ስንክሳር ዘወርኀ ጷጉሜ 1 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 23, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ጷጉሜ 1

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።ወርኀ ጳጉሜን
እግዚአብሔር አዝማናትን የፈጠራቸው ለሰው ልጆች ጥቅም መሆኑ ይታወቃል:: እርሱ ባወቀ: በረቂቅ ሥልጣኑ ዓለምን ፈጥሮ: ጊዜያትን እንዲከፍሉ ብርሃናትን (ፀሐይ: ጨረቃ: ከዋክብትን) ፈጥሮልናል::
ጊዜያትንም በደቂቃ: በሰዓት: በቀን: በሳምንት: በወር: በዓመታት: በኢዮቤልዩ: በክፍላተ ዘመናት እንድንቆጥር ያስማረንም እርሱ ነው:: የሰከንድ 540,000 ክፋይ ከሆነችው 'ሳድሲት' እስከ ትልቁ ቀመር (532 ዓመት) ድረስ እርሱ ለወደዳቸው እንዲያስተውሉት ገልጧል::
በየዘመኑም በቅዱስ ድሜጥሮስ: በቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ : በቅዱስ አቡሻኽር እና በሌሎቹም አድሮ መልካሙን አቆጣጠር አስተምሯል:: ሃገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ የአሥራ ሦስት ወራት የፀሐይ ጸጋ (thirteen months sun shine) ያላት: አራቱ ወቅቶች የተስማሙላት ናት::
🙏
ሌላው ዓለም ወሮችን 31,30,29 (28) እያደረገ ሲጠቀም እኛ ግን እንደ ኖኅ (ዘፍ. 8:1-15) አቆጣጠር ወሮችን በሠላሳ ቀናት ወስነን: ጳጉሜንን ለብቻዋ እናስቀምጣለን:: ጳጉሜን 'ኤጳጉሚኖስ' ከሚል የግሪክ (ጽርዕ) ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም 'ትርፍ: ጭማሪ' እንደ ማለት ነው::
የወርኀ ዻጉሜን አምስቱ (ስድስቱ) ቀናትም ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ እንደ መሆናቸው ብዙ ምሳሌያት (ምሥጢራት) አሏቸው:: ዋናው ግን በዚህ ጊዜ ዳግም ምጽዓት ይታሠባል:: ጊዜውንም በጾምና በጸሎት ሊያሳልፉት ይገባል:: ግን በፈቃድ ነው እንጂ የግዴታ አይደለም::
🙏
† ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ †
🙏
¤የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ
¤በማኅጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት
¤በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ
¤እሥራኤልን ለንስሐ ያጠመቀ
¤የጌታችንን መንገድ የጠረገ
¤ጌታውን ያጠመቀና
¤ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው::
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን:-
ነቢይ:
ሐዋርያ:
ሰማዕት:
ጻድቅ:
ገዳማዊ:
መጥምቀ መለኮት:
ጸያሔ ፍኖት:
ቃለ ዐዋዲ ብላ ታከብረዋለች::
††† ቅዱሱ በዚህች ዕለት ወደ እሥር ቤት ገብቷል:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ንጉሡ ሔሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሔሮድያዳን በማግባቱና በመሰል ክፋቶቹ ቅዱስ ዮሐንስ ይገስጸው ነበር:: ቅዱስ ዮሐንስ "መምሕር ወመገስጽ: ዘኢያደሉ ለገጽ - ፊት አይቶ የማያዳላ" ነውና ገሰጸው::
ሔሮድስ ቅዱሱን ይፈራው: ያከብረውም ነበር:: በኋላ ግን ፈቃደ ሥጋው ስላየለበት: በተለይ ደግሞ ከሰባት ቀናት በኋላ ልደቱን ሲያከብር እንዳይረብሸው በመስጋት በዚህች ቀን በወታደሮቹ አስይዞ እሥር ቤት ውስጥ
ጥሎታል:: ለሰባት ቀናት በጨለማ ውስጥ አሥሮ መስከረም 2 ቀን አንገቱን እንዴት እንዳስቆረጠው ዕለቱን ጠብቀን እንመለከታለንና የዚያ ሰው ይበለን::
🙏
† ቅዱስ ዑቲኮስ ሐዋርያ †
🙏
††† ቅዱሱ ሐዋርያ ጭራሽ ከነስማቸው እንኳ እየተዘነጉ ከሔዱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን ቁጥሩም ከሰባ ሁለቱ አርድእት ነው:: በወጣትነት ዘመኑ የጌታችን ደቀ መዝሙር መሆንን መርጦ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ምሥጢረ ወንጌልን ጠንቅቆ ተምሯል::
መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜም እንደ መጠኑ ተቀብሎ ለአገልግሎት ወጥቷል:: በመጀመሪያ የወንጌላዊው ዮሐንስ ተከታይ ሁኖ ብዙ ምሥጢራትን ተካፍሏል:: ቀጥሎም ቅዱስ ጳውሎስን ተከትሎ ብዙ አሕጉራትን በስብከተ ወንጌል አዳርሷል::
በመጨረሻም በእስያ አካባቢ ለብቻው ተጉዞ: ብዙ ነፍሳትን ማርኮ: ጣዖታትን አጥፍቷል:: ስለዚህ ፈንታም በእሳት: በስለትና በግርፋት ብዙ መከራዎችን አሳልፏል:: በዚህች ቀንም በበጐው እርግና (ሽምግልና) ዐርፏል::
✍
† ቅዱስ ብሶይ ቀሲስ †
✍
†. ከ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ካህናት አንዱ የነበረው አባ ብሶይ ለአገልግሎት ወጥቶ ሲመለስ የቤተሰቦቹ ቤት ሰው አልነበረበትም:: "የት ሔዱ?" ብሎ ቢጠይቅ "ወንድምህ አባ ሖር እና እናትህ ቅድስት ይድራ ወደ እስክንድርያ ሔደዋል:: በዚያም ስለ ክርስቶስ ፍቅር ተሰውተዋል::" አሉት::
በማግስቱ የኔ ብጤዎችን ጠርቶ ሃብቱን: ንብረቱን: ቤቱን አካፈላቸው:: ለራሱ ግን አንዲት በትር እና ሦስት የዳቦ ቁራሾች ይዞ ጉዞ ተነሳ:: ወደ እስክንድርያ እንደ ደረሰ አፈላልጐ የቤተሰቦቹን መቃብር አገኘ:: ከፊታቸው ወድቆም የናፍቆት ለቅሶን አለቀሰ::
ወዲያውም እንዲህ አላቸው:- "ፈጥኜ ወደ እናንተ ስለምመጣ ጠብቁኝ:: ደግሞም ጸልዩልኝ::" ከዚያ ተነስቶ በመኮንኑ ፊት ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት መሰከረ:: በዚህ ምክንያት ብዙ ተሰቃይቶ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆኗል:: ከወገኖቹም ጋር ተቀብሯል::
††† አምላከ ቅዱሳን ተረፈ ዘመኑን ባርኮ ለአዲሱ ዘመን በቸር ያድርሰን:: ከወዳጆቹም ጸጋ በረከትን ይክፈለን::
ጳጉሜን 1 ቀን የሚከበሩ
ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ (የታሠረበት)
2.ቅዱስ ዑቲኮስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
3.ቅዱስ ብሶይ ቀሲስ (ሰማዕት)
4.አባ ጳኩሚስ /ባኹም (የሦስት ሺ ቅዱሳን አባት)
5.አባ ሰራብዮን /ሰራፕዮን (የአሥር ሺ ቅዱሳን አባት)
✍
ወርኀዊ በዓላት. (የለም)
"ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ . . . ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን . . . እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም . . . ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ:: ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይሕ ነው:: የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ::" (ማቴ. ፲፩፥፯-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ጷጉሜን

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages