ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 28 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 23, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 28

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።



እኒህ ቅዱሳን ከሰው ወገን እጅግ ክቡራን ከመሆናቸው የተነሳ መንግስተ ሰማያት በእነርሱ ስም ተጠርታለች:: ጽድቃቸውና ክብራቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነውና ጽፈንም: ተናግረንም አንፈጽመውም:: እንዲሁ "ዕጹብ! ዕጹብ!" እያልን ፈጣሪያቸውን ከማመስገን በቀር::
ቅዱስ አብርሃም ርዕሰ አበው
የሃይማኖት: የደግነት: የምጽዋት: የፍቅር አባት የሆነው አብርሃም በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር:: ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር::
በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር:: አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ:: "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ:: መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም?" በሚል አናገረው::
"እርቦኛል አብላኝ?" አለው:: መልስ የለም:: "እሺ አጠጣኝ?" አለው:: አሁንም ያው ነው:: "ባይሆን እሺ አጫውተኝ?" አለው:: ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር:: ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዓይን እያለው የማያይ: ጆሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ?" እያለ ይጮህ ጀመር::
ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል::" ብለውት ሔደዋል:: ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ:: "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ::" ብሎ ሰባበረው::
ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው:: የመንግስተ ሰማያት አበጋዝ: የእግዚአብሔር ወዳጅ አባታችን አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት የሆነው አብርሃም እግዚአብሔርን አምልኮ: ጣዖታትን ሰብሮ ወደ ከነዓን ከወጣ በኋላ ብዙ ችግርን አሳልፏል:: በረሃብ ምክንያት ከአንድም ሁለት ጊዜ ወደ ግብጽና ፍልስጥኤም ተሰዷል:: በዚያ ግን ፈጣሪው አክብሮታል::
ሁለቱ ነገሥታት (ፈርኦንና አቤሜሌክ) ሣራን እንነካለን ቢሉ ተግሣጽ ደርሶባቸዋል:: ነቢይ ነውና በአብርሃም ጸሎት ተፈውሰዋል:: ቅዱስ አብርሃም ከደግነቱ የተነሳ በኬብሮን (በተመሳቀለ መንገድ) ላይ ድንኳን ሠርቶ እንግዳ ይቀበል ነበር:: ምሥክር ሳይዝም እህል አይቀምስም ነበር::
ሰይጣን ከፍቶ እንግዳ ቢያስቀርበት ያለ ምግብ ለሦስት ቀናት ቆይቷል:: በፍጻሜውም ሥላሴ በእንግድነት መጥተውለት በክብር ላይ ክብር: በጸጋ ላይ ጸጋ: በጣዕም ላይ ጣዕም ተጨምሮለታል:: እርሱ የሥላሴን እግር ያጥብ ዘንድ: በጀርባውም ይሸከማቸው ዘንድ አድሎታልና:: ሥላሴም በቤቱ ተስተናግደው: ልደተ ይስሐቅን አብሥረውታል:: ጻድቁ ሰውም በፈጣሪው ፊት ስለ ሰዶምና ገሞራ ለምኗል::
አብርሃም በአምልኮው ፍጹም ነውና የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን ለመስዋዕት አቅርቧል:: በዚህም የነቢያት: የሐዋርያት: የነገሥታት: የካህናት አባት: ሥርወ ሃይማኖት (የሃይማኖት ሥር) ተብሏል:: ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አያቱም ተብሏል::
አንድ ቀን እግዚአብሔር መላእክቱን "ብየ አርክ አብርሃም በዲበ ምድር - በምድር ላይ ወዳጄ አብርሃም አለ::" አላቸው:: ያን ጊዜ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ:-
*"አብርሃም አርከ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ)"
*"አብርሃም ብእሴ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ሰው)"
*"አብርሃም ገብረ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር አገልጋይ)"
*"አብርሃም ምዕመነ እግዚአብሔር
(አብርሃም የእግዚአብሔር ታማኝ)
*"አብርሃም ፍቁረ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ተወዳጁ ነው::) እያሉ አሰምተው ተናግረዋል::
አባታችን አብርሃም በክብር: በቅድስናና በሞገስ ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ ተጠቅሷል:: ፈጣሪ በስሙ ለቅዱሳን ተለምኗል:: ስለ ክብሩም በሲዖል ውስጥ እንኳ ማረፊያን ሠርቶለታል:: አጋንንትም ሊቀርቡት አልተቻላቸውም:: ያረፈውም ከክርስቶስ ልደት አንድ ሺ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ነው:: እድሜውም መቶ ሰባ አምስት ዓመት ነበር::
*ፍቅሩን የተረዱ ሊቃውንት ድንግል ማርያምን "ሐይመቱ (ድንኳኑ): ተናግዶቱ (እንግድነቱ) ለአብርሃም" ሲሉ አመስግነዋታል::
ሊቁም:-
"አብርሃም ፍጹም በሒሩት ወበአምልኮ:
እግዚአብሔር አዕበየከ ወባረከከ ባርኮ:
እስከ ሰመየከ ዲበ ምድር አርኮ::" ብሎ በምሥጢር ገልጾታል::
ቅዱስ ይስሐቅ ርዕሰ አበው
የደግ ዛፍ ፍሬ: የአብርሃም ልጅ ደጉ ይስሐቅ እጅግ ንጹሕ በመሆኑ የወልድ ክርስቶስ ምሳሌ ተብሏል:: የይስሐቅ ልደት እጅግ የተጠበቀ ከመሆኑ ባሻገር የተፈጸመውም በብሥራተ አምላክ ነው:: ስሙንም ያወጡለት ሥላሴ ናቸው:: ቡሩክ ይስሐቅ በብዙ ነገሩ ድንቅ ነው::
ለእርሱ ሃያ ዓመት ለአባቱ መቶ ሃያ ዓመት በሆናቸው ጊዜ ጭንቅ ትዕዛዝ ከፈጣሪ ዘንድ ተሰማ:: አብርሃም ይሰዋው ዘንድ ወደ ደብረ ምሥጢር ይዞት ከወጣ በኋላ መስዋዕቱ እርሱ እንደ ሆነ አወቀ:: ለፈጣሪውና ለአባቱ ይታዘዝ ዘንድ "እሺ" አለ::
በዚያውም ላይ አባቱን "አባ ስንፈራገጥ እንዳልጐዳህ እሠረኝ:: ዓይኔን አይተህ እንዳትራራ በሆዴ አስተኛኝ::" አለው::
አቤት ትሕትና! አቤት መታዘዝ! ወዮ አባታችን ይስሐቅ! ቅንነትህ ምን ይደንቅ! ለዚህ አነጋገርህ አንክሮ ይገባል!
"ሰላም ለይስሐቅ ዘኢያግዘፈ ክሳዶ:
ለደኒን ወለተሐርዶ"
እንዲል::
ቸር ፈጣሪ ግን የአብርሃምን አምልኮ: የይስሐቅን ንጹሕ መታዘዝ ለዓለም ገለጠ እንጂ እንዲሞት አላደረገም:: ቅዱስ ይስሐቅ በዚህች ዓለም ለመቶ ሰማንያ ዓመታት: በትዳር ደግሞ ለመቶ ሃያ ዓመታት ቆይቷል:: ከቅድስናው የተነሳ በእነዚህ ጊዜያት ከአንድ ቀን በቀር ከሚስቱ ርብቃ ጋር አልተኛም:: በዚህቺው ዕለትም ያዕቆብና ኤሳው ተጸንሰዋል::
እግዚአብሔር በመቶ ሰማንያ ዓመቱ ወደ ሰማይ ይዞት ወጣ:: በዚያም ግሩም ምሥጢርን ተመለከተ:: በእሳት መጋረጃ መካከል አብርሃምን አየው:: ከአምላክ ዙፋንም እንዲህ የሚል ቃል ወጣ::
*"ወዳጄን ይስሐቅን የሚያከብረውን አከብረዋለሁ::
*ልጁን አምኖ "ይስሐቅ" ብሎ የሚጠራውን
*በስሙ ለነዳያን የሚራራውን
*ለቤቱ እጣን ያመጣውን
*በዚህች ሌሊት በጸሎት የተጋውን
*'አምላከ ይስሐቅ' እያለ መቶ (100) ጊዜ የሰገደውን
*ዜና ይስሐቅን የጻፈውን: ያነበበውን ሁሉ በመንግስተ ሰማያት ዋጋውን እከፍለዋለሁ::
ይህንንም ልጁ (አባታችን ያዕቆብ) ተመልክቶ ከትቦታል:: ቅዱስ ይስሐቅም ከንጽሕናው ሳይጐድል በበረከት እንዳጌጠ ዐርፏል::
ወገኖቼ! ከላይ ካነበባችሁት መርጣችሁ አንዷን በእምነት እንድትፈጽሙ አደራ እላለሁ!
ቅዱስ ያዕቆብ ርዕሰ አበው
የአባቶች አለቃ የተሰኘ ቅዱስ ያዕቆብ ለሁለቱ ታላላቅ አባቶቹ እርሱ ሦስተኛቸው ነው:: እነርሱን መስሎ: እነርሱንም አህሎ በጐዳናቸው ተጉዟል:: በፈቃደ እግዚአብሔር ብኩርናን ከኤሳው ተቀብሎ ወደ ሶርያ ሲሸሽ ቤቴል (ፍኖተ ሎዛ) ላይ ድንጋይ ተንተርሶ በተኛበት ግሩም ራዕይን አይቷል::
ይህችውም የወርቅ መሰላል የድንግል ማርያም ምሳሌ ናት::
"አንቲ ውዕቱ ሰዋስው ዘርእየ ያዕቆብ" እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም (ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ)
ተነስቶም "ዛቲ ይእቲ ኈኅታ ለሰማይ: ዝየ ይትሐነጽ ቤተ እግዚአብሔር - ይህች የሰማይ ደጅ ናት: ቤተ እግዚአብሔርም ይታነጽባታል::" ብሎ ትንቢት ተናግሯል::
ይህ ቅዱስ አባት ለድንግል ማርያም ቅድመ አያት ከመሆኑ ባሻገር ነቢያትን: ካህናትን: ነገሥታትንና መሣፍንትን ወልዷል:: ከሁለቱ ሚስቶቹ (ልያና ራሔል) : ከሁለቱ ደንገጥሮች አሥራ ሁለት ልጆችን ወልዷል::
ከአጐቱ ከላባ ዘንድ ለሃያ አንድ ዓመታት አገልግሎ: ሃብት ንብረቱን ጠቅልሎ ወደ ርስቱ ከነዓን ሲመለስ ለብቻው ራቅ ብሎ ይጸልይ ገባ:: በዚያም እግዚአብሔር ሲታገለው አደረ:: (ይኸውም የፍቅርና የምሥጢር ነው::) ለጊዜው ጌታ ያዕቆብን "ልቀቀኝ?" ቢለው "ካልባረከኝ አለቅህም?" አለው:: ጌታም ስሙን "እሥራኤል" ብሎ ባርኮታል::
ቅዱስ ያዕቆብ በስተእርጅና ብዙ መከራ አግኝቶታል:: ልጁን ዮሴፍን ወንድሞቹ ሽጠው "አውሬ በላው" ብለውታልና በለቅሶ ዓይኑ ጠፋ:: በረሃብ ምክንያትም በመቶ ሰላሳ ዓመቱ ከሰባ አምስት ያህል ቤተሰቦቹ ጋር ወደ ግብጽ ወረደ:: በዚያም ለሰባት ዓመታት ኑሮ በመቶ ሰላሳ ሰባት ዓመቱ ዐርፏል:: ልጆቹም ቀብረውታል::
በሰማይና በምድር ከሞላው ከአባቶቻችን በረከት ፈጣሪያቸው አብዝቶ: አትርፎ: አትረፍርፎም ያድለን::
ነሐሴ 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አብርሃም (የአባቶች አለቃ)
2.ቅዱስ ይስሐቅ (የአባቶች አለቃ)
3.ቅዱስ ያዕቆብ (የአባቶች አለቃ)
ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
3.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
4.ቅዱሳን እንድራኒቆስና አትናስያ
"አብርሃምንና ይስሐቅን: ያዕቆብንም: ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግስት ባያችሁ ጊዜ: እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል::" †††
(ሉቃ. ፲፫፥፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages