ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 10 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, February 22, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 10

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነሐሴ ዐሥር በዚህች ቀን የታላቁ ጻድቅና ገዳማዊ አባ ዓቢየ እግዚእ ዓመታዊ የተአምር በዓል ነው፣ ቅዱስ መጥራ በሰማዕትነት ሞተ፣ ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ በሰማዕትነት ሞተ፣ የከበሩ ቅዱሳን ቢካቦስና ዮሐንስ በሰማዕትነት ሞቱ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አባ ዓቢየ እግዚእ ኢትዮጵያዊ
ነሐሴ ዐሥር በዚህች ቀን የታላቁ ጻድቅና ገዳማዊ አባ ዓቢየ እግዚእ ዓመታዊ የተአምር በዓል ነው። አባ ዓቢየ እግዚእ የተወለዱት በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ትግራይ ተንቤን (መረታ) ውስጥ ነው። የተባረኩ ወላጆቻቸው ያፍቅረነ እግዚእ እና ጽርሐ ቅድሳት ይባላሉ። አጥምቀው "ዓቢየ እግዚእ" ሲሉ ስም ያወጡላቸው የወቅቱ ጳጳስ ሰላማ መተርጉመ መጻሕፍት ናቸው። ትርጉሙም 'በጌታ ዘንድ ታላቅ ሰው' ማለት ነው።
ዓቢየ እግዚእ በሕፃንነታቸው ሌሊት ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ አድረው ቀን ቀን እየተማሩ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ። ገና በወጣትነታቸው ወደ ታላቁ መነኮስ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ (ደብረ በንኮል) ሔደው መንኩሰዋል።
በገዳሙ በጾም በጸሎትና በስግደት ተወስነው ከኖሩ በኋላ ወደ ዋልድባ ሔደው የተሰወረች ቤተ ክርስቲያን አግኝተዋል። በጊዜው በአርባ ቀን አንዲት ቅጠል ብቻ ለቁመተ ሥጋ ይበሉ ነበር።
ከዚያም ወደ ሃገራቸው ተንቤን ተመልሰው ዛሬም ድረስ ድንቅ ሆኖ የሚታየውን ገዳም መሥርተው ብዙ መናንያንን አፍርተዋል። ዓቢየ እግዚእ ገዳማዊና ጻድቅ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያዊ አባትም ነበሩ። ከትግራይ እስከ ደንቢያ ደግሞ ሃገረ ስብከታቸው ነው።
አንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርትን አስከትለው ለስብከት ሲንቀሳቀሱ ተከዜ ወንዝ አካባቢ ደረሱ። ቀኑ ነሐሴ ዐሥር ነውና ተከዜ እስከ ገደፉ ሞልቶ ለሦስት ቀናት ባለመጉደሉ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች ሲያለቅሱ ደረሱ። ጻድቁ በአካባቢው የነበሩት ኢ-አማንያን (አሕዛብ) ቢሆኑም ራርተዋልና "አምላከ ሙሴ" ብለው ጸልየው ወደ ጥልቁ ውስጥ ገቡ።
ቅዱስ ሚካኤል አብሯቸው ነበርና ተከዜ ግራና ቀኝ ተከፍሎ መሃሉ የብስ ሆነ። ይሕን ድንቅ ያዩ ከዘጠኝ መቶ አርባ በላይ አሕዛብም አምነው በጻድቁ እጅ ተጠምቀዋል። ይሕም ዘወትር ነሐሴ ዐሥር ቀን በቤተ ክርስቲያናቸው (ጐንደር) ይከበራል።
ከዚያም እያስተማሩ ጐንደር ደረሱ። ያኔ ጐንደር በቀሃና አንገረብ ወንዞች የታጠረች አንዲት መንደር ነበረች። ጻድቁ ቀን ቀን እየሰበኩ ማታ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናቸው የታነጸበት ሥፍራ ላይ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር።
በዚያ ዘመን ጐንደር ውስጥ ጅብ እባብና መሠል አራዊት ገብተው ሕዝቡን ጨረሱት። ይሕንን የተመለከቱት አባ ዓቢየ እግዚእ ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ። በፍጹም ልባቸውም ስለ ሕዝቡ ለመኑ። የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ወደ ጻድቁ ቀርቦ "በስምሕ የተማጸኑ በቃል ኪዳንህ ያመኑ: በምድር አራዊት አይሠለጥኑባቸውም። በሰማይም እሳትን አያዩም። ጐንደርንም አራዊት ገብተው ሰውን አይጐዱም።" ብሏቸው አርጓል።
አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው ተንቤን ለብዙ ዘመናት በቅድስና ኑረው ሦስት ሙታንን አስነስተው ብዙ ድውያንን ፈውሰው ብሔረ ብጹዓንን ጎብኝተው የድኅነት ቃል ኪዳንም ተቀብለው በመቶ አርባ ዓመታቸው ግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ ቀን አርፈዋል። የጻድቁ ክብር ለሁሉ ነውና እናስባቸው።
ይህች ዕለት ባሕረ ተከዜን ከፍለው ሕዝቡን ያሻገሩባት አሕዛብንም ያጠመቁባት ናትና በገዳማቸው ጐንደር ውስጥ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያናቸውም ይከበራል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ መጥራ
በዚህች ቀን በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በቅዱስ ዲሜጥሮስ ዘመንና በከሀዲው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘመነ መንግሥት ቅዱስ መጥራ በሰማዕትነት ሞተ።
ይህም ቅዱስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክደው ለጣዖት መስገድን የሚያዝ የንጉሡን ደብዳቤ በሰማ ጊዜ ይህ ቅዱስ ወዲያውኑ ሒዶ ከወርቅ የተሠራ የአጵሎንን ክንድ ሰረቀ በየጥቂቱም ሰባብሮና ቆራርጦ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጣቸው።
የጣዖቱም አገልጋዮች ክንዱ ተቆርጦ አጵሎንን በአገኙት ጊዜ ስለርሱ ብዙዎችን ሰዎች ያዟቸው። በዚያንም ጊዜ ወደ መኰንኑ ቀርቦ ክርስቲያን እንደሆነ በፊቱ ታመነ ሁለተኛም የአጵሎንን የወርቅ ክንድ የወሰድኩ እኔ ነኝ ለድኆችና ለችግረኞችም ሰጠኃ ኋቸው አለው።
መኰንኑም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ አስጨናቂ የሆነ ታላቅ ሥቃይንም አሠቃየው ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጨመሩት እግዚአብሔርም አዳነው ያለ ጥፋትም በጤና አወጣው።
ከዚህም በኋላ እጆቹንና እግሮቹን ቆረጡ ብዙ ደም ከአፍንጫው ወደ ምድር እስከ ሚወርድ ዘቅዝቀው በዕንጨት ላይ ሰቀሉት።
በዚያንም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ ቅዱስ መጥራንን ፈታው ከተሰቀለበትም አውርዶ በመዳሠሥ አዳነው። አንድ ዕውር ሰውም መጣ ከአፍንጫው ከወረደውም ደም ወስዶ ዐይኖቹን ቀባ ወዲያውኑ አየ። መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀዳጀ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ
በዚህችም ቀን ዳግመኛ በከሀዲ መክስምያኖስ እጅ ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ በሰማዕትነት ሞተ። በንጉሥ መክስምያኖስ ፊት በአቆሙት ጊዜ ለአማልክት ሠዋ አለው። የከበረ ሐርስጥፎሮስም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን አመልከዋለሁ ለእርሱም እሠዋለሁ። ንጉሡም ተቆጥቶ ሥጋው ተቆራርጦ በምድር ላይ እስቲወድቅ በበትር ይደበድቡት ዘንድ አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት።
ከዚህም በኋላ ወደ ወህኒ ቤት ጣሉት በላህያቸውም እንዲአስቱት ሁለት ሴቶችን ንጉሡ ወደርሱ ላከ ቅዱሱ ግን የክርስቶስን ሃይማኖት አስተማራቸው የዛሬ የሆነ የዚህንም ዓለም ኃላፊነት አስገነዘባቸው ወደ መክስምያኖስም በተመለሱ ጊዜ እንዴት አደረጋችሁ አላቸው።
እነርሱም እንዲህ አሉት በከበረ ሐርስጥፎሮስ አምላክ የክብር ባለቤት በሆነ በክርስቶስ እኛ እናምናለን ንጉሡም ሰምቶ አንዲቱን በዕንጨት ላይ ሰቅለው እንዲአቃጥሏት ሁለተኛዋን በአንገቷ ደንጊያ አንጠልጥለው ቊልቊል እንዲሰቅሏት አዘዘና ምስክርነታቸውን እንዲህ ፈጸሙ።
ከዚህም በኋላ ዕንጨቶችን ሰብስበው በማንደጃው ውስጥ አድርገው አነደዱ የከበረ ሐርስጥፎሮስን እጅና እግሩ እንደ ታሠረ ከውስጡ ጨመሩት ያን ጊዜም በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አለ እሳቱ ከቶ ምንም አልነካውም። ሕዝቡም ይህን አይተው የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ዐሥር ሺህ ያህል ሰዎች አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።
ሁለተኛም የብረት ሠሌዳዎችን በእሳት አግለው አመጡ ቅዱሱንም በላያቸው በአስተኙት ጊዜ ምንም ምን የነካው የለም። ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃያ ሺህ አንድ መቶ ሰዎችና አርባ ሕፃናት አምነው ምስክር ሁነው ሞቱ።
ንጉሥ መክስምያኖስም አይቶ እጅግ ተቆጣ የቅዱስ ሐርስጥፎሮስንም ራስ በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ።ከንጉሡም ዘንድ በወጣ ጊዜ ጸሎትን አደረገ ፊቱንም በመስቀል ምልክት አማተበ ከዚህም በኋላ ምስክርነቱን ፈጸመ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱሳን ቢካቦስና ዮሐንስ
በዚህችም ቀን እስሙናይን ከሚባል አገር የከበሩ ቢካቦስና ዮሐንስ ሌሎችም ከእሳቸው ጋራ በሰማዕትነት ሞቱ። ይህም ቅዱስ ቢካቦስ ክርስቲያን ሲሆን በሥውር ወታደር ሆነ። አንጥያኮስ ለሚባል መኰንንም ስለ ዮሐንስና ስለ ኤጲስቆጶስ አባ አክሎግ ከተርሴስ አገር ስለ ናሕር ስለ አባ ፊልጶስም እነርሱ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ነገር ሠሩባቸው።
መኰንኑም እነርሱን አቅርቦ እናንት ክርስቲያኖች ናችሁን አላቸው እኛ በእውነት ክርስቲያን ነን በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን አሉት። መኰንኑም ይህን ነገር ትታችሁ ለአማልክት ሠዉ አላቸው።
ቅዱሳኑም እንዲህ ብለው መለሱለት እኛስ ለረከሱና ለተናቁ አማልክት አንሠዋም ሰማይና ምድርን ከፈጠረ ከጌታችን ኢየሱስ በቀር። መኰንኑም ሰምቶ እጅግ ተቆጣ ምስክርነታቸውንም እስከፈጸሙ ድረስ አሠቃያቸው።
ቅዱስ ቢካቦስን ግን ከአሠቃየው በኋላ አሠረውና ከመንኰራኲር ውስጥ ጨመረው ዘቅዝቆም ሰቀለው ሕዋሳቱንም ቆራረጠው ጌታችንም ያስታግሠውና ያበረታው ነበር ያለ ጉዳትም ጤናማ አድርጎ አስነሳው።
ከዚህም በኋላ በርሙን ወደሚባል አገር ከብዙዎች ሰማዕታት ጋራ ላከው በመርከብም ውስጥ እህልና ውኃ ሳይቀምሱ ሃያ ስድስት ቀኖች ኖሩ። በርሙን ወደሚባል አገርም በደረሱ ጊዜ ጽኑ ሥቃይን አሠቃይተው በምሳር ቆረጡት የምስክርነቱንም ተጋድሎ ፈጸመ መንግሥተ ሰማያትም አክሊልን ተቀበለ።
ከሀገረ በርሙን ሹማምንቶችም አንድ ባለ ጸጋ ሰው መጥቶ የቅዱስ ቢካቦስን ሥጋ ወስዶ በአማሩ ልብሶች ገነዘው ወደ አገሩ እስሙናይንም ላከው። በመከራውም ወራት ቊጥር የሌላቸው ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ ከእርሱም ጋራ የተገደሉ ዘጠና አምስት ሰዎች ናቸው።
ከዚህም በኋላ ለቅዱሱ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለት ሥጋውን በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ብዙ ድንቅ ተአምር ተገለጠ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages