አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ ሦስት በዚች ቀን ቅድስት መሪና ሰማዕት ሆነች፣ ቅዱስ ለንጊኖስ ሰማዕት ሆነ።
ቅድስት መሪና
ሐምሌ ሃያ ሦስት በዚች ቀን ቅድስት መሪና ሰማዕት ሆነች። የዚችም ቅድስት የአባቷ ስም ዳኬዎስ ነበር እርሱም በአንጾኪያ ሀገር ለጣዖታት ካህናት አለቃ ነበር ያን ጊዜ ንጉሡም ከሀዲው ዳኬዎስ ነበር።
አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ እናቷ ሞተች አባቷም ከከተማ ውጭ ለምትኖር ሞግዚት ሰጣት እርሷም ክርስቲያናዊት ነበረች የክርስቶስ የሆነ የሃይማኖት ትምህርትን ሁሉ አስተማረቻት። ዐሥራ አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ አባቷ ሞተ።
ከዚህም በኋላ ሰዎች የሰማዕታትን ተጋድሏቸውንና መከራቸውን ሲናገሩ ሰምታ የጌታ ክርስቶስ ፍቅር በልቧ አደረ በሰማዕትነት መሞትንም ፈልጋ ሔደች።
በዚያን ጊዜም ከሀዲ መኰንን ወደዚያች አገር ደረሰ እርሷንም አይቶ ወደርሱ አስመጣትና ከወዴት ነሽ አላት ክብር ይግባውና ከጌታ ኢየሱስ ሰዎች ወገን ነኝ ስሜም መሪና ነው አለችው። ደም ግባቷንና ላሕይዋንም አይቶ መታገሥ ተሳነው እሺ ትለው ዘንድ በብዙ ነገር አባበላት። እርሷ ግን ረገመችው የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመች።
ያን ጊዜም በብረት ዘንጎች ይደበድቧት ዘንድ ደሟ እንደ ውኃ እስኪፈስ ሕዋሳቷን ይቆራርጡ ዘንድ አዘዘ። ያን ጊዜም ወደ ጌታ እግዚአብሔር ጸለየች የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም መጥቶ አዳናት። ሁለተኛም ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧት ዘንድ አዘዘ ጌታችንም ወደ ሰማይ አውጥቶ የቅዱሳን ሰማዕታትንና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳይቶ ወደ ቦታዋ መለሳት። በማግሥቱም ሥጋዋን በመጋዝ እንዲሠነጥቁ ጐኖቿንም እንዲሰነጣጥቁና በእሥር ቤት እንዲጥሏት አዘዘ ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ አዳናት።
በወህኒ ቤቱ ውስጥም ቁማ ስትጸልይ እጅግ የሚያስፈራ ታላቅ ዘንዶ ወደ ርሷ መጣ በአየችውም ጊዜ ደነገጠች ሰውነቷ ሁሉ ተንቀጠቀጠ መናገርም ተሳናት። ያን ጊዜም እጆቿ በመስቀል ምልክት አምሳል እንደተዘረጉ በልቧም ስትጸልይ ወደርሷ ቀርቦ ዋጣት። ያን ጊዜም ሆዱ ተሠንጥቆ ያለ ጉዳት ወጣች እግዚአብሔርንም አመሰገነችው።
ሁለተኛም በጥቁር ሰው አምሳል ሰይጣንን አየችው እጆቹም በጉልበቶቹ ላይ ተጨብጠው ነበር። ፊቷንም በመስቀል ምልክት አማትባ በራሱ ጠጉር ይዛ ደበደበችው። በእግሮቿም ረገጠችው ያን ጊዜም ክብር ይግባውና የጌታ ክርስቶስ ዕፀ መስቀል ተገለጠላት በላዩም ነጭ ርግብ ተቀምጣ እንዲህ ብላ አነጋገረቻት መሪና ሆይ የመንፈስ ቅዱስን የጸጋ አረቦን ተቀብለሻልና ደስ ይበልሽ።
በማግሥቱም መኰንኑ ልብሷን አራቁተው ዘቅዝቀው ሰቅለው እንዲአቃጥሏት ደግሞም ውኃ ከአፈሉበት ጋን ውስጥ እንዲጨምሩዋት አዘዘ። በውስጡም ሁና ስትጸልይ ከሰማይ ርግብ መጣ በአፉም ውስጥ የወርቅ አክሊል ነበር ማሠሪያዋንም ፈትቶ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ አጠመቃት እግዚአብሔርንም እያመሰገነች ከውኃው ውስጥ ወጣች።
መኰንኑም እንደ ዳነች በአየ ጊዜ ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ወደ ሰማዕትነቱ ቦታም በደረሰች ጊዜ ነፍሷን በፍቅር ይቀበል ዘንድ ወደ ጌታችን ጸለየች። ክብር ይግባውና ጌታችንም ተገለጠላት ስሟን ለሚጠራ መታሰቢያዋንም ለሚያደርግ ገድሏንም ለሚጽፍ ወይም ለሚያነበውና ለሚሰማው ኃጢአቱን እንዲአስተሠርይለት ለርሷም ርሱን እንዲሰጣት ቃል ኪዳን ሰጣት።
ከዚህም በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጡ ከእርሷም ብዙ ተአምር ተገለጠ ዕውራን አይተዋልና፣ ሐንካሶች በትክክል ሔደዋልና፣ ደንቆሮዎችም ሰምተዋልና፣ ዲዳዎችም ተናግረዋልና ቁጥር የሌላቸው ብዙ ሰዎችም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ለንጊኖስ
በዚችም ቀን ከቀጰዶቅያ አገር ለንጊኖስ ሰማዕት ሆነ። ይህም ቅዱስ ከጲላጦስ ጭፍሮች ውስጥ ነበር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ደኅንነት መከራ እንዲቀበል የፈቀደበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ በእርሱ ላይ የፈለጉትን ያደርጉ ዘንድ ለዐመፀኞች ፈቅዶላቸው ነበር። ይህም ለንጊኖስ ጌታን ይሰቅሉት ዘንድ ጲላጦስ ከአዘዛቸው ወታደሮች ውስጥ ነበር።
በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ ጌታችንን የቀኝ ጐኑን ወጋው ከጐኑም ደምና ውኃ ፈሰሰ። ይህንንም አይቶ እጅግ አደነቀ ከዚህም በፊት ፀሐይ እንጨለመ፣ ጨረቃ ደም እንደሆነ፣ ዐለቱም እንደተሠነጠቀ፣ ሙታንም እንደተነሡ አይቶ ነበር።
ጌታችንም በተነሣ ጊዜ ስለ ትንሣኤው የሆነውን ሰምቶ ይህን ምሥጢር ይገልጽለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ሐዋርያው ጴጥሮስንም ላከለት እርሱም ነቢያት ስለ ጌታችን፣ ስለ መከራው፣ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ መሞቱ፣ ስለ መነሣቱ፣ ስለ ዕርገቱም ትንቢት እንደተናገሩ ነገረው። እርሱም ከቅድስት ድንግል በሥጋ ተወልዶ ዓለምን ለማዳን የመጣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደሆነ አስረዳው።
ያን ጊዜም በቅዱስ ጴጥሮስ ቃል አመነ የምድራዊ ንጉሥ አገልግሎትንም ትቶ ወደ ቀጰዶቅያ ሔደ በውስጧም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንደ ሐዋርያት ሰበከ።
አይሁድም በጠላትነት ተነሡበት በመሳፍንትም ዘንድ ከሰሱት በላዩም የሐሰት ምስክር አስነሡበት ስለዚህም ራሱን በሰይፍ አስቆረጡት የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ
No comments:
Post a Comment