አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ አንድ በዚህችም ቀን ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ የሰማዕትነቱ መታሰቢያ ነው፣ ሰውነቷን ለእግዚአብሔር የሰጠች ቅድስት ቅፍሮንያ ሰማዕት ሆነች፣ቅዱሳን ብዮክና ብንያሚን አረፉ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በመሸታ ቤት በአረዷት ሴት ላይ ተአምርን አደረገ።
ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ
ሐምሌ አንድ በዚችም ቀን የሊቀ ጳጳሳቱ የአግናጥዮስ የሰማዕትነቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ይህም ቅዱስ የወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙሩ ነው በስብከተ ወንጌልም በማገልገል ከእርሱ ጋር ብዙ አገሮችን ዙሮ አስተምሮአል ከዚህም በኋላ በአንጾኪያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾመው በውስጥዋመሰ ሕይወተሰ የሆነ የወንጌልን ትምህርት አስተማረ ብዙዎችንም እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው በትምህርቱም ልቡናቸውን አበራላቸው።
ከዚህም በኋላ ጣዖትን ለሚያመልኩ ስሕተቻተውን በገለጠላቸው ጊዜ ተቆጡ። ወደ ከሀዲው ንጉሥ ወደ ጠራብዮስ ሔደው ከሰሱት እንዲህም አሉት "አግናጥዮስ የአማልክቶችህን አምልከሸ ይሽራል እኮን ሰዎችንም እያስተማረ ክርስቶስን ወደ ማመን ያስገባቸዋል"። በዚያንም ጊዜ ወታደሮች ልኮ ወደርሱ አስመጣውና "አግናጥዮስ ሆይ ለምን ይህን አደረግህ የአማልክቶቼን አምልኮስ ለምን ሻርክ ሰዎችን ሁሉ እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ አስገብተሃቸዋልና" አለው።
አግናጥዮስም "ንጉሥ ሆይ ቢቻለኝስ ያክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ ክርስቶስ አምልኮት ባስገባሁህ ነበር" አለው ንጉሡም "ይህን ነገር ትተህ ለአማልክቶቼ ሠዋ አለዚያ በታላቅ ሥቃይ አሠቃይሃለሁ" አለው። "በእኔ ላይ የምትሻውን አድርግ እኔ ግን ለረከሱ አማልክቶችህ አልሠዋም ሥቃይህንም እሳትም ቢሆን አንበሳንም ቢሆን አልፈራም ከሕያው ንጉሥ ከክርስቶስ ፍቅር ልትለየኝ አትችልም" አለው። ይህንንም ሲሰማ ንጉሡ ተቆጣ ያሠቃዩትም ዘንድ አዘዘ በተለያዩ በብዙ ሥቃዮችም አሠቀሠዩት በእጆቹም ውስጥ እሳት አድርገወሰ ከእጆቹ ጋር በጉጠት ይዘው አቃጠሉት።
ከዚህም በኋላ በዲንና በቅባት እያነደዱ ጎኖቹን አቃጠሉ በሾተሎችም ሥጋውን ሠነጠቁ። ከማሠቃየትም በደከሙ ጊዜ የሚያደርጉበትን እስከመክሩ ድረስ ከወህኒ ቤት ጨመሩት ብዙ ቀኖችም በዚያ ኖረ።
ከዚህም በኋላ አስታውሱት ከወህኒቤትም አውጥተው በንጉሡ ፊት አቆሙት ንጉሡም "አግናጥዮስ ሆይ አማልክቶቼን ብታያቸው ውበታቸው ባማረህ ነበር" አለው። ቅዱሱም "ንጉሥ ሆይ አንተ በክብር ባለቤት ክርስቶስ ብታምን ሙታኖችን የምታሥነሣቸው በሽተኞችንም የምትፈውሳቸው ባደረገህ ነበር"። ንጉሡም "ለፀሐይ ከመስገድ የተሻለ የለም" አለ የከበረ አግናጥዮስም "መንግሥቱ የማያልቀውን ፈጣሪ ትተህ ለተፈጠረ ፀሐይ ትሰግዳለህን?" ብሎ መለሰ ንጉሡም "ለራስህ መልካም አልክ ግን በመተላለፍ የአንጾኪያና የሶርያን ሰዎች ስበሕ ወደ ክርስቶስ አምልኮት አስገባሃቸው እንጂ" አለው። የከበረ አግናጥዮስም ተቆጥቶ "ንጉሥ ሆይ ከንቱ የሆነ ጣዖትን ከማምለክ ሰዎችን ስለሳብኳቸውና ሰማይና ምድርን ወደ ፈጠረ ወደ ክርስቶስ አምልኮት ስለአስገባኋቸው በእኔ ላይ ትቆጣለህን ለረከሱ ጣዖቶችህስ እንድሠዋ ታዘኛለህን እኔ ግን ቃልህን ተቀብዬ ለሰይጣናት አልሠዋም ለእውነተኛ አምላክ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እሠዋለሁ እንጂ" አለው።
በዚያንም ጊዜ ንጉሥ ተቆጣ ከሥጋው ምንም ምን ሳያስቀሩ ይበሉት ዘንድ ሁለት የተራቡ አንበሶችን በላዩ እንዲሰዱ አዘዘ። የከበረ አግናጥዮስም አንበሶች ወደርሱ ሲቀርቡ በአያቸው ጊዜ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሕዝብን እንዲህ አላቸው "ከዚህ የተሰበሰባችሁ እናንተ የሮሜ ሰዎች ቃሌን ስሙ እወቁም እኔ ይህን ሥቃይ የታገሥኩት በትዕቢትና በትምክህት አይደለም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታዬና በፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንጂ። አሁንም እኒህ አንበሶች እንደ ሥንዴ ይፈጩኝ ዘንድ ነፍሴ ወደደች የክብር ባለቤት ወደ ሆነ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ልትሔድ ነፍሴ ሽታለችና"።
ንጉሡም ቃሉን ሰምቶ አደነቀ ድንጋጤ አድሮበት እንዲህ አለ "የክርስቲያኖች ትዕግሥታቸው ምን ይብዛ ስለ አምልኮት ከአረማውያን በእንዲህ ያለ ሥቃይ ላይ የሚታገሥ ማን ነው" አለ። እነዚያ አንበሶችም ወደ ቅዱሱ ቀረብ ብለው ደንግጠው ቆሙ። ከዚህም በኋላ አንዱ አንበሳ እጁን ዘርግቶ አንገቱን ያዘው በዚያንም ጊዜ ደስ ብሎት ነፍሱን በፈጣሪው ክርስቶስ እጅ ሰጠ ልመናውንም ፈጸመለት።
ለእነዚያ አንበሶችም ሥጋውን ይዳስሡት ዘንድ አልተቻላቸውም የክብር ባለቤት ክርስቶስ ዳግመኛ እስከ ሚመጣ የተጠበቀ ሆነ እንጂ ከዚህም በኋላ በክብር በምስጋና ከከተማ ውጭ ቀበሩት እንደዚህም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመልካም ተጋድሎ ምስክርነቱን ፈጸመ ለምእመናንም ጠቃሚ ይሆን ዘንድ ገድሉን ጻፉ የበዓሉንም መታሰቢያ አደረጉለት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስት ቅፍሮንያ
በዚህች ቀን ሰውነቷን ለእግዚአብሔር የሰጠች ቅድስት ድንግልና መስተጋድልት ቅፍሮንያ ሰማዕት ሆነች።
እርሷም በደናግል ገዳም ቁጥራቸው ሃምሳ ለሆኑ ለደናግሉ እመ ምኔት እኅት ነበረች። የእመ ምኔትዋም ስሟ ኦርያና ነው። ይህችንም ቅድስት በፈሪሀ እግዚአብሔር አሳደገቻት። በትሩፋት ሥራ ተጋዳሊት እስከሆነችም ድረስ አምላካውያት የሆኑ መጻሕፍትን አስተማረቻት።
ከዚህም በኋላ ፍጹም ገድልን ጀመረች በየሁለት ቀኑ ትጾም ነበር ብዙ ጸሎታትንም ትጸልይ ነበር። ያቺም እመ ምኔት ሥራዋ ያማረ በሃይማኖቷም የጸናች ነበረች። በበጎ ሥራ ሁሉ እንዲጸኑ ወገኖቿን ታስተምራቸው ነበር።
ከዚህም በኋላ ሰዎች ሁሉ ጣዖታትን እንዲያመልኩ ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ በአዘዘ ጊዜ ብዙዎች ክርስቲያኖችን ይዘው አሠቃዩአቸው ሰማዕታትም ሆኑ። እሊያ ደናግልም ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም ከገዳም ወጥተው ሸሽተው ተሠወሩ። እመ ምኔቷ ግን ከዚች ቅድስት ቅፍሮንያ ጋራ ብቻዋን ቀረች።
በማግሥቱም የንጉሡ መልክተኞች ወደ ዚያ ገዳም በመጡ ጊዜ እመ ምኔቷን አግኝተው ያዟት ሌሎችንም ደናግል ፈለጓቸው ግን አላገኟቸውም። ቅድስት ቅፍሮንያም በእርሷ ፈንታ እኔን ውሰዱኝ ይቺንም አሮጊት ተውዋት አለቻቸው። እነርሱም ያዟት በብረት ሰንሰለትም አሠሩዋት መኰንኑ ወደአለበትም ከተማ ወሰዱዋት እመ ምኔቷም እያለቀሰች ተከተለቻቸው።
ወደ መኰንኑም በአደረሷት ጊዜ ለአማልክት ሠዊ አላት ብዙ ቃል ኪዳንም ገባላት እርስዋ ግን ቃል ኪዳኖቹን አቃለለች ትእዛዙንም አልተቀበለችም እንዲደበድቧትም አዘዘና በበትሮች ደበደቧት።
ዳግመኛም ልብሷን ገፍፈው ሥጋዋን ግልጥ እንዲያደርጉ አዘዘ እመ ምኔቷ ኦሪያናም አንተ ከሀዲ ይቺን ታናሽ ብላቴና እንዳጐሳቈልሃት እግዚአብሔር ያጐሳቍልህ ዘንድ አለው ብላ ጮኸች። መኰንኑም እጅግ ተቈጥቶ ይህቺን ቅድስት ቅፍሮንያን አሥረው በመንኰራኵር ውስጥ እንዲያሠቃዩዋት በብረት መጋዝም እንዲሠነጥቋት አዘዘ ሁሉንም አደረጉ ይህንም ሁሉ ፈጸሙባት እርሷም ርዳታን ሽታ ወደ እግዚአብሔር ጮኸች ወዲያውኑ ከሕመሟ ሁሉ ድና ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባት ሆነች።
ከዚህም በኋላ ደግሞ ምላሷንና ሕዋሳቷን ሁሉ ቆረጡ ጥርሶቿንም ሰበሩ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለ ሕማም አስነሣት። መኰንኑም እሷን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጧት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጀች።
አንድ ባለ ጸጋ ምእመን ሰውም መጥቶ የቅድስት ቅፍሮንያን ሥጋ ወሰደ በአማሩ የሐር ልብሶችም ገንዞ በወርቅ ሣጥን አኖራት ከሥጋዋም ብዙ ድንቅ ታአምር ተገለጠ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱሳን ብዮክና ብንያሚን
በዚህችም ቀን ቅዱሳን መስተጋድላን ብዮክና ብንያሚን አረፉ። እሊህም ቅዱሳን በግብጽ ደቡብ በቴዎዳ አውራጃ ቱና በሚባል አገር የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ነበሩ። እነርሱም ወንድማማች ነበሩ። አባታቸውም የቤተ ክርስቲያን ሹም የሆነ ደግና የዋህ ሰው ነበረ እሊህም ሁለቱ ልጆቹ በእግዚአብሔር ጸጋና በቅድስና ፍጹማን ነበሩ።
እግዚአብሔርም በእጆቻቸው ተአምራትን ያደርግ ነበር በሽተኞችን ሁሉ ይፈውሱ ነበር እነርሱም ከቤተ ክርስቲያኑ የጉድጓድ ውኃ ቀድተው በሽተኞችን ያጥቧቸዋል ወዲያውኑም ከበሽታቸው ይድኑ ነበር።
የአባታቸው የዕረፍቱ ቀን በቀረበ ጊዜ በዚያን ሰዓት ቀሲስ ብንያሚን ቍርባን ያሳርግ ዘንድ የቅዳሴ ልብስ ለብሶ በቤተ መቅደስ ነበረ መልዕክተኞችም መጥተው አባቱ ለመሞት እንደ ተቃረበ እርሱንም እንደሚፈልገው ነገሩት።
ብንያሚንም የቍርባኑን ሥርዓት ሳልፈጽም ልብሰ ተክህኖውን አላወልቅም ከመሞቱ በፊት እንዳየው እግዚአብሔር ከፈቀደ ይቆየኛል ካልሆነም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን አለ። አባቱም ሁለተኛና ሦስተኛ ጊዜ ላከ አባ ብንያሚን ግን የቍርባኑን ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ ወደ አባቱ ሔደ ሙቶም አገኘው ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ንዋየ ቅድሳትም እጅግ አዘነ እነርሱ በእርሱ ዘንድ እየኖሩ ዕቃዎችን ያኖረበትን ቦታ አላመለከታቸውም ነበርና።
ወንድሙ ብዮክም አባታቸው ስለ አስቀመጠው ንዋየ ቅድሳት ወደ አስቄጥስ ገዳም ወደ ቅዱሳን አረጋውያን ሒዶ እንዲጠይቅ መከረው። አባ ብንያሚንም በሔደ ጊዜ የአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት አባ ዳንኤልን አገኘው አባ ዳንኤልም ስለርሱ የመጣበትን ሥራ ሁሉ ነገረው ነገር ግን ወደ አንድ ጻድቅ ሰው እንዲሔድ አዘዘው እርሱም ንዋየ ቅድሳቱ ያለበትን እንደሚያስረዳው ነገረው።
በሔደም ጊዜ እንደ አመለከተው ያንን ጻድቅ ሰው አገኘው። እርሱም ገልጾ አስረዳው በተመለሰም ጊዜ እንዳስረዳው አገኘው። ከዚህም በኋላ በመልካም ገድል ሁሉ ከወንድሙ ጋራ ተጠምዶ ኖረ። ለሕሙማን ነፍሳችው ሳትወጣ ያቀብሏቸው ዘንድ ከቅዱስ ቍርባን ከፍለው በሣጥን የማኖር ሥርዓት ነበራቸው ሰይጣንም ከይሲን አነሣሣውና ሣጥኑን ቀድዶ ከዚያ ከቅዱስ ቍርባኑ በላ።
ብዮክና ብንያሚንም ይህን ባወቁ ጊዜ እጅግ አዘኑ ከይሲውንም ገደሉት ከዚህም በኋላ የተቀደሰውን ቍርባን ስለ በላ ከይሲውን ይበሉት ዘንድ ተማከሩ ፈቃዱም ከሆነ እንዲያስረዳቸው እግዚአብሔርን ለመኑት የእግዚአብሔር መልአክም ተገለጸላቸውና ያን ከይሲ ይበሉት ዘንድ አዘዛቸው እነርሱም በሉት። ከበሉትም በኋላ አረፉ።
እግዚአብሔርም ሥራቸውንና ገድላቸውን ለአንዲት ድንግል ሴት ገለጸ እርሷም የእሊህን ቅዱሳን ገድል ለሕዝብ ተናገረች እነርሱም የአማረች ቤተ ክርስቲያንን ሠርተው ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከሥጋቸውም ብዙ ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በመሸታ ቤት በአረዷት ሴት ላይ ተአምርን አደረገ። ሥራ የሚሠራ አንድ ጎልማሳ ነበር ከሐዋርያው ቶማስም እጅ የተባረከ እንጀራ ከሕዝብ ጋራ ተቀበለ። ወደ አፉም ሊጨምረው በወደደ ጊዜ እጆቹ ደረቁ። ያዩት ሰዎች ግን በዚህ ሰው ላይ የሆነውን ለሐዋርያው ነገሩት።
ሐዋርያው ቶማስም ጠራው ልጄ ሆይ አትፈር ንገረኝ የእግዚአብሔር ቸርነት በግልጽ ዘልፎሃልና አለው። ያም ሰው ከሐዋርያው እግር በታች ሰገደ መልካም ሥራ የሠራሁ መስሎኝ ክፉ ሥራን ሠርቻለሁ አንዲት የጠጅ አበዛ ሴት ነበረች አስቀድሞ ወደርሷ እኔ እገባ ነበር። አንተም በንጽሕና እንድንኖር አስተማርከን ያችም ሴት ከእርሷ ጋራ እተኛ ዘንድ ነዘነዘችኝ ስለዚህም ሰይፍ አንሥቼ አረድኳት ሐዋርያውም እንዴት እንዲህ ያለ ቁጣና የአውሬ ሥራን ሠራህ አለው።
ከዚህ በኋላም ውኃ ያመጡ ዘንድ ሐዋርያው አዘዘና በውኃው ላይ ጸለየ ጐልማሳውንም በእግዚአብሔር ታምነህ እጆችህን ታጠብ አለው ሲታጠብም ዳነ። ከዚህም በኋላ የዚያች ሴት በድን ወደ አለበት ና ምራኝ አለው ያም ጐልማሳ መርቶ ወደ ቦታዋ አደረሰው በደረሰም ጊዜ አይቷት እጅግ አዘነ።
ወደ ውጭም አውጥተው በዐልጋ ላይ ያኖሯት ዘንድ አዘዘ እንዳዘዛቸውም አደረጉ እጁንም በላይዋ ጭኖ ጸለየ። ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ጐልማሳውን ሒድ እጇን ይዘህ እኔ ቀድሞ በእጄ ገደልኩሽ አሁን ግን በሃይማኖት በእኔ እጅ ክርስቶስ ያስነሣሽ በላት አለው። እርሱም እንዳዘዘው አደረገ እጇንም ይዞ ሳባት ፈጥናም ተነሣች ሐዋርያውንም አየችው ዐልጋዋንም ትታ ከሐዋርያ ቶማስ እግር በታች ሰገደች የልብሱንም ጫፍ ይዛ በአንተ ዘንድ አደራ ያስጠበቀኝ ባልንጀራህ ወዴት አለ አለችው።
ሐዋርያም ወደየት ደርሰሽ ነበር ንገሪኝ አላት እርሷም አንተ ከእኔ ጋራ እያለህ እንዴት ንገሪኝ ትለኛለህ አለችው ያየሽውን ንገሪ አላት። ከሥጋዬ በተለየሁ ጊዜ አንድ ልብሱ የቆሸሸ ሽታውም የሚከረፋ ጠቋራ ተቀበለኝ የእሳት ጉድጓድና የእሳት መንኰራኵር ወደአለበት ቦታ ወሰደኝ ደግሞም እድፍንና ትልን የተመላ ጉድጓድን አየሁ ነፍሳትም በውስጡ ይንከባለላሉ። በዚያም በምላሳቸው የተንጠለጠሉ አሉ በጠጉራቸውም የተንጠለጠሉ አሉ በእጆቻቸውም በእግሮቻቸውም የተንጠለጠሉ አሉ በላያቸውም ድኝ ይጤስባቸዋል ያስጨንቋቸዋልም።
ያ የሚመራኝም እኒህ ነገረ ሰሪዎች፣ ሐሰተኞች፣ አመንዝራዎችና ቀማኞች፣ ሌቦች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ድኆችንና በሽተኞችን የማይጐበኙ፣ የእግዚአብሔርንም ሕግ የማያስታውሱ ናቸው ስለዚህ እንደ ሥራቸው ይቀጣሉ አለኝ አለች።
ሐዋርያው ቶማስም ከዚያ የነበሩትን ይቺ ሴት የምትለውን ሰማችሁን ያለው ሥቃይ ይህ ብቻ አይደለም ነገር ግን ከዚህ የሚከፋ አለ እናንተም የኃጢአትን ሥራና ክፉ አሳብን ትታችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። ትሕትናን፣ የዋህነትንና ፍቅርን፣ ንጽሕናንም ጠብቁ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ጸጋን ትቀበላላችሁ አላቸው።
ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም ሕዝብ አመኑ ለድኆችም ምጽዋትን ሊሰጡ ብዙ ገንዘብ ሰብስበው አመጡ ለድኆች ምጽዋት መስጠት ለሐዋርያው ልማዱ ነበርና።
ወሬውም በየሀገሩ ሁሉ ደርሶ በሽተኞችን ሁሉ አጋንንት የያዟቸውንም አምጥተው በጎዳና ዳር አኖራአቸው ሁሉንም በእግዚአብሔር ኃይል አዳናቸው።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ
No comments:
Post a Comment