ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 26 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, July 3, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 26

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሰኔ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን የከበረ የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤል በዓሉ ነው እንዲሁም ኔቅሎን በሚባል አገር በፍዩም ገዳም ቤተ ክርስቲያኑ የተከበረችበት ነው፣ የታላቁ ነቢይና መስፍን የነዌ ልጅ የቅዱስ ኢያሱ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤል
ሰኔ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን የከበረ የመላእክት አለቃ የገብርኤል በዓሉ ነው እንዲሁም ኔቅሎን በሚባል አገር በፍዩም ገዳም ቤተ ክርስቲያኑ የተከበረችበት ነው።
በውስጧም ከቤተ ክርስቲያንዋ የጣራ ዕንጨት ብዙ ተአምር ይገለጽ ነበር ጽጋብ በሚሆንባት በዚያች ዓመት ውኃ ይንጠፈጠፋል ረሀብ ከሆነ ግን ላብ እንኳ አይታይም ነበር። የዚህ የከበረ የመላእክት አለቃ ገብርኤል ተአምራቶቹ ብዙዎች ናቸው።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአማላጅነቱ ይማረን ረድኤቱም ከእኛ ጋራ ትሁን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን
በዚህችም ቀን የታላቁ ነቢይና መስፍን የነቢያት አለቃ የሙሴ ደቀ መዝሙር የነዌ ልጅ የኢያሱ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ይህም ከታናሽነቱ ጀምሮ ለሙሴ አንገቱን ዝቅ አድርጎ የሚታዘዝ ፍጹም ትሑት ሆነ ስለዚህም በሙሴ ላይ ያደረ መንፈስ ቅዱስ አደረበት። ነቢዩ ሙሴም ከአረፈ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ የእስራኤልን ሕዝብ ተረከባችው።
እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው ከሙሴ ጋራ እንደኖርሁ ከአንተም ጋራ እኖራለሁ ጽና በርታ ለባለሟሌ ሙሴ ያዘዝሁትን ሕጌን ጠብቅ ከእርሱም ፈቀቅ አትበል ሕጉንም ትጠብቀውና በሱም ትጸና ዘንድ በውስጡም የተጻፈውን ታደርገው ዘንድ በቀንም በሌሊትም አንደበትህ ማንበብን አያቋርጥ።
የኢያሱም ልቡ ጸና ሰላዮችንም ወደ ኢያሪኮ ላከ ሀገሪቱንም አይተው ሲመለሱ የኢያሪኮ ሰዎች አዩአቸው ሰላዮችም እንደሆኑ አውቀው ተከተሏቸው። እነርሱም ረዓብ በሚሏት አመንዝራ ሴት ዘንድ ተሸሸጉ እርሷም ሠወረቻቸው እነርሱም በሚመጡ ጊዜ ከቤተሰቦቿና ከዘመዶቿ ጋራ እንደሚያድኗት ቃል ገቡላት።
በደኅናም ሸኘቻቸው። ከዚህም በኋላ ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ የዮርዳኖስን ወንዝ አሻገረ ካህናቱ የእግዚአብሔርን ታቦተ ሕግ ተሸክመው በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ቆመው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እስከሚሻገሩ ድረስ የወንዙን ውኃ እግዚአብሔር እንደ ግድግዳ አቁሞት ነበርና።
ከዚህም በኋላ ደግሞ በግንብ የተከበበች ኢያሪኮን ሰባት ቀን ዞራት ከእርሱም ጋራ የልዑል ታቦተ ሕጉ ነበረች ቅጽሮቿንም አፈረሰ በውስጧም የሚኖሩ አሕዛብን ሁሉ ከንጉሥዋ ጋር ገደለ ሁሉንም አጠፋቸው።
አሕዛብ ሁሉ የእስራኤልን ልጆች ፈሩአቸው ከመፍራታቸውም ጽናት የተነሣ የገባዖን ሰዎች ተንኰል አደረጉ ስንቃቸውን ሰንቀውና አዘጋጅተው መጡ አሮጌ አቁማዶቻቸውን ያረጁና የተቀደዱ የተጠቀሙም የወይን ረዋቶችን በትክሻቸው ተሸከሙ። ጫማቸውም ያረጀና የተተበተበ ነበር ልብሳቸውም በላያቸው ያረጀ ነበር። ለስንቅም የያዙት እንጀራ የደረቀና የሻገተ ነበረ።
ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ወደ ገልገላ መጥተው እኛ ከሩቅ አገር መጥተናል አሁንም ለእኛ ማሉልን አሏቸው። የእስራኤልም ልጆች ኤዎያውያንን ከእናንተ ጋራ እንዴት መሐላን እንማማላለን አሁንም በአቅራቢያችን ትኖሩ እንደሆነ ተጠንቀቁ አሏቸው። ኢያሱንም እኛ ከሩቅ አገር የመጣን ባሮችህ ነን አሉት እርሱም ከወዴት ናችሁ ከወዴትስ አገር መጣችሁ አላቸው። እነርሱም እኛ ባሮችህ በፈጣሪህ በእግዚአብሔር ስም እጅግ ከራቀ አገር መጣን በግብጻውያን ያደረገውን ሁሉ በዮርዳኖስ ማዶ በሚኖሩ በሁለቱ በአሞሬዎን ነገሥታትም ያደረገውን ሁሉ ሰምተን መጥተናል አሉት።
የአገራችን ሰዎች ሁሉና አለቆቻችን ለመንገድ ስንቅ ያዙ ትቀበሏቸውም ዘንድ ሒዱ እኛ ባሮቻችሁ ነን አሁንም ለእኛ ማሉልን በሉአቸው አሉን። እነሆ ወደእናንተ እንመጣ ዘንድ ከቤታችን በወጣንበት ቀን ይህ እንጀራችን ትኩስ ነበር አሁን ግን ሻግቷል ደርቋልም ይህም የወይን ረዋት አዲስ ሳለ መላንበት አሁን ግን ተራቁቷል አርጅቶም ተቀድዷል መንገዳችን እጅግ የራቀ ነውና ይህም ልብሳችን ይህም ጫማችን አርጅቷል አሏቸው።
መኳንንቱም ስንቃቸውን ተቀብለው አዩ የእግዚአብሔርንም ቃል አልጠየቁም ኢያሱም ከነሱ ጋራ ሰላምን አደረገ ሊያድናቸውም ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን አደረገ የሕዝቡም አለቆች ማሉላቸው። ከሦስት ቀን በኋላም እስራኤል ከቅርብ እንደሆኑ ሰሙ። ኢያሱም በቅርብ እንደሆኑ በሰማ ጊዜ በሽንገላ ለምን ወደእኛ መጣችሁ አሁንም ለእግዚአብሔር ቤትና ለእኛ ባሮች ትሆናላችሁ አላቸው።
የአሞሬዎን ነገሥታትም የገባዖን ሰዎች ሔደው ለእስራኤልና ለኢያሱ እንደ ተገዙ በሰሙ ጊዜ እነዚህ አምስቱ የኢየሩሳሌም ንጉሥ፣ የኬብሮን ንጉሥ፣ የኢያሪሞት ንጉሥ፣ የለኪሶ ንጉሥ፣ የአዶላም ንጉሥ ተሰብስበው ዘመቱ መጥተውም ገባዖንን ከበቡአት ሊዋጉም ጀመሩ። የገባዖን ሰዎችም በገልገላ ውስጥ ወደ እስራኤል ሰፈር ወደ ኢያሱ ልከው ባሮችህን ለመርዳት እጅህ አትስነፍ ከተራሮች ላይ የሚኖሩ የአሞሬዎን ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበውብናልና ወደ እኛ መጥተህ ርዳን ፈጥነህ አድነንም አሉ።
ኢያሱም ከገልገላ ወጣ ሰልፈኞችም የሆኑ ሕዝብ ሁሉ ከእርሱ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው በእጅህ እጥላቸዋለሁና በፊታችሁም አንድ ስንኳ የሚቀር የለምና አትፍሯቸው አለው ኢያሱም ሲገሠግሥ አድሮ ድንገት በሌሊት ደረሰባቸው።
እግዚአብሔርም ከእስራኤል ፊት የተነሣ አስደነገጣቸው ኢያሱም ብርቱ ጥፋትን አጠፋቸው ከእነርሱም ወደ ቢቶሮን ቍልቍለት በሸሹትም እግዚአብሔር የበረድ ድንጋይ ከሰማይ አውርዶ ጨረሳቸው። የእስራኤል ልጆች በጦራቸው ከገደሏቸው በደንጊያ በረዶ የሞቱ በዙ።
ያንጊዜም እግዚአብሔር አሞሬዎንን በእስራኤል ልጆት እጅ አሳልፎ በሰጣቸው ጊዜ ኢያሱ ፀሐይ በገባዖን ጨረቃም በኤሎም ቈላ ትቁም ብሎ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገረ ፀሐይና ጨረቃም ቆሙ። ጠላቶችንም ሁሉንም አጠፋቸው ከእነርሱም የቀረ የለም።
ከዚህም በኋላ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ርስትን አካፈላቸው ያለ ዕውቀት በስሕተት ሰው የገደለ በውስጡ ይማጠን ዘንድ ስባት መማጸኛ ከተሞችን እግዚአብሔር እንደ አዘዘው ሠራ። ዕድሜውም መቶ ሃያ በሆነው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች ሰበሰባቸው የኦሪትን ሕግ እንዲጠብቁ በአምልኮተ እግዚአብሔርም እንዲጸኑ ትእዛዞቹንም እንዳይተላለፉ አዘዛቸው። እንዲህም አላቸው እርሱ ፈጣሪያችን ቀናተኛ ነውና ጣዖት ብታመልኩ ያጠፋችኋል ሕጉን ብትጠብቁ ግን የበረከት ልጆች ትሆናላችሁ።
ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ ያዕቆብ ከኤሞር ልጆች በመቶ በጎች በገዛው ናብሎስ በሚባል ቦታም ተቀበረ ሠላሳ ቀኖችም ያህል ታላቅ ልቅሶ አለቀሱለት።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages