮ ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሆነች የቀናች ሃይማኖት ብዙዎቹን መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው እውነተኛውንም የሃይማኖት ብርሃን አበራላቸው።
ይህም ሐናንያ ሐዋርያው ጳውሎስን ይቅር ባይ ጌታችን በቸርነቱ ከክህደቱ በጠራውና ምርጥ ዕቃ በአደረገው ጊዜ ያጠመቀው ነው እጁንም በራሱ ላይና በዐይኖቹ ላይ ጭኖ ያዳነው እርሱ ነው።
ጌታችንም በእጆቹ ታላላቅ ድንቆችንና ተአምራቶችን አደረገ በስብከቱም ብዙዎች አሕዛብ አመኑ ከአይሁድም ብዙዎቹን ክብር ይግባውና ክርስቶስን ወደ ማመን መለሳቸው።
ከዚህም በኋላ ዐመፀኛው መኰንን ሉክያኖስ ይዞ ታላቅና አስጨናቂ ሥቃይን አሠቃየው ጐኖቹንም ሠንጥቆ በእሳት መብራቶች አቃጠለው። ከዚህም በኋላ ከከተማው አውጥተው በደንጊያ እንዲወግሩት አዘዘ በዚያም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ነፍሱን ሰጠ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ቶማስ ሰንደላት
በዚህችም ቀን ሰንደላት ከሚባል አገር ቅዱስ ቶማስ በሰማዕትነት ሞተ። ከእርሱም ጋራ ሰባት መቶ ወንዶችና ዘጠኝ ሴቶች በሰማዕትነት ሞቱ ።
ይህም ቅዱስ ዕድሜው ዐሥራ አንድ ዓመት በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በበረሀ እሪያዎችን ሲጠብቅ ተገለጸለት ወደ መኰንኑ ሔዶ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢያሱስ ክርስቶስ ስም ይታመን ዘንድ አዘዘው። ያን ጊዜም ተነሥቶ የገመድ አለንጋ ይዞ ብቻውን ወደ እስክንድርያ አገር ሔደ በመኰንኑም ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰም ታመነ።
መኰንኑም ለአማልክት ሠዋ አለው ጸሐፊውም ሊያደርገው ቃል ኪዳን ገባለት ቅዱስ ቶማስም ተቆጥቶ ያቺን አለንጋ አውጥቶ መኰንኑን ብዙ ግርፋት ገረፈው የመኰንኑ ሎሌዎችም ይዘው ጽኑ ሥቃይን አሠቃዩት ሥጋውንም በብረት መጋዝ ሠነጠቁ ክብር ይግባውና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ርዳታን ለመነ ወዲያውኑም መልአኩን ልኮ አዳነው።
ከዚህ በኋላ በእሥር ቤት አሠሩት የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ስለ ታመመው ልጁ ለመነው እርሱም ያንን የገመድ አለንጋ ሰጠውና ይህን አለንጋ በልጅህ ላይ አኑር አለው እንዲሁም አደረገ። ያን ጊዜም ልጁ በእግዚአብሔር ኃይል ዳነ።
መኰንኑም በሰማ ጊዜ ወደርሱ አቅርቦ ለአማልክት ሠዋ አለው ቅዱስ ቶማስም በፊትህ ዕሠዋ ዘንድ ና እንሒድ ብሎ መለሰለት። መኰንኑም ዕውነት መስሎት ደስ አለው ወደ ጣዖቶቹ ቤትም ወሰደው ያን ጊዜ ቅዱስ ቶማስ ጣዖታቱን ያጠፋቸው ዘንድ ወደ ጌታችን ለመነ። ወዲያውኑ ሁሉም ጣዖታት ተሰባበረ ሰይጣኑም በመኰንኑ ላይ ተቀመጠ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም ብሎ እስከሚታመን ድረስ አነቀው። አሕዛብም ይህንን ድንቅ ነገር አይተው እጅግ አደነቁ ክብር ይግባውና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም እያሉም ጮኹ በእርሱም አመኑ።
ያላመኑት ግን በጨለማ ቤት ውስጥ አሠሩት ያለ መብልና ያለ መጠጥ ከብዙ ሥቃይም የተነሣ ከአፉ ደም እየፈሰሰ ዐሥራ አምስት ቀን በዚያ ተቀመጠ የእግዚአብሔር መልአክም ወርዶ ፈወሰው።
አንዲት ሴት ዕውር ልጅ ነበራት ከዚያም ደም ወስዳ የልጅዋን ዐይን አስነካችው ወዲያውኑም አየ። ቅዱስ ቶማስንም ከወህኒ ቤት አውጥተው ሴት አንበሳ ሰደዱበት ወደርሱም በደረሰች ጊዜ እግሮቹን ላሰች ሰገደችለትም ።
ዳግመኛም በብረት መንደልቶ አፉ ላይ ደበደቡት በዚያን ጊዜ በሥቃይ ውስጥ ከእርሱ ጋራ ከበንደላ አገር ቅዱስ በብኑዳ ከበልኪም አገር ቅዱስ ሙሴ ነበሩ። እርስ በርሳቸው አንዱ አንዱን ያጽናናው ነበር።
ከዚህም በኋላ ቅባትና የነዳጅ ድፍድፍ አፍልተው በቅዱስ ቶማስ ራስ ላይ ደፉት ነገር ግን ምንም ምን ጉዳት አልደረሰበትም። እንደገናም አባለ ዘሩን ቈርጠው በአውድማ ውስጥ አበራዩት ደግመውም ታላቅ ደንጊያ በአንገቱ ላይ ሰቅለው አሠቃዩት። ከማሠቃየቱ የተነሣ በደከመው ጊዜ መኰንኑ አርያኖስ ወደ እንዴናው ከተማ ሊወስደው ይዞት ተነሣ ጣው ወደሚባል አገርም በደረሱ ጊዜ የቅዱስ ቶማስን ራስ ቆረጡት በዚያም ምስክርነቱን ፈጸመ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ ከእርሱ ጋራ መከራ ተቀብለው የሞቱ ሰባት መቶ ወንዶችና ዘጠኝ ሴቶችም እርሱ ሥቃይ በተቀበለበት ወራት የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የድሃው አልዓዛር
በዚህች ቀን የድሀው አልዓዛር መታሰቢያው ነው፡፡ ይኸኛው አልዓዛር በሉቃስ ወንጌል ላይ እንደተነገረው ባለጸጋው ነዌ ድሀው አልዓዛር በደጁ ወድቆ ትራፊውን ፍርፋሪ ይመኝ የነበረ ውሾች ቁስሉን እስኪልሱለት ድረስ በባጸጋው ዘንድ የተናቀና የወደቀ ነበር። ሁለቱም ሲሞቱ ግን ባለጸጋው ነዌ በሲኦል ሆኖ እየተሠቃየ ድሀው አልዓዛርን በአብርሃም እቅፍ አይቶታል። ቅዱስ አልዓዛር በዚህች ዕለት በዓመታዊ በዓሉ ታስቦ ይውላል። ሙሉ ታሪኩ በሉቃስ ወንጌል 16፡19-31 ላይ እንዲህ ተቀምጧል። ‹‹ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፣ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፣ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፣ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ድሀውም ሞተ፣ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፣ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። እርሱም እየጮኸ አብርሃም አባት ሆይ ማረኝ፣ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ። አብርሃም ግን (ልጄ ሆይ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሠቃያለህ። ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፣ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል› አለ። እርሱም ‹እንኪያስ አባት ሆይ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና። እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው› አለ። አብርሃም ግን ‹ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ› አለው። እርሱም አይደለም፣ አብርሃም አባት ሆይ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ› አለ። አብርሃምም ‹ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም› አለው።›› ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ
በዚህችም ቀን ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ልደቱ ነው፡፡ ዕረፍቱ ግን ሰኔ 7 ነው እየተባለም በሊቃውንት ይነገራል። የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ሀገሩ ሶርያ ሲሆን አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር። በኤጲስ ቆጶስነት የተሾመባት ሀገር በጤግሮስና በኤፍራጥስ መካከል በምትገኝ ሥሩግ በምትባል ሀገር ስለሆነ ያዕቆብ ዘሥሩግ ተባለ። በሦስት ዓመቱ እናቱ ቤተ መቅደስ ስትወስደው መልአክ እጁን ይዞ በሊቀ ጳጳሱ እጅ እንዲቆርብ አድርጎታል። በዚህም ጊዜ ምሥጢራት ሁሉ ተገልጠውለታል። ገና በ7 ዓመቱ ስለ ሦስት ነገሮች በእጅጉ ያለቅስ ነበር። ይኸውም ‹‹ነፍሴ ከሥጋዬ ተለይታ ስትወጣ፣ ከጌታችን ጋር ስገናኝና መጨረሻውን ፍርድ ስሰማ እነዚህን ሦስት ነገሮች በእጅጉ እፈራለሁ›› እያለ ያለቅስ ነበር። አቡነ ያዕቆብ በ12 ዓመቱ ብሉይንና ሐዲስን አጠናቆ ተምሮ ጨርሷል። ጸጋውን ዐውቀው 5ቱ ታዋቂ ሊቃነ ጳጳሳት መጥተው እጅ ነስተውት አዲስ ድርሰት ድረስልን ቢሉት እርሱም በፍጹም ትሕትና ‹‹በእናንተ ፊት እንኳን አዲስ ድርሰት ልደርስ ቀርቶ የተደረሰውንም መናገር አልችልም›› አላቸው። ያንጊዜም ሕዝቡና ሊቃነ ጳጳሳቱ ‹‹እግዚአብሔር በዚህ ሕጻን ላይ አድሮ ገሠጸን›› እያሉ ንስሓ ገብተዋል። ቅዱስ ያዕቆብ በነበረበት ዘመን በሮማው መናፍቅ ልዮን አማካኝነት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት የተከፈለችበት ጊዜ ነበርና እነ ዲዮስቆሮስ ‹‹የውሾች ጉባኤ›› ከተባለው ከኬልቄዶን ጉባኤ ተለይተው ሃይማኖትን ሲያጸኑ ልዮንንም ማውገዛቸውን ያዕቆብ ሲሰማ በዲዮስቆሮስ ጽናት በእጅጉ ተደስቶ ደብዳቤ ጽፎ አመስግኖታል። እነ ልዮንን ግን አውግዞ እረግሟቸዋል። ልዮንም ተከታይ ባገኝ ብሎ ‹‹እኔን ምሰል›› በማለት ለቅዱስ ያዕቆብ ደብዳቤ ጻፈለት። አቡነ ያዕቆብም ‹‹ሳጥናኤል ከመላእክት ጋር ምን አንድ አደረገው? አንተ ርኩስ ነህ፣ የዲዮስቆሮስን ጥርስ አስወልቀህ፣ ጢሙን አስነጭተህ፣ ሃይማኖትህን የቀየርህ ከሁለት ዓለም ስደተኛ ጋር አልተባበርም፣ ይልቅስ ንስሓ ግባ፣ ንስሓ ባትገባ ግን አንተ ዲያብሎስ ነህ ተከታዮችህም አጋንንት ናቸው›› በማለት መልሱን ጽፎለታል። ልዮንም እምቢ ብሎ በክህደቱ ቢጸናበት አውግዞና እረግሞ ለይቶታል። ንጽሕናውና ቅድስናው ‹‹እንደ መላእክት ነው›› የተባለለት ያዕቆብ ዘሥሩግ ጻድቅም ሐዋርያም ደራሲም ተከራካሪ መምህርም ነው። ሦስት ድርሰቶች ያሉት ሲሆን በስሙ የተጠራው ቅዳሴም አለው።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages