ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 25 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, August 12, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 25

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሐምሌ ሃያ አምስት በዚች ቀን ቅዱስ መርቆሬዎስ ቅዳሴ ቤቱ እና ልደቱ ነው፣ የደብረ ሊባኖሱ አባ ሕጻን ሞዐ አረፈ፣ ቅድስት ቴክላ አረፈች፣ ቅዱስ አንዲኒና በሰማዕትነት አረፈ፣ አባ ይስሐቅ በሰማዕትነት ሞተ፣ቅድስት ኢላርያ ሰማዕት ሆነችች፣ ቅዱሳት ቴላና ሙጊ ሰማዕታት ሆኑ፣ ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት ሆነ፣ቅዱስ ዲማድዮስ አረፈ፣ ነቢዩ ቅዱስ ሄኖክ የዕርገቱ መታሰቢያ ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ መርቆሬዎስ
ሐምሌ ሃያ አምስት በዚች ቀን ቁጥር የሌላቸው ተአምራትንና ድንቆችን ባሳየባት በምስር አገር የቅዱስ መርቆሬዎስ ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ ሆነ። ልደቱም በዚሁ ዕለት ነው፡፡
ታላቁ ሰማዕት የቅዱስ መርቆሬዎስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ‹‹መርቆሬዎስ›› ማለት የአብ ወዳጅ ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ወላጆቹ አስሊጥ ከምትባል ሀገር ቢሆኑም እርሱ ግን ተወልዶ ያደገው በሮሜ ከተማ ነው፡፡ አያቱና አባቱ ሥራቸው አውሬ ማደን ስለነበር አንድ ቀን እንደልማዳቸው አውሬ ሲያድኑ ከገጸ ከለባት ወገን የሆኑ ሁለት ወንዶች አግኝተዋቸው የመርቆሬዎስን አያት በሉት፡፡ አባቱንም ሊበሉት ሲሉ የታዘዘ መልአክ ከለከላቸው፡፡ ዙሪያቸውንም በእሳት አጥሮ ከበባቸው፡፡ እነርሱም በተቸገሩ ጊዜ ለመርቆሬዎስ አባት ሰገዱለት፡፡ በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር ፍጥረታቸውን ወደገራምነት ለወጠውና እንደበጎች የዋሆች ሆነው አብረውት ወደ መንደር ገቡ፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ ተወለደና ስሙ ፒሉፓዴር ተባለ፡፡ የውሻ መልክ ያላቸውም በእርሱ ዘንድ ብዙ ዘመናት ኖሩ፡፡ ከዚህም በኋላ ክርስቲያኖች ሆኑ፡፡ የቅዱስ መርቆሬዎስም ወላጆች አስቀድመው አረማውያን ነበሩና የክርስትና ጥምቀትን በጸጋ ተቀበሉ፡፡ አባቱን ኖህ እናቱንም ታቦት ብለው ሰየሟቸው፡፡ ቀድሞ ፒሉፓዴር የነበረውም ስሙ ተለውጦ መርቆሬዎስ ተባለ፡፡ የውሻ መልክ ያላቸው ግን መልአኩ በተገለጠላቸው ጊዜ እንደነገራቸው ለቅዱስ መርቆሬዎስ አባት የሚታዘዙና የሚያገለግሉ ሆኑ፡፡ ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባትና የውሻ መልክ ያላቸውን ዜናቸውን ሲሰማ ወታደሮቹን ልኮ በፊቱ አቆማቸው፡፡ እግዚአብሔርም የቀድሞ ፍጥረታቸውን መልሶላቸው አራዊት አደረጋቸውና ንጉሡን እጅግ አስፈሩት፡፡ ንጉሡም የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት የአራዊት ተፈጥሮአቸውን ያርቅለት ዘንድ ለመነው፡፡ የቅዱስ መርቆሬዎስም አባት በለመነ ጊዜ ተፈጥሮአቸውን መልሶላቸው ገራሞች ሆኑ፡፡
ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባት ገዥና የሠራዊቱ አለቃ አድርጎ ሾመው፡፡ የውሻ ፊት ያላቸውም አብረው ያገለግሉት ስለነበር ሁሉም ይፈራው ነበር፡፡ ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባት ወደ ጦርነት ከላከው በኋላ ሳይመለስ ስለቀረ ሚስቱን ሊያገባት አሰበ፡፡ የመርቆሬዎስ አባትም የመርዶሳውያን አገሮች ሁሉ ገዢ በነበረው ንጉሥ ተይዞ ቢማረክም ገዥው ክርስቲያን መሆኑን አይቶ አከበረው፡፡ ቆይቶም በሀገሩ ላይ ሾመው፡፡ ሚስቱም ጠፍታ ከሀገሯ ወጥታ ሄዳ ስለነበር ከባሏ ተገናኝተው በዚያው መኖር ጀመሩ፡፡ መርቆሬዎስም አባቱና እናቱ ከሞቱ በኋላ ንጉሡ በአባቱ ፈንታ በመርዶሳውያን አገር ላይ ሾመው፡፡
መርቆሬዎስ መኰንንነት በተሾመም ጊዜ ገጸ ከለባቱ አብሮት ነበር፡፡ ለመዋጋትም በወጣ ጊዜ የቀድሞው የአራዊት የሆነ ተፈጥሮውን እግዚአብሔር ይመልስለት ስለነበር ማንም አይቋቋመውም ነበር፡፡ ለቅዱስ መርቆሬዎስ ታላቅ የድል አድራጊነት ኃይል ተሰጠውና ዜናው በሁሉም ሀገሮች ተሰማ፡፡ በሮሜ ሀገር ጣዖትን የሚያመልከው ዳኬዎስ የተባለውም ንጉሥ የበርበር ሰዎች ጋር ጦርነት ሊገጥም በወጣ ጊዜ እጅግ ሲበዙበት ፈራ፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስም በጦሩ መሀል የተሳለ ሰይፍ የያዘ የእግዚአብሔርን መልአክ ስላየ ንጉሡን እግዚአብሔር ያጠፋቸዋልና አትፍራ›› አለው፡፡ መልአኩም ሰይፉን ለቅዱስ መርቆሬዎስ ሰጠውና ‹‹ጦርነቱን ድል ባደረግህ ጊዜ እግዚአብሔርን አስበው›› አለው፡፡
ጦርነቱን ድል አድርጎ ሲጨርስም መልአኩ ድጋሚ ተገልጦለት ‹‹ለምን የፈጣሪህን ስም መጥራት እረሳህ?›› አለው፡፡ ከጦርነቱም በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረግ በዓልን አደረገ፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስም በዚያ ስላልተገኘ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረጉ እንዳልተባበረ ንጉሡ ሲያውቅ መልእክተኞችን ልኮ አስመጣው፡፡ ንጉሡም ‹‹ከእኔ ጋር ለምን አታጥንም?›› ባለው ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ ትጥቁንና ልብሱን አውልቆ ከወረወረለት በኋላ ‹‹ክብር ይግባውና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጽሞ አልክደውም፣ ለረከሱ ጣዖቶችህም አልሰግድም›› አለው፡፡ ንጉሡም ተናዶ ልዩ ልዩ በሆኑ ሥቃዮችም እጅግ አሠቃየው፡፡
ንጉሡም ስለ መርቆሬዎስ ብለው የአገሩ ሰዎች እንዳይነሱበት ፈርቶ በብረት ችንካር ቸንክሮ የቀጵዶቅያና የእስያ ክፍል ወደሆነች ወደ ቂሳርያ ከደብዳቤ ጋር ላከው፡፡ በዚያም እጅግ ካሠቃዩት በኋላ ንጉሡ ዳኬዎስ እንዳዘዘ ኅዳር 25 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነት ተጋድሎውን ፈጸመ፡፡ የሕይወትንም አክሊል ተቀዳጀ፡፡ በዓለሙ ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ታነጹለት፡፡ እግዚአብሔርም ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን በቅዱስ መርቆሬዎስ ስም አደረገ፡፡
ከብዙ ተአምራቱም አንዱ የቂሳርያውን ሊቀ ጳጳስ ባስልዮስን እረድቶ ከሃዲውን ዑልያኖስን የገደለበት ነው፡፡ ዑልያኖስ ነግሦ የክብር ባለቤት ጌታችንን ክዶ ጣዖታትን ማምለክና ክርስቲያኖችን ማሠቃየት ጀመረ፡፡ የቂሳርያው ሊቀ ጳጳስ ባስልዮስም አስተምሮ ሊመልሰው ወደ ንጉሡ ቢመጣ ክብር ይግባውና ዑልያኖስ ጌታችንን ሰድቦ ባስልዮስንም አሰረው፡፡ ባስልዮስም በእሥር ቤት ሳለ በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ፊት ጸለየ፡፡ ሥዕሉም ወዲያው ተሰወረው፡፡ ያንጊዜም ወደ ከሃዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ዘንድ ሄዶ በጦር ወግቶ ገደለውና ወዲያው ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡
ከጦሩም አንገት ደም ይንጠፋጠፍ ነበር፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ከሃዲውን ንጉሥ እንደገደለው ዐውቆ ‹‹የክርስቶስ ምስክር ጌታዬ ሆይ የእውነት ፀር የሆነ ዑልያኖስን ገደልከውን?›› አለው፡፡ ሥዕሉም ያን ጊዜ አዎን እንደሚል ራሱን ዘንበል አደረገ፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ደስ ብሎት እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡
ሌላው ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በተአምሩ ከእስልምና እምነት መልሶ ክርስቲያን ያደረገው አንድ እስላም ሰው አለ፡፡ ይኸውም የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያኑ በተሠራችበት በምስር አገር የሚኖር ከመሳፍንት ወገን የሆነ ወጣት ነበረ፡፡ ከብዙ ሰዎችም ጋር ሆኖ ወደ መሐመድ መቃብር ለመሄድ እንዳሰበ ለአባቱ ሲነግረው ስንቅ ሰንቀው በሰላም ወደ መካ መዲና ሸኙት፡፡
መካ ደርሰውም ሥራቸውም ፈጽመው ወደቤታቸው እየተመለሱ ሰባት ቀን ተጓዙ፡፡ በሌሊትም ሲጓዙ ስለ ሥጋዊ ግዳጁ ያ እስላም ወጣት ከግመል ላይ ወርዶ ለመጸዳዳት ዘወር አለ፡፡ እነርሱም አብሯቸው የሚጓ መስላቸው ስለነበር ባልንጀሮቹም በበረሃው ውስጥ ትተውት ሄዱ፡፡ እርሱም ወዴት እንደሚሄድ ስላላወቀ አራዊትም እንዳይበሉት ፈርቶ እጅግ ደነገጠ፡፡ በዚያም ጊዜ በምስር አገር በአባቱ ቤት አቅራቢያ ያለች የሰማዕቱ የቅዱስ መርቆሬዎስን ቤተ ክርስቲያን አስታውሶ በልቡ ቅዱስ መርቆሬዎስን እንዲያድነው በመለመን ተሳለ፡፡ ወዲያውም ቅዱስ መርቆሬዎስ በፈረሱ ተቀምጦ ወደ እርሱ መጣና ‹‹ከወዴት ነህ? ከዚህ በረሃ ውስጥስ እንዴት ጠፋህ?›› አለው፡፡ ወጣቱ እስላምም የሆነውን ነገረው፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስም ‹‹ና በኋላዬ በፈረሱ ላይ ተፈናጠጥ›› አለውና በአየር ላይ እየበረረ በምስር አገር ወዳለች የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ዐይን ጥቅሻ አደረሰውና እንደተዘጋች በውስጧ አስገባውና ከእርሱ ተሰወረ፡፡ ይህም ወጣት በኋላ አምኖ ተጠምቆ ብዙ ሰማዕትነት ተቀብሏል፡፡ ገዳምም ገብቶ ብዙ ከተጋደለ በኋላ እንደገና ወደ አገሩ ተመልሶ ብዙዎችን ወደ ክርስትና አምጥቷል፡፡ በቅዱስ መርቆሬዎስ ስም ቤተ ክርስቲያን አሠርቶ አበ ምኔትም ሆኖ ብዙ መነኮሳትን አፍርቷል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ሕጻን ሞዐ
በዚህችም ቀን የደብረ ሊባኖሱ አባ ሕፃን ሞዐ አረፈ። በአባታቸው አርከሌድስ እናታቸው ትቤ ጽዮን ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ጥር 25 ነው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ እና ከእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የሥጋ ዝምድና አላቸው፡፡ ይኸውም አባታቸው አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ወንድማማቾቸ ናቸው፡፡ አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ሌሎች ሌሎች አራት ወንድሞች አሏቸው፡፡
እነርሱም እንድርያስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ቀሲስ ዮናስ እና ቀሲስ ዮሐንስ ናቸው፡፡ አርከሌድስ ሕፃን ሞዐን ይወልዳል፣ ጸጋ ዘአብ ተክለ ሃይማኖትን ይወልዳል፣ እንድርያስ ሳሙኤል ዘወገግን፣ ዘርዐ አብርሃም ታላቁ አኖሬዎዮስን፣ ቀሲስ ዮናስ ገላውዲዮስንና የፈጠጋሩን ማትያስን፣ እና ቀሲስ ዮሐንስ ዜናማርቆስን ይወልዳሉ፡፡ እነዚህ የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን በእናታቸውም ወገን ቢሆን እንዲሁ በዝምድና የተቆራኙ ናቸው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ በሌላኛው ስማቸው ሕፃን ዘደብረ በግዕ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይኸውም የደብረ በግዕን ገዳም የመሠረቱት እርሳቸው ስለሆኑ ነው፡፡
ከ47ቱ የሀገራችን ቀደምት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በመንዝና በተጉለት የሚገኙ ታላላቅ ገዳማትን አብዛኞቹን የመሠረቷቸው አቡነ ሕፃን ሞዐ ናቸው፡፡ ጻድቁ በክፉዎች ወሬና ሴራ ምክንያት ከበሬ ጋር ተጠምደው ሰማዕትነት የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ ከበሬ ጋር ሲታረሱ ውለው በእጅጉ ከደከማቸው በኋላ በኃይል የተነፈሱባት ምድሪቱ ዛሬም ድረስ ልክ እንደሰው የሚሞቅ ትንፋሽ ታወጣለች፡፡ ያም በጻድቁ እስትንፋስ አምሳል ከመሬት ውስጥ የሚወጣው እስትንፋስ ለአስም በሽታ መድኃኒት ሆኖ ብዙዎችን እየፈወ ነው፡፡
ገዳማቸው ከደብረ ብርሃን ከተማ በእግር የ2 ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይኸውም ከወንይዬ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አጠገብ ነው፡፡ ጻድቁ ጥር 25 ቀን ልደታቸው፣ ጥቅምት 25 ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ሲሆን ሐምሌ 25 ደግሞ ዕረፍታቸው ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስት ቴክላ
በዚህችም ቀን ከኒቆምድያ አገር ሐዋርያዊት ቅድስት ቴክላ አረፈች። ይህችም ቅድስት በቅዱስ ሐዋርያ በጳውሎስ ዘመን ሐዋርያዊት ሆነች። ቅዱስ ጳውሎስም ከአንጾኪያ ከተማ በወጣ ጊዜ ወደ ኒቆምድያ ከተማ ሔደ በዚያም ስሙ ሰፋሮስ የሚባል ምእመን ሰው ነበረ ቅዱስ ጳውሎስን ወስዶ በቤቱ አኖረው ብዙ አሕዛብም የሐዋርያው የጳውሎስን ትምህርት ይሰሙ ዘንድ በእርሱ ዘንድ ይሰበሰቡ ነበር። ይህች ቅድስት ቴክላም በቤቷ መስኮት ተመለከተች የሐዋርያውንም ትምህርት ሰማች እንዲሁም ትምህርቱን እያዳመጠች ሳትበላና ሳትጠጣ ሦስት ቀኖች ቆየች ትምህርቱም በልቧ አደረ አባትና እናቷ ቤተሰቦቿ ሁሉ አዘኑ። ከምክርዋም እንድትመለስ ሐዋርያው ጳውሎስንም እንዳትከተል ለመኑዋት ነገር ግን አልሰማቻቸውም።
ሁለተኛም አባቷ ወደ ንጉሡ ሒዶ ሐዋርያው ጳውሎስን ከሰሰው ንጉሡም ወደ እርሱ አስቀርቦ ስለ ሥራው ጠየቀው። ነገር ግን የሚቀጣበት ምክንያትን በላዩ አላገኘም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስንም እንዲአሥሩት አዘዘ።
ይህች ቅድስት ቴክላም ልብሶቿንና ጌጦቿን ከላይዋ አስወገደች። ወደ ቅዱስ ጳውሎስም ሒዳ ከእግሩ በታች ሰገደች በእርሱም ዘንድ እየተማረች ተቀመጠች። ወላጆቿም በፈለጓት ጊዜ አላገኟትም በሐዋርያው ጳውሎስ ዘንድ እርሷ እንዳለች ሰዎች ነገሩዋቸው በመኰንኑም ዘንድ ከሰሱዋት እርሱም በእሳት እንዲአቃጥሉዋት አዘዘ። እናቷም ስለርሷ ሴቶች ሁሉ እንዲገሠጹና እንዲፈሩ አቃጥሏት እያለች ጮኸች ብዙዎች የከበሩ ሴቶች በሐዋርያው ጳውሎስ ትምህርት አምነው ነበርና እርሷ ግን በሚአቃጥሏት ጊዜ ልቧን አጽንታ ቅዱስ ጳውሎስን ተመለከተችው።
ዳግመኛም ሲጸልይ ቅዱስ ጳውሎስን አወጡት በላይዋም በመስቀል ምልክት አማተበ። ራሷንም ወደ እሳቱ ምድጃ ወረወረች። ሴቶችም ያለቅሱላት ነበር። ያን ጊዜም እግዚአብሔር ብዙ ዝናብን በረድና መብረቅን ላከ የእሳቱም ምድጃ እንደ ቀዝቃዛ ጠል ሆነ ቴክላም ሩጣ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ተሠውሮ ወደ አለበት ቦታ ደረሰች ራሷንም ላጭቶ ትከተለው ዘንድ ለመነችው እንዲሁም አደረገላት።
ወደ አንጾኪያ ከተማም በሔደች ጊዜ ከመኳንንቶች አንዱ ሊአገባት ፈለገ መልኳ እጅግ ውብ ነበረና እርሷም ዘለፈችው ረገመችውም እርሱም በዚያች አገር ገዥ በሆነ በሌላ መኰንን ዘንድ ከሰሳት እርሱም ለአንበሶች እንዲጥሏት አዘዘ። በአንበሶች መካከልም ሁለት መዓልት ሁለት ሌሊት ኖረች እነዚያም አንበሶች እግርዋን ይልሱ ነበር እንጂ ምንም አልከፉባትም።
ከዚህም በኋላ በሁለት በሬዎች መካከል አሥረው በከተማው ውስጥ ሁሉ አስጐተቷት። ነገር ግን ምንም ምን ክፉ ነገር በላይዋ አልደረሰም ከዚያም በኋላ ለቀቁዋት። ወደ ቅዱስ ጳውሎስም ሔደች እርሱም አረጋጋት አጽናናትም። ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድትሰብክ አዘዛት።
ከዚህም በኋላ ቆሎንያ ወደሚባል አገር ሔዳ ሰበከች ከዚያም ወደ አገርዋ ሔዳ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አስተማረች አባትና እናቷንም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን መለሰቻቸው።
ተጋድሎዋንም ፈጽማ በሰላም አረፈች። የሐዋርያነት አክሊልንም ተቀበለች። ሥጋዋም በግብጽ ደቡብ ሰንጋር በሚባል አገር እስከ ዛሬ አለ። ከሥጋዋም ብዙ ድንቅና ተአምር ተገለጠ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አንዲኒና
በዚህችም ቀን ባና ከሚባል አገር ቅዱስ እንዲኒና በሰማዕትነት አረፈ።ይህም ቅዱስ ጎልማሳ ነበር። ወላጆቹም ከሀገር ሽማግሌዎች የሆኑ ምዕመናን ነበሩ።
ከዚህም በኋላ ይህ ቅዱስ ወደ እንዴናው ከተማ ሔደ። በመኮንኑም ፊት በመቆም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። መኮንኑም በፍላፃ ይነድፉት ዘንድ አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት ነገር ግን ከፍላፃዋች ምንም ምን ጉዳት አልደረሰበትም።
ከዝህም በኋላ አሥሮ ወደ እስክንድርያ ከተማ ላከው ከእርሱም ጋር ቅዱስ ቢማኮስና ሌሎች ሁለት ሰማዕታት ነበሩ። የእስክንድርያውም ገዥ አሠራቸው።
ቅዱስ እንዲኒናን ግን በአፍንጫው ብዙ ዳም እስኪፈስ ድረስ ዘቅዝቆ ሰቀለው። በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም ብዙ አሠቃየው። ከማሠቃየትም በሰለቸ ጊዜ ፈርማ ወዳሚባል አገር ላከው።
በዚያም በወህኒ ቤት ቅዱስ ሚናስን አገኘውና ደስ አለው። እርስ በርሳቸውም ተፅናኑ። ከዚህም በኋላ መኮንኑ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ አሠቃየው በእሳት ባጋሉትም መጋዝ ሥጋውን ሰነጥቀው። በብረት ምጣድ ውስጥም አበሰሉት ጌታችንም ያለጉዳት በጤና አስነሣው።
መኮንኑም ማሠቃየቱ በሰለቸው ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንተአምራት የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ከሥጋውም ታላላቅ ተአምራት ተደረጉ። ለበሽተኞችም ፈውስ ተደረገ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ይስሐቅ
በዚህችም ቀን ደግሞ ይስሐቅ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ሳምሳ ከምባል አገር ነበር እሱም የአታክልት ቦታዎች ጠባቅ ነበረ ደግ የዋህና ፁሙድ አገልጋይ ነበረ ሰጋም አይበላም ነበር ወይንም አይጠጣም ነበር በየሁለት ቀን ይፆም ነበረ ቅጠልም ይበላ ነበረ ድሆችንና ችግረኞችንም ይጎበኛቸው ነበረ ከደመዙም የምተርፈውም ይሰጣቸዋል።
ክብር ይግባውና ጌታችንም በራእይ ተገለጠለትና ወደ መኩንኑም ሒዶ በቅዱስ ስሙ እንዲታመን አዘዘው ከዝህም ቡኃላ ብዙ ቃል ክዳን ሰጠው ያዘጋጀለትንም የደስታ አክልሎችን ተስፍ አስደረገው።
በነቃ ግዜም እጅግ ደስ አለው ተነሥቶም ከእርሱ ያለውን ገንዘብ ለድሆች ሰጠ ከዝያም ቡኃላ ይረዳው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ወደ መኩንኑም ደርሶ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኩንኑም ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው በእሳትም አቃጠለው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ሰቀለው በመንኩራኲርም አበራየው ጌታችንም ያጸናውና ይፈውሰው ነበር ከመሠቃየቱም የተነሣ በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነትንም አክልሊ በመንግስተ ሰማያት ተቀበለ።
ከዚህም በኃላ ምእመናን ሰዎች ከሀገሩ ሳምሳ መጥተው ሥጋውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችንም ገንዘው የመከራው ዘመን እስክፈጸም ድረስ በመልካም ቦታ አኖሩትከዝያም ቡኃላ ውብ የሆነች ቤተክርስትያን ሠሩለት ሥጋውን በዝያ አኖሩት ከእርሱም ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስት ኢላርያ
ዳግመኛም በዚች ቀን በድሜራ አቅራብያ ድምድል ከሚባል አገር ቅድስት ኢላርያ በሰማዕትነት ሞተች። የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ደጎች ምእመናን ነበሩ እርሷዋም በስጋዋና በነፍሷ የነጻች ነበረች ሁሉ ጊዜም ተጻምና ትጸልይ ነበረች።
አሥራ አንድ አመትም በሆናት ጊዜ እርሷ ቆማ ስትጸልይ ጌታችን ታላቅ። ብርሃንን ገለጠላት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሩፍኤልም ተገልጦ እንድህ አላት ተጋድሎ ተዘርግቶ ሳለ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ስም ለምጋደሉም አክልሎች ተዘጋጅተው ሳሉ አንቺ ለምን ከዝህ ተቀምጣሻል አላት።
ይህንንም በሰማች ግዜ ደስ አላት ገንዘቧዋንም ሁሉ ለድኖችና ለችግረኞች ሰጥታ ጣው ወደ ምባል አገር ሔደች ከዝያም ስርስና ወደ ምባል አገር ሒዳ በመኩንኑ ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰም ታመነች ጌታችንም ሳኑሲ ለሚባል ሰው ለዝች ቅድስት ከእርሷ የሚሆነውን ነገረው።
ባያትም ጊዜ በእርሷ ደስ አለው አረጋጋት ልቧንም አጸናናት መኩንኑም ታላቅ ሥቃይን አሰቃያት ሥጋዋን ሁሉ ሠነጣጠቀ በእሳት ያጋሏቸውንም የብረት ችንካሮች በሥጋዋ ውስጥ ቸነከሩ።
ከዝህም ቡኃላ ከአምስት መቶ ባልንጀራሞች ሰማዕታት ጋራ አሠራት በመርከቦችም ከእርሱ ጋራ ወስዳቸው እነርሱም በመርከብ ስጓዙ አንበሪ መጥቶ ከእናቱ እቅፍ አንዱን ሕፃን ልጅ ነጥቆ ወሰደ እናቱም ከእርሱ በቀር ሌላ ስለሌላት እጅግ አዝና አለቀሰች ይች ቅድስትም አይታ ራራችላት ስለእርስዋም ጌታችንን ለመነችው ጌታችንም አንበርውን አዘዘውና ሕፃኑን ደኅና እንደሆነ ወደ እናቱ መለሰው ምንም ጥፋት አላገኘውም።
ከዚህም በኃላ ሕዋሳቷን ቆራረጡ የእጆቿንና የእግሮቿን ጥፍሮች ነቀሉ ምላሷንም ቆረጡ እግሮቿንም በብረት ችንካሮች ቸነከሩ። በብረት ዐልጋ ላይም አስተኝተው ከበታችዋ እሳትን አነደዱ። ነገር ግን ምንም ምን ጥፋት አልደረሰባትም ክብር ይግባውና ጌታችን አድኗታልና።
መኮንኑም እርሷን ከማሠቃየት የተነሣ በሰለቸ ጊዜ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱሳት ቴላና ሙጊ
በዚችም ቀን ከእስክንድርያና ከባሕያራ አውራጃ ቀራቁስ ከሚባል መንደር የከበሩ ቴክላና ሙጊ ሰማዕታት ሆኑ። እሊህም ቅዱሳት ቀራቁስ በሚባል መንደር በአንዲት እግዚአብሔርን በምትፈራ አማኒት ሴት ዘንድ አደጉ።
ወደ ባሕር ዳርቻ በአለፉ ጊዜም የክርስቲያን ወገኖችን ሲአሠቃያቸው መኰንኑን አዩት። እነዚያም ደናግል ስለ ልቡ ደንዳናነት አደነቁ ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠላቸው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም መከራን ለሚታገሡ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጀውን ክብራቸውን አሳያቸውና አጽናናቸው።
ከዚህም በኃላ በመርከብ ተጭነው ወደ እስክንድርያ ተጓዙ። እመቤታችን ማርያምም አልቃሾች በሆኑ በሁለት ሴቶች አምሳል ከኤልሳቤጥ ጋራ ተገለጸችላቸው ከእርሳቸውም ጋራ ወደ ከተማው በደረሱ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመኮንኑ ፊት ታመኑ መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸው።
ከዚህም በኃላ የቅድስት ሙጊን ራስ በሰይፍ ቆረጠ ተጋድሎዋንም ፈጸመች። ቅድስት ቴክላን ግን ድሙጢ ወደሚባል አገር ላካት በዚያ ሰማዕት ሆነች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አበከረዙን
በዚችም ቀን ዳግመኛ ባንዋን ከሚባል አገር ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት ሆነ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ወንበዴ ነበር ሌሎችም ሁለት ወንበዴዎች ነበሩ ገንዘቡን ሊሰርቁ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወደ አንድ መነኩስ በአንድነት ሔዱ በጸሎትም እየተጋ አገኙት ጸሎቱን ጨርሶ እስቲተኛ ድረስ ጠበቁት እርሱ ግን ከቶ አልተኛም በልቡናቸውም ፍርሀት አደረባቸውና ደነገጡ።
በነጋ ጊዜም ያ ሽማግሌ መነኰስ ወደ ሽፍቶቹ ወጣ ባዩትም ጊዜ ከእግሩ በታች ሰገዱ ሰይፎቻቸውንም በፊቱ ጥለው ደቀ መዝሙሮቹ ያደርጋቸው ዘንድ ለመኑት በርሱም ዘንድ መነኰሱ። ቅዱስ አባ አበከረዙንም በሥጋውም በመንፈሱም ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ። አንድ አረጋዊም ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰማዕት ይሆን ዘንድ እንዳለው ነገረው።
ከሰባት ዓመት በኃላም ሰይጣን በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራን አመጣ አባ አበከረዙንም ተነሥቶ መንፈሳዊ አባቱን እጅ ነሥቶ ከእርሱም ቡራኬ ተቀብሎ ኒቅዮስ ወደሚባል አገር ሔደ ንጉሥ መክስምያኖስንም አገኘው ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰም በፊቱ ታመነ መኰንኑም በጽኑ ስቃይ አሰቃየው በብረት መጋዝም ስጋውን መገዘው ቁስሉንም በመጣጣና በጨው አሸው።
ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ከተማ ሲወስዱት አምስት ጊዜ በመርከብ ምሰሶ ላይ ሰቀሉት ገመዶችም ተበጠሱ ከማስ በተሠራ ጋን ውስጥም አድርገው በባሕር ጣሉት ከእግዚአብሔርም የተላከ መላክ ከባሕር አውጥቶ ወደ ገምኑዲ ከተመሰ እንዲሔድ አዘዘው ብንውም ወደሚባል አገር ደረሰ ስለ አባ አበከረዙንም ጠየቀ እነርሱም አላወቁትም ነበርና ከብዙ ጊዚያትም ጀምሮ ከዚህ ሔዷል ወዴት እንዳለም አናውቅም ወሬውንም አልሰማንም አሉት።
አንዲት ብላቴና ግን አስተውላ አወቀችው ፈራችም ከፍርሀቷም ብዛት የተነሣ ወደቀችና እንስራዋ ተሰበረ እርሷም ሰዎች ይህ አባ አበከረዙን ነው አለቻቸው የአገሩ ሰዋችም ሁሉም ፈጥነው መጥተው ከእርሱ ተባረኩ ደዌ ያለባቸውም ወደርሱ ይመጡ ነበር እርሱም በዘይት ላይ ጸልዮ ሲቀባቸው ወዲያውኑ ይድኑ ነበር።
ከዚህም በኋላ ወደ ገመኑዲ ከተማ ሔደ ከወታደሮቹም አንዱን እኔ ክርስቲያን ነኝና በዚች ከተማ ውስጥ አሥረህ ጎትተኝ አለው እርሱም ወደ መኰንኑ እስከሚአደርሰው እንደ አዘዘው አደረገ መኰንኑም በእንጨት ላይ ዘቅዝቆ ሰቀለው በአፍንጫውና በአፋም ብዙ ደምእየፈሰሰ ዐሥር ቀኖች ኖረ አባ አበከረዙንም የጭፍራ አለቃውን ልጅ ረገማትና ወዲያውኑ ሞተች በመቃብርም ዐሥራ ሁለት ቀኖች ኖረች። ስለ እርሷም አባ አበከረዙንን ለመኑት ክብር ይግባውና ወደጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየ ያንጊዜም ከሙታን ተለይታ ተነሥታ በሲኦል ያየችውን ሁሉ ነገረቻቸው ከጭፍሮቹ ጋር ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ሞቱ ቁጥራቸውም ዘጠኝ መቶ አርባ አምስት ነፍስ ነበር።
ከዚህ በኋላ አባ አበከረዙንን ወደ እስክንድርያ ሰደደው በዚያም ጽኑ ሥቃይን አሠቃዩት ዳግመኛ ወደ ገምኑዲ ላኩት በዚያም በብረት በትሮች ደብድበው የጀርባውን አጥንት ሰበሩት እርሱ ግን በፈጣሪው ኃይል ዳነ።
መኰንኑም ማሰቃየት በደከመ ጊዜ ዳግመኛ ወደ እስክንድርያ ከተማ ላከው ወደ እስክንድርያም በሚያዚያ ወር በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለትና አጽናናው ገድሉንም በዚያ እንደሚፈጽም ነገረው።
ስሙን ለሚጠራ ሁሉ መታሰቢያውንም ለሚያደርግ ኃጥያቱን እንደሚያስተሠርይለት ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚህም በኃላ ራሱን ቆረጡት ተጋድሎውንም ፈጽሞ የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ።
የእግዚአብሔር መልአክም መኑፍ ከሚባል አገር ለአንድ ቄስ ተገልጦ የቅዱስ አበከረዙን ሥጋ ያለበትን ቦታ ነገረውና እንዲወስደው አዘዘ። እርሱም ወስዶ ባማሩ ልብሶች ገነዘው የመከራውም ወራት እስከሚፈጸም በመልካም ቤት አኖረው ከዚህም በኋላ ቦታ ክርስቲያን ሰርተውለት ሥጋውን በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ዲማድዮስ
ዳግመኛም በዚች ቀን የሶርያ ሰው ቅዱስ ሰማዕት ዱማድዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ በፋርስ አገር አደገ የከዋክትን ምግብን ጥበብ ተማረ ከዚህም በኋላ ክርስርስቲያን ሊሆን ወደደ ከፋርስ ሰዎችም ስሙ አጋሊዮስ የሚባል ቄስ በገበያ ውስጥ አገኘ እርሱም ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ ሃይማኖትን አስተማረው እጅግ ደስ ብሎት ቤተሰቦቹን ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ ያስተምራቸው ጀመረ አሳመናቸውም።
ከዚህም በኋላ በሶሪያና በሮም መካከል ወዳለች አገር ሔደ በዚያም የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቆ መነኮሰ ታላቅ ተጋድሎንም መጋደል ጀመረ መነኰሳቱም ታላቅ የሆነ ተጋድሎውን በአዩ ጊዜ በእርሱ ላይ ቀንተው ከገዳም ሊያሳድዱት ወደዱ።
በአወቀም ጊዜም ወጥቶ ወደ ቅዱስ ሰርጊዮስ ገዳም ሔደ በዚያም በአንድ ባህታዊ ቄስ ዘንድ ተቀመጠ ከዚህም በኋላ ዲቁና እንዲሾመውና ከእርሱ ጋር በቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲያገለግል ቅዱስ ዲማድዮስን አስገደደው ትዛዙንም መተላለፍ ባልተቻለው ጊዜ ዲቁና ተሾመ።
አረጋዊው ቄስ በመሰዊያው ላይ በሚሰየም ጊዜ በቅዳሴው እኩሌታ በምሥዋቱ ላይ ርግብ ስትወርድ ቀዱስ ዱማድዮስ ያያት ነበር እርሱም ሥጋዊት ርግብ እንደሆነች ያስብ ነበር ሽማግሌው ግን አያያትም ነበር የቅዳሴው ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ባሕታዊው ቄስ እንዲህ ብሎ ጠየቀው በቅዳሴ ጊዜ የምትደነግጥ እጅህንም ወደ መሥዋቱ የምትዘረጋው ምን ሆነህ ነው እርሱም ርግቧን እንዳያት ነገረው ከእንግዲህ ስታያት ንገረኝ አለው።
ከዚያም በኋላ በአያት ጊዜ አባቴ ሆይ ያቺ ርግብ መጣች ብሎ ነገረው ሽማግሌው ግን አላያትምእጅግም አዝኖበእግዚአብሔር ፊት ሰገደ ያቺንም ርግብ እስከሚያያት ድረስ ፈጽሞ ይጸልይና ይማልድ ነበር ያቺ ርግብ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና ለዲያቆን አባ ዱማድዮስም ልቡ እንዳይታበይ አልነገረውም።
ከዚህ በኃላም ሽማግሌው ቄስ ወደ ኤጲስቆጶስ ሒዶ ዱማድዮስን የቅስና መዐረግ ይሾምለት ዘንድ ለመነው ልመናውንም ተቀብሎ ያለ ውዴታው ቅስናን ሾመው።
ሊቀ ጳጳሳቱም ዜናውንና ገድሉን በሰማ ጊዜ ከእርሱ ጋራ ወገኖቹን ወሰደ ከወገኖቹ ጋራም ወደርሱ ሔዶ በረከቱን ሊቀበል ወደደ። ቅዱስ ዱማድዮስ ግን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ከዚያ ተሠውሮ ሔደ ወደ ሰማዕቱ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንም ደረሰ ከዚያም ወደ በረሀ ሔዶ በዚያ ሣር እየበላ ኖረ እርሱ ከከንቱ ውዳሴ ይሸሽ ነበረና።
እግዚአብሔርም በእጆቹ ድንቆችንና ተአምራቶችን ያደርግ ነበር። በአንዲት ቀንም ውኃ ሊቀዳ ወደ ወንዝ ሔደ ውኃ የሚቀዱ ሴቶችም አይተውት በመጠቃቀስ በእርሱ ላይ ተዘባበቱ በልቡም እያዘነ ውኃ ሳይቀዳ ተመለሰ ያን ጊዜም ወንዙ ደረቀ።
ሰዎችም ቅዱስ ዱማድዮስ እንዳደረቀው በአወቁ ጊዜ ሴቶችና ወንዶች ሁሉ ወጥተው በብዙ ለቅሶ ለመኑት ልቅሶአቸውንም አይቶ ክብር ይግባውና ጌታችንን ለመነው የወንዙንም ውኃ እንደ ቀድሞው መለሰላቸው።
ሰዎችም ሲያከብሩት በአየ ጊዜ ከዚያ መጠለያ ከሰማይ በታች ያለውን የበጋውን ቃጠሎና የክረምቱን ቅዝቃዜ ታግሦ እየተጋደለ ዓመት ሙሉ ኖረ በብዙ ድካምም አስገድደው ትንሽ ጎጆ ሠርተው በውስጧ አስገብት።
ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ ከእነርሱም አንድ ዐይኑ የታወረች አንድ ሰው ነበረ ከእርሱም በተባረከ ጊዜ ዐይኑ ድና አየች እንደ ሁለተኛዋም ሆነች ሁለተኛም ጉባጣ ሰው ወደርሱ አመጡ በውኃና በዘይትም ላይ ጸልዮ የመጻጉዑን ሥጋ አጥቦ አዳነው ዲዳውንም እንዲሁ አዳነው።
ከዚህም በኃላ ባልና መካን ሚስቱ መጡ ስለ እነርሱም ይጸልይ ዘንድ ለመኑት እርሱም ክብር ይግባውና እግዚአብሔርን ለምኖላቸው ልጆችን ሰጣቸው ወደርሱም ልጆቻቸውን አምጥተው ባረካቸው። ከዚህም የሚበዛ ብዙ ተአምራትን አደረገ።
በከሀዲው በዋሊጦስ ዘመንም የአምላክ ወዳጅ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ ያሠራቸውን አብያተ ክርስቲያናት ጭፍሮቹ ወደ አንጾኪያ መጥተው አፈረሱ። ከዚህም በኃላ የፋርስ ሰዎች ጦርነት ሊገጥሙት መጡ ሲጓዙም ወደ ቅዱስ ዱማድዮስ ማደሪያ ደረሱ ስለ ርሱም ለመኵንኑ ነገሩት እርሱም ይወግሩት ዘንድ አዘዘ ከረድኡም ጋራ በድንጊያ ወገሩት። የጣሉባቸው ድንጋይም በበዐታቸው ላይ ታላቅ ኮረብታ ሆነ። እርሱና ረድኡም እንዲህ በሆነ ድርጊት አረፉ።
ከአንድ ዓመትም በኃላ ለአንድ መንገደኛ ነጋዴ ሰው ገለጠለት።ገመልም ጭኖ ነበር። እርሱም ሲያልፍ ገመሉ ከምድር በታች በጉድጓድ ውስጥ ወደቀ። ሰዎችም ገመሉን ሊያወጡት በመጡ ጊዜ የቅዱስ ዱማድዮስ በዐት ተገለጠ። ቆፍረውም የቅዱስ ዱማድዮስንና የረድኡን ሥጋ በክብር አወጡ ይኸውም በአረፈበት በሐምሌ ሃያ አምስት ቀን ነበር። ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው የእርሱን ሥጋና የረድኡን ሥጋ በውስጥዋ አኖሩ ጌታችንም ከእርሱ ብዙዎች ተአምራትን ገለጠ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ነቢዩ ቅዱስ ሄኖክ
በዚችም ቀን አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ በሞት ፋንታ የተሰውረው ነቢዩ ቅዱስ ሄኖክ የዕርገቱ መታሰቢያ በዚህች ዕለት ሆነ፡፡ ዘፍ 5፡21፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም "ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ መስክሮለታልና" በማለት ገልጾታል፡፡ ዕብ 11፡5፡፡
ነቢዩ ሄኖክ ብዙ ሰማያዊ ምሥጢራትን ያየ ነው፡፡ ስለጌታችንም እንዲህ ብሎ ትንቢትን ተናገረ፡- ‹‹የዘመናት አለቃ ወደሆነው የሰው ልጅ ተጠራ፣ ዓለም ከመፍጠሩ አስቀድሞ የነበረ ሆነ፣ ሁለተኛም ለጻድቃን የጽድቅ በትር ለአሕዛብም ብርሃን ተስፋ ለሌላቸውም አለኝታ ይሆናል›› አለ፡፡ ዳግመኛም ስለምኩራብ ሲናገር ‹‹ያንን አሮጌ ቤት እስኪያሳንሰው ድረስ አየሁ፣ ምሰሶዎቹንም ከውስጡ አውጣ፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያንም ጌታ አዲስ የበጎች ቤት አምጥቶ ሲሠራ አየሁ፣ ከቀድሞውም የበለጠ ነው፣ በጎችም ሁሉ በውስጧ ይሰማራሉ›› አለ፡፡ ስለ ምእመናንም ‹‹የእነዚህ በጎች ፀጉራቸው ንጹሕ ነጭ ነው፣ የተበተኑትም ከአራዊት ጋራ ይሰማራሉ፤ ሁሉም በአንድነት ተሰብስበው ገራሞች ሆነዋል›› አለ፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages