ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 25 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 23, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 25

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

 ነሐሴ ሃያ አምስት በዚች ቀን ቅዱስ እንድርያስ በሰማዕትነት ሞተ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሃያ አራቱ ባልንጀሮቹ በሰማዕትነት ሞቱ፣ ቅዱሱ አባት አባ ቢጻርዮን አረፈ።



✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ እንድርያስ
ነሐሴ ሃያ አምስት በዚህች ቀን ቅዱስ እንድርያኖስ በሰማዕትነት ሞተ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሃያ አራቱ ባልንጀሮቹ በሰማዕትነት ሞቱ። ይህም እንድርያኖስ ከመክስምያኖስ መኳንንቶች አንዱ ነበር እርሱም የጐልማሶች አለቃ ነበረ። ለጣዖት መስገድን እምቤ ስለአሉ ንጉሡ ምእምናንን ሲአሠቃያቸው ቅዱስ እንድርያኖስ የሰማዕታትን የልባቸውን ቆራጥነትና በመከራቸው ላይ መታገሣቸውን ተመልክቶ አደነቀ።
እንዲህም አላቸው ይህን ያህል ስትታገሡ ምን ታገኛላችሁ ቅዱሳን ሰማዕታትም የሚጠብቀንን ተሰፋ ለመናገር አንደበታችን አይችልም አሉት ስለ ዓለም ድኅነትም ክርስቶስ መከራ እንደ ተቀበለ ከብሉይና ከሐዲስ መጽሐፍ ነገሩት።
እንድርያኖስም በሰማ ጊዜ ጽሕፈትን ወደ ሚያውቁ ብልሆች ሰዎች ሔደና እኔ ከዛሬ ጀምሮ ክርስቲያን ነኝ ስሜን ከገድለኞቹ ጋራ ጻፉ አላቸው።
ለንጉሥ መክስምያኖስም እንዲህ እንዳለ በነገሩት ጊዜ ጠርቶ እንድርያኖስ ሆይ አበድክን አለው እንድርያኖስም ከቀድሞው እብደቴ ተመለስኩ እንጂ እኔ አላበድኩም ብሎ መለሰለት።
ንጉሡም ሰምቶ ወደ ወህኒ ቤት ከንጹሐን ሰማዕታት ጋራ እንዲጨምሩት አዘዘ። ከአገልጋዮቹም አንዱ ሒዶ ለሚስቱ እንጣልያ ነገራት በስማችም ጊዜ ደስ እያላት ወደ ወህኒ ቤት ሔደች ሃያ አራቱ ቅዱሳን ሰማዕታት የታሠሩበትን ማሠሪያቸውን ሳመች በሥቃዩ እንዲታገሥ የባሏን ልብ ያጽናኑ ዘንድ ለመነቻቸው። እርሱንም እንዲህ አለችው ላህይህ ደምግባትህም ርስትህም ጥሪትህም አያስትህ ሁሉም ከንቱ ነውና ነገር ግን በእርሱ ዘንድ የማያልፍ መንግሥትን ትወርስ ዘንድ የክብር ንጉሥ ክርስቶስን ተከተለው ይህንንም ብላ ወደቤቷ ገባች።
ከዚህም በኃላ እንድርያኖስ ለፍርድ እንደ ሚአቀርቡት በአወቀ ጊዜ ሊሰናበታት ወደ ሚስቱ ሔደ መምጣቱንም ሰምታ የሸሸ መሰላት ደጇንም ዘግታ በውስጥ ሁና እንዲህ እያለች ዘለፈችው ትላንት ሰማዕት ተብለኽ ዛሬ ክርስቶስን ካድከውን እንድርያኖስም ሰምቶ የሃይማኖቷን ጽናት አደነቀ እንዲህም አላት እኅቴ ሆይ እንድስናበትሽ ክፈችልኝ አላት።
በሰማችም ጊዜ ከፈተችለት ከዚህም በኃላ ሁሉን እያነጋገራት እስከ በኃላ ሁሉን እያነጋገራት እስከ እሥር ቤት ወሰዳት እንጣልያም ከዚያ በደረሰች ጊዜ የታሠሩትን ቅዱሳን ተሳለመቻቸው ቅስላቸውንም አጠበች።
ከዚህም በኃላ ንጉሡ ቅዱሳኑን ከእሥር ቤት እንደአመጧቸው አዘዘ በመጡም ጊዜ ከሥቃይ ብዛት የተነሣ እንደደከሙ አያቸው። እንድርያኖስንም በፊቱ አቁሞ ለአማልክት ሠዋ አለው ቅዱሱም እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ ንጉሡም የሆድ ዕቃው እስኪፈስስ ሆዱን እንዲደበድቡት አዘዘ በዚያን ጊዜም የእንድርያኖስ ዕድሜው ሃያ ስምንት ዓመት ነበር።
ከዚህም በኃላ እንድርያኖስን ከባልንጀሮቹ ሰማዕታት ጋራ ወደ እሥር ቤት መለሱት እንጣልያም መጥታ የቅዱሳንን ደማቸውን ጠራረገችላቸው። እሊህ ቅዱሳንም እንድርያኖስን እንዲህ ብለው ተሳለሙት እንድርያኖስ ሆይ ስምህ ተሳለሙት በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎአልና ደስ ይበልህ ።
ንጉሡም መሰፍ አምጥተው የቅዱሳኑን ሁሉ ጭናቸውን በድጅኖ ይሰብሩ ዘንድ አዘዘ እንጣልያም የእንድርያኖስን እጆቹንና እግሮቹን በመስፍ ላይ ለማኖር ቀደመች ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ እስከ ሰጠ ድረስ የእንድርያኖስን ዐጥንቶቹን ወታደሮች ቀጠቀጡ የቅዱሳኑንም ሁሉ ጭናቸውን ሰብረው ወደ እሳት ወረወሯቸው እሳቱ ግን ከቶ አልነካቸውም ።
ምእመናንም መጥተው በጭልታ ወደ ሌላ ቦታ ወሰዱአቸው የመከራውም ወራት እስቲያልፍ ሠወሩአቸው። እንጣልያም የእንድርያኖስን የእጁን ቁራጭ ወስዳ በትርአሷ ውስጥ አኖረችው።
ከዚህም በኃላ የሀገሩ ገዥ እንጣልያን ሊአገባት ወደደ በአወቀችም ጊዜ የባሏን የእጅ ቁራጭ ይዛ በመርከብ ሸሸች የቅዱሳኑ ሥጋ ወዳለበትም ደርሶ ወደ እነርሱ ይቀበሏት ዘንድ ለመነች ጌታችንም ልመናዋን ተቀብሎ አሳረፋት ከእነርሱም ጋራ ተቀበረች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱሱ አባት አባ ቢጻርዮን
በዚህችም ቀን ቅዱሱ አባት አባ ቢጻርዮን አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ምእመናን ነበሩ። በአደገም ጊዜ የምንኵስና ልብስን ለብሶ እግዚአብሔርን ሊአገለግል ወደደ ዓለምንም ንቆ ወደ አባ እንጦንስ ሔደ ለእርሱም ደቀ መዝሙር ሆኖ ብዙ ዘመናት አገለገለው።
ከዚህም በኃላ ወደ አባ መቃርስ ሒዶ ቅዱሳን አረጋውያን መነኰሳትንም አገለገላቸው። በአስቄጥስም ገዳም ይዘዋወር ነበር በቤት ውስጥም አያድርም ነበር። ምንጣፍና ልብስ እስኪአጣ ድረስ ምንም ምን ጥሪት አልነበረውም መነኰሳቱም የማቅ ጨርቅ ይሰጡት ነበር። ወገቡንም ታጥቆ በመነኰሳቱ መንደር ይዞር ነበር በቤቶቻቸውም ደጃፍ እያለቀሰ ይቀመጥ ነበር።
የማያውቀውም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ አባቴ ሆይ ምን ያስለቅስሃል ይለው ነበር። እርሱም ንብረቴን ስለዘረፉኝ እንዳልሞት ሸሸሁ ከወገኔም ክብር ተለይቼ በጉስቁልና ወደቅሁ ይለው ነበር። የቃሉንም ምልክት የማያውቅ የጠፋውን ገንዘብህን እግዚአብሔር ይመልስልህ ብሎ ካለው ይሰጠው ነበር። እርሱም ተቀብሎ ይሔድና ለሌለው ይሰጥ ነበር።
የቃሉን ምልክት የሚያውቅ ግን በፈቃደ ነፍስ የሚሠሩ ትሩፋትን ሰይጣን ከሰዎች የማረካቸው መሆኑን ልብ ብሎ ያስተውል ነበር። አባቶችም ጭንቅ የነበረ ተጋድሎውን ስለርሱ ይናገሩ ነበር። እርሱ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከቶ ሳይተኛ ቁሞ ኖሮአልና ።
በምንኩስናውም ወራት ብዙ ጊዜ በየአርባ ቀን ጾመ እነሆ እንዲህ እየተጋደለ ድንቆችንም እያደረገ ኀምሳ ሰባት ዓመታት ኖረ። ቅዱሳን አባ ዱላስና አባ ዮሐንስም ከተአምራቱ ተናገሩ እነርሱ ከርሱ ጋር ወደ ኤርትራ ባሕር ዳርቻ ሔዱ። እጅግም በተጠሙ ጊዜ እንደተጠሙ አውቆ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ መራራውንም ውኃ ጣፋጭ አድርጎላቸው ጠጥተዋል።
በሁለተኛም ጊዜ ወደ ፈሳሽ ውኃ ደርሶ መሸጋገሪያ አጣ ወደ ጌታችንም ጸለየ ያን ጊዜም እንደ የብስ በባሕሩ ላይ ሔደ። በአንዲት ቀንም የከበሩ አባቶች በጸሎታቸው ያድኑት ዘንድ ጋኔን ያደረበትን ሰው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሰዎች አመጡ አባቶችም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ እርሱ ከከንቱ ውዳሴ ስለሚሸሽ ብንነግረው ይህን ጋኔን የያዘውን አያድነውም ።
አባ ቢጻርዮን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጸሎት ወደሚቆምበት ቦታ ያንን ጋኔን ያደረበትን ሰው አስተኙት። አባ ቢጻርዮንም በገባ ጊዜ ያን ጋኔን ያደረበትን ሰው ተኝቶ አገኘውና ቀሰቀሰው እጁንም ይዞ ተነሥ አለው ያን ጊዜም ድኖ ተነሣ አእምሮውም ተመለሰ። ያዩትም እጅግ አደነቁ ለሚፈሩት ስለሚሰጠው ጸጋውም እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
የዚህም ቅዱስ ተአምራቶቹ ከነገርናችሁ የበዙ ናቸው እግዚአብሔርንም አገልገሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን። በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages