ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 30 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, July 16, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 30

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሰኔ ሠላሳ በዚች ዕለት ነቢይ ሰማዕትና ሐዋርያ የሆነ መጥምቁ ዮሐንስ ተወለደ፣ በሕንደኬ ካሉ ደሴቶች በአንዲቱ ውስጥ የሚኖር ገድለኛ የሆነ አባ ጌሬን አረፈ፣ የአልዓዛር እህቶች የቅዱሳን ማርያ እና የማርታ መታቢያቸው ሆነ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
መጥምቁ ዮሐንስ
ሰኔ ሠላሳ በዚች ዕለት ነቢይ ሰማዕትና ሐዋርያ የሆነ መጥምቁ ዮሐንስ ተወለደ። ይህም በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ ለእግዚአብሔር ልጅ የሰገደው ነው። ይህም በመድኅን ክርስቶስ ራስ ላይ እጁን ጭኖ በውኃ ያጠምቀው ዘንድ የተገባው ነው። በቅዱስ ወንጌል እንደ ተነገረ ወንድ ልጅን ትወልድ ዘንድ የኤልሳቤጥ የፅንሷ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወንድ ልጅን ወለደች። ዘመዶቿና ጐረቤቶቿ እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ስለርስዋ ደስ አላቸው።
በስምንተኛውም ቀን ሊገዝሩት መጡ በአባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን አይሆንም ዮሐንስ ይባል አለች። ከዘመዶችሽ ስሙ እንዲህ የሚባል የለም አሏት። አባቱንም ጠቅሰው ማን ሊባል ትወዳለህ አሉት። እርሱም ብራና ለምኖ ስሙ ዮሐንስ ይባል ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያን ጊዜም አንደበቱ ከድዳነት ተፈትቶለት ተናገረ እግዚአብሔርንም ፈጽሞ አመሰገነው። ስለ ልጁና ስለ መድኃኒታችን መምጣት ልጁ ዮሐንስም የልዑል ነቢይ እንደሚባልና በእግዚአብሔርም ፊት እንደሚሔድ ትንቢት ተናገረ።
ሰብአ ሰገልም መጥተው ከሔዱ በኋላ ሄሮድስ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ስለ ሕፃኑ ዮሐንስ ለሄሮድስ ነገሩት እንዲገድሉትም ጭፍሮችን ላከ ጭፍሮችም ወደ አባቱ ዘካርያስ መጡ ሕፃኑንም ከእርሱ ፈለጉት አባቱም አንሥቶ በትከሻዎቹ ተሸክሞ ወደ ቤተ መቅደስ ከእርሱ ጋራ እንዲሔዱና ሕፃኑን ከዚያ እንዲወስዱት ወታደሮችን ለመናቸው።
ከዚህም በኋላ ሕፃኑን በመሠዊያው ጠርዝ ላይ አኖረውና ከዚህ ራሳችሁ ተቀብላችሁ ውሰዱት አላቸው ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መልአክ ነጥቆ ወደ በረሀ ወሰደው። ጭፍሮችም ባላገኙት ጊዜ አባቱ ዘካርያስን ገደሉት። ሕፃኑ ግን አድጎ ለእስራኤል እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ በበረሀ ውስጥ ኖረ።
የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እነሆ ብሎ ኢሳይያስ የተናገረለት ይህ ነው። ሚልክያስም ስለሱ እንዲህ አለ። በፊትህ ጐዳናዬን አስተካክሎ የሚጠርግ መልእክተኛዬን እኔ እሰዳለሁ።
ራሱ መድኃኒታችንም ስለርሱ ሲናገር ሴቶች ከወለዱአቸው መጥምቁ ዮሐንስን የሚበልጠው የለም ብሏል። ይህ የእግዚአብሔርን ልጅ በአጠመቀውና የማትዳሠሥ ራሱን በዳሠሠው ጊዜ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል የአብን ቃል ሰምቷልና።
ዳግመኛም ክብር ይግባውና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሲቀመጥ አየ። እኛም መድኃኒታችን እንዲምረንና ይቅር እንዲለን በአማላጅነቱ እያመን መታሰቢያውን እናድርግ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ጌሬን
በዚህችም ዕለት ደግሞ በሕንደኬ ካሉ ደሴቶች በአንዲቱ ውስጥ የሚኖር ገድለኛ የሆነ አባ ጌራን አረፈ። እርሱም እግዚአብሔርን የሚፈራውና የሚወደው ጾምና ጸሎትንም የሚወድ ነበር። ወደ እግዚአብሔርም የሚለምነውን ሁሉ ይሰማው ነበር። በጸሎቱም ከዚያች አገር ንዳድ፣ አባር፣ ድርቅ፣ በጠላት መማረክ፣ የደም መፍሰስና የመርከቦች መሥጠም ተወገደ የፈለገውንም ሁሉ በጸሎቱ ያገኝ ነበር።
ሰይጣንም ስለዚህ ስለ ተሰጠው ጸጋ ቀናበት በዕንቊ ያጌጠ የነገሥታትን ልብስ በለበሰች መልከ መልካም ሴት አምሳልም ታየው እርሷም ብቻዋን ትንጐራደድ ነበር። በአያትም ጊዜ ወደርሷ ሒዶ ሥራዋን ጠየቃት እርሷም እንዲህ አለችው። የንጉሥ ሰርስባን ልጅ ነኝ እኅቴ ለአባቷ ባሮች ጋራ በአመነዘረች ጊዜ ሁላችንንም ሊገድለን ፈለገ። ስለዚህ ፈርቼ በሌሊት ወጣሁ ወደዚች በረሀም መጣሁ ቅዱሱን ሰው አንተን በማግኘቴም እድለኛ ነኝ። እርሱም ወደ እኔ የሚመጡ ሰዎች እንዳያዩሽ ወደዚያች የዐለት ዋሻ ሒጂ አላት።
በሌሊትም ከአራዊት የተነሣ እንደፈራ ሰው እየጮኸች መጥታ የዱር አራዊት እንዳይበሉኝ ክፈትልኝ አለችው። እርሱም ከፈተላትና ገባች በጐኑም ተኝታ ደረቱን አቀፈችው ልቡን ወደ ፍቅርዋ እስከ አዘነበለችው ድረስ ነገሯን አለሰለሰችለት። ያን ጊዜ ያደረበት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተለየው ከእርሷም ጋር ተኝቶ ኃጢአት እንደሚሠራ ሆነ።
ከስህተት ስካርም በነቃ ጊዜ በጠላት ሰይጣን ተንኰል ተሸንፎ እንደ በደለ አወቀ። ከዚህም በኋላ ከሰይጣን ተንኰል የተነሣ ያገኘውን ሁሉ በሥጋውም ኃጢአት እንደሠራ ጻፈ። ከዚህ በኋላም ከደሴቱ ተራራ ደንጊያ አንሥቶ እስከሚሞት ድረስ ራሱንና ደረቱን እየደበደበ ኖረ። ነፍሱም ድና ወደ ዘላለም ሕይወት በጌታ ቸርነት ገባች።
ከዚህም በኋላ እንደ ልማዳቸው ከእርሱ ቡራኬ ሊቀበሉ ሰዎች መጥተው አላገኙትም በፈለጉትም ጊዜ ተኝቶ አገኙትና ያንቀላፋ መስሏቸው ሊቀሰቅሱት ጀመሩ ግን ሞቶ አገኙት አለቀሱለት ተሳለሙት ገንዘውም ቀበሩት።
ከዚህም በኋላ ሞቱ በጠላት ሰይጣን ተንኮል ምክንያት ስለመሆኑ የጻፈውን አገኙ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የቅዱሳን ማርያ እና የማርታ (የአልዓዛር እህቶች)
በዚህችም ዕለት ከአራት ቀኖች በኋላ ጌታችን ከመቃብር ያስነሳው የአልዓዛር እህቶች የማርያ እና የማርታ መታቢያቸው ሆነ፡፡ በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ 'እንተ ዕፍረት-ባለ ሽቱ' ተብለው የሚጠሩ 2 እናቶች ነበሩ:: 2ቱም ስማቸው ማርያም ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን 'ማርያም ኃጥዕት ከኃጢአት የተመለሰች': 2ኛዋን ደግሞ 'ማርያም እኅተ አልዓዛር - በቢታንያ የነበረችው ብለው አበው ይጠሯቸዋል::
በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት የተመለሰችው ስትሆን በዮሐንስ ወንጌል 12:1 ላይ ያለችው የአልዓዛር እህት (ድንግሊቱ) ናት:: ዛሬም የምናስባት ይህቺውን እናታችን ነው::
ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሚያስተመርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች ድንግል ወጣት ናት:: ወላጆች ባልነበረበት ቤት ውስጥ ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል::
በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው:: አልዓዛርን ከ72ቱ አርድእት: ማርያምና ማርታን ደግሞ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል:: ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር::
ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ:: በ4ኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርያም በጌታ ፊት ሰግዳ "እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እሑየ-አንተ በዚህ በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር" ብላ አለቀሰች:: (ዮሐ.11)
ጌታም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አምላክነቱ አራርቶት አለቀሰ:: ወዲያውም በስልጣነ ቃሉ አዞ አልዓዛርን አስነሳው:: ከፋሲካ (ጌታ ከመሰቀሉ 6 ቀናት) በፊትም ቅዱሳኑ ለጌታ ግብር አገቡ:: እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታደመላቸው:: (ዮሐ. 12:1)
በዚያም አልዓዛር ከጌታ ጐን ሲቀመጥ: ቅድስት ማርያም ከጌታ ሥር ተንበርክካ: ናርዶስ የሚሉትን የ300 ዲናር ሽቱ በጌታ ላይ አፈሰሰች:: መዓዛ መለኮቱና ሽቱው ሲገናኝ "መልዐ መዓዛሁ" እንዲል ምስጥ የሚያደርግ ሽታ ቤቱን ሞላው::
በወቅቱ ይሁዳ ቢቃወምም ጌታ ምላሹን ሰጥቶታል:: ቅድስት ማርያምንም "ማርያምሰ ኃርየት መክፈልተ ሠናየ ዘኢየኃይድዋ" ብሎ አመስግኗታል:: ያስመሰገናት ቁጭ ብላ በተመስጦ መማሯ ብቻ እንዳልሆነ አባ ሕርያቆስ መስከሯል::
ሲመክረንም "አርምሞንና ትዕግስትን እንደ ማርያም ገንዘብ እናድርግ" ብሎናል:: (ቅዳሴ ማርያም) ቅድስት ማርያም በጌታችን ክርስቶስ በኅማሙ ጊዜ: ሲቀብሩት ነበረች:: ትንሳኤውንም ዐይታለች:: ከጌታ እርገት በኋላም መንፈስ ቅዱስን ተከትላ ለወንጌል አገልግሎት ተግታለች::
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት ጸሎት መንፈሳውያን በሆኑ በቅዱሳን መላእክትም አማላጅነት ይልቁንም አምላክን በወለደች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጸሎቷና በአማላጅነቷ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages