ስንክሳር ዘወርኀ ጷጉሜ 2 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 23, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ጷጉሜ 2

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።ቅዱስ ቲቶ ሐዋርያ
❣
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ቲቶ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሲሆን በተወሰነ መንገድም ቢሆን የተዘነጋ ሐዋርያ አይደለም:: በተለይ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ከጻፋቸው አሥራ አራት መልእክታት መካከል አንዷ የተላከችው ለዚህ ቅዱስ በመሆኗ ታሪኩ እንኳ ባይነገር ስሙ አይረሳም:: ቅዱስ ጳውሎስም በመልዕክታቱ በጐ ስሙን እየደጋገመ ያነሳዋል::
❣
ለመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ ማን ነው?
ቅዱስ ቲቶ የተወለደው በ1ኛው መቶ ክ/ዘመን እስያ ውስጥ: ቀርጤስ በምትባል ከተማ ነው:: የዘር ሐረጉ ከእሥራኤልም: ከጽርእም (ግሪክ ለማለት ነው::) ይወለዳል:: አካባቢው አምልኮተ እግዚአብሔር የጠፋበት ስለሆነ እሱም: ቤተሰቦቹም የሚያመልኩት ከዋክብትን ነበር::
❣
መዳን በእውቀት ይመስላቸው ስለ ነበር የአካባቢው ሰዎች የግሪክን ፍልስፍና ጠንክረው ይማሩ ነበር:: ቅዱስ ቲቶም በወጣትነቱ ወደ ት/ቤት ገብቶ የግሪክን ፍልሥፍናና የዮናናውያንን ጥበበ ሥጋ ተማረ:: በጥቂት ጊዜም የሁሉ የበላይ ሆነ::
❣
ቅዱሱ በወቅቱ ምንም እውነተኛውን ፈጣሪ አያምልክ እንጂ በጠባዩ እጅግ ቅንና ደግ ነበር:: ምክንያቱን ሳያውቀው ለእኔ ቢጤዎች ያበላ: ያጠጣ: ይንከባከባቸውም ነበር:: እግዚአብሔር ግን የዚህ ቅን ሰው በጐነቱ እንዲሁ እንዲቀር አልወደደምና አንድ ቀን በራዕይ ተገለጠለት::
❣
በራዕይም አንድ ምንነቱን ያልተረዳው ነገር "ቲቶ ሆይ! ስለ ነፍስህ ድኅነት ተጋደል:: ይህ ዓለም ኃላፊ ነው::" ሲለው ሰማ:: ከእንቅልፉ ነቅቶ በእጅጉ ደነገጠ:: የሚያደርገውንም አጣ:: ያናገራቸው ሁሉ ምንም ሊገባቸው አልቻለም::
❣
ለተወሰነ ጊዜም ለጉዳዩ ምላሽ ሳያገኝለት በልቡ እየተመላለሰ ኖረ:: ድንገት ግን በዚያ ሰሞን ከወደ ኢየሩሳሌም አዲስ ዜና ተሰማ:: "ክርስቶስ የሚሉት ኢየሱስ: እርሱም የባሕርይ አምላክ የሆነ ወደ ምድር ወርዶ: ስለ እግዚአብሔር መንግስትም እየሰበከ ነው::" ሲሉ ለቲቶ ነገሩት::
❣
"ሌላስ ምን አያችሁ?" አላቸው:: "በእጆቹ ድውያን ይፈወሳሉ:: ሙታን ይነሳሉ:: እውራን ያያሉ:: ለምጻሞች ይነጻሉ:: ሌሎች ብዙ ተአምራትም እየተደረጉ ነው::" አሉት:: የወቅቱ የሃገረ አክራጥስ መኮንን ፈላስፋ ነበርና ስለ ክርስቶስ ሲሰማ ሊመራመር ወደደ::
❣
እርሱ መሔድ ስላልተቻለው "ብልህ ጥበበኛ ሰው ፈልጉልኝ::" ብሎ ተከታዮችን ቢልካቸው ከቲቶ የተሻለ በአካባቢው አልነበረምና እርሱኑ አመጡት:: መኮንኑ ቲቶን "ነገሩ ትክክል ወይም ስሕተት መሆኑን በጥልቅ መርምረህ ምላሽ አምጣልኝ::" ብሎ ላከው::
❣
ቅዱስ ቲቶም ፈጥኖ ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም ገሰገሰ:: ወደ ከተማዋ እንደገባም ጌታችንን አፈላልጐ አገኘው::
👉
1.ጌታችን ክርስቶስ በሥልጣነ ቃሉ ደዌያትን ሲያርቅ: አጋንንትን ሲያሳድዳቸው ተመልክቶ ይህ ሥራ የፍጡር እንዳልሆነ ተረዳ::
👉
2.ጌታችን የሚያስተምረው ትምሕርት ከግሪክ ፍልሥፍና እጅግ ርቆና መጥቆ አገኘው:: የግሪክ ፍልሥፍና መነሻውም ሆነ መድረሻው ሥጋዊ ነው:: ጌታ ግን በጣዕመ ቃሉ የሚያስተምረው ሰማያዊ: በዚያ ላይ ዘላለማዊ የሆነ ትምሕርት ነው:: በራዕይ "ስለ ነፍስህ ተጋደል::" ያለው ምሥጢር አሁን ተተረጐመለት::
❣
በዚህ ምክንያትም ጊዜ አላጠፋም:: ወዲያውኑ አምኖ ተከታዩ ሆነ:: ጌታም ከሰባ ሁለቱ አርድእት ደመረው:: የአክራጥስ መኮንን "ምነው ዘገየህ?" ቢለው ያየውን ሁሉ ጽፎ: እንደማይመለስም አክሎ ደብዳቤ ላከለት::
❣
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ቲቶ ከጌታችን እግር ለሦስት ዓመታት ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ: በመላው እስያ ለስምንት ዓመታት ወንጌልን ሰብኳል:: ቅዱስ ጳውሎስ ባመነ ጊዜ ደግሞ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆኖ ለሃያ አምስት ዓመታት አስተምሯል::
❣
ቅዱስ ጳውሎስ ሰማዕት ከሆነ በኋላ ደግሞ ወደ አክራጥስ ተመልሶ: ሕዝቡን አሳምኖና አጥምቆ: ቤተ ክርስቲያንን አንጿል:: ዕድሜው በደረሰ ጊዜም መምሕራንን: ካህናትን ሹሞላቸው: ባርኳቸውም በዚህች ቀን ዐርፏል::
🌹
አምላከ ቅዱስ ቲቶ መልካሙን የሕይወት ምሥጢር ይግለጽልን:: ከሐዋርያውም በረከቱን ያድለን::

ጳጉሜን 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቲቶ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
ወርኀዊ በዓላት(የለም)
"የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ. . . መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ: ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ: በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ለሚሆን ልጄ ቲቶ:: ከእግዚአብሔርም አብ: ከመድኃኒታችንም ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት: ሰላምም ይሁን::" (ቲቶ. ፩፥፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ጳጉሜ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages