ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 11 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, February 22, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 11

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።ቅዱስ አባ ሞይስስ ጻድቅ
ቅዱሱ በኋላ ዘመን ከተነሱ አበው አንዱ ሲሆን ትውልዱ: ነገዱ ከግብፅ ነው:: ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ ቢሆንም ክርስቲያኖች ጠንካሮች ነበሩ:: አባ ሞይስስ ከክርስቲያን ወላጆቹ ተወልዶ: ገና በልጅነት ወደ ትምህርት ቤት ገብቷል::
የዘመኑ ትምሕርት ሁለት ወገን ሲሆን
1ኛው የሃይማኖት ትምሕርት:
2ኛው ደግሞ ፍልስፍና ነበር::
የጻድቁ ምርጫው የቤተ ክርስቲያን ትምሕርት ነበርና ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል:: እንደሚገባ ተምሮ ስለ ነበርም ዲቁናን ሹመውት ተግቶ አገልግሏል::
ከጥቂት ዘመናት በኋላም በተሻለው ጐዳና እግዚአብሔርን ሊያገለግል ተመኘ:: ይህቺን ዓለምም ይንቃት ዘንድ ወደደ:: መልካም ምኞትን መፈጸም ለእግዚአብሔር ልማዱ ነውና የልቡናውን ተምኔት ፈጸመለት:: ከከተማ ወጥቶ: ቁራጭ ጨርቅ ለብሶ ገዳም ገባ::
በዚያም በረድእነት ያገለግል ገባ:: በፍጹም ልቡ በትሕትና እግዚአብሔርን ደስ አሰኘ:: በጉብዝናው ወራት ይህንን መርጧልና:: ገዳሙንም ሲያገለግል ዕረፍትም አልነበረውምና በመነኮሳት ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነው::
ከጊዜም በኋላ "በቅተሃል" ብለው አበው ከአሞክሮ ወደ ምንኩስና: ከምንኩስና ወደ አስኬማ አሸጋግረውታል:: እርሱም ለአሥራ ስምንት ዓመታት አገልግሎቱን ሳያስታጉል: ወጥቶ ወርዶ ገዳሙን ረድቷል:: በእነዚህ ጊዜያት በጸሎት: በጾምና በስግደት ይጋደል ነበር::
በጠባዩም ትእግስትን: ትሕትናን: ተፋቅሮን የሚያዘወትር ነበር:: ጐን ለጐንም ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ይፋጠን ነበር:: በዘመኑ የግብፅ ፓትርያርክ አባ ሚካኤል ይባሉ ነበር::
አውሲም በምትባል አውራጃ ኤጲስ ቆጶስ ዐርፎባቸው "ማንን ልሹም" እያሉ ይጨነቁ ነበርና እግዚአብሔር ስለ አባ ሞይስስ ገለጠላቸው::
አባ ሚካኤልም "ለሕዝቤ የሚጠቅም መልካም እረኛ አገኘሁ" ብሎ ደስ አለው:: ጊዜ ሳጠፋም እርሱን አስጠርቶ "ተሾም" አለው:: አበው ትሕትና ሙያቸው ነውና "አይቻለኝም: ተወኝ ይቅርብኝ" ሲል መለሰ::
አባ ሚካኤል ግን "የምሾምህ መቼ በሰው ፈቃድ ሆነና: በእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ" ብሎ ዕለቱኑ ሹመውታል:: እርሱም የአውሲም ጳጳስ ሆኗል:: ቅዱሱ አባ ሞይስስም ወደ ሃገረ ስብከቱ ሔዶ አገልግሎቱን ጀመረ::
በጵጵስና ዘመኑ እንደ ከተማ ሰው መኖርን: የሥጋ ምቾትን አልፈለገምና ጠባቡን መንገድ መርጧል:: በገዳም ሲሰራው ከነበረው ተግባር መካከል ያቋረጠው አልነበረም:: ከብቃቱ የተነሳ ለወደፊት የሚደረገውን ያውቅ ነበር:: እርሱ የተነበየው ሁሉ ተፈጽሟልና::
ሕዝቡን ይመራቸው ዘንድም ተግቶ ያስምራቸው ነበር:: ዘወትርም ከክፋት: ከኃጢአት ይጠብቃቸው ዘንድ ይጸልይላቸው ነበር:: ያዘኑትን ሲያጽናና: በደለኞችን ሲገስጽ ዘመናት አለፉ:: አንድ ወቅት ላይም ስለ ሃይማኖቱ ታሥሮ በረሃብ ተቀጥቷል: ግርፋትንም ታግሷል::
ጻድቁ ጳጳስ አባ ሞይስስ እንዲህ ተመላልሶ የሚያርፍበት ቀን ቢደርስ ሕዝቡን ሰበሰባቸው:: "እኔ ወደ ፈጣሪዬ እሔዳለሁና ሃይማኖታችሁንና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቁ" ብሏቸው በትእምርተ መስቀል አማትቦ ዐረፈ:: ምዕመናንም በብዙ እንባና ምስጋና ቀብረውታል:: ከተቀደሰ ሥጋውና ከመቃብሩም ብዙ ተአምራት ታይተዋል::
አምላከ ቅዱሳን ከቅዱሱ አባት በረከት ይክፈለን::
ነሐሴ 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ሞይስስ
2.ቅዱስ አብጥልማዎስ
3.ሦስት መቶ ሰማዕታት (የቅዱስ ፋሲለደስ ማኅበር)
ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
3.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
4.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
5.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
"ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት: ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::"
(ሐዋ. ፳፥፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages