ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 26 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, August 12, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 26

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሐምሌ ሃያ ስድስት በዚች ቀን የእመቤታችን ድንግል ማርያም እጮኛዋ ለጌታችንም አሳዳጊው ለመሆን የተገባው ጻድቁ ዮሴፍ አረፈ፣ ለኢትዮጵያ ሀገር ብርሃንን የገለጠ ቅዱስ አባት አባ ሰላማ አረፈ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ጢሞቴዎስ አረፈ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌ ሉያ ዕረፍታቸው ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ጻድቁ ዮሴፍ
ሐምሌ ሃያ ስድስት በዚች ቀን መልካም ሽምግልና የነበረው የእመቤታችን ድንግል ማርያም እጮኛዋ ድካሟን ለመሳተፍ ክብር ይግባውና ለጌታችንም አሳዳጊው ለመሆኑ የተገባው ጻድቁ ዮሴፍ አረፈ።
እርሱም እምቤታችንን በርሱ ዘንድ ካስጠበቋት ጀምሮ በሁሉ ነገር ያገለግላት ነበር። በመከራዋም ሁሉ አልተለያትም። በወለደችም ጊዜ በቤተ ልሔም ከርሷ ጋራ ነበረ። ወደ ግብጽም በተሰደደች ጊዜ ከእርሷ ጋራ ብዙ መከራ ደረሰበት። ከዚህም ዓለም የሚለይበት ጊዜው በደረሰ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን ጠርቶ ተሰናበታቸው እጆቹንም ዘርግቶ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። የዘላለምንም ሕይወት ወረሰ።
በአረፈበትም ጊዜ ጌታችን ወደርሱ መጥቶ እጆቹን በላዩ ጫነ ለሥጋውም መፍረስና መበስበስ እንዳያገኘው ኃይልን ሰጠው በአባቱ በያዕቆብም መቃበር አኖሩት። ዕረፍቱም ክብር ይግባውና ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዊ በዐሥራ ስድስት ዓመት ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን
በዚችም ቀን ለኢትዮጵያ ሀገር ብርሃንን የገለጠ ቅዱስ አባት አባ ሰላማ አረፈ። ዜናውም እንዲህ ነው ስሙ ሜሮጵዮስ የሚባል የጥበበኞች አለቃ አንድ ሰው ወደ ሕንድ አገር ሊአልፍ ወዶ ከጢሮስ አገር መጣ ከእርሱም ጋራ ከዘመዶቹ ወገን የሆኑ ሁለት ብላቴኖች ነበሩ። የአንደኛው ስሙ ፍሬምናጦስ የሁለተኛውም ኤዴስዮስ ይባላል። ሲድራኮስ የሚሉትም አሉ። በኢትዮጵያ በኩል ወዳለው ወደ አፍሪቃ ባሕር ወደብ ደረሱ ልቡ የተመኘችውን የኢትዮጵያን አገር መልካምነቷን ሁሉ ተመለከተ።
ከዚህም በኃላ በድንገት ወንበዴዎች ተነሥተው በመርከብ ከአሉት ሁሉ ጋር ገደሉት እኒህ ሁለት ልጆች ግን ተረፉ። የአገሩ ሰዎችም አገኙዋቸው ወደ ንጉሥም ወስደው አንድ እጅ መነሻ አድርገው እነርሱን ሰጡት ንጉሡም ተቀበላቸው።
ከጥቂት ቀኖች በኃላም ንጉሡ ኤዴስዮስን በፊቱ የሚቆም ጋሻ ዣግሬ አድርጎ ሾመው ፍሬምናጦስን ግን በገንዘቡ ሁሉ ላይ በጅሮንድ አድርጎ ሾመው ይህም ንጉሥ የአብርሀና የአጽብሐ አባታቸው ስሙ አይዛና የተባለው ነበር። እነርሱ ሕፃናት ሳሉም አረፈ። እኒህም አካለ መጠን እስከሚያደርሱ ድረስ የንጉሡን ልጆች እያሳደጉ ኖሩ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ማመንንም አስተማሩዋቸው።
የንጉሡም ልጆች አድገው በነገሡ ጊዜ ኤዴስዮስ ወደ አገሩ ተመለሰ ፍሬምናጦስ ግን ወደ ግብጽ ሔደ ወደ እስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ አትናቴዎስም ደረሰ። የደረሰብትንም ሁሉ ነገረው።ስለ ኢትዮጵያውያንም ሃይማኖት ጳጳስ ሳይኖራቸው ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንዳመኑ ነገረው። አባ አትናቴዎስም በሰማ ጊዜ እጅግ አደነቀ ፍሬምናጦስንም የነጻ ሕዝብ አገር ለሆነችው ለኢትዮጵያ አገር ጳጳስ ይሆን ዘንድ ግድ አለው። ጵጵስነትንም ሾመ ከታላቅ አክብሮት ጋራ ላከው በአብርሀና በአጽብሐ ዘመነ መንግሥትም ወደ ኢትዮጵያ በደረሰ ጊዜ በክብር ተቀበሉት።
በኢትዮጵያም አገሮች ሁሉ የቀናች ሃይማኖትን ሰበከ አስተማረም ክብር ይግባውና ክርስቶስን የጌትነቱን ብርሀን በሁሉ አገሮች ገለጠ ስለዚህም ብርሃንን ገላጭ ሰላማ ተባለ ሁሉንም አስተካክሎ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ጢሞቴዎስ
በዚችም ቀን ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ቁጥር ውስጥ የሆነው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ጢሞቴዎስ አረፈ። በተሾመ ጊዜም የክርስቶስን መንጋዎች ከአርዮስ ከመቅዶንዮስና ከሰባልዮስ ተኩላዎች ጠበቀ።
ይህም አባት በተሾመ በስድስተኛው ዓመት ለክርስቲያን ወገኖች ደግ የሆነ ቴዎዶስዮስ ነገሠ በዚያችም ዓመት ክብር ይግባውና መንፈስ ቅዱስን ስለ ካደው ስለ መቅዶንዮስ በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡ የመቶ ሃምሳ ቅዱሳን ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ተደረገ ይህም አባት ጢሞቴዎስ ሊቀ ጉባኤ ሆኖ መቅዶንዮስንና ሰባልዮስን አቡሊናርዮስንም ተከራከራቸው። ረትቶም አሳፈራቸው። እነሆ የክህደታቸውንና የክርክራቸውንም ነገር የካቲት አንድ ቀን ላይ ጽፈናል።
ከዚህም በኃላ ይህ አባት በሹመቱ ዘመን አብያተ ክርስቲያናትን በማነፅና በሚገባውም ሥራ ሁሉ በእድሳታቸውም አሰበ። ለመጻተኞችም ቤቶችን ሠራላቸው።
መንጋዎቹንም ሁልጊዜ ያስተምራቸው ነበር በመልካም እውቀቱና በትምህርቱ ጣዕም ሁልጊዜም በማስረዳቱ በቀናች ሃይማኖት አጸናቸው። ከአርዮስና ከመቅዶንዮስ ወገኖችም ብዙዎቹን መልሶ ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሆነች የቀናች ሃይማኖት አስገባቸው።
በወንጌላዊው ማርቆስ መንበርም ላይ ዘጠኝ ዓመት ተኩል ኖረ ከዚያም በኃላ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌ ሉያ
በዚህችም ቀን አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌሉያ ዕረፍታቸው ነው፡፡ የትውልድ ሀገራቸው ተንቤን ነው፡፡ አባታቸው ይስሐለነ እግዚእ እናታቸው ትቀድሰነ ማርያም ይባላሉ፡፡ አቡነ አቢየ እግዚእ አጎታቸው ናቸው፡፡ እናታቸው እሳቸውን ፀንሳ ሳለ ቡራኬ ለመቀበል ወደ ወንድሟ ስትሄድ አቡነ አቢየ እግዚእ መሬት ላይ ወድቀው ሰግደውላታል፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ‹‹ለዚህች ሴት እንዴት ሰገዱላት?›› ብለው ቢጠይቋቸው አቡነ አቢየ እግዚእ ስለ አቡነ ሳሙኤል ክብርና ጽድቅ ትንቢት ነግረዋቸዋል፡፡
አቡነ ሳሙኤል ሲወለዱ እናታቸው ለአቡነ አቢየ እግዚእ ሰጠቻቸው፣ እርሳቸውም በሃይማኖት በመግባር ኮትኩተው ሁሉን አስተምረው አሳደጓቸው፡፡ አባታችን የጻድቃንና የሰማዕታትን ታሪክ እያነበቡ ያዝኑና ያለቅሱ ነበር፡፡ እንደ እነርሱ በሆንኩም እያሉ ይመኙ ነበር፡፡ አቡነ አቢየ እግዚእ ሀሳባቸውን በመንፈስ ተረድተውላቸው ነበርና መርቀው ባርከው አሰናበቷቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤልም በሕፃንነታቸው መንነው ወደ አቡነ እንጦንዮስ ገዳም ገብተው በ14 ዓመታቸው መነኮሱ፡፡
ከየት እንደመጣ የማይታወቅና መላ አካሉ እንደበረዶ ነጭ የሆነ አንበሳ መጥቶ እየመራቸው አሁን ደብረ ሃሌሉያ እየተባለ ወደሚጠራው ገዳማቸው ሄደው በዓታቸውን አጽንተው ገዳሙን መሠረቱት፡፡ አቡነ ሳሙኤል ዘሀለሎም እየተባሉ ይጠራሉ፡፡
ጻድቁ የጌታችን መከራ በማሰብ ከተወለዱ ጀምሮ ተላጭተውት የማያውቁትን ፀጉራቸውን ከትልቅ ዛፍ ላይ እያሠሩ ይጸልዩ ነበር፡፡ እንዲሁ አድርገው ዛፍ ላይ ራሳቸውን ሰቅለው 40 ቀንና 40 ሌሊት ሲጸልዩ በመጨረሻ የታሠሩበት ፀጉራቸው ተነቅሎ ከመሬት ላይ ወደቁ፡፡ ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ጌታችንም ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን አስከትሎ ተገልጦላቸው እጃቸውን ይዞ አንሥቷቸዋል፡፡ ‹‹ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ?›› ቢላቸው ስለ ሀገራችን ሰላም ይልቁንም በዚህ በቆረቆሩት ገዳማቸው የሚኖሩትን ልጆቻቸውን እንዲጠብቅላቸው ለመኑት፡፡ ጌታችንም በገዳማቸው ውስጥ በፍጹም ሕማም፣ ደዌና ተስቦ በሽታ እንደማይገባ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
ለመንግሥተ ሰማያትም ያልታጨ ሰው በዚህ ገዳም ገብቶ አይቀበርም፡፡ ጻድቁ ከዛፉ ላይ ወድቀው ሳለ ጌታችንን እጨብጣለሁ ብለው የዘረጓት እጃቸው እያበራች ኖራለች፡፡ እንደ መብረቅም እየጮኸች ለገዳሙ እንደ ደወል ታገለግል ነበር፡፡ በመጨረሻም ሊያርፉ ሲሉ ልጆቻቸውን ሰብስበው ባርከዋቸዋል፡፡ ያ አቡነ ሳሙኤል የባረኩበት ቡራኬም በመጽሐፈ ግንዘት ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ዛሬም ድረስ ሰው ሲሞት ‹‹ቡራኬ ዘአቡነ ሳሙኤል›› ብሎ ካህኑ ይደግማል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በከተማ አካባቢ ግን እየተደረገ አይደለም፡፡ አቡነ ሳሙኤል ብዙዎችን ያመነኮሱ ሲሆን እንደነ አቡነ ተጠምቀ መድኅን፣ አቡነ ዘኢየሱስ፣ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ያሉ ሌሎችንም በርካታ መነኮሳትን አፍርተዋል፡፡
አባታችንን ያመነኮሷቸው አባት አቡነ እንጦንዮስ ሊጠይቋቸው ወደ ደብረ ሃሌሉያ ሄደው ሲመለሱ እንዲላላካቸው አንድ ትንሽ ልጅ ትተውላቸው ተመለሱ፡፡ አቡነ ሳሙኤልም በጥበብ መንፈሳዊ ኮትኩተው አሳደጉት፡፡
አንድ ቀን ምግባቸው የሚሆን የእንጨት ፍሬዎችን ለመልቀም ከበዓታቸው ሲወጡ ልጃቸው እንዳይደክምባቸው በማሰብ በገዳማቸው ትተውት ለመሄድ አሰቡ፡፡ ብቻውን ስለሆነ አስፈሪ አራዊት እንዳያስደነግጡት በማሰብ ጉድጓድ ቆፍረው በዚያ አኑረውት ሄዱ፡፡ ርቀው ሄደው የእንጨቶችን ፍሬ ሲለቅሙ በጫካው እሳት ተስቶ ገዳማቸውንም ሙሉ በሙሉ አቃጠለው፡፡ ጻድቁ ስለ ልጃቸው ወደ ፈጣሪያቸው ጸልየው ካበቁ በኋላ ወደ ገዳማቸው ቢሄዱ የልጃቸው የራስ ፀጉር እንኳን ሳትቃጠል በሰላም አገኝተውታል፡፡ ያ ልጅም በኋላ አቡነ ገብረ መስቀል የተባለው ገድለኛ አባት ነው፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages