ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 24 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, August 12, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 24

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሐምሌ ሃያ አራት በዚች ቀን ከንሒሳ ከተማ ቅዱስ አባ ኖብ ሰማዕት ሆኖ ሞተ፣ ጣና ክብራን ገብርኤል ገዳምን የመሠረቱት አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዕረፍታቸው ነው፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አባ ኖብ
ሐምሌ ሃያ አራት በዚች ቀን ከደቡባዊ ግብጽ ከታችኛው ምድር አውራጃ ከንሒሳ ከተማ ቅዱስ አባ ኖብ ሰማዕት ሆኖ ሞተ።
የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ቅዱሳን ንጹሐንና የሚራሩ ነበሩ። ይህንንም ቅዱስ ኖብን በወለዱት ጊዜ ዐሥራ ሁለት ዓመት እስኪሆነው ፈሪሀ እግዚአብሔርን እያስተማሩ አሳደጉት። ቤተ ክርስቲያንን የመጻሕፍትን ቃል መስማትንና መማርን የሚወድ ሆነ።
ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የክርስቲያን ወገኖችን ዲዮቅልጥያኖስ በአሠቃያቸው ጊዜ ይህ ቅዱስ ደሙን ስለ ጌታችን ሊአፈስ አሰበ ያን ጊዜም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ ቄሱንም ምእመናንን እንዲህ እያለ ሲያስተምራቸውና ሲያበረታቸው ‘’ጣዖታትን ከምታመልኩ ክብር ይግባውና ስለ መድኃኒታችን ስለ ክርስቶስ ነፍሳችሁን ለሞት አሳልፋችሁ ብትሰጡ ለእናንተ መልካም ነው’’ ሲላቸው ሰማው።
ይህም ቅዱስ እያዘነና እየተከዘ ወደ ቤቱ ተመለሰ አባቱም የተወለትን ወርቁንና ብሩን ልብሶችን ሁሉ ተመልክቶ እንዲህ አለ ሁሉ ነገር የዚህ ዓለም ፍላጎቱም ሁሉ እንደ ሚያልፍ እነሆ ተጽፏል። ከዚህም በኋላ ገንዘቡን ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠ።
ከዚህም በኋላ ወደ ሀገረ ገምኑዲ ሔደ በእግሩም ሲጓዝ በባሕሩ ዳርቻ ሉስዮስ የሚባለውን መኰንን አገኘው በፊቱም ቁሞ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ። መኰንኑም ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት በእርሱ ላይም የሚደርሰውን ሁሉ ነግሮት አጽናናው።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ ሰሜን አገር ሲጓዝ የከበረ ኖብን ከእርሱ ጋራ በመርከብ ወሰደው በመርከቡም ምሰሶ ላይ ዘቅዝቆ ሰቀለው መኰንኑም ሊበላና ሊጠጣ ተቀመጠ በመኰንኑም እጅ የነበረው ጽዋ ወዲያውኑ እንደ ደንጊያ ሆነ የወታደሮቹም ዐይኖቻቸው ታወሩ የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ወርዶ አባ ኖብን ፈትቶ ከተሰቀለበት አወረደው በአፍንጫውና በአፉ የወረደውንም ደሙን አሻሸለት።
ከዚህ በኋላም መልካም ነፋስ ነፍሶ መርከቢቱ ተጓዘች። ወደ አትሪብ ከተማም ደረሱ ወታደሮችም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው ትጥቃቸውን ፈተው በመኰንኑ ፊት ጣሉ። ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመኑ ሰማዕታትም ሆነው ራሳቸውን ቆረጡአቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።
መኰንኑም በአትሪብ ከተማ ቅዱስ አባ ኖብን ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው በብረት ዐልጋ ላይም አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ በጸለየ ጊዜም እግዚአብሔር ከእሳት አዳነው። ከዚህም በኋላ በመጋዝ መገዙት ሕዋሳቱንም ቆራረጡ የእግዚአብሔር መልአክም ወርዶ አዳነው ያለ ጉዳትም በጤና አስነሣው።
ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ከተማ ወሰዱት በዚያም ብዙ አሠቃዩት በላዩም እባቦችን ሰደዱ ግን አልቀረቡትም ከእባቦችም አንዱ ሒዶ በመኰንኑ አንገት ተጠመጠመ ያስጥሉትም ዘንድ ሟርተኞቹን አዘዛቸው ግን አልተቻላቸውም ከዚህም በኋላ ያድነው ዘንድ ቅዱስ አባ ኖብን ለመነው ቅዱሱም ከይሲውን ትቶት ከአንገቱ እንዲወርድ አዘዘው።
መኰንኑም ሁለተኛ በእሳት እንዲአቃጥሉት ሟርተኞችንና ሥራየኞችን አዘዛቸው እሳቱም ምንም አልነካውም። አቅፋሐስ ከሚባል አገርም ዮልዮስ መጣ ከእርሱም እንደ ተረዳ ገድሉን ጻፈ። መኰንኑም ማሠቃየቱን በሰለቸ ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ።
ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተገልጾለት አጽናናው እንዲህ ብሎም ቃል ኪዳን ሰጠው ሥጋህ በሚኖርበት ቦታ ከእርሱ ታላቅ ፈውስ ይሆናል እንዲሁም በመከራው ጊዜ ስምህን በመጥራት ከእግዚአብሔር ርዳታ ለሚሻ ሁሉ ድኅነት ይደረግለታል። መታሰቢያህንም ለሚያደርግ ሁሉ የተራበ ለሚያጠግብ፣ የተጠማም ለሚያጠጣ፣ ለቤተ ክርስቲያንም በስምህ መባ ለሚሰጠው፣ የገድልህንም መጽሐፍ ለሚጽፍ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ መንግሥተ ሰማያትንም አወርሰዋለሁ።
ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡ ተጋድሎውንም ፈጸመ ሥጋውንም ቅዱስ ዮልዮሰ አንሥቶ ከሁለት አገልጋዮቹ ጋራ ንሒሳ ወደ ሚባል አገሩ ላከው። የመከራውም ወራት በተፈጸመ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናትን ሠሩለት በውስጣቸውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ (ኢትዮዽያዊ)
ዳግመኛም በዚህች ቀን ጣና ክብራን ገብርኤል ገዳምን የመሠረቱት አቡነ ዘዮሐንስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ይኸውም አባቱ ዘካርያስና እናቱ ሶፍያ እግዚአብሔርን በማመን የተመሰገኑ ምግባር ሃይማኖታቸው የቀና ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የሀገር ሰዎችም መክረው ዘካርያስን በእነርሱ ላይ ጌታና ገዥ አደረጉት፡፡ እርሱም በጥሩ አገዛዝ በፍቅር ገዛቸው፡፡ እነርሱም እንደ አሽከሮች ሆኑት፣ እርሱም እስከ አማራ ጠረፍ ድረስ ለሸዋ ሰዎች እንደ ቸር እረኛ ሆናቸው፡፡ ዘካርያስና ሚስቱ ሶፍያም በጎ ሥራን ሁሉ አላቋጡም፡፡ ምጽዋትን መስጠትን፣ ከገንዘባቸውም ከፍለው ለእግዚአብሔር አሥራት መስጠትን አላቋረጡም፡፡ የተቸገሩትን፣ የተራቡትንና የተጠሙትን ሁሉ ያበላሉ፣ ያጠጣሉ፡፡ ይህንንም ሲሄዱም ሲመለሱም ሁልጊዜ ያደርጋሉ፡፡
የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስንና የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የጻድቃንና የሰማዕታን መታሰቢያም ያድርጋሉ፡፡ ልጅም አልነበራቸውምና ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ይማፀኑ ነበር፡፡ ሶፍያም ጠዋት ማታ እንዲህ እያለች ትጸልይ ነበር፡- ‹መካን ለነበረች ለሐና ልጅ እንደሰጠኻት፣ ለአብርሃም ሚስት ለሣራም፣ ለጸጋ ዘአብ ሚስት እግዚእ ኀረያም እንደሰጠኻቸው አቤቱ እንደ እነርሱ አንተን ደስ የሚያሰኝህን ልጅ ስጠኝ› እያለች እመቤታችንንም እየተማፀነች ታለቅስ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም መጥምቁ ዮሐንስን የመሰለ ልጅ ‹አባ ዘዮሐንስ› የተባለ ቅዱስ ልጅ ሰጣቸው፡፡ እሱም በሸዋ፣ በመራቤቴ እስከ አማራ ጠረፍ ድረስ የሚያበራ መብራት ሆነ፡፡››
በኋላም በጣና ሐይቅ ላይ የሚገኘውን ‹‹ክብራን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን›› የመሠረቱት እኚህ አባ ዘዮሐንስ የተባሉ ጻዲቅ ናቸው፡፡
ቀጥሎ ደግሞ ታሪካቸውንና የተሰጣቸውን አስደናቂ ቃልኪዳን እንመለከት፡- ለአባ ዘዮሐንስ በጌታ ዘንድ ታዘው ነቢዩ ኤልያስና ዮሐንስ በእኩለ ሌሊት ተገልጠውላቸው አስኬማና ቆብ ሰጥተዋቸዋል፡፡ እመቤታችንም ተገልጣላቸው ወደ ደብረሊ ሊባኖስ ሄደው እንዲመነኩሱ ነግራቸው ኤልያስና ዮሐንስ እየመሩ ከቦታው አድርሰዋቸዋል፡፡ ሰባት ዓመትም በዚያ ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡ ስግታቸውም ሁልጊዜ ስምንት ሺህ ነበር፡፡ ጌታም በደብሊባኖስ ሲያጥኑ ተገልጦላቸው ስምህ ‹‹ዘዮሐንስ ይሁን›› ብሎ ትልቅ ቃልኪዳን ተጥቷቸዋል፡፡ ደመናም ተሸክማ ወስዳ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም አድርሳቸው በዚያም ከቆዩ በኋላ ደመናዋ መልሳ ወደ ሸዋ አምጥታቸዋለች፡፡ በትግራይ ለራሳቸው መጠለያ ሲሠሩ የጌታ ፈቃድ አልነበረምና ከባድ የሆድ ሕመም መጣባቸው፡፡ ደመናዋም ደራ ሮቢት አደረሰቻቸው፡፡ በዚያም እንደደረሱ ገብርኤልና መስቀል ክብራ በሚባሉ እግዚአብሔርን በሚወዱ ደጋግ ባለትዳሮች ቤት ዕረፍት አደረጉ፤ ለሰባት ቀናትም በዚያ ቆዩ፡፡ ከዚያም መልአኩ ተገልጦ ወደ ደሴቷ እንዲሄዱና እርሷም ዕጣ ክፍላቸው እንደሆነች ነገራቸው፡፡
አባ ዘዮሐንስም በደሴቷ ላይ በጾም በጸሎት ጸንተው ተቀመጡ፣ ትሎችም ሰውነታቸውን እንዲመገቡ ያድርጉ ነበር፡፡ ገብርኤልና መስቀል ክብራ የተባሉትም ደጋግ ባለትዳሮች የሚያስፈልጋቸውን ይወሰዱላቸው ነበርና ባገኙዋቸው ጊዜ ትሎቹን ከሰውነታቸው ላይ ሲያራግፉላቸው ‹‹ተዋቸው እኔን ሊመገቡ ተፈቅዶላቸዋል›› አሏቸው፡፡ አባታችን አንድ ቀን የሰው ድምፅ ሰምተው ወደ ውጭ ወጥተው ሲመለከቱ የአካባቢው ሰዎች አንድ ማድጋ ወተት፣ አንድ በግና አንድ ከብት ለዘንዶ ሲገብሩ አይተው ያንን ዘንዶ በሥላሴ ስም በመስቀል ምልክት አማትበው ከሰዎቹ ፊት ገደሉት፡፡ ይህን የሰማውና ሰዎቹን እንዲገብሩ የላካቸው ጃን ቹሐይ የተባለው ጣኦት አምላኪ የአገሩ ሹም ‹‹የማመልከውን ዘንዶ እንዴት ትገድላለህ?›› በማለት እንዲታሰሩ አደረጋቸው፡፡ ንጉሥ ዐምደ ፅዮንም ይህን ሲሰማ ሠራዊቱን ልኮ ያንን ጣኦት አምላኪ የአገሩን ሹም ገድለው አባ ዘዮሐንስ እንዲፈቷቸው አደረገ፡፡
አባ ዘዮሐንስም ወንጌልን እያስተማሩ፣ ሙትን እያስነሱና ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ በደሴቷ ላይ ተወስነው ተቀመጡ፡፡ በደመናም ተጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ታቦተ ቅዱስ ገብርኤልን አምጥተው በደሴቷ ላይ ክብራን ገብርኤል ገዳምን መሠረቱ፡፡ ደመናም ደሴቷ ላይ ስታደርሳቸው ኤልያስና ዮሐንስ በቀኝ በግራው እየተራዱአቸው እርሳቸው ሠራዒ ቄስ ሆነው ቀደሱ፡፡ ደሴቷንም መጀመሪያ እንደመጡ ባሳረፈቻቸው ገደኛ ሴት ስም ሰየሟት፡፡ ለሴቶች መነኮሳት ከዚያው አጠገብ የሚገኘውን እንጦንስ ገዳምን አድርገው ክብራን ገብርኤልን ለወንዶች ብቻ አደረጓት፡፡
አንድ ቀን አባ ዘዮሐንስ በደብረ ሊባኖስ መሥዋዕት ለማቅረብ እያጠነ ሳለ ለስም አጠራሩ ክብርና ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሌላ ሀገር የመጣ እንግዳ ሰው መስሎ ታየውና ‹ሰላም ለአንተ ይሁን› አለው፡፡ አባታችን ዘዮሐንስም ‹ወንድሜ ሆይ! የእግዚአብሔር ፍቅር አንድነት ከአንተ ጋር ይሁን› አለው፡፡ ‹አንተ እንግዳ ሰው ከየት ሀገር የመጣህ ነህ? ከዚህ በፊት አላውቅህም› አለው፡፡ ጌታችንም ከልቡናው ፍግግ አለና ‹ከእናትህ ማኅፀን ሳትወጣ እኔ አውቅሃለሁ› አለው፡፡ ይህንንም ብሎ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ ያደረገለትን ከመወለዱም አስቀድሞ የሆነውን ሁሉ፣ ከተወለደም በኋላ እስከዚያ ቀን ድረስ ያደረገለትን፣ አባቱንም በአመፀኛው በጎዶልያ እጅ ከመሞት እንዳዳነው፣ እናቱንም ዕቁባቱ ሊያደርጋት እንደነበረ ምሥጢሩንም ሁሉ ነገረው፡፡ ይህንንም ብሎ ዳግመኛ ተነጋገረው፡- ‹ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ዘዮሐንስ ይሁን፣ አንተ የዓለሙ ሁሉ ደስታ ነህና የሚያለቅሱም በአንተ ደስ ይላቸዋል› አለው፡፡›› ‹‹በደመናም ተጭነው ኢየሩሳሌም ደርሰው ታቦተ ቅዱስ ገብርኤልን አምጥተው ክብራን ገብርኤል አስገብተው በዚያም ሲኖሩ በጣም አርጅተው ነበርና ራሳቸውን ወደ ምድር አጎንብሰው ይሄዱ ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ሐምሌ 10 ቀን ለዓርብ አጥቢያ ሲጸልዩና በግንባራቸው ወደ ምድር ሲሰግዱ ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክረስቶስ ሚካኤልንና ገብርኤልን አስከትሎ መጥቶ ‹ወዳጄ አባ ዘዮሐንስ ሆይ! ከድካም ወደ ዕረፍት፣ ከበሽታ ወደ ሕይወት፣ ከዚህ ዓለም ዐይን ወዳላየውና ጆሮ ወዳልሰማው ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት አሳርፍህ ዘንድ ወደ አንተ መጣሁ› አለው፡፡ ይህንንም ብሎ ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ከእርሱ በረከት እንደማይጠፋ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ ‹ገድልህን የሚጽፍ ወይም የሚያነብ እኔን እንደመሰለ እንደ መልከጼዴቅ ካህን በእኔ ዘንድ የተመረጠና የተወደደ ይሆናል፣ በበዓልህ ማኅሌት የቆመ የመላእክት ባልንጀራ ይሆናል፣ እነዚህን ልጆችህንም የመላእክት አምሳያ አደርጋቸዋለሁ› አለው፡፡ ‹ይህችን ደሴት እንደ ኢየሩሳሌም ሀገሬ፣ እንደ ደብረ ዘይትና ለባሪያዬ ለሙሴ ሕግን እንደ ሰጠሁባት እንደ ደብረ ሲና አድርጌያታለሁ፣ በረከቴም ከእርሷ አይታጣም፣ እኔም ከእርሷ አልለይም ይልቁንም በተጠመቅሁባት ቀን ከዚህች ገዳምህ አልለይም፣ የዚህች ደሴትና የሀገሬ የኢየሩሳሌም መክፈቻ በአንድ ላይ አንድ ይሁን› አለው፡፡ ‹ከዚህች ሀገርም ያለንስሓ የሕፃናትና የጎልማሶች ሞት አይሁን፣ እስከ ዘለዓለምም ድረስ ጸሎት ከእርሷ አይቋረጥ› አለው፡፡
ጌታችንም ለአባ ዘዮሐንስ ይህን ከተናገረው በኋላ ቡራኬ ሰጥቶት ከቅዱሳን መላእክት ጋር ወደቀደመ ቦታው ዐረገ፡፡›› ጻድቁ በ105 ዓመታቸው ሐምሌ 24 ቀን በክብር ዐርፈዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አባ ስምዖን
በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ሁለተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን አረፈ። ይህም ቅዱስ ከምሥራቅ አገር ሰዎች ወገን ነው። ወላጆቹም ከእስክንድርያ በስተምዕራብ ወዳለች በውስጧም የቅዱስ ሳዊሮስ ሥጋ ወደ አለባት ገዳም አመጠትና በዚያ መንኵሶ ጽሕፈትን ተማረ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት ሁሉ አጠና ቅስናም ተሾመ።
ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳት ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር መረጠው። በተሾመ ጊዜም መንፈሳዊ መምህሩ የሊቀ ጵጵስናውን ሥራ አስተማረው በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ። እንጀራና ጨውም አይበላም ነበር ነገር ግን በእሳት ያላበሰሉትን ጎመን ከተልባ ጋራ ይበላ ነበር። እንዲህም አድርጎ ደማዊት ነፍሱን ለነባቢት ነፍሱ አስገዛ።
እግዚአብሔርም ታላላቅ የሆኑ ብዙዎች ድንቆችንና ተአምራትን በእጆቹ ላይ አደረገ ከእነዚህም ከእስክንድርያ ካህናት ክፉዎች ሰዎች ቀኑበት ወደመተተኞችም ሒደው ብዙ ገንዘብ ሰጧቸው የሚገድል መርዝንም አዘጋጁለት እሊህ ክፉዎችም ያን መርዝ ወስደው ከሚጠጣው መጠጥ ጋራ በብርሌው ውስጥ ደባለቁት ጠጥቶም ይባርካቸው ዘንድ እንዲጠጣ እየለመኑት ለሊቀ ጳጳሳቱ ሰጡት እርሱም ቅዱስ ቍርባንን ከተቀበለ በኋላ ያንን መርዝ ጠጣው ከክፉም ነገር ምንም ምን አልደረሰበትም ሁለተኛም ሦስተኛም ሰጥተውት ምንም ምን አልጎዳውም ከመዳኑም የተነሣ አደነቁ።
ከዚህም በኋላ ወደ ገበያ ሒደው ሁለት አዳዲስ በለስን ገዙ በውስጡም የሚገድል መርዝን አደረጉ ቅዱስ ቍርባንን ከመቀበሉ በፊት በጾም ሳለ ይሰጡት ዘንድ ተስማሙ መሠርያኖች ይህን በለስ ከቍርባን በፊት ቢበላ ሆዱ ይሠነጠቃል ብለዋቸው ነበርና።
ያን ጊዜም ወደርሱ በተንኮል ሒደው ከዚያ በለስ ይበላ ዘንድ ሊቀ ጳጳሳቱን ለመኑት አብዝተውም አስገደዱት ከቅዱስ ቍርባን በፊት ሳይፈቅድ በእጁ ውስጥ አደረጉለትና በላ ነገር ግን መሠርያኖች እንዳሉአቸው አልሆነም ሆዱም አልተሠነጠቀም ነገር ግን አርባ ቀን ታመመ።
ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸለትና የደዌውን ምክንያት አስረዳው ያንን መርዝ ያደረጉበትንም ስማቸውን ገለጠለት።
በዚያ ወራትም የግብጽ ንጉሥ አብዶ አልዓዚዝ ወደ እስክንድርያ ከተማ መጣ ይህ አባት ሊቀ ጳጳሳት ስምዖንም ሊቀበለው ወጣ ንጉሡም በሊቀ ጳጳሳቱ ፊት ላይ የደዌ ምልክት አይቶ መሳፍንቶቹን መልኩ እንዲህ እስኪለወጥ ድረስ ሊቀ ጳጳሳቱ ምን ደረሰበት ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ክፉዎች ካህናት በእርሱ ላይ እንዳደረጉበት መርዝንም እንዳበሉት ነገሩት ንጉሡም ተቆጣ ካህናቱንና መሠርያኑንም በእሳት እንዲአቃጥሏቸው አዘዘ ያን ጊዜም ይህ አባት ከንጉሡ እግር በታች ወድቆ ይምራቸው ዘንድ እያለቀሰ ለመነው ንጉሡም አይደለም እንደሚገባቸው ያቃጥሏቸው እንጂ አለው። ይህም አባት ስለእኔ አንተ ከአቃጠልካቸው ለእኔ ክህነትና ሊቀ ጵጵስና አይገባኝም አለው። ንጉሡም ሰምቶ ከየዋህነቱና ከርኅራኄው የተነሣ አደነቀ እነዚያን ካህናትና መሠርዮች ከእስክንድርያ እንዲያሳድዷቸው አዘዘ።
ንጉሡም ይህን አባት እጅግ ወደደው አከበረውም እንደወደደም አብያተ ክርስቲያናትን ገዳማትን ይሠራ ዘንድ ፈቀደለት። እርሱም በምስር ሰሜን አልዋህ በሚባል አገር አብያተ ክርስቲያን ሠራ በሹመቱም ዘመን ሌሎች ብዙዎችን ሠራ።
ካደረጋቸው ተአምራቶቹ ሌላው ይህ ነው ሚናስ የሚባል አንድ ቄስ ነበረ ሙቶ ከተገነዘ በኋላ በዚህ አባት ጸሎት ተነሣ። የመነሣቱ ምክንያትም እንዲህ ነበር ይህ አባት ስምዖን በመላው አብያተ ክርስቲያናት ንብረት ንዋየ ቅድሳትና አልባሳት ላይ መጋቢ አድርጎ ይጠብቅ ዘንድ ቄሱን ሾመው። ሁልጊዜም የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በቤትህ ውስጥ አታኑር እያለ ያዝዘው ነበር።
ከዚህም በኋላ ድንገተኛ ደዌ አገኘውና አንደበቱና ጒረሮው ተጣጋ። ሊቀ ጳጳሳቱም ሰምቶ እጅግ አዘነ ስለ አቢያተ ክርስቲያናትም ንብረት ያንን ቄስ ከሞት ያድነው ዘንድ በዚያች ሌሊት እግዚአብሔርን እየለመነ መላዋን ሌሊት ለጸሎት ተጋ።
መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ያ ቄስ ለመሞት እንደተቃረበ ይህ አባት ሰምዖን ሰማ ስለ አቢያተ ክርስቲያናት ነብረት ይጠይቃት ዘንድ አዝዞ ወደ ቄሱ ሚስት ረዳቱን ላከ።
ወደ ቄሱ ቤትም በቀረበ ጊዜ ሰዎች እያለቀሱለት ጩኸታቸውን ሰማ በገባ ጊዜም ሙቶ ልብሰ ተክህኖ መጐናጸፊያ ሲያለብሱት በዐልጋ ላይም ሲያስተኙት ብዙዎችም በዙሪያው ሲያለቅሱ አገኛቸው ያም ረዳቱ የቄሱን በድን ሊሳለም ዘንበል አለ። ያን ጊዜም ያ የሞተው ቄስ ተነሥቶ አቀፈውና የክቡር አባ ስምዖን ፈጣሪ እግዚአብሔር ሕያው ነው አለው። ረዳቱም በርታ አትፍራ አለው። ቄሱም በጌታው በአባ ስምዖን ጸሎት አዎ በእውነት ጸናሁ እግዚአብሔር ሕይወትን ሰጥቶ ከሞት አስነሥቶኛልና አለ።
ያን ጊዜም ያ ረዳት ስለ መሞቱ ደንግጠው የነበሩትን ካህናት እነሆ ቄሱ ከሞት ተነሥቷል ብሎ ጠራቸው። ካህናቱና ሕዝቡም ወደርሱ በቀረቡ ጊዜ ቄሱ እንዲህ አላቸው እኔ ሙቼ እንደነበረ ዕወቁ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ዙፋን ፊት አቆሙኝ ከአባት ሐዋርያ ማርቆስ እስከ አባ ይስሐቅ ያሉትን ሁሉንም የጳጳሳት አለቆች ክብር ይግባውና በክርስቶስ ዙፋን ፊት ቁመው አየኋቸው እኔንም ከወንድማችን ከሊቀ ጳጳሳት ስምዖን የአብያተ ክርስቲያናትን ንብረት ለምን ሸሸግህ ብለው ገሠጹኝ። ያን ጊዜም ጌታ ክርስቶስ ይቺን ነፍስ በውጭ ወዳለ ጨለማ ውሰዱአት ብሎ አዘዘ።
ሊወስዱኝም በጐተቱኝ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ዙፋን ፊት የጳጳሳት አለቆች ሰገዱ እንዲህ እያሉም ማለዱ ይህን ሰው አንድ ጊዜ ማረው ንብረታቸውን ስለሚጠብቅላቸው አብያተ ክርስቲያናት ብሎ ወንድማችን ስምዖን ስለ እርሱ እነሆ ቁሞ ይጸልያልና። ጌታችንም ልመናቸውን ተቀብሎ ነፍሴን ወደ ሥጋዬ መለሰ እንዲህም አለኝ እነሆ ስለ ምርጦቼና ስለ ወንድማቸው ስለ ሊቀ ጳጳሳት ስምዖን ማርኩህ አንተም የአብያተ ክርስቲያናትንም ንብረት ግለጥለት። አለዚያ ግን ወደዚህ እመልስሃለሁ የእነዚህንም ልመናቸውን ስለአንተ ሁለተኛ አልቀበልም።
በዚያ የነበሩም ሰዎች ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ኀዘናቸውም ወደ ደስታ ተለወጠ ይህም ቄስ ይህን ተአምር ለሁሉ እየተናገረ ብዙ ዘመናት ኖረ።
ይህም አባት ስምዖን በበዐቱ ውስጥ በገድል የተጸመደ ሁኖ ኖረ መንጋዎቹንም ያስተምራቸው፣ ይገሥጻቸውና በቀናች ሃይማኖትም ያጸናቸው ነበር። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በርከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages