ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 20 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 23, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 20

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።


ቅዱሳን 7ቱ ደቂቅ
እነዚህ 7 ቅዱሳን ከዘመነ ሰማዕታት እስከ ዘመነ ጻድቃን የተዘረጋ ታሪክ አላቸው:: 7ቱም ባልንጀሮች ሲሆኑ በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን በኤፌሶን ተወልደው አድገዋል:: ክርስትናን ተምረውም በወጣትነታቸው የንጉሥ ጭፍሮች ሁነዋል:: የተቀጠሩትም የቤተ መንግስቱን ግምጃ ቤት ለመጠበቅ ነው::
በሥራቸውም ሆነ በጠባያቸው ደጐች ነበሩና ንጉሡ ዳኬዎስም: ሕዝቡም ይወዷቸው ነበር:: እነርሱ ግን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን ማሰብን መርጠው በፍቅር: በጸሎትና በምጽዋት ይተጉ ነበር:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ ግን ጭንቅ መከራ መጣ::
ንጉሡ ዳኬዎስ ክርስትናውን ትቶ ጣዖት አምላኪ ሆነ:: አዋጅም አስነገረ:: አዋጁም "ክርስቶስን ያልካደ: ለጣዖትም ያልሰገደ: ሃብት ንብረቱ ለዘረፋ: እጅ እግሩ ለእስር: ደረቱ ለጦር: አንገቱ ለሰይፍ: ቤቱም ለእሳት ይሰጣል" የሚል ነበር:: በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ::
የበርካቶቹም ደማቸው ፈሰሰ:: ኤፌሶን የግፍና የአመጻ ከተማ ሆነች:: የመከራ ጽዋው ጊዜውን ጠብቆ ወደ 7ቱ ወጣቶች ዘንድ ደረሰ:: ንጉሡ እነሱንም አስጠርቶ "ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: እነርሱ ግን የአምላካቸውን ፍቅር በዋዛ የሚቀይሩ አልነበሩምና "እንቢ" አሉት::
ንጉሡ ምንም ክፉና አውሬ ቢሆንም ይወዳቸዋል:: ሊገድላቸው አልፈለገምና አሳሰራቸው:: ከቀናት በሁዋላ አስጠርቶ ሊያታልላቸው ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: በዚያ ወራት ጦርነት ይበዛ ነበርና ግዛት ለማስፋትም ቢሉ ለማስገበር ወጣ::
ከመውጣቱ በፊት ግን 7ቱን አስጠርቶ "አሁን ከእስር ፈትቻቹሃለሁ:: ከጦርነት እስክመለስ ከልባችሁ ጋር ምከሩ:: ካልሆነ ሞት ይጠብቃቹሃል" ብሏቸው ነበር የወጣው:: ቅዱሳኑ ንጉሡ እንደ ወጣ ተቀምጠው መከሩ:: ውሳኔንም አስተላለፉ::
ዓለምን ንቀው: ሃብት ንብረታቸውን መጽውተው: ትንሽ ሳንቲም ብቻም ይዘው በድብቅ ወጡ:: አንድ ወታደር (በጐች አሉት) ይከተላቸው ነበርና የት እንደ ገቡ ተመለከተ:: ቅዱሳኑ ዘወትር በመዓልትና በሌሊት በበዓታቸው ውስጥ ይተጉ ነበር:: ከእነሱም አንዱ በተራ እየወጣ ቂጣ ይገዛ ነበር::
አንድ ቀን ግን ከእነሱ አንዱ ራት ሊገዛ ሲወጣ ንጉሡ መመለሱን ሰማ:: ወደ በዓቱ ተመልሶ ለወንድሞቹ ነገራቸው:: ከዚያች ቀን በሁዋላ 7ቱም አልወጡም:: በዓታቸውን ዘግተው ሲጸልዩ ደክሟቸው ተኙ:: ከዚያች ቀን በሁዋላ ግን አልነቁም::
ያ የበጐች ባለቤት (ወታደር) ለብዙ ቀናት አለመውጣታቸውን ሲመለከት "ሙተዋል" ብሎ አዘነ:: በድብቅ ክርስቶስን ያመልከው ነበርና:: እርሱ የቅዱሳኑን ተጋድሎ በድንጋይ ሰሌዳ ላይ ጽፎ ወደ በዓታቸው ውስጥ ጣለው::
ትልቅ ድንጋይም አምጥቶ ገጠመው:: እነዚህ ቅዱሳን ተኝተዋልና አልነቁም:: ቀናት: ወራት: ዓመታት ተዋልደው ለ372 ዓመት ተኙ:: አንድ ቀን አንድ እረኛ ለሥራ ፈልጐት ድንጋዩን ፈነቀለው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳኑ ነቁ::
በወቅቱ መልካቸው የወጣት ነው:: እድሜአቸው ግን 400 ሊሞላ ትንሽ ቀርቶት ነበር:: ልክ እንደ አቤሜሌክ ብዙ መተኛታቸው አልታወቃቸውምና ከመካከላቸው አንዱ የራት ዳቦ ሊገዛ ቢወጣ ግራ ተጋባ:: ኤፌሶን የማያውቃት ሌላ ሃገር ሆነችበት:: ከተማዋ ዘምናለች::
በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት: ቅዱስ መስቀልም በየአደባባዩ ተተክለዋል:: ነገሩ ግር ቢለው አንዱን ከመንገድ ጠርቶ "ወንድሜ! ይህቺ ከተማ ኤፌሶን አይደለችምን?" አለው:: እርሱም "አዎ ናት" ብሎት አለፈ::
ችግሩ ግን "ራት ልግዛ" ብሎ ወደ ገበያ ሲሔድ: እርሱ የያዘው ገንዘብ የዳኬዎስ ስም የተጻፈበት መሆኑ የፈጠረው ነበር:: በነጋዴዎቹ "የተደበቀ የጥንት ገንዘብ አግኝተሃል" በሚል ተከሶም ወደ ንጉሡ ቴዎድስዮስ ዘንድ ቀረበ:: (ትንሹ ቴዎዶስዮስ ነው:: የነገሠውም በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው)
በክርክሩ መካከል ቅዱሱ የእሱንና የወንድሞቹን ነገር ሲናገር ንጉሡም: ሊቀ ዻዻሱም አባ ቴዎድሮስ ይባላል) ተገረሙ:: አብረው ከከተማ ወጥተው ሔደው: 7ቱንም ሲጸልዩ አገኟቸው:: ፊታቸውም እንደ እግረ ፀሐይ ያበራ ነበር:: 7ቱም ለ7 ቀናት በኤፌሶን ድውያንን እየፈወሱ: ሰውን ሁሉ እየባረኩ ቆዩ::
ይህ ሁሉ የተደረገው በወቅቱ "ትንሳኤ ሙታን የለም" የሚሉ መናፍቃን ተነስተው ብዙ ሰው ክዶ ነበርና ለእነሱ ምሥክር ሊሆንባቸው ነው:: በርካቶችም በዚህ ድንቅ ተስበው ወደ ሃየማኖት ተመልሰዋል:: 7ቱ ቅዱሳን ግን በ7ኛው ቀን በክብር ዐርፈዋል:: ንጉሡ በ7 የወርቅ ሣጥኖች ቀብሯቸዋል::
††† አቡነ ሰላማ ካልዕ †††
††† እኒህ ታላቅ ደግ ሰው የነበሩት በሃገራችን ኢትዮዽያ ከ1340 እስከ 1380 ዓ/ም ነው:: በትውልድ ግብጻዊ ቢሆኑም ለኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ውለታን ውለዋል:: በዘመኑ ዻዻስ ሁነው ቢመጡም እንደ ሌሎቹ ዻዻሳት በቤተ መንግስት አካባቢ ሥራ ፈትተው መቀመጥን አልፈለጉም::
ወዲያው እንደ መጡ የግዕዝ ልሳንን ልቅም አድርገው ተማሩ:: ቀጥለው ኢትዮዽያውያን ሊቃውንትን ሰብስበው ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተረጉሙ ገቡ:: አሥራው መጻሕፍትን (81ዱን) ጨምሮ ብዙ መሠረታዊ መጻሕፍትን መተርጐም ችለዋል::
††† ይህም ሥራ አድካሚ በመሆኑ ከ30 ዓመታት በላይ ጊዜን ወስዷል:: ከተረጐሟቸው መጻሕፍትም:-
* ስንክሳር
* ግብረ ሕማማት
* ላሐ ማርያም
* ፊልክስዩስ(መጽሐፈ መነኮሳት)
* መጽሐፈ ግንዘት
*ድርሳን ዘቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ. . . ይጠቀሳሉ::
አቡነ ሰላማ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸውና በገዳማዊ ሕይወታቸው ይታወቁ ነበር:: በተጨማሪም በየቦታው እየዞሩ ይናዝዙ: ያጠምቁም ነበር:: በወቅቱ ልክ እንደ ስማቸው ሰላም እንዲሰፍን ይተጉ ነበር:: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን እያስታረቁ ለቤተ ክርስቲያን በአንድነት እንዲቆሙ አድርገዋል::
ጻድቁ አቡነ ፊልዾስን ጨምሮ ቅዱሳንን ገንዘውም ቀብረዋል:: በቀደመ ስማቸው አባ ፊቅጦር የሚባሉት ካልዕ (2ኛው) ሰላማ በ1380 ዓ/ም ከ40 ዓመታት ትጋት በሁዋላ ዐርፈዋል:: ሲጠሩም:-
* መተርጉም (መጻሕፍትን የተረጐሙ)
* ብርሃነ አዜብ(የኢትዮዽያ ብርሃን)
* መጋቤ ሃይማኖት ተብለው ነው::
አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹን እንዳጸናቸው ያጽናን:: ከበረከታቸውም ያድለን::
ነሐሴ 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (5ኛ ቀን)
2.ቅዱሳን 7ቱ ደቂቅ
3.አቡነ ሰላማ ካልዕ (መተርጉም)
4.ቅድስት ሔዛዊ
ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
2.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
3.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
4.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
5.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
6.ቅዱስ ወክቡር ማር ቴዎድሮስ ሰማዕት
"በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ:: ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላቹሃል:: የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ: የእግዚአብሔርም ፍቅር: የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን::" †††
(2ቆሮ. 13:12)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages