ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 4 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 16, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 4
እንኳን ለጻድቅ ንጉሥ ሕዝቅያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ቅዱስ ሕዝቅያስ
ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን ከመድኃኒታችን ክርስቶስ ልደት ሰባት መቶ ዓመታት በፊት ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር:: ደጋጉ ዳዊትና ሰሎሞን ካረፉ በኋላ የሕዝቅያስን ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእሥራኤል ላይ አልነገሰም:: ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም ነበር::
ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት:: ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ ከመቶ ሰማንያ አምስት ሺ በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::
"እገብርልሃለሁ: የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ:: ነገር ግን ሃገሬን አታጥፋ:: ኢየሩሳሌምን አታቃጥል: ሕዝቤንም አትግደል" በሚል ለመነው:: እጅ መንሻ ግብሩንም ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት::
ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ: ቅዱስ ስሙንም ተገዳደረ:: ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ ማነው? ሕዝቡንም እግዚአብሔር ያድናል ብለህ አታታልላቸው" ሲል ላከበት:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::
መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ ልኮ እርሱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ አለቀሰ::
በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከተማዋን አድናታለሁ::"
በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው ከአሕዛብ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ:: በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል::
በድንጋጤ ወደ ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት:: ትዕቢተኛው ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖት የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት:: (1ነገ. 18:13, 19:1)
ቅዱስ ሕዝቅያስ የነሐስ እባቡን በማጥፋቱ: ሕዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በመመለሱ ቢደነቅም ሰው ነውና አንዲት ጥፋት አጠፋ:: በዘመኑ ታላቁ ነቢይ ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ነበረና ሐረገ ትንቢትን ያፈስ ነበር:: ከተናገራቸው ትንቢቶችም አንዱ "ድንግል ትጸንሳለች: ወንድ ልጅም ትወልዳለች" የሚል ነበር:: (ኢሳ. 7:14)
በወቅቱ የነበሩ አንዳንድ ክፉ መካሪዎች ቀርበው ንጉሡን በውዳሴ ከንቱ ጠለፉት:: "ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ንገሥ:: እንዳንተ ያለ ማንም የለም:: ነቢዩ የተናገረው ትንቢትም እኮ ላንተ ነው:: "ድንግል" የተባለች ኢየሩሳሌም ስትሆን "ወልድ-ወንድ ልጅ" የተባልክ ደግሞ አንተ ነህ" አሉት::
ይሕንን ጠማማ ትርጉም እህ ብሎ የሰማቸው ቅዱስ ሕዝቅያስ አልወቀሳቸውም:: ይልቁኑ ልቡ ወደ እነሱ አዘነበለ እንጂ:: በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ኢሳይያስን ላከው::
ነቢዩም በቀጥታ መጥቶ ንጉሡን አለው:- "ትሞታለህ እንጂ አትተርፍምና ቤትህን ሥራ::"
ወዲያውኑ ሕዝቅያስ ታመመ: ደከመ:: ነገር ግን ፊቱን ወደ ቤተ መቅደስ አዙሮ ሊያዝን: ሊተክዝም ጀመረ:: አባቶቻችን ለየት የሚያደርጋቸው ይኼ ነው:: በቅድስና ኑረው: ሰው ናቸውና ይሳሳታሉ:: ነገር ግን ንጹሕና ፍጹም ንስሐን ከማቅረብ አያቋርጡም::
ንጉሡ ቅዱስ ሕዝቅያስ ወደ ፈጣሪ:- "ጌታ ሆይ! እንደ ቸርነትህ በፊትህ በቅን መንገድ መሔዴን አስብና ይቅር በለኝ" ሲል ተማጸነ:: ይህ ሲሆን ቅዱስ ኢሳይያስ ገና ከንጉሡ አካባቢ አልራቀም ነበርና የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ::
ሕዝቅያስን በለው:- "ጸሎትህን ሰምቼ: ስለ ባለሟሌ ስለ ዳዊት ብዬ ምሬሐለሁ:: በዘመንህም ላይ አሥራ አምስት ዓመታትን ጨምሬልሃለሁ በለው" አለው:: ነቢዩም ወደ ንጉሡ ተመልሶ ይሕንኑ ነግሮ "እስከ ሦስት ቀን ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ ድነህ ትመለሳለህ" አለው::
ቅዱስ ሕዝቅያስ "ይሕ እንደሚደረግ በምን አውቃለሁ?" አለው:: (ተጠራጥሮ ግን አይደለም: ድንቅ ተአምር ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ) ኢሳይያስም ፀሐይን ዓለም እያየ አሥር መዓርጋትን ወደ ኋላ መለሳት:: በወቅቱ ይህ ተአምር በመላው ዓለም ታይቶ: ተሰምቶም ነበርና ሕዝቅያስ ከፍ ከፍ አለ::
በቅን የሔደ: እግዚአብሔርም የወደደው እንዲህ ነው:: የዓለም ነገሥታት ሁሉ ለሕዝቅያስ አዘነበሉ: ገበሩለትም:: ለእርሱ ጌታ ድንቅ ነገርን አድርጐለታልና::
ቅዱስ ሕዝቅያስ በተጨመሩለት ዘመናት ሁሉ እግዚአብሔርን አመለከ:: በፊቱም በቅን ተጓዘ:: ከክርስቶስ የዘር ሐረግም በቀጥታ ተቆጠረ:: (ማቴ.1:10) ለአሥራ አምስት ዓመታት ሕዝቡን አስተዳድሮ በዚህች ቀን እድሜ ጠግቦ ዐርፏል:: በእርሱ ዙፋን ላይም ልጁ ምናሴ ተተክቷል::
አባ ማቴዎስ ገዳማዊ
እኒህ ቅዱስ ሰው በ4ኛው መቶ ክ/ዘ ፋርስ አካባቢ የነበሩ ጻድቅ ናቸው:: በወቅቱ ምንኩስና በአካባቢው ባለመስፋፋቱ ወደ ዱር እየወጡ የሚኖሩ አበው ነበሩና አባ ማቴዎስ አንዱ ናቸው:: እርሳቸው በበርሃ ልብሳቸው አልቆ አካላቸው የሚሸፈነው በጸጉራቸው ነበር::
የአቶር ንጉሥ የሰናክሬም ልጅ መርምሕናምን(እጅግ ታላቅ ሰማዕት ነው) ያሳመኑትና ያጠመቁት እርሳቸው ናቸው:: እኅቱን ሣራንም ከለምጿ አንጽተው ወደ ክርስትና መልሰዋል:: በዚህ ምክንያትም የፋርስ አውራጃ የሆነችው አቶር በሙሉ የክርስቲያኖች ቤት ሆናለች:: አባ ማቴዎስ ከዘመናት ተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ዐርፈዋል::
አምላከ ቅዱሳን እድሜ ለንስሐ: ዘመን ለፍስሃ አይንሳን:: የጻድቃኑ በረከትም ይደርብን::
ነሐሴ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሕዝቅያስ ጻድቅ (ንጉሠ ይሁዳ)
2.አባ ማቴዎስ ገዳማዊ
3.ቅዱስ ዳዊት ሰማዕት
ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ (ወንጌላዊው)
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)
"አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል::
በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል::
የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው:: የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም::
በበጐ በረከት ደርሰህለታልና::
ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ::
ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም:: ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ::
በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው::"
(መዝ. ፳፥፩-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages